የሉቃስ ወንጌል 24:1-53

  • ኢየሱስ ከሞት ተነሳ (1-12)

  • ወደ ኤማሁስ በሚወስደው መንገድ ላይ (13-35)

  • ኢየሱስ ለደቀ መዛሙርቱ ታየ (36-49)

  • ኢየሱስ ወደ ሰማይ አረገ (50-53)

24  ይሁን እንጂ በሳምንቱ የመጀመሪያ ቀን፣ ያዘጋጇቸውን ጥሩ መዓዛ ያላቸው ቅመሞች ይዘው ጠዋት በማለዳ ወደ መቃብሩ ሄዱ።+ 2  ሆኖም ድንጋዩ ከመቃብሩ ተንከባሎ አገኙት፤+ 3  ወደ ውስጥ ሲገቡም የጌታ ኢየሱስን አስከሬን አላገኙም።+ 4  በሁኔታው ግራ ተጋብተው እያሉ የሚያንጸባርቅ ልብስ የለበሱ ሁለት ሰዎች ድንገት አጠገባቸው ቆሙ። 5  ሴቶቹ ፈርተው ወደ መሬት አቀርቅረው ሳሉ ሰዎቹ እንዲህ አሏቸው፦ “ሕያው የሆነውን ለምን ከሙታን መካከል ትፈልጉታላችሁ?+ 6  እሱ እዚህ የለም፤ ከሞት ተነስቷል። ገና በገሊላ በነበረበት ጊዜ ምን እንዳላችሁ አስታውሱ፤ 7  ‘የሰውን ልጅ ለኃጢአተኞች አሳልፈው ሊሰጡት፣ በእንጨት ላይ ሊሰቀልና በሦስተኛው ቀን ሊነሳ ይገባል’ ብሎ ነበር።”+ 8  በዚህ ጊዜ ሴቶቹ የተናገረውን ቃል አስታወሱ፤+ 9  ከዚያም መቃብሩ ካለበት ስፍራ ተመልሰው እነዚህን ነገሮች በሙሉ ለአሥራ አንዱና ለቀሩት ሁሉ ነገሯቸው።+ 10  እነሱም መግደላዊቷ ማርያም፣ ዮሐናና የያዕቆብ እናት ማርያም ነበሩ። ከእነሱ ጋር የነበሩት ሌሎቹ ሴቶችም እነዚህን ነገሮች ለሐዋርያት ነገሯቸው። 11  ይሁን እንጂ እንዲሁ የሚቀባጥሩ ስለመሰላቸው ሴቶቹ የሚናገሩትን አላመኗቸውም። 12  ጴጥሮስ ግን ተነስቶ ወደ መቃብሩ ሮጠ፤ ጎንበስ ብሎም ወደ ውስጥ ሲመለከት በፍታውን ብቻ አየ። በሆነውም ነገር እየተገረመ ከዚያ ሄደ። 13  ይሁንና በዚያው ቀን ከመካከላቸው ሁለቱ ከኢየሩሳሌም አሥራ አንድ ኪሎ ሜትር* ያህል ርቃ ወደምትገኝ ኤማሁስ ወደምትባል መንደር እየተጓዙ ነበር፤ 14  እነሱም ስለሆነው ነገር ሁሉ እርስ በርሳቸው እየተነጋገሩ ነበር። 15  ስለዚህ ጉዳይ እየተነጋገሩና እየተወያዩ ሳሉም ኢየሱስ ራሱ ቀርቦ አብሯቸው መሄድ ጀመረ፤ 16  ሆኖም ማንነቱን እንዳይለዩ ዓይናቸው ተጋርዶ ነበር።+ 17  እሱም “እየተጓዛችሁ እንዲህ እርስ በርስ የምትወያዩበት ጉዳይ ምንድን ነው?” አላቸው። በዚህ ጊዜ በሐዘን እንደተዋጡ ባሉበት ቆሙ። 