የሕይወት ታሪክ
እጅ ባይኖረኝም እውነትን አጥብቄ ይዣለሁ
አብዛኛውን ጊዜ ሰዎች ፍርሃት ሲሰማቸው የሆነ ነገር ሙጭጭ አድርገው ይይዛሉ። እኔ ግን እንዲህ ማድረግ አልችልም፤ ምክንያቱም እጅ የለኝም። የሰባት ዓመት ልጅ ሳለሁ ሕይወቴን ለማትረፍ ሲባል ሁለቱም እጆቼ ተቆረጡ።
የተወለድኩት በ1960 ሲሆን እናቴ እኔን ስትወልድ ገና 17 ዓመቷ ነበር። አባቴ፣ እናቴን ጥሏት የሄደው እኔ ከመወለዴ በፊት ነው። በመሆኑም እኔና እናቴ በቀድሞዋ ጀርመን ዲሞክራቲክ ሪፑብሊክ (በምሥራቅ ጀርመን) ትገኝ በነበረችው በርግ በተባለች ከተማ ከአያቶቼ ጋር እንኖር ነበር። በዚያ የነበሩት አብዛኞቹ ሰዎች አምላክ የለሾች ነበሩ፤ የእኔ ቤተሰቦችም ተመሳሳይ አመለካከት ነበራቸው። አምላክ በእኛ ሕይወት ውስጥ ምንም ቦታ አልነበረውም።
ወንድ አያቴ ልዩ ትኩረት ይሰጠኝ ነበር። የተለያዩ ሥራዎችን እንድሠራ ይፈቅድልኝ ነበር፤ ለምሳሌ ዛፍ ላይ ወጥቼ ቅርንጫፎችን በመጋዝ እንድቆርጥ ያደርገኛል። ልጅ ስለነበርኩ እንዲህ ዓይነት ነገሮችን ማድረግ እንደ ጀብድ እቆጥረው ነበር። ነፃና አስደሳች የሆነ ሕይወት ነበረኝ።
የደረሰብኝ አደጋ ሕይወቴን ቀየረው
የሰባት ዓመት ልጅ ሳለሁ አንድ አሰቃቂ ነገር ገጠመኝ። የሁለተኛ ክፍል ትምህርቴን ገና መጀመሬ ነበር። ከትምህርት ቤት ወደ ቤት እየተመለስኩ ሳለ አንድ የብረት ኤሌክትሪክ ምሰሶ ላይ ተንጠላጥዬ ወጣሁ። ስምንት ሜትር ከፍታ ላይ እያለሁ ኤሌክትሪክ ያዘኝና ራሴን ስቼ ወደቅኩ። ሆስፒታል ውስጥ ስነቃ እጆቼ በድን ሆነው ነበር። በእጆቼ ላይ የደረሰው ጉዳት አሰቃቂ ነበር፤ እጆቼ በጣም ተቃጥለው ስለነበር ደሜ እንዳይመረዝ ለመከላከል ሲባል ሁለቱም እጆቼ ተቆረጡ። እናቴና አያቶቼ ምን ያህል በሐዘን ሊደቆሱ እንደሚችሉ መገመት አያዳግትም። ልጅ ስለነበርኩ እጆቼን ማጣቴ በሕይወቴ ላይ ምን ዓይነት ለውጥ እንደሚያመጣ ሙሉ በሙሉ አልገባኝም ነበር።
ከሆስፒታል ከወጣሁ በኋላ ትምህርቴን ቀጠልኩ። ትምህርት ቤት ልጆች ያሾፉብኝ፣ ይገፈትሩኝ እንዲሁም ራሴን መከላከል ስለማልችል አንዳንድ ነገሮች ይወረውሩብኝ ነበር። ልጆቹ ስለሚያሾፉብኝና አንዳንድ የጭካኔ ድርጊት ስለሚፈጽሙብኝ ስሜቴ በጣም ተጎዳ። በኋላም ቢርከቨርደር የሚባል ትምህርት ቤት ገብቼ መማር ጀመርኩ፤ ይህ ትምህርት ቤት አካል ጉዳተኛ የሆኑ ልጆች የሚማሩበት አዳሪ ትምህርት ቤት ነው። ትምህርት ቤቱ የሚገኘው ከቤታችን ርቆ ስለነበር እናቴና አያቶቼ በየጊዜው እየመጡ እኔን ለመጠየቅ የገንዘብ አቅማቸው አይፈቅድም ነበር። ስለሆነም እነሱን ማግኘት የምችለው ትምህርት በሚዘጋበት ጊዜ ብቻ ነበር። ከዚያ በኋላ ባሉት አሥር ዓመታት የኖርኩት ከእናቴና ከአያቶቼ ተነጥዬ ነው።
እጄን ካጣሁ በኋላ ያሳለፍኩት ሕይወት
