ሀ2
የዚህ ትርጉም ገጽታዎች
በ1950 የክርስቲያን ግሪክኛ ቅዱሳን መጻሕፍት አዲስ ዓለም ትርጉም በእንግሊዝኛ ቋንቋ ወጣ፤ በ1961 ደግሞ ሙሉው አዲስ ዓለም ትርጉም ታተመ። ይህ ትርጉም መጽሐፍ ቅዱስ መጀመሪያ በተጻፈባቸው ቋንቋዎች ሊተላለፍ የተፈለገውን ሐሳብ በትክክል ሆኖም ለማንበብ ቀላል በሆነ መንገድ አስቀምጦታል፤ በመሆኑም ከዚያን ጊዜ አንስቶ በብዙ ሚሊዮን የሚቆጠሩ አንባቢዎች ከ210 በላይ በሚሆኑ ቋንቋዎች ከታተመው ከዚህ ትርጉም ተጠቃሚዎች ሆነዋል።
የአዲስ ዓለም የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉም ኮሚቴ በዛሬው ጊዜ ያሉትን አንባቢዎች ልብ የሚነካ ቋንቋ መጠቀም አስፈላጊ መሆኑን ያምናል። በመሆኑም በዚህ ትርጉም ውስጥ የሚከተሉትን ነጥቦች ግምት ውስጥ ያስገቡ አንዳንድ የአጻጻፍ ስልቶችና የቃላት አጠቃቀሞች ሥራ ላይ ውለዋል፦
-
በአሁኑ ጊዜ የምንጠቀምባቸው ለመረዳት ቀላል የሆኑ ቃላት ጥቅም ላይ ውለዋል። ለምሳሌ ያህል፣ ብዙ የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉሞች የሚጠቀሙበት “ጋለሞታ” የሚለው ቃል “ዝሙት አዳሪ” በሚለው ተተክቷል።–ዘፍጥረት 38:15
-
የመጽሐፍ ቅዱስ ቃላት ግልጽ ተደርገዋል። አንዳንድ ቃላት አንባቢው ትርጉማቸውን በትክክል እንዲገነዘብ ለመርዳት ሲባል ይበልጥ ግልጽ ተደርገዋል። ለምሳሌ ያህል፣ የዕብራይስጡ ቃል “ሲኦል” እና የግሪክኛው ቃል “ሐዲስ” የሰው ልጆችን መቃብር ያመለክታሉ። ብዙዎች እነዚህን ቃላት እምብዛም የማያውቋቸው ከመሆኑም ሌላ አንዳንዶች “ሲኦል” የሚለውን ቃል በተሳሳተ መንገድ ይረዱታል፤ በተጨማሪም “ሐዲስ” የሚለው ቃል በግሪክ አፈ ታሪኮች ውስጥ በሌላ መንገድ ስለተሠራበት ቃሉ ሁለት ትርጉሞች አሉት። ስለሆነም ሁለቱም ቃላት የመጽሐፍ ቅዱስ ጸሐፊዎቹ ሊያስተላልፉት በፈለጉት ሐሳብ ይኸውም “መቃብር” በሚለው ቃል ተተክተዋል። በእነዚህ ቦታዎች ላይ “ሲኦል” እና “ሐዲስ” የሚሉት ቃላት የግርጌ ማስታወሻ ላይ እንዲቀመጡ ተደርጓል።–መዝሙር 16:10፤ የሐዋርያት ሥራ 2:27
ከዚህም በተጨማሪ ነፈሽ የሚለው የዕብራይስጥ ቃልና ፕስኺ የተባለው የግሪክኛ ቃል “ነፍስ” ተብሎ ሲተረጎም ቆይቷል። እነዚህ ቃላት እንደየአገባባቸው (1) ሰውን፣ (2) የአንድን ሰው ሕይወት፣ (3) ሕያዋን ፍጥረታትን (4) የአንድን ሰው ምኞትና ፍላጎት አልፎ ተርፎም (5) የሞተ ሰውን ሊያመለክቱ ይችላሉ። ይሁንና በአሁኑ ጊዜ “ነፍስ” የሚለውን ቃል ብዙ ሰዎች ስለማይጠቀሙበት ቃሉ እንደየአገባቡ በተለያየ መንገድ ተተርጉሟል፤ በተጨማሪም በአብዛኛው ቦታ ላይ “ወይም ‘ነፍስ’” የሚል የግርጌ ማስታወሻ ገብቶለታል። (ለምሳሌ ያህል፣ የሚከተሉትን ጥቅሶች ተመልከት፦ ዘፍጥረት 1:20፤ 2:7፤ ዘሌዋውያን 19:28፤ መዝሙር 3:2፤ ምሳሌ 16:26፤ ማቴዎስ 6:25) ያም ሆኖ ቅኔያዊ አነጋገሮች ባሉበት ቦታ ወይም የቃሉ አገባብ ግልጽ በሆነባቸው የተወሰኑ ጥቅሶች ላይ “ነፍስ” የሚለው ቃል እንዲገባ የተደረገ ሲሆን አንባቢውን ወደ ቃላት መፍቻው የሚመራ ወይም የቃሉን ሌላ ትርጉም የሚጠቁም የግርጌ ማስታወሻ ገብቶለታል።–ዘዳግም 6:5፤ መዝሙር 131:2፤ ምሳሌ 2:10፤ ማቴዎስ 22:37
ይህ ትርጉም ያሉት ሌሎች ገጽታዎች፦
