መዝሙር 139:1-24
ለሙዚቀኞች ቡድን መሪ። የዳዊት መዝሙር። ማህሌት።
139 ይሖዋ ሆይ፣ በሚገባ መርምረኸኛል፤ ደግሞም ታውቀኛለህ።+
2 አንተ ስቀመጥም ሆነ ስነሳ ታውቃለህ።+
ሐሳቤን ከሩቅ ታስተውላለህ።+
3 ስጓዝም ሆነ ስተኛ በሚገባ ታየኛለህ፤መንገዶቼን ሁሉ ታውቃለህ።+
4 ይሖዋ ሆይ፣ ገና ቃል ከአፌ ሳይወጣ፣እነሆ፣ አንተ ሁሉን ነገር አስቀድመህ በሚገባ ታውቃለህ።+
5 ከኋላም ከፊትም ከበብከኝ፤እጅህንም በላዬ ላይ ታደርጋለህ።
6 እንዲህ ያለው እውቀት እኔ ልረዳው ከምችለው በላይ ነው።*
በጣም ከፍ ያለ ከመሆኑ የተነሳ ልደርስበት አልችልም።*+
7 ከመንፈስህ ወዴት ላመልጥ እችላለሁ?ከፊትህስ ወዴት ልሸሽ እችላለሁ?+
8 ወደ ሰማይ ብወጣ አንተ በዚያ አለህ፤በመቃብር* አልጋዬን ባነጥፍም እነሆ፣ አንተ በዚያ ትኖራለህ።+
9 እጅግ ርቆ በሚገኝ ባሕር አቅራቢያ ለመኖር፣በንጋት ክንፍ ብበር፣
10 በዚያም እንኳ እጅህ ትመራኛለች፤ቀኝ እጅህም ትይዘኛለች።+
11 “በእርግጥ ጨለማ ይሰውረኛል!” ብል፣
በዚያን ጊዜ በዙሪያዬ ያለው ሌሊት ብርሃን ይሆናል።
12 ጨለማው ለአንተ አይጨልምብህም፤ይልቁንም ሌሊቱ እንደ ቀን ብሩህ ይሆናል፤+ጨለማ ለአንተ እንደ ብርሃን ነው።+
13 አንተ ኩላሊቴን ሠርተሃልና፤በእናቴ ማህፀን ውስጥ ጋርደህ አስቀመጥከኝ።*+
14 በሚያስደምም ሁኔታ ግሩምና ድንቅ ሆኜ ስለተፈጠርኩ+ አወድስሃለሁ።
ሥራዎችህ አስደናቂ ናቸው፤+ይህን በሚገባ አውቃለሁ።*
15 በስውር በተሠራሁ ጊዜ፣በማህፀን ውስጥ እያደግኩ በነበረበት ወቅት፣*አጥንቶቼ ከአንተ አልተሰወሩም ነበር።+
16 ፅንስ እያለሁ እንኳ ዓይኖችህ አዩኝ፤የአካሌ ክፍሎች በሙሉ በመጽሐፍህ ተጻፉ፤አንዳቸውም ወደ ሕልውና ከመምጣታቸው በፊት፣የተሠሩባቸውን ቀኖች በተመለከተ በዝርዝር ተጻፈ።
17 ሐሳቦችህ ለእኔ ምንኛ ውድ ናቸው!+
አምላክ ሆይ፣ ቁጥራቸው ምንኛ ብዙ ነው!+
18 ልቆጥራቸው ብሞክር ከአሸዋ ይልቅ ይበዛሉ።+
ከእንቅልፌ ስነቃም ገና ከአንተው ጋር ነኝ።*+
19 አምላክ ሆይ፣ ምነው ክፉውን በገደልከው!+
በዚያን ጊዜ ጨካኞች* ከእኔ ይርቁ ነበር፤
20 እነሱ በተንኮል ተነሳስተው በአንተ ላይ ክፉ ነገር* ይናገራሉ፤ስምህን በከንቱ የሚያነሱ ጠላቶችህ ናቸው።+
21 ይሖዋ ሆይ፣ አንተን የሚጠሉትን እጠላ የለም?+በአንተ ላይ የሚያምፁትንስ እጸየፍ የለም?+
22 እጅግ ጠላኋቸው፤+ለእኔ የለየላቸው ጠላቶች ሆነዋል።
23 አምላክ ሆይ፣ በሚገባ ፈትሸኝ፤ ልቤንም እወቅ።+
መርምረኝ፤ የሚያስጨንቁኝንም* ሐሳቦች እወቅ።+
24 በውስጤ ጎጂ የሆነ ዝንባሌ ካለ እይ፤+በዘላለምም መንገድ ምራኝ።+
የግርጌ ማስታወሻዎች
^ ወይም “ለእኔ እጅግ አስደናቂ ነው።”
^ ወይም “ከመረዳት አቅሜ በላይ ነው።”
^ ወይም “በሲኦል።” የሰው ልጆችን ሁሉ መቃብር ያመለክታል። የቃላት መፍቻውን ተመልከት።
^ “አበጃጅተህ ሠራኸኝ” ማለትም ሊሆን ይችላል።
^ ወይም “ነፍሴ ይህን በሚገባ ታውቃለች።”
^ ቃል በቃል “ጥልቅ በሆኑ የምድር ክፍሎች ውስጥ በተሸመንኩ ጊዜ።”
^ “ገና እየቆጠርኳቸው እገኛለሁ” ማለትም ሊሆን ይችላል።
^ ወይም “የደም ዕዳ ያለባቸው ሰዎች።”
^ ወይም “የመሰላቸውን።”
^ ወይም “እረፍት የሚነሱኝንም።”