በእግሮቼ ብዙ ነገር መሥራት ተማርኩ። ሹካ ወይም ማንኪያ በእግር ጣቶች ይዞ መመገብ ምን ሊመስል እንደሚችል መገመት ትችላላችሁ? በብዙ ጥረት ይህን ችሎታ አዳበርኩ። በተጨማሪም በእግሬ ተጠቅሜ ጥርሴን መቦረሽ እንዲሁም ፀጉሬን ማበጠር
ቻልኩ። ከሰዎች ጋር ሳወራ ጭምር አካላዊ መግለጫዎችን በእግሬ እጠቀም ነበር። አዎ፣ እግሮቼ እንደ እጅ ሆነውልኛል።በአሥራዎቹ ዕድሜ ሳለሁ ሳይንሳዊ ልብ ወለዶችን ማንበብ እወድ ነበር። አንዳንዴ ሁሉንም ነገር ማድረግ የሚያስችለኝ በተራቀቀ ቴክኖሎጂ የተሠራ እጅ ቢኖረኝ ኖሮ ብዬ እመኝ ነበር። በ14 ዓመቴ ማጨስ ጀመርኩ። ማጨሴ በራስ የመተማመን ስሜቴን የጨመረልኝና ልክ እንደ ሌሎች ሰዎች እንደሆንኩ እንዲሰማኝ ያደረገኝ መስሎኝ ነበር። እንዲህ ብዬ የመናገር ያክል ነው፦ ‘አዎ፣ እጅ ኖራቸውም አልኖራቸው የሚያጨሱ ሰዎች የሰለጠኑ ናቸው። እኔም ደግሞ ማጨስ እችላለሁ።’
ራሴን በተለያዩ ማኅበራዊ እንቅስቃሴዎች አስጠምጄ ነበር። ፍሪ ጀርመን ዩዝ የተባለ በመንግሥት ድጋፍ የሚደረግለት የወጣት ሶሻሊስቶች ማኅበር አባል በመሆን በጸሐፊነት አገለግል ጀመር፤ ይህም ትልቅ ኃላፊነት ነበር። ከዚያም የአንድ የሙዚቃ ክበብ አባል ሆንኩ፤ እንዲሁም ግጥም ማቅረብና በአካል ጉዳተኞች ስፖርታዊ እንቅስቃሴ መሳተፍ ጀመርኩ። በከተማችን ውስጥ በሚገኝ አንድ ድርጅት ውስጥ ሥልጠና ከወሰድኩ በኋላ እዚያው ተቀጥሬ መሥራት ጀመርኩ። እያደግኩ ስመጣ የአካል ጉዳተኛ ሆኖ መታየት ያስጠላኝ ስለነበር ሁልጊዜ ሰው ሠራሽ እጄን አላወልቅም ነበር።
የመጽሐፍ ቅዱስን እውነት ተቀበልኩ
አንድ ቀን ወደ ሥራ ለመሄድ ባቡር እየጠበቅኩ ሳለ አንድ ሰው አነጋገረኝ። አምላክ እጆቼን መልሶ ሊተካልኝ እንደሚችል አስቤ አውቅ እንደሆነ ጠየቀኝ። በጥያቄው ግራ ተጋባሁ። እርግጥ እጆቼን መልሼ ባገኝ ደስ ይለኛል፤ ሆኖም የተናገረው ነገር የማይመስልና ከእውነታው የራቀ ሆኖ ተሰማኝ። አምላክ የለሽ እንደመሆኔ መጠን አምላክ የለም የሚል ጠንካራ እምነት ነበረኝ። ከዚያ ጊዜ አንስቶ በተቻለኝ መጠን ከዚያ ሰው መሸሽ ጀመርኩ።
ከተወሰነ ጊዜ በኋላ አንዲት የሥራ ባልደረባዬ ቤተሰቦቿ ቤት ጋበዘችኝ። ቡና እየጠጣን ሳለ ወላጆቿ ይሖዋ ስለሚባለው አምላክ ማውራት ጀመሩ። ለመጀመሪያ ጊዜ አምላክ ስም እንዳለው ሰማሁ። (መዝሙር 83:18) ሆኖም በልቤ ‘ስሙ ማንም ሆነ ማን አምላክ ሊኖር አይችልም። እነዚህ ሰዎች እንደተሳሳቱ አሳምናቸዋለሁ’ ብዬ አሰብኩ። ስለማምንበት ነገር እርግጠኛ ስለነበርኩ ስለ መጽሐፍ ቅዱስ ለመወያየት ተስማማሁ። የሚገርመው ግን እንዳሰብኩት አምላክ አለመኖሩን ላሳምናቸው አልቻልኩም።
