ከከባድ ሕመም ጋር ስትታገል
አንተ ወይም አንድ የቤተሰብህ አባል ለሕይወት አስጊ የሆነ በሽታ እንዳለባችሁ ተነግሮህ የሚያውቅ ከሆነ ሁኔታው ምን ያህል ቅስም እንደሚሰብር መረዳት አይከብድህም። ሕመሙ ከሚያስከትለው ሥቃይ በተጨማሪ ሁኔታው የሚፈጥረውን የስሜት መደቆስ መቋቋም ያስፈልግሃል። ከእያንዳንዱ የሕክምና ቀጠሮ በፊት የሚሰማህ ፍርሃት፣ ሕክምና ማግኘት ወይም ወጪውን መሸፈን አለመቻልህ የሚፈጥረው ውጥረት እንዲሁም ሕክምናው የሚያስከትለው የጎንዮሽ ጉዳት ጭንቀትህን ሊያባብሰው ይችላል። በእርግጥም ከባድ ከሆነ የጤና እክል ጋር ተያይዞ የሚመጣው የስሜት ሥቃይ ከአቅም በላይ ሊሆን ይችላል።
ታዲያ እንዲህ ያለውን አስጨናቂ ሁኔታ መቋቋም የምትችለው እንዴት ነው? ብዙዎች ወደ አምላክ በመጸለይና በመጽሐፍ
ቅዱስ ውስጥ የሚገኙትን አጽናኝ ሐሳቦች በማንበብ ብርታት ማግኘት ችለዋል። በተጨማሪም ቤተሰቦችህና ወዳጆችህ የሚሰጡህ ፍቅራዊ ድጋፍ የብርታት ምንጭ ሊሆንልህ ይችላል።አንዳንዶች ሁኔታውን መቋቋም የቻሉት እንዴት ነው?
የ58 ዓመቱ ሮበርት እንዲህ የሚል ምክር ሰጥቷል፦ “በአምላክ ላይ እምነት በመጣል በሽታህን ፊት ለፊት ተጋፈጠው፤ አምላክ ሕመምህን መቋቋም እንድትችል ይረዳሃል። ወደ ይሖዋ ጸልይ። ስሜትህን ሁሉ አውጥተህ ንገረው። ለቤተሰብህ ስትል ጠንካራ መሆንና ሁኔታውን በተረጋጋ መንፈስ መወጣት እንድትችል እንዲረዳህ ለምነው።
“ቤተሰቦቼ የሚያደርጉልኝ ስሜታዊ ድጋፍ በእጅጉ ረድቶኛል። በየቀኑ ቢያንስ አንድ ወይም ሁለት ሰው ስልክ ደውሎ ስላለሁበት ሁኔታ ይጠይቀኛል። በተለያየ ቦታ የሚኖሩ ጓደኞቼም ያበረታቱኛል። እነሱ የሚያደርጉልኝ ድጋፍ፣ ብርታት የሚሰጠኝ ሲሆን ይህም ፈጽሞ ተስፋ እንዳልቆርጥ ይረዳኛል።”
የታመመ ጓደኛህን ለመጠየቅ ስትሄድ ሊንዳ የሰጠችውን የሚከተለውን ምክር ልብ ማለትህ ይጠቅምሃል፦ “ታማሚው በተቻለው መጠን እንደ ጤነኛ ሰው ሕይወቱን መምራት ስለሚፈልግ ሁልጊዜ ስለ በሽታው ማውራት ላያስደስተው ይችላል። ስለዚህ ሌላ ጊዜ የምታወሯቸውን ጉዳዮች ለማውራት ሞክር።”
ከከባድ ሕመም ጋር እየታገልንም እንኳ በሕይወታችን ደስተኛ መሆን እንችላለን። አምላክ የሚሰጠን ብርታትና ከመጽሐፍ ቅዱስ የምናገኘው መጽናኛ እንዲሁም አፍቃሪ የሆኑ ቤተሰቦቻችንና ወዳጆቻችን የሚያደርጉልን ድጋፍ ሁኔታውን ተቋቁመን መኖር እንድንችል ይረዳናል።