በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የአምላክ ወዳጅ መሆን የምችለው እንዴት ነው?

የአምላክ ወዳጅ መሆን የምችለው እንዴት ነው?

ምዕራፍ 35

የአምላክ ወዳጅ መሆን የምችለው እንዴት ነው?

ጄረሚ ከአምላክ ጋር ወዳጅነት መመሥረት ያለውን ጥቅም የተረዳው በሕይወቱ ውስጥ ካጋጠመው አሳዛኝ ሁኔታ ነበር። እንዲህ ብሏል፦ “የ12 ዓመት ልጅ ሳለሁ አባቴ ቤተሰቡን ጥሎ ሄደ። አንድ ምሽት አልጋዬ ላይ ሆኜ አባቴ የሚመለስበትን መንገድ እንዲያመቻች ይሖዋን በጸሎት ለመንኩት።”

ከዚያም ጄረሚ በጭንቀት ተውጦ መጽሐፍ ቅዱሱን ማንበብ ጀመረ። መዝሙር 10:14 (NW) ላይ ያለው ሐሳብ ልቡን ነካው። ጥቅሱ ስለ ይሖዋ ሲናገር “አባት የሌለው ልጅ ራሱን ለአንተ በአደራ ይሰጣል። አንተ ራስህ ረዳቱ ሆነሃል” ይላል። ጄረሚ እንዲህ ብሏል፦ “ይሖዋ እያነጋገረኝ እንደሆነ እንዲሁም ረዳቴና አባቴ መሆኑን እየነገረኝ እንዳለ ሆኖ ተሰማኝ። ከእሱ የተሻለ አባት የት ላገኝ እችላለሁ?”

አንተም ከጄረሚ ጋር የሚመሳሰል ሁኔታ አጋጥሞህ ሊሆን ይችላል፤ ይህ ባይሆንም እንኳ ይሖዋ የእሱ ወዳጅ እንድትሆን የሚፈልግ መሆኑን መጽሐፍ ቅዱስ ይናገራል። እንዲያውም መጽሐፍ ቅዱስ “ወደ አምላክ ቅረቡ፤ እሱም ወደ እናንተ ይቀርባል” ይላል። (ያዕቆብ 4:8) ይህ አባባል ምን ትርጉም እንዳለው አስተዋልክ? ይሖዋ አምላክን ልታየው ባትችልም እንዲሁም በምንም መልኩ እኩያህ ባይሆንም እንኳ ከእሱ ጋር ወዳጅነት እንድትመሠርት እየጋበዘህ ነው!

ይሁንና ከአምላክ ጋር ወዳጅነት መመሥረት በአንተ በኩል ጥረት ማድረግ ይጠይቅብሃል። ነገሩን በምሳሌ ለማስረዳት፦ በቤትህ ውስጥ የተከልከው አበባ ቢኖር እንዲያድግ የግድ የአንተ እንክብካቤ እንደሚያስፈልገው የታወቀ ነው። አበባው እንዲመቸው ከተፈለገ በየጊዜው ውኃ ልታጠጣውና ለእድገቱ ተስማሚ በሆነ ስፍራ ልታስቀምጠው ይገባል። ከአምላክ ጋር ወዳጅነት በመመሥረት ረገድም ሁኔታው ተመሳሳይ ነው። ታዲያ ከአምላክ ጋር ያለህ ወዳጅነት እያደገ ወይም እየተጠናከረ እንዲሄድ ምን ማድረግ ትችላለህ?

ጥናት አስፈላጊ ነው

ወዳጅነት እንዲጠናከር ሁለቱም ወገኖች የሐሳብ ልውውጥ ማድረግ ይኸውም መነጋገርና መደማመጥ ያስፈልጋቸዋል። ከአምላክ ጋር ባለን ወዳጅነት ረገድም ይህ እውነት ነው። አምላክ የሚነግረንን መስማት የምንችለው መጽሐፍ ቅዱስን በማንበብና በማጥናት ነው።​—መዝሙር 1:2, 3

በእርግጥ ጥናት የምትወደው ነገር ላይሆን ይችላል። ብዙ ወጣቶች ከማጥናት ይልቅ ቴሌቪዥን ማየት፣ ጌም መጫወት ወይም ከጓደኞቻቸው ጋር ጊዜ ማሳለፍ ይመርጣሉ። ይሁንና ከአምላክ ጋር ወዳጅ ለመሆን ሌላ አቋራጭ መንገድ የለም። ቃሉን በማጥናት እሱን ማዳመጥ ይኖርብሃል።

