ምሳሌ 12:1-28
12 ተግሣጽን የሚወድ እውቀትን ይወዳል፤+ወቀሳን የሚጠላ ግን የማመዛዘን ችሎታ* ይጎድለዋል።+
2 ጥሩ ሰው የይሖዋን ሞገስ ያገኛል፤ክፋት የሚያሴርን ሰው ግን እሱ ይፈርድበታል።+
3 በክፋት ጸንቶ መቆም የሚችል ሰው የለም፤+ጻድቅ ግን ፈጽሞ አይነቀልም።
4 ጥሩ ሚስት ለባሏ ዘውድ ናት፤+አሳፋሪ* ሚስት ግን አጥንቱ ውስጥ እንዳለ ንቅዘት ናት።+
5 የጻድቃን ሐሳብ ፍትሐዊ ነው፤የክፉዎች ምክር ግን አሳሳች ነው።
6 የክፉዎች ቃል ገዳይ ወጥመድ ነው፤*+የቅኖች አፍ ግን ይታደጋቸዋል።+
7 ክፉዎች ሲገለበጡ ደብዛቸው ይጠፋል፤የጻድቃን ቤት ግን ጸንቶ ይኖራል።+
8 ሰው አስተዋይ በሆነ አንደበቱ ይመሰገናል፤+ልቡ ጠማማ የሆነ ግን ይናቃል።+
9 የሚበላው* ሳይኖረው ራሱን ከፍ ከፍ ከሚያደርግ ሰው ይልቅአገልጋይ ኖሮት ራሱን ዝቅ አድርጎ የሚኖር ሰው ይሻላል።+
10 ጻድቅ የቤት እንስሳቱን* ይንከባከባል፤+ክፉዎች ግን ርኅራኄያቸው እንኳ ጭካኔ ነው።
11 መሬቱን የሚያርስ ሰው የተትረፈረፈ ምግብ ያገኛል፤+ከንቱ ነገሮችን የሚያሳድድ ግን ማስተዋል* ይጎድለዋል።
12 ክፉ ሰው፣ ሌሎች መጥፎ ሰዎች ባጠመዱት ነገር ይቀናል፤የጻድቃን ሥር ግን ፍሬ ያፈራል።
13 መጥፎ ሰው በክፉ ንግግሩ ይጠመዳል፤+ጻድቅ ግን ከመከራ ያመልጣል።
14 ሰው ከአፉ ፍሬ መልካም ነገር ይጠግባል፤+የእጁ ሥራም ብድራት ይከፍለዋል።
15 የሞኝ መንገድ በራሱ ዓይን ትክክል ነው፤+ጥበበኛ ግን ምክር ይቀበላል።+
16 ሞኝ ሰው ቁጣውን ወዲያውኑ* ይገልጻል፤+ብልህ ሰው ግን ስድብን ችላ ብሎ ያልፋል።*
17 ታማኝ ምሥክር እውነቱን* ይናገራል፤ውሸታም ምሥክር ግን ያታልላል።
18 ሳይታሰብበት የሚነገር ቃል እንደ ሰይፍ ይወጋል፤የጥበበኞች ምላስ ግን ፈውስ ነው።+
19 እውነት የሚናገሩ ከንፈሮች ለዘላለም ጸንተው ይኖራሉ፤+ሐሰተኛ ምላስ ግን የሚቆየው ለቅጽበት ብቻ ነው።+
20 ተንኮል በሚሸርቡ ሰዎች ልብ ውስጥ ማታለያ አለ፤ሰላምን የሚያራምዱ* ግን ደስተኞች ናቸው።+
21 ጻድቅ ምንም ዓይነት ጉዳት አያገኘውም፤+የክፉዎች ሕይወት ግን በመከራ የተሞላ ይሆናል።+
22 ይሖዋ ውሸታም ከንፈሮችን ይጸየፋል፤+በታማኝነት የሚመላለሱ ግን ደስ ያሰኙታል።
23 ብልህ ሰው እውቀቱን ይሰውራል፤የሞኝ ልብ ግን ሞኝነቱን ይዘከዝካል።+
24 የትጉ ሰዎች እጅ ገዢ ትሆናለች፤+ሥራ ፈት እጆች ግን ለባርነት ይዳረጋሉ።+
25 በሰው ልብ ውስጥ ያለ ጭንቀት ልቡ እንዲዝል ያደርገዋል፤*+መልካም ቃል ግን ደስ ያሰኘዋል።+
26 ጻድቅ የግጦሽ መሬቱን በሚገባ ይቃኛል፤የክፉዎች መንገድ ግን እንዲባዝኑ ያደርጋቸዋል።
27 ሰነፍ ሰው አደኑን አሳድዶ አይዝም፤+ትጋት ግን የሰው ውድ ሀብት ነው።
28 የጽድቅ ጎዳና ወደ ሕይወት ይመራል፤+በጎዳናው ላይ ሞት የለም።
የግርጌ ማስታወሻዎች
^ ወይም “ማስተዋል።”
^ ወይም “አሳፋሪ ድርጊት የምትፈጽም።”
^ ቃል በቃል “ደም ለማፍሰስ ያደባል።”
^ ቃል በቃል “ዳቦ።”
^ ወይም “የቤት እንስሳቱን ነፍስ።”
^ ቃል በቃል “ልብ።”
^ ወይም “በዚያው ቀን።”
^ ቃል በቃል “ይሸፍናል።”
^ ቃል በቃል “ጽድቅ የሆነውን።”
^ ቃል በቃል “የሰላም አማካሪ የሆኑ።”
^ ወይም “የመንፈስ ጭንቀት ያስከትልበታል።”