18  ቀለዮጳ የተባለውም መልሶ “በኢየሩሳሌም ውስጥ ለብቻህ የምትኖር እንግዳ ሰው ነህ እንዴ? ሰሞኑን በዚያ የተፈጸመውን ነገር አታውቅም ማለት ነው?”* አለው። 19  እሱም “ምን ተፈጸመ?” አላቸው። እነሱም እንዲህ አሉት፦ “በአምላክና በሰው ሁሉ ፊት በሥራም ሆነ በቃል ኃያል ነቢይ ከሆነው ከናዝሬቱ ኢየሱስ+ ጋር በተያያዘ የተፈጸመው ነገር ነዋ!+ 20  የካህናት አለቆቻችንና ገዢዎቻችን ለሞት ፍርድ አሳልፈው ሰጡት፤+ እንዲሁም በእንጨት ላይ ቸነከሩት። 21  እኛ ግን ይህ ሰው እስራኤልን ነፃ ያወጣል ብለን ተስፋ አድርገን ነበር።+ ከዚህም በላይ ይህ ነገር ከተፈጸመ እነሆ ዛሬ ሦስተኛ ቀኑ ነው። 22  ደግሞም ከእኛው መካከል አንዳንድ ሴቶች በማለዳ ወደ መቃብሩ ሄደው ስለነበር+ የሚያስገርም ነገር ነገሩን፤ 23  አስከሬኑንም ባጡ ጊዜ ተመልሰው መጥተው በተአምር የተገለጡላቸውንና እሱ ሕያው እንደሆነ የነገሯቸውን መላእክት እንዳዩ ነገሩን። 24  ከዚያም ከእኛ መካከል አንዳንዶች ወደ መቃብሩ ሄደው ነበር፤+ እነሱም ሴቶቹ እንደተናገሩት ሆኖ አገኙት፤ እሱን ግን አላዩትም።” 25  እሱም እንዲህ አላቸው፦ “እናንተ ማስተዋል የጎደላችሁና ነቢያት የተናገሩትን ሁሉ ከማመን ልባችሁ የዘገየ! 26  ክርስቶስ እነዚህን መከራዎች መቀበልና+ ክብር ማግኘት አይገባውም?”+ 27  ከዚያም ከሙሴና ከነቢያት ሁሉ+ ጀምሮ ስለ እሱ በቅዱሳን መጻሕፍት ሁሉ የተጻፈውን በሚገባ አብራራላቸው። 28  በመጨረሻም ወደሚሄዱበት መንደር ተቃረቡ፤ ይሁንና እሱ አልፎ የሚሄድ ይመስል ነበር። 29  እነሱ ግን “ቀኑ እየተገባደደና ምሽቱ እየተቃረበ ስለሆነ እኛ ጋ እደር” ብለው አጥብቀው ለመኑት። እሱም እነሱ ጋ ለማደር ገባ። 30  ከእነሱ ጋር እየበላ ሳለም ዳቦውን አንስቶ ባረከ፤ ቆርሶም ይሰጣቸው ጀመር።+ 31  በዚህ ጊዜ ዓይናቸው ሙሉ በሙሉ ተከፈተና ማን መሆኑን በሚገባ አወቁ፤ እሱ ግን ከአጠገባቸው ተሰወረ።+ 32  እነሱም እርስ በርሳቸው “በመንገድ ላይ ሲያነጋግረንና ቅዱሳን መጻሕፍትን በሚገባ ሲገልጥልን* ልባችን እንደ እሳት ይቃጠልብን አልነበረም?” ተባባሉ። 33  በዚያኑም ሰዓት ተነስተው ወደ ኢየሩሳሌም ተመለሱ፤ አሥራ አንዱንና ከእነሱ ጋር የነበሩትንም አንድ ላይ ተሰብስበው አገኟቸው፤ 34  እነሱም “ጌታ በእርግጥ ተነስቷል፤ ለስምዖንም ተገልጦለታል!” ይሉ ነበር።