ይህ የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉም የግርጌ ማስታወሻዎች አሉት። በጥቅሉ ሲታይ የግርጌ ማስታወሻዎቹ በሚከተሉት ምድቦች ውስጥ ሊካተቱ ይችላሉ፦
-
“ወይም” የዕብራይስጡ፣ የአረማይኩ ወይም የግሪክኛው ጽሑፍ ሊተረጎም የሚችልባቸውን ከሞላ ጎደል ተመሳሳይ ሐሳብ የሚያስተላልፉ አማራጭ አተረጓጎሞችን ይጠቁማል።–ዘፍጥረት 1:2፣ “የአምላክም ኃይል” በሚለው ሐረግ ላይ ያለው የግርጌ ማስታወሻ፤ ኢያሱ 1:8፣ “በለሆሳስ አንብበው።”
-
“‘. . .’ ማለትም ሊሆን ይችላል” ጽሑፉ ሊተረጎም የሚችልባቸውን፣ ተቀባይነት ያላቸው ሆኖም ለየት ያለ ሐሳብ የሚያስተላልፉ አማራጭ አተረጓጎሞችን ይጠቁማል።–ዘፍጥረት 21:6፣ “ከእኔ ጋር አብሮ ይስቃል”፤ ዘካርያስ 14:21፣ “ከነአናዊ”
-
“ቃል በቃል” የዕብራይስጡ፣ የአረማይኩ ወይም የግሪክኛው ጽሑፍ ቃል በቃል ሲተረጎም የሚያስተላልፈው ሐሳብ ወይም መጽሐፍ ቅዱስ የተጻፈባቸው የመጀመሪያዎቹ ቋንቋዎች የተጠቀሙበት አገላለጽ መሠረታዊ ትርጉም ምን እንደሆነ ይጠቁማል።–ዘፍጥረት 30:22፣ “መፀነስ እንድትችል በማድረግ”፤ ዘፀአት 32:9፣ “ግትር”
-
ትርጉምና ተጨማሪ መረጃ የስሞች ትርጉም (ዘፍጥረት 3:17 “አዳም”፤ ዘፀአት 15:23 “ማራ”)፣ የሚዛንና የመለኪያዎች መጠን (ዘፍጥረት 6:15 “ክንድ”) እንዲሁም ተውላጠ ስሙ ማንን እንደሚያመለክት (ዘፍጥረት 38:5 “እሱ”) የሚጠቁም የግርጌ ማስታወሻ ገብቶለታል። ተጨማሪው መረጃና የቃላት መፍቻውም ጠቃሚ መረጃዎች ይዘዋል።–ዘፍጥረት 37:35 “መቃብር”፤ ማቴዎስ 5:22 “ገሃነም”
በመጀመሪያዎቹ ገጾች ላይ የሚገኘው “ከአምላክ ቃል ጋር ተዋወቅ” የሚለው ርዕስ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚገኙትን መሠረታዊ ትምህርቶች ይዟል። ከመጨረሻው የመጽሐፍ ቅዱስ መጽሐፍ ቀጥሎ “የመጽሐፍ ቅዱስ መጻሕፍት ሰንጠረዥ፣” “የመጽሐፍ ቅዱስ ቃላት ማውጫ” እና “የመጽሐፍ ቅዱስ ቃላት መፍቻ” ይገኛሉ። የቃላት መፍቻው አንባቢው አንዳንድ የተመረጡ ቃላት በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ እንዴት እንደተሠራባቸው ለመረዳት ያስችለዋል። ተጨማሪ መረጃ ሀ የሚከተሉት ክፍሎች አሉት፦ “ለመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉም መሠረት ሆነው የሚያገለግሉ መመሪያዎች፣” “የዚህ ትርጉም ገጽታዎች፣” “መጽሐፍ ቅዱስ እስከ ዘመናችን ድረስ ተጠብቆ የቆየው እንዴት ነው?” “መለኮታዊው ስም በዕብራይስጥ ቅዱሳን መጻሕፍት ውስጥ፣” “መለኮታዊው ስም በክርስቲያን ግሪክኛ ቅዱሳን መጻሕፍት ውስጥ፣” “ሰንጠረዥ፦ የይሁዳና የእስራኤል ነቢያትና ነገሥታት” እና “የኢየሱስ ምድራዊ ሕይወት አበይት ክንውኖች።” ተጨማሪ መረጃ ለ ካርታዎችን፣ ሰንጠረዦችንና ትጉ የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎችን የሚረዱ ሌሎች ጠቃሚ መረጃዎችን ይዟል።
በእያንዳንዱ የመጽሐፍ ቅዱስ መጽሐፍ መጀመሪያ ላይ የምዕራፎቹን ይዘትና ሐሳቡ የሚገኝባቸውን ጥቅሶች የሚጠቁም መረጃ አለ። በእያንዳንዱ ገጽ መሃል ላይ ደግሞ ተመሳሳይ ሐሳብ የያዙ ጥቅሶችን የሚጠቁሙ በጣም ጠቃሚ የሆኑ ማጣቀሻዎች ይገኛሉ።