አምላክ ማን ነው?
ብዙ ሰዎች በአምላክ እንደሚያምኑ ይናገራሉ። “አምላክ ማን ነው?” ተብለው ቢጠየቁ የሚሰጡት መልስ ግን የተለያየ ነው። አንዳንዶች አምላክ ሰዎችን በሆነ ባልሆነው የሚቀጣ ጨካኝ ዳኛ እንደሆነ ይሰማቸዋል። ሌሎች ደግሞ ምንም ዓይነት ጥፋት ቢሠሩ አምላክ ይቅር እንደሚላቸውና ምንጊዜም እንደሚወዳቸው ያምናሉ። አምላክ ሊቀረብ እንደማይችልና ለእኛ ምንም ደንታ እንደሌለው የሚያስቡ ሰዎችም አሉ። አምላክን በተመለከተ እንዲህ ያሉ እርስ በርሳቸው የሚጋጩ አመለካከቶች መኖራቸው በርካታ ሰዎች ‘አምላክ ማን እንደሆነ ማወቅ አይቻልም’ ብለው እንዲያስቡ አድርጓል።
የአምላክን ማንነት ማወቅ ያን ያህል አስፈላጊ ነው? አዎ። ስለ አምላክ እውነቱን ማወቅህ ሕይወትህ ዓላማና ትርጉም ያለው እንዲሆን ያደርጋል። (የሐዋርያት ሥራ 17:26-28) ወደ አምላክ ይበልጥ በቀረብክ መጠን እሱም ይበልጥ ይወድሃል፤ እንዲሁም ይረዳሃል። (ያዕቆብ 4:8) በተጨማሪም ስለ አምላክ ትክክለኛ እውቀት መቅሰምህ ወደፊት የዘላለም ሕይወት እንድታገኝ ያስችልሃል።—ዮሐንስ 17:3
አምላክን ማወቅ የምትችለው እንዴት ነው? እስቲ በደንብ ስለምታውቀው ሰው፣ ለምሳሌ ስለ ቅርብ ወዳጅህ ለማሰብ ሞክር። በመካከላችሁ እንዲህ ያለ ወዳጅነት ሊመሠረት የቻለው እንዴት ነው? ስሙን፣ ባሕርይውን፣ የሚወደውንና የሚጠላውን፣ ከዚህ በፊት ያደረገውንና ወደፊት ሊያደርግ ያሰበውን ጨምሮ ስለ እሱ የተለያዩ ነገሮችን ስላወቅክ እንደሆነ ግልጽ ነው። ከዚህ ሰው ጋር እንድትቀራረብ ያደረገህ ስለ እሱ ማወቅህ ነው።
በተመሳሳይም ስለ አምላክ ማወቅ የምትችለው ስለ እሱ በመማር ነው፤ በመሆኑም የሚከተሉትን ጥያቄዎች መልስ ማወቅህ አስፈላጊ ነው፦
ይህ መጽሔት መጽሐፍ ቅዱስ ለእነዚህ ጥያቄዎች የሚሰጠውን መልስ ይዟል። በዚህ መጽሔት ውስጥ ያሉት ርዕሶች አምላክ ማን እንደሆነ እንድታውቅ ብቻ ሳይሆን ከእሱ ጋር የቀረበ ዝምድና መመሥረትህ ምን ጥቅም እንዳለው እንድትገነዘብ ይረዱሃል።