+ 35  ሁለቱ ደግሞ በመንገድ ላይ ያጋጠማቸውን ነገርና ዳቦውን በቆረሰበት+ ጊዜ እንዴት እንዳወቁት ተረኩላቸው። 36  እነዚህን ነገሮች እየተነጋገሩ ሳለ እሱ ራሱ በመካከላቸው ቆመ፤ ከዚያም “ሰላም ለእናንተ ይሁን” አላቸው።+ 37  እነሱ ግን ከመደንገጣቸውና ከመፍራታቸው የተነሳ መንፈስ ያዩ መሰላቸው። 38  በዚህ ጊዜ እንዲህ አላቸው፦ “ለምን ትረበሻላችሁ? ለምንስ በልባችሁ ውስጥ ጥርጣሬ ያድራል? 39  እኔ ራሴ መሆኔን እንድታውቁ እጆቼንና እግሮቼን ተመልከቱ፤ ደግሞም ዳስሳችሁኝ እዩ፤ መንፈስ በእኔ ላይ እንደምታዩት ሥጋና አጥንት የለውምና።” 40  ይህን እያለም እጆቹንና እግሮቹን አሳያቸው። 41  እነሱ ግን በጣም ከመደሰታቸው የተነሳ ለማመን ተቸግረው በነገሩ እየተገረሙ ሳሉ “የሚበላ ነገር አላችሁ?” አላቸው። 42  እነሱም የተጠበሰ ቁራሽ ዓሣ ሰጡት፤ 43  እሱም ተቀብሎ በፊታቸው በላ። 44  ከዚያም እንዲህ አላቸው፦ “ከእናንተ ጋር በነበርኩበት ጊዜ ‘በሙሴ ሕግ፣ በነቢያትና በመዝሙራት ስለ እኔ የተጻፉት ነገሮች ሁሉ+ መፈጸም አለባቸው’ ብዬ የነገርኳችሁ ቃሌ ይህ ነው።”+ 45  ከዚያም የቅዱሳን መጻሕፍትን ትርጉም መረዳት እንዲችሉ አእምሯቸውን ከፈተላቸው፤+ 46  እንዲህም አላቸው፦ “እንደሚከተለው ተብሎ ተጽፏል፤ ክርስቶስ መከራ ይቀበላል፤ በሦስተኛውም ቀን ከሞት ይነሳል፤+ 47  በስሙም የኃጢአት ይቅርታ የሚያስገኝ+ ንስሐ ከኢየሩሳሌም አንስቶ+ ለብሔራት ሁሉ ይሰበካል።+ 48  እናንተም ለእነዚህ ነገሮች ምሥክር ትሆናላችሁ።+ 49  እኔም አባቴ ቃል የገባውን ነገር እልክላችኋለሁ። እናንተ ግን ከላይ የሚመጣውን ኃይል እስክትለብሱ+ ድረስ በከተማዋ ውስጥ ቆዩ።” 50  ከዚያም እስከ ቢታንያ ይዟቸው ሄደ፤ እጆቹንም አንስቶ ባረካቸው። 51  እየባረካቸውም ሳለ ከእነሱ ተለይቶ ወደ ሰማይ ተወሰደ።+ 52  እነሱም ሰገዱለት፤* ከዚያም በታላቅ ደስታ ወደ ኢየሩሳሌም ተመለሱ።+ 53   ዘወትር በቤተ መቅደስ እየተገኙም አምላክን ያወድሱ ነበር።+

የግርጌ ማስታወሻዎች

ቃል በቃል “60 ስታዲዮን።” አንድ ስታዲዮን 185 ሜትር ነው። ለ14ን ተመልከት።
“ሰሞኑን በኢየሩሳሌም የተፈጸሙትን ነገሮች የማታውቅ እንግዳ አንተ ብቻ ነህ?” ማለትም ሊሆን ይችላል።
ወይም “በግልጽ ሲያብራራልን።”
ወይም “እጅ ነሱት።”