በዚህ ረገድ ሐሳብ አይግባህ። መጽሐፍ ቅዱስን ማጥናት ሥራ ሊሆንብህ አይገባም። ማጥናት የምትወድ ሰው ባትሆንም እንኳ መጽሐፍ ቅዱስን ማጥናት አስደሳች እንዲሆንልህ ማድረግ ትችላለህ። ልትወስደው የሚገባው የመጀመሪያው እርምጃ መጽሐፍ ቅዱስን የምታጠናበት ጊዜ መመደብ ነው። ልያ የተባለች ወጣት “መጽሐፍ ቅዱስን የማነብበት ፕሮግራም አለኝ፤ ሁልጊዜ ጠዋት ከእንቅልፌ እንደተነሳሁ አንድ ምዕራፍ አነባለሁ” ብላለች። ማሪያ የተባለችው የ15 ዓመት ወጣት ፕሮግራም ደግሞ ከዚህ የተለየ ነው። “ሁሌ ማታ ማታ ከመተኛቴ በፊት መጽሐፍ ቅዱስን አነባለሁ” ብላለች።

አንተም እንዴት ማጥናት እንደምትችል ሐሳብ ለማግኘት  በገጽ 292 ላይ የሚገኘውን ሣጥን ተመልከት። ከዚያም የአምላክን ቃል ለ30 ደቂቃ ያህል ማጥናት የምትችለው መቼ እንደሆነ አስብ፤ ያወጣኸውን ፕሮግራም ከዚህ በታች ጻፍ።

․․․․․

ፕሮግራም ማውጣት የመጀመሪያው እርምጃ ብቻ ነው። ማጥናት ስትጀምር መጽሐፍ ቅዱስን ማንበብ ቀላል የማይሆንበት ጊዜ እንደሚኖር ትገነዘብ ይሆናል። አንተም ጄዝሬል እንደተባለው የ11 ዓመት ልጅ ይሰማህ ይሆናል፤ “አንዳንዶቹ የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍሎች ለመረዳት ያስቸግራሉ፤ ደግሞም ያን ያህል አይማርኩኝም” በማለት በግልጽ ተናግሯል። እንደዚህ የሚሰማህ ከሆነ ተስፋ አትቁረጥ። ምንጊዜም ቢሆን፣ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናትህን ወዳጅህ የሆነውን ይሖዋ አምላክን ለመስማት የሚያስችል አጋጣሚ እንደሚከፍትልህ አድርገህ ልትመለከተው ይገባል። የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናትህ አስደሳችና የሚክስ መሆኑ በምታደርገው ጥረት ላይ የተመካ ነው!

ጸሎት ወሳኝ ነው

ጸሎት አምላክን የምናነጋግርበት መንገድ ነው። ጸሎት እንዴት ያለ ግሩም ስጦታ እንደሆነ አስብ! ቀንም ሆነ ማታ በማንኛውም ሰዓት ይሖዋ አምላክን ማነጋገር ትችላለህ። አንተን ለማዳመጥ ምንጊዜም ዝግጁ ነው። ከዚህም በላይ የምትለውን ለመስማት ፍላጎቱ አለው። መጽሐፍ ቅዱስ “ስለ ሁሉም ነገር በጸሎትና በምልጃ ከምስጋና ጋር ልመናችሁን ለአምላክ አቅርቡ” በማለት የሚያሳስበን ለዚህ ነው።​—ፊልጵስዩስ 4:6

ከዚህ ጥቅስ መረዳት እንደሚቻለው ይሖዋን ስለ ብዙ ነገሮች ልታነጋግረው ትችላለህ። ለምሳሌ ስለሚያጋጥሙህ ችግሮችና ስለሚያስጨንቁህ ነገሮች ልትነግረው ትችላለህ። በተጨማሪም ምስጋናህን ልትገልጽለት ትችላለህ። ስላደረጉልህ መልካም ነገሮች ጓደኞችህን አታመሰግናቸውም? ማንኛውም ጓደኛ ሊያደርግልህ ከሚችለው በላይ ብዙ ነገሮችን ላደረገልህ ለይሖዋስ ምስጋናህን ልትገልጽ አይገባም?​—መዝሙር 106:1