ስለ መጽሐፍ ቅዱስ ትንቢቶች እየመረመርን ስንሄድ ‘አምላክ የለም’ የሚለው አመለካከቴ እየተፈረካከሰ መጣ። ብዙ ትንቢቶች ከተጻፉ በመቶዎች አልፎ ተርፎ በሺዎች ከሚቆጠሩ ዓመታት በኋላ ፍጻሜያቸውን አግኝተዋል። በአንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ውይይታችን ላይ በዓለማችን ላይ ያለውን ሁኔታ በማቴዎስ ምዕራፍ 24፣ በሉቃስ ምዕራፍ 21 እና በ 2 ጢሞቴዎስ ምዕራፍ 3 ላይ ከሚገኙት ትንቢቶች ጋር አወዳደርን። አንድ ሐኪም የተለያዩ ምልክቶችን ተመልክቶ ታማሚው ያለበትን በሽታ ማወቅ እንደሚችል ሁሉ በእነዚህ ትንቢቶች ላይ የተገለጹት ነገሮች መጽሐፍ ቅዱስ ‘የመጨረሻዎቹ ቀናት’ ብሎ በሚጠራው ጊዜ ውስጥ እንደምንኖር እንድገነዘብ ረዱኝ። * የተማርኩት ነገር በጣም አስደነቀኝ። እኔ አላስተዋልኩም እንጂ እነዚህ ትንቢቶች እየተፈጸሙ ነበር።
የምማረው ነገር እውነት እንደሆነ አመንኩ። ለይሖዋ አምላክ መጸለይ የጀመርኩ ሲሆን ከአሥር ዓመት በላይ ኃይለኛ አጫሽ የነበርኩ ቢሆንም ማጨሴን አቆምኩ። ለአንድ ዓመት ያህል
መጽሐፍ ቅዱስን አጠናሁ። በወቅቱ በምሥራቅ ጀርመን የይሖዋ ምሥክሮች ሥራ ታግዶ ስለነበር ሚያዝያ 27, 1986 በአንድ ገላ መታጠቢያ ገንዳ ውስጥ በድብቅ ተጠመቅኩ።ሌሎችን መርዳት
በእገዳው ምክንያት ስብሰባዎቻችንን የምናደርገው በትናንሽ ቡድኖች ተከፋፍለን በግለሰቦች ቤት ውስጥ ነበር፤ በመሆኑም የማውቃቸው የእምነት ባልንጀሮቼ ቁጥር ጥቂት ነበር። የሚገርመው ነገር የመንግሥት ባለሥልጣናት ባልተጠበቀ መልኩ ወደ ምዕራብ ጀርመን እንድጓዝ ፈቀዱልኝ፤ በዚያ የይሖዋ ምሥክሮች ሥራ አልታገደም ነበር። በሕይወቴ ለመጀመሪያ ጊዜ በትልቅ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ስብሰባ ላይ የተገኘሁ ሲሆን በሺዎች የሚቆጠሩ ወንድሞቼንና እህቶቼን ማየት ቻልኩ። ይህ የማልረሳው አጋጣሚ ነው።
የበርሊን ግንብ ከወደቀ በኋላ በይሖዋ ምሥክሮች ላይ ተጥሎ የነበረው እገዳ ተነሳ። በስተ መጨረሻም ይሖዋ አምላክን በነፃነት ማምለክ ቻልን። በስብከቱ ሥራ ሰፋ ያለ ሰዓት ማሳለፍ እፈልግ ነበር። ሆኖም የማላውቃቸውን ሰዎች ማነጋገር በጣም ያስፈራኝ ነበር። የአካል ጉዳተኛ በመሆኔ እንዲሁም አብዛኛውን የልጅነት ሕይወቴን ያሳለፍኩት በአካል ጉዳተኞች አዳሪ ትምህርት ቤት ውስጥ በመሆኑ የበታችነት ስሜት ይሰማኝ ነበር። ነገር ግን በ1992 በአንድ ወር ላይ 60 ሰዓት በስብከቱ ሥራ ለማሳለፍ ጥረት አደረግኩ። ስለተሳካልኝም በጣም ተደሰትኩ። በመሆኑም በየወሩ እንደዚያው ለማድረግ ወሰንኩ፤ ለሦስት ዓመታት በዚህ መንገድ ማገልገል ችያለሁ።
“ድካም የሚሰማው አለ? እኔስ ብሆን ድካም አይሰማኝም?” የሚለውን የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅስ ሁልጊዜ አስታውሳለሁ። (2 ቆሮንቶስ 11:29) የአካል ጉዳት ቢኖርብኝም እንኳ ማሰብና መናገር እችላለሁ። በመሆኑም የቻልኩትን ያህል ሌሎችን ለመርዳት እጥራለሁ። እኔ ራሴ እጅ የሌለኝ መሆኑ ለሌሎች የአካል ጉዳተኞች ከልብ እንዳስብ አድርጎኛል። አንድን ነገር ለማድረግ በጣም እየፈለጉ ማድረግ አለመቻል ምን ስሜት እንደሚፈጥር አውቃለሁ። ስለዚህ እንዲህ የሚሰማቸውን ሰዎች ለማበረታታት እጥራለሁ። በዚህ መልኩ ሌሎችን መርዳት ለእኔም ደስታ ያስገኝልኛል።
