ለዮሐንስ የተገለጠለት ራእይ 6:1-17
6 እኔም በጉ+ ከሰባቱ ማኅተሞች አንዱን ሲከፍት አየሁ፤+ ከአራቱ ሕያዋን ፍጥረታትም+ አንዱ እንደ ነጎድጓድ ባለ ድምፅ “ና!” ሲል ሰማሁ።
2 እኔም አየሁ፣ እነሆ ነጭ ፈረስ ነበር፤+ በእሱም ላይ የተቀመጠው ቀስት ነበረው፤ አክሊልም ተሰጠው፤+ እሱም ድል እያደረገ ወጣ፤ ድሉንም ለማጠናቀቅ ወደ ፊት ገሰገሰ።+
3 ሁለተኛውን ማኅተም በከፈተ ጊዜ ሁለተኛው ሕያው ፍጡር+ “ና!” ሲል ሰማሁ።
4 ደማቅ ቀይ ቀለም ያለው ሌላ ፈረስ ወጣ፤ በእሱም ላይ ለተቀመጠው ሰዎች እርስ በርሳቸው ይተራረዱ ዘንድ ሰላምን ከምድር እንዲወስድ ተፈቀደለት፤ እንዲሁም ትልቅ ሰይፍ ተሰጠው።+
5 ሦስተኛውን ማኅተም በከፈተ ጊዜ+ ሦስተኛው ሕያው ፍጡር+ “ና!” ሲል ሰማሁ። እኔም አየሁ፣ እነሆ ጥቁር ፈረስ ነበር፤ በእሱም ላይ የተቀመጠው በእጁ ሚዛን ይዞ ነበር።
6 ከአራቱ ሕያዋን ፍጥረታት መካከል እንደ ድምፅ ያለ ነገር “አንድ እርቦ* ስንዴ በዲናር፣*+ ሦስት እርቦ ገብስም በዲናር፤ ደግሞም የወይራ ዘይቱንና የወይን ጠጁን አትጉዳ” ሲል ሰማሁ።+
7 አራተኛውን ማኅተም በከፈተ ጊዜ አራተኛው ሕያው ፍጡር+ “ና!” ሲል ሰማሁ።
8 እኔም አየሁ፣ እነሆ ግራጫ ፈረስ ነበር፤ በእሱም ላይ የተቀመጠው ስሙ ሞት ነበር። መቃብርም* በቅርብ ይከተለው ነበር። ሞትና መቃብርም በረጅም ሰይፍ፣ በምግብ እጥረት፣+ በገዳይ መቅሰፍትና በምድር አራዊት እንዲገድሉ በምድር አንድ አራተኛ ላይ ሥልጣን ተሰጣቸው።+
9 አምስተኛውን ማኅተም በከፈተ ጊዜ በአምላክ ቃል የተነሳና በሰጡት ምሥክርነት የተነሳ የታረዱትን ሰዎች ነፍሳት*+ ከመሠዊያው በታች+ አየሁ።+
10 እነሱም “ቅዱስና እውነተኛ የሆንከው ሉዓላዊ ጌታ ሆይ፣+ በምድር በሚኖሩት ላይ የማትፈርደውና ደማችንን የማትበቀለው እስከ መቼ ነው?”+ ብለው በታላቅ ድምፅ ጮኹ።
11 ለእያንዳንዳቸውም ነጭ ልብስ ተሰጣቸው፤+ እንዲሁም ወደፊት እንደ እነሱ የሚገደሉት ባልንጀሮቻቸው የሆኑ ባሪያዎችና የወንድሞቻቸው ቁጥር እስኪሞላ ድረስ ለጥቂት ጊዜ እንዲጠብቁ ተነገራቸው።+
12 ስድስተኛውንም ማኅተም ሲከፍት አየሁ፤ ታላቅ የምድር ነውጥም ተከሰተ፤ ፀሐይም ከፀጉር* እንደተሠራ ማቅ ጠቆረች፤ ጨረቃም ሙሉ በሙሉ ደም መሰለች፤+
13 ኃይለኛ ነፋስ የበለስን ዛፍ ሲያወዛውዝ ያልበሰሉት ፍሬዎች ከዛፉ ላይ እንደሚረግፉ፣ የሰማይ ከዋክብትም ወደ ምድር ወደቁ።
14 ሰማይም እየተጠቀለለ እንዳለ የመጽሐፍ ጥቅልል ከቦታው ተነሳ፤+ እንዲሁም ተራሮች ሁሉና ደሴቶች ሁሉ ከቦታቸው ተወገዱ።+
15 ከዚያም የምድር ነገሥታት፣ ከፍተኛ ባለሥልጣናት፣ የጦር አዛዦች፣ ሀብታሞች፣ ብርቱዎች፣ ባሪያዎች ሁሉና ነፃ ሰዎች ሁሉ በዋሻዎች ውስጥና ተራራ ላይ ባሉ ዓለቶች መካከል ተደበቁ።+
16 ተራሮቹንና ዓለቶቹንም እንዲህ እያሉ ተማጸኑ፦ “በላያችን ውደቁና+ በዙፋኑ ላይ ከተቀመጠው+ ፊትና ከበጉ+ ቁጣ ሰውሩን፤
17 ምክንያቱም ቁጣቸውን የሚገልጹበት ታላቁ ቀን መጥቷል፤+ ማንስ ሊቆም ይችላል?”+
የግርጌ ማስታወሻዎች
^ ወይም “ሐዲስም።” የሰው ልጆችን ሁሉ መቃብር ያመለክታል። የቃላት መፍቻውን ተመልከት።
^ መሠዊያው ላይ የፈሰሰውን ለሕይወታቸው ወሳኝ የሆነውን ደማቸውን እንደሚያመለክት ግልጽ ነው። የቃላት መፍቻውን ተመልከት።
^ የፍየል ፀጉር ሳይሆን አይቀርም።