የሕይወት ታሪክ
“ለሁሉም ዓይነት ሰዎች ሁሉንም ነገር” መሆን
“ከተጠመቅሽ ጥዬሽ እሄዳለሁ!” አባቴ ይህን ያለው እናቴን ለማስፈራራት ነበር። እናቴ ግን ዛቻው አልበገራትም፤ ለይሖዋ አምላክ ራሷን መወሰኗን ለማሳየት ተጠመቀች። አባቴም ልክ እንደዛተው ጥሎን ሄደ። ይህ የሆነው በ1941 ሲሆን በወቅቱ ገና የስምንት ዓመት ልጅ ነበርኩ።
ለመጽሐፍ ቅዱስ እውነት ፍላጎት ያደረብኝ ይህ ከመሆኑ ቀደም ብሎ ነበር። እናቴ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ጽሑፎችን አግኝታ ነበር፤ ጽሑፎቹ ውስጥ ያለው ሐሳብ በተለይም ሥዕሎቹ በጣም ማረኩኝ። ሆኖም አባቴ፣ እናቴ የምትማረውን ነገር እንድትነግረኝ አልፈለገም። እኔ ግን የማወቅ ጉጉት ስላደረብኝ ጥያቄዎችን እጠይቃት ነበር፤ ስለሆነም አባቴ ቤት ውስጥ በማይኖርበት ጊዜ ታስጠናኝ ነበር። ከጊዜ በኋላ እኔም ሕይወቴን ለይሖዋ ለመስጠት ወሰንኩ። በ1943 በአሥር ዓመቴ በብላክፑል፣ እንግሊዝ ተጠመቅኩ።
ይሖዋን ማገልገል ጀመርኩ
ከዚያ ጊዜ አንስቶ ከእናቴ ጋር በመስክ አገልግሎት አዘውትሬ መካፈል ጀመርኩ። የመጽሐፍ ቅዱስን መልእክት ለሰዎች ለማስተዋወቅ የሸክላ ማጫወቻዎችን እንጠቀም ነበር። የሸክላ ማጫወቻው ትልቅ ሲሆን 4.5 ኪሎ ግራም ገደማ ይመዝናል። እንደ እኔ ያለ ትንሽ ልጅ ይህን የሚያህል ነገር ተሸክሞ ሲሄድ ይታያችሁ!
አሥራ አራት ዓመት ሲሞላኝ አቅኚ መሆን ፈለግኩ። እናቴ የወረዳ የበላይ ተመልካቹን በቅድሚያ ማነጋገር እንዳለብኝ ገለጸችልኝ። ይህ ወንድም፣ አቅኚ ሆኜ ሳገለግል ወጪዬን ለመሸፈን የሚያስችለኝ ሙያ እንድማር ሐሳብ አቀረበልኝ። እኔም እንደነገረኝ አደረግኩ። ለሁለት ዓመታት ያህል ከሠራሁ በኋላ አቅኚ የመሆን ግቤን በተመለከተ ሌላ የወረዳ የበላይ ተመልካች አማከርኩ። “ጥሩ ግብ ነው! ትችላለህ” አለኝ።
በመሆኑም ሚያዝያ 1949 እኔና እናቴ፣ በተከራየነው ቤት ውስጥ ካሉን የቤት ዕቃዎች የተወሰነውን ለሰዎች ከሰጠንና ሌላውን ደግሞ ከሸጥን በኋላ ማንቸስተር አቅራቢያ ወደሚገኘው ወደ ሚድልተን ተዛውረን በአቅኚነት ማገልገል ጀመርን። ከአራት ወር በኋላ፣ የአቅኚነት ጓደኛ የሚሆነኝ ወንድም አገኘሁ። ቅርንጫፍ ቢሮው በኧርላም በሚገኝ አዲስ የተቋቋመ ጉባኤ ውስጥ እንድናገለግል ሐሳብ አቀረበልን። እናቴ ደግሞ ከአንዲት እህት ጋር በሌላ ጉባኤ ታገለግል ነበር።
በወቅቱ ገና የ17 ዓመት ልጅ ብሆንም በአዲሱ ጉባኤ ውስጥ ያሉት ብቃት ያላቸው ወንድሞች ጥቂት ስለነበሩ እኔና ጓደኛዬ የጉባኤ ስብሰባዎችን የመምራት ኃላፊነት ተሰጠን። ከጊዜ በኋላ ደግሞ በጣም ትንሽ አስፋፊዎች ባሉትና እርዳታ በሚያስፈልገው በበክስተን ጉባኤ ውስጥ እንዳገለግል ተጠየቅኩ። በወጣትነቴ እነዚህን ኃላፊነቶች መቀበሌ ወደፊት ለተሰጡኝ ሌሎች ኃላፊነቶች እንዳሠለጠነኝ ይሰማኛል።
በ1951 በጊልያድ የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ቤት ለመሠልጠን አመለከትኩ። ነገር ግን ታኅሣሥ 1952 የውትድርና አገልግሎት እንድሰጥ ተጠራሁ። የሙሉ ጊዜ አገልጋይ ስለሆንኩ ከውትድርና አገልግሎት ነፃ እንድደረግ ጠየቅኩ፤ ሆኖም ፍርድ ቤቱ የሙሉ ጊዜ አገልጋይ መሆኔን ስላልተቀበለው የስድስት ወር እስራት ተፈረደብኝ። እስር ቤት ሳለሁ፣ በጊልያድ ትምህርት ቤት 22ኛ ክፍል እንድሠለጥን መጋበዜን የሚገልጽ ደብዳቤ ደረሰኝ። ከእስር ከተለቀቅኩ በኋላ ሐምሌ 1953 ጆርጂክ በምትባል መርከብ ተሳፍሬ ወደ ኒው ዮርክ ተጓዝኩ።
እዚያ እንደደረስኩ በ1953 በተደረገው የአዲሱ ዓለም ኅብረተሰብ የተባለው ትልቅ ስብሰባ ላይ ተገኘሁ። ከዚያም ባቡር ተሳፍሬ ትምህርት ቤቱ ወደሚገኝበት ወደ ሳውዝ ላንሲንግ፣ ኒው ዮርክ ሄድኩ። ገና ከእስር ቤት መውጣቴ ስለነበር ያለኝ ገንዘብ በጣም ጥቂት ነበር። ከባቡር ከወረድኩ በኋላ ወደ ሳውዝ ላንሲንግ የምሄደው በአውቶቡስ ነበር፤ ለጉዞው የሚያስፈልገኝን 25 ሳንቲም የከፈልኩት አብሮኝ ከተሳፈረ ሰው ተበድሬ ነው።
በሌላ አገር ተመደብኩ
በሚስዮናዊነት አገልግሎታችን “ለሁሉም ዓይነት ሰዎች ሁሉንም ነገር” እንድንሆን የሚረዳን ግሩም ሥልጠና ከጊልያድ ትምህርት ቤት አግኝተናል። (1 ቆሮ. 9:22) እኔ፣ ፖል ብሩን እና ሬመንድ ሊች በፊሊፒንስ እንድናገለግል ተመደብን። ቪዛ ለማግኘት ለወራት መጠበቅ አስፈልጎን ነበር፤ ከዚያም በሮተርዳም፣ በሜዲትራኒያን ባሕር፣ በስዊዝ ቦይ፣ በሕንድ ውቅያኖስ፣ በማሌዥያና በሆንግ ኮንግ በኩል ለ47 ቀናት በመርከብ ተጓዝን! በመጨረሻም ኅዳር 19, 1