አንተ በግልህ ይሖዋን እንድታመሰግን የሚያነሳሱህን አንዳንድ ነገሮች ከዚህ በታች ጻፍ።

․․․․․

የሚያስጨንቁህና ስጋት እንዲያድርብህ የሚያደርጉ ነገሮች አልፎ አልፎ እንደሚያጋጥሙህ እሙን ነው። መዝሙር 55:22 “የከበደህን ነገር በእግዚአብሔር ላይ ጣል፤ እርሱ ደግፎ ይይዝሃል፤ የጻድቁንም መናወጥ ከቶ አይፈቅድም” ይላል።

የሚያሳስቡህንና በጸሎት ወደ ይሖዋ ልታቀርባቸው የምትፈልጋቸውን ጉዳዮች ቀጥሎ ባለው ክፍት ቦታ ላይ ጻፍ።

․․․․․

የራስ ተሞክሮ

ከአምላክ ጋር ባለህ ወዳጅነት ረገድ ልትዘነጋው የማይገባ ሌላም ነገር አለ። መዝሙራዊው ዳዊት “እግዚአብሔር ቸር መሆኑን ቀምሳችሁ እዩ” በማለት ጽፏል። (መዝሙር 34:8) ዳዊት 34ኛውን መዝሙር ከማቀናበሩ ትንሽ ቀደም ብሎ በጣም አስፈሪ ሁኔታ አጋጥሞት ነበር። በወቅቱ ሊገድለው ከሚፈልገው ከንጉሥ ሳኦል እየሸሸ ነበር፤ ይህ በራሱ በጣም አስጨናቂ ነገር ሆኖ ሳለ ዳዊት ጠላቶቹ ወደሆኑት ፍልስጥኤማውያን በመሄድ መሸሸግ ግድ ሆኖበት ነበር። ዳዊት ከሞት ጋር በተፋጠጠበት በዚያ ወቅት እንዳበደ ሰው በመሆን በዘዴ ማምለጥ ችሏል።​—1 ሳሙኤል 21:10-15

ዳዊት ከሞት ለጥቂት ሊያመልጥ የቻለው በራሱ ብልሃት እንደሆነ አልተሰማውም። ከዚህ ይልቅ ይሖዋ እንደረዳው ገልጿል። ከላይ በተጠቀሰው መዝሙር ላይ እንዲህ ሲል ጽፏል፦ “እግዚአብሔርን ፈለግሁት፤ እርሱም መለሰልኝ፤ ከፍርሀቴም ሁሉ አዳነኝ።” (መዝሙር 34:4) ከዚህ ለማየት እንደምንችለው ዳዊት “እግዚአብሔር ቸር መሆኑን ቀምሳችሁ እዩ” ብሎ ሌሎችን የመከረው ከራሱ ተሞክሮ በመነሳት ነበር። *

ይሖዋ እንደሚያስብልህ የሚያሳይ በሕይወትህ ውስጥ ያጋጠመህ አንድ ተሞክሮ ማስታወስ ትችላለህ? ከሆነ ከዚህ በታች ጻፈው። ፍንጭ፦ ተአምር የሆነ ነገር እንዲያጋጥምህ መጠበቅ የለብህም። በዕለት ተዕለት ሕይወትህ ይሖዋ ያደረገልህን ጥቃቅን የሚመስሉ ነገሮች ለማሰብ ጥረት አድርግ፤ ምናልባትም አንዳንዶቹ እምብዛም ትኩረት የማንሰጣቸው ነገሮች ሊሆኑ ይችላሉ።

․․․․․

ወላጆችህ ስለ መጽሐፍ ቅዱስ አስተምረውህ ሊሆን ይችላል። ከሆነ ተባርከሃል። ያም ሆኖ ከአምላክ ጋር የግል ዝምድና መመሥረት ያስፈልግሃል። ከአምላክ ጋር የግል ዝምድና ካልመሠረትክ በዚህ ምዕራፍ ላይ በቀረበው ሐሳብ በመጠቀም እንዲህ ማድረግ ትችላለህ። ይሖዋ የምታደርገውን ጥረት ይባርክልሃል። መጽሐፍ ቅዱስ “ደጋግማችሁ ለምኑ፣ ይሰጣችኋል፤ ሳታቋርጡ ፈልጉ፣ ታገኛላችሁ” ይላል።​—ማቴዎስ 7:7

