የሉቃስ ወንጌል 20:1-47

  • የኢየሱስን ሥልጣን ተገዳደሩ (1-8)

  • ነፍሰ ገዳይ የሆኑት ገበሬዎች ምሳሌ (9-19)

  • ‘የቄሳርን ለቄሳር፣ የአምላክን ለአምላክ’ (20-26)

  • ትንሣኤን በተመለከተ የቀረበ ጥያቄ (27-40)

  • ክርስቶስ የዳዊት ልጅ ነው? (41-44)

  • “ከጸሐፍት ተጠንቀቁ” (45-47)

20  አንድ ቀን ኢየሱስ በቤተ መቅደሱ ውስጥ ሕዝቡን እያስተማረና ምሥራቹን እያወጀ ሳለ የካህናት አለቆችና ጸሐፍት ከሕዝቡ ሽማግሌዎች ጋር መጡ፤ 2  ከዚያም “እስቲ ንገረን፤ እነዚህን ነገሮች የምታደርገው በምን ሥልጣን ነው? ይህን ሥልጣን የሰጠህስ ማን ነው?” አሉት።+ 3  እሱም መልሶ እንዲህ አላቸው፦ “እኔም አንድ ጥያቄ እጠይቃችኋለሁ፤ እናንተም መልሱልኝ፦ 4  ዮሐንስ የማጥመቅ ሥልጣን ያገኘው ከአምላክ* ነው ወይስ ከሰው?” 5  እነሱም እርስ በርሳቸው እንዲህ ተባባሉ፦ “‘ከአምላክ’ ብንል ‘ታዲያ ለምን አላመናችሁትም?’ ይለናል፤ 6  ‘ከሰው’ ብንል ደግሞ ሕዝቡ ሁሉ ዮሐንስ ነቢይ ነው ብለው ስለሚያምኑ+ በድንጋይ ይወግሩናል።” 7  ስለዚህ ‘ከየት እንደሆነ አናውቅም’ ብለው መለሱለት። 8  ኢየሱስም “እኔም እነዚህን ነገሮች በምን ሥልጣን እንደማደርግ አልነግራችሁም” አላቸው። 9  ከዚያም ለሕዝቡ የሚከተለውን ምሳሌ ይነግራቸው ጀመር፦ “አንድ ሰው የወይን እርሻ+ አለማና ለገበሬዎች አከራየ፤ ወደ ሌላ አገር ሄዶም ረዘም ላለ ጊዜ ቆየ።+ 10  ወቅቱ ሲደርስ ከወይኑ ፍሬ ድርሻውን እንዲልኩለት አንድ ባሪያ ወደ ገበሬዎቹ ላከ። ይሁንና ገበሬዎቹ ባሪያውን ከደበደቡት በኋላ ባዶ እጁን ሰደዱት።+ 11  እሱ ግን በድጋሚ ሌላ ባሪያ ወደ እነሱ ላከ። ይሄኛውንም ደብድበውና አዋርደው* ባዶ እጁን ሰደዱት። 12  አሁንም ሦስተኛ ባሪያ ላከ፤ እሱንም ካቆሰሉት በኋላ አውጥተው ጣሉት። 13  በዚህ ጊዜ የወይን እርሻው ባለቤት ‘ምን ባደርግ ይሻላል? የምወደውን ልጄን+ እልካለሁ። መቼም እሱን ያከብሩታል’ አለ። 14  ገበሬዎቹ ልጁን ባዩት ጊዜ እርስ በርሳቸው ‘ወራሹ ይሄ ነው። ርስቱ የእኛ እንዲሆን እንግደለው’ ተባባሉ። 15  ከዚያም ከወይን እርሻው ጎትተው በማውጣት ገደሉት።+ ታዲያ የወይኑ እርሻ ባለቤት ምን የሚያደርጋቸው ይመስላችኋል? 16  ይመጣና እነዚህን ገበሬዎች ይገድላል፤ የወይን እርሻውንም ለሌሎች ይሰጣል።” ሕዝቡም ይህን ሲሰሙ “ይህስ ከቶ አይሁን!” አሉ። 17  ኢየሱስም እነሱን ትኩር ብሎ በመመልከት እንዲህ አለ፦ “ታዲያ ‘ግንበኞች የናቁት ድንጋይ እሱ የማዕዘን ራስ ድንጋይ* ሆነ’+ ተብሎ የተጻፈው ትርጉሙ ምንድን ነው? 18  በዚህ ድንጋይ ላይ የሚወድቅ ሁሉ ይሰባበራል።+ ድንጋዩ የሚወድቅበት ሰው ሁሉ ደግሞ ይደቅቃል።” 19  በዚህ ጊዜ ጸሐፍትና የካህናት አለቆች ይህን ምሳሌ የተናገረው እነሱን አስቦ እንደሆነ ስለተረዱ በዚያኑ ሰዓት ሊይዙት ፈለጉ፤ ሆኖም ሕዝቡን ፈሩ።+ 20  በቅርብ ሲከታተሉት ከቆዩ በኋላ በንግግሩ እንዲያጠምዱት ጻድቅ መስለው የሚቀርቡ ሰዎችን በድብቅ ቀጥረው ላኩ፤+ ይህን ያደረጉት ለመንግሥትና ለአገረ ገዢው* አሳልፈው ለመስጠት ነው። 21  የተላኩትም ሰዎች እንዲህ ሲሉ ጠየቁት፦ “መምህር፣ አንተ ትክክለኛውን ነገር እንደምትናገርና እንደምታስተምር እንዲሁም እንደማታዳላ፣ ከዚህ ይልቅ የአምላክን መንገድ በእውነት እንደምታስተምር እናውቃለን፦ 22  ለመሆኑ ለቄሳር ግብር መክፈል ይገባናል ወይስ አይገባንም?”