ይሖዋ በየዕለቱ ይረዳኛል
እርግጥ ነው፣ አንዳንድ ጊዜ ይከፋኛል። ‘ሙሉ አካል ቢኖረኝ ምናለ?’ ብዬ አስባለሁ። በራሴ የማከናውናቸው ብዙ የዕለት ተዕለት ሥራዎች አሉ፤ እነዚህን ሥራዎች ማከናወን ግን ከሌሎች ሰዎች የበለጠ ጊዜ፣ ጥረትና ጉልበት ይጠይቅብኛል። “ኃይልን በሚሰጠኝ በእሱ አማካኝነት ለሁሉም ነገር የሚሆን ብርታት አለኝ” የሚለው ጥቅስ በየዕለቱ የሕይወቴ መመሪያ ነው። (ፊልጵስዩስ 4:13) ይሖዋ በየቀኑ የዕለት ተዕለት ተግባሮችን ለማከናወን የሚያስችል ኃይል ይሰጠኛል። ይሖዋ ምንጊዜም ቢሆን እኔን ከመርዳት ወደኋላ እንደማይል አይቻለሁ። እኔም ብሆን ምንጊዜም እሱን ከማገልገል ወደኋላ ማለት አልፈልግም።
ይሖዋ በልጅነቴና በወጣትነቴ ያጣሁትን ነገር ይኸውም ቤተሰብ በመስጠት ባርኮኛል። አፍቃሪና ሩኅሩኅ የሆነች ኤልከ የምትባል ጥሩ ሚስት አለችኝ። በተጨማሪም በሚሊዮን የሚቆጠሩ የይሖዋ ምሥክሮች መንፈሳዊ ወንድሞቼና እህቶቼ ሆነዋል፤ ስለሆነም ዓለም አቀፋዊ ቤተሰብ አለኝ።
አምላክ ምድርን ገነት እንደሚያደርግ የገባውን ቃል ማሰብም ያጽናናኛል፤ አምላክ በዚህ ገነት ውስጥ የእኔን እጆች ጨምሮ “ሁሉንም ነገር አዲስ” ያደርጋል። (ራእይ 21:5) ኢየሱስ ምድር ላይ ሳለ ባደረገው ነገር ላይ ሳሰላስል ይህ ተስፋ ይበልጥ እውን ይሆንልኛል። በአንድ ወቅት ኢየሱስ እጁ ሽባ የሆነን ሰው በቅጽበት ፈውሷል፣ እንዲሁም የአንድን ሰው የተቆረጠ ጆሮ አድኗል። (ማቴዎስ 12:13፤ ሉቃስ 22:50, 51) ይሖዋ የሰጣቸው ተስፋዎችና የኢየሱስ ተአምራት እኔም ወደፊት ሙሉ አካል እንደሚኖረኝ እንድተማመን አድርገውኛል።
ያገኘሁት ከሁሉ የላቀው በረከት ግን ይሖዋ አምላክን ማወቄ ነው። ይሖዋ አባቴና ወዳጄ እንዲሁም አጽናኜና ብርታቴ ነው። “ይሖዋ ብርታቴ . . . ነው፤ ከእሱ እርዳታ ስላገኘሁ ልቤ ሐሴት ያደርጋል” በማለት የተናገረውን የንጉሥ ዳዊትን ስሜት እኔም እጋራለሁ። (መዝሙር 28:7) ይህን አስደናቂ እውነት መቼም ቢሆን መልቀቅ አልፈልግም። እጅ ባይኖረኝም እውነትን አጥብቄ እንደያዝኩ እቀጥላለሁ።
^ አን.17 የመጨረሻዎቹን ቀናት ለይቶ የሚያሳውቀውን ምልክት በተመለከተ ሰፋ ያለ ማብራሪያ ለማግኘት በይሖዋ ምሥክሮች በተዘጋጀው ትክክለኛው የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ምንድን ነው? በተባለው መጽሐፍ ላይ “የምንኖረው ‘በመጨረሻው ዘመን’ ውስጥ ነው?” የሚለውን ምዕራፍ 9ን ተመልከት፤ መጽሐፉ www.ps8318.com/am ላይም ይገኛል።