ተጨማሪ ሐሳብ ለማግኘት የዚህን መጽሐፍ ጥራዝ 1 ምዕራፍ 38 እና 39 ተመልከት

በሚቀጥለው ምዕራፍ

ስለ አምላክ ለሌሎች መናገር ይከብድሃል? ስለ እምነትህ ለሌሎች ማስረዳት የምትችለው እንዴት እንደሆነ ከሚቀጥለው ምዕራፍ ትምህርት ታገኛለህ።

[የግርጌ ማስታወሻ]

^ አን.24 አንዳንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉሞች “ቀምሳችሁ እዩ” የሚለውን ሐረግ “ራሳችሁ ተመልከቱ፣” “ራሳችሁ ድረሱበት” እንዲሁም “ከተሞክሮ ታያላችሁ” በማለት አስቀምጠውታል።​—ኮንቴምፖራሪ ኢንግሊሽ ቨርዥን፣ ቱዴይስ ኢንግሊሽ ቨርዥን እና ዘ ባይብል ኢን ቤዚክ ኢንግሊሽ

ቁልፍ ጥቅስ

“በመንፈሳዊ ድሆች መሆናቸውን የሚያውቁ ደስተኞች ናቸው።”​—ማቴዎስ 5:3

ጠቃሚ ምክር

በየዕለቱ አራት ገጽ ገደማ ብታነብ በአንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ ሙሉውን መጽሐፍ ቅዱስ መጨረስ ትችላለህ።

ይህን ታውቅ ነበር?

ይህንን መጽሐፍ ማንበብህና በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ ተመሥርቶ የሚሰጠውን ምክር ተግባራዊ እያደረግህ መሆንህ ይሖዋ በግለሰብ ደረጃ ለአንተ ትኩረት እየሰጠህ መሆኑን የሚያሳይ ነው።​—ዮሐንስ 6:44

ላደርጋቸው ያሰብኳቸው ነገሮች

ከግል የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቴ የበለጠ ጥቅም ለማግኘት እንዲህ አደርጋለሁ፦ ․․․․․

አዘውትሮ የመጸለይ ልማድ እንዲኖረኝ እንዲህ አደርጋለሁ፦ ․․․․․

ከዚህ ርዕሰ ጉዳይ ጋር በተያያዘ ወላጆቼን ልጠይቃቸው የምፈልገው ነገር ․․․․․

ምን ይመስልሃል?

● የግል የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናትህ ይበልጥ አስደሳች እንዲሆን ምን ማድረግ ትችላለህ?

● ይሖዋ ፍጽምና የጎደላቸው የሰው ልጆች የሚያቀርቡትን ጸሎት ለመስማት የሚፈልገው ለምንድን ነው?

● የጸሎትህን ይዘት ማሻሻል የምትችለው እንዴት ነው?

[በገጽ 291 ላይ የሚገኝ የተቀነጨበ ሐሳብ]

ትንሽ ልጅ እያለሁ ጸሎቴ ሁልጊዜ ተመሳሳይ ነበር። አሁን ግን በእያንዳንዱ ቀን ስላጋጠሙኝ ጥሩም ሆነ መጥፎ ነገሮች አንስቼ ለመጸለይ እሞክራለሁ። እንዲህ ማድረጌ አሁንም አሁንም ተመሳሳይ ነገር እንዳልጸልይ ረድቶኛል፤ ምክንያቱም አንዱ ቀን ከሌላው የተለየ ነው።”​—ኢቭ

[በገጽ 292 ላይ የሚገኝ ሣጥን/​ሥዕል]

 መጽሐፍ ቅዱስህን መርምር

1. ልታነብ የምትፈልገውን አንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ታሪክ ምረጥ። የምታነበውን ለመረዳት የሚያስችልህ ጥበብ እንዲሰጥህ ወደ ይሖዋ ጸልይ።

2. ታሪኩን በትኩረት አንብበው። ተረጋግተህ አንብብ። ታሪኩን በምታነብበት ጊዜ ሁኔታውን በዓይነ ሕሊናህ ሳለው። በቦታው እንዳለህ አድርገህ በማሰብ የሚከናወነውን ነገር ለማየት፣ ባለታሪኮቹ ሲነጋገሩ ለመስማት፣ አካባቢውን ያወደውን መዓዛ ለማሽተት እንዲሁም የቀረበውን ምግብ ለማጣጣም ሞክር። ታሪኩ ሕያው ሆኖ ይታይህ!