* 23  እሱ ግን ተንኮላቸው ገብቶት እንዲህ አላቸው፦ 24  “እስቲ አንድ ዲናር* አሳዩኝ። በላዩ ላይ ያለው ምስልና የተቀረጸው ጽሑፍ የማን ነው?” እነሱም “የቄሳር” አሉ። 25  እሱም “እንግዲያው የቄሳር የሆነውን ለቄሳር፣+ የአምላክ የሆነውን ደግሞ ለአምላክ+ ስጡ” አላቸው። 26  እነሱም በሕዝቡ ፊት በንግግሩ ሊያጠምዱት አልቻሉም፤ ከዚህ ይልቅ በመልሱ በመገረም ዝም አሉ። 27  ሆኖም በትንሣኤ ከማያምኑት+ ሰዱቃውያን መካከል አንዳንዶቹ መጥተው ጥያቄ አቀረቡለት፦+ 28  “መምህር፣ ሙሴ ‘አንድ ሰው ሚስት አግብቶ ልጅ ሳይወልድ ቢሞት ወንድሙ ሚስትየዋን አግብቶ ለወንድሙ ዘር መተካት አለበት’ ብሎ ጽፎልናል።+ 29  እንግዲህ ሰባት ወንድማማቾች ነበሩ። የመጀመሪያው ሚስት አገባ፤ ሆኖም ልጅ ሳይወልድ ሞተ። 30  ሁለተኛውም እንደዚሁ፤ 31  ሦስተኛውም አገባት። በዚሁ አኳኋን ሰባቱም አግብተዋት ልጆች ሳይወልዱ ሞቱ። 32  በመጨረሻም ሴትየዋ ሞተች። 33  እንግዲህ ሰባቱም ስላገቧት በትንሣኤ ለየትኛው ሚስት ትሆናለች?” 34  ኢየሱስ እንዲህ አላቸው፦ “የዚህ ሥርዓት* ልጆች ያገባሉ እንዲሁም ይዳራሉ፤ 35  ሆኖም የሚመጣውን ሥርዓት መውረስና የሙታን ትንሣኤን ማግኘት የሚገባቸው አያገቡም እንዲሁም አይዳሩም።+ 36  እንዲያውም እንደ መላእክት ስለሆኑ ከዚያ በኋላ ሊሞቱ አይችሉም፤ የትንሣኤ ልጆች ስለሆኑም የአምላክ ልጆች ናቸው። 37  ይሁንና ሙሴም እንኳ ስለ ቁጥቋጦው በሚገልጸው ታሪክ ላይ ይሖዋን* ‘የአብርሃም አምላክ፣ የይስሐቅ አምላክና የያዕቆብ አምላክ’+ ብሎ በጠራው ጊዜ ሙታን እንደሚነሡ አስታውቋል። 38  እሱ የሕያዋን እንጂ የሙታን አምላክ አይደለም፤ በእሱ ፊት* ሁሉም ሕያዋን ናቸውና።”+ 39  በዚህ ጊዜ አንዳንድ ጸሐፍት “መምህር፣ ጥሩ ብለሃል” አሉ። 40  ከዚያ በኋላ አንድም ጥያቄ ሊጠይቁት አልደፈሩም። 41  እሱ ደግሞ እንዲህ ሲል ጠየቃቸው፦ “ሰዎች ክርስቶስ የዳዊት ልጅ ነው እንዴት ይላሉ?+ 42  ምክንያቱም ዳዊት ራሱ በመዝሙር መጽሐፍ ላይ እንዲህ ብሏል፦ ‘ይሖዋ* ጌታዬን እንዲህ ብሎታል፦ “በቀኜ ተቀመጥ፤ 43  ጠላቶችህን ለእግርህ መርገጫ እስከማደርግልህ ድረስ በቀኜ ሁን።”’+ 44  ስለዚህ ዳዊት ‘ጌታ’ ብሎ ጠርቶታል፤ ታዲያ እንዴት ልጁ ይሆናል?” 45  ከዚያም ሕዝቡ ሁሉ እየሰሙት ደቀ መዛሙርቱን እንዲህ አላቸው፦ 46  “ዘርፋፋ ልብስ ለብሰው መዞር ከሚወዱ፣ በገበያ ቦታ ሰዎች እጅ እንዲነሷቸው ከሚሹ እንዲሁም በምኩራብ ከፊት መቀመጥ፣* በራት ግብዣ ላይም የክብር ቦታ መያዝ ከሚፈልጉ+ ከጸሐፍት ተጠንቀቁ፤ 47  እነሱ የመበለቶችን ቤት* ያራቁታሉ፤ ለታይታ ብለውም* ጸሎታቸውን ያስረዝማሉ። እነዚህ የከፋ* ፍርድ ይጠብቃቸዋል።”

የግርጌ ማስታወሻዎች

ቃል በቃል “ከሰማይ።”
ወይም “አቃለው።”
ቃል በቃል “የማዕዘኑ ራስ።”
ቃል በቃል “ለአገረ ገዢው ሥልጣን።”
ወይም “ትክክል ነው ወይስ አይደለም?”
ለ14ን ተመልከት።
ወይም “የዚህ ዘመን።” የቃላት መፍቻውን ተመልከት።
ከተጨማሪው መረጃ ላይ ሀ5ን ተመልከት።
ወይም “ከእሱ አመለካከት አንጻር።”
ከተጨማሪው መረጃ ላይ ሀ5ን ተመልከት።
ወይም “በምኩራብ የተሻለውን መቀመጫ።”
ወይም “ንብረት።”
ወይም “ማሳበቢያ እንዲሆናቸውም።”
ወይም “ይበልጥ ከባድ የሆነ።”