3. ያነበብከውን ነገር ቆም ብለህ አስብበት። ራስህን እንዲህ እያልክ ጠይቅ፦

● ይሖዋ ይህን ታሪክ በቃሉ ውስጥ እንዲሰፍር ያደረገው ለምንድን ነው?

● በታሪኩ ውስጥ ከተጠቀሱት መካከል ልከተለው የሚገባኝ የማንን ምሳሌ ነው? የማስጠንቀቂያ ምሳሌ የሚሆኑትስ እነማን ናቸው?

● ከዚህ ምንባብ ምን ጠቃሚ ትምህርት ማግኘት እችላለሁ?

● ይህ ታሪክ ስለ ይሖዋና እሱ ነገሮችን ስለሚያከናውንበት መንገድ ምን ያስተምረኛል?

4. ወደ ይሖዋ አጠር ያለ ጸሎት አቅርብ። ከመጽሐፍ ቅዱስ ጥናትህ ምን ቁም ነገር እንዳገኘህ እንዲሁም ትምህርቱን በሕይወትህ ውስጥ እንዴት ተግባራዊ ለማድረግ እንዳሰብክ ንገረው። ይሖዋን ለሰጠህ ስጦታ ይኸውም ለቃሉ ለመጽሐፍ ቅዱስ ምንጊዜም አመስግነው!

[ሥዕል]

“ሕግህ ለእግሬ መብራት፣ ለመንገዴም ብርሃን ነው።”​—መዝሙር 119:105

[በገጽ 294 ላይ የሚገኝ ሣጥን/​ሥዕል]

ቅድሚያ ለሚገባው ቅድሚያ ስጥ

ለመጸለይና መጽሐፍ ቅዱስን ለማጥናት ጊዜ አጥተሃል? ብዙውን ጊዜ ለእነዚህ ነገሮች ጊዜ ማግኘትህ ወይም አለማግኘትህ የተመካው ‘ለየትኞቹ ነገሮች ቅድሚያ ትሰጣለህ?’ ለሚለው ጥያቄ በምትሰጠው መልስ ላይ ነው።

ሙከራ፦ አንድ ባልዲ ውስጥ በርከት ያሉ ትላልቅ ድንጋዮች ጨምር። ከዚያም ባልዲው የቻለውን ያህል አሸዋ ሙላው። አሁን ባልዲው በድንጋይ እና በአሸዋ ተሞልቷል።

ቀጥለህ ደግሞ ባልዲውን በመገልበጥ አሸዋውንና ድንጋዩን ለየብቻ አስቀምጠው። አሁን ከበፊቱ በተቃራኒ መጀመሪያ አሸዋውን ባልዲው ውስጥ ጨምረው፤ ከዚያም ድንጋዮቹን ክተት። ሁሉንም ድንጋዮች ለመጨመር ቦታ አነሰህ አይደል? ይህ የሆነው ባልዲው ውስጥ መጀመሪያ አሸዋውን በመጨመርህ ነው።

ከዚህ የምናገኘው ትምህርት ምንድን ነው? መጽሐፍ ቅዱስ “ይበልጥ አስፈላጊ የሆኑትን ነገሮች ለይታችሁ [እወቁ]” ይላል። (ፊልጵስዩስ 1:10) እንደ መዝናኛ ላሉት ትናንሽ ነገሮች ቅድሚያ ከሰጠህ ትልልቅ ለሆኑት ነገሮች ይኸውም ለመንፈሳዊ ጉዳዮች በቂ ጊዜ አይኖርህም። በሌላ በኩል ግን የመጽሐፍ ቅዱስን ምክር ተግባራዊ ካደረግህ ከመንግሥቱ ጋር ለተያያዙ ጉዳዮችም ሆነ በተወሰነ መጠን ለመዝናናት ጊዜ ይኖርሃል። ጊዜ ማግኘትህ የተመካው ባልዲው ውስጥ መጀመሪያ በምትጨምረው ይኸውም በሕይወትህ ውስጥ ቅድሚያ በምትሰጠው ነገር ላይ ነው!

[በገጽ 290 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

አንድ አበባ ለማደግ እንክብካቤ እንደሚያስፈልገው ሁሉ ከአምላክ ጋር የመሠረትከው ወዳጅነትም እንዲጠናከር ጥረት ማድረግ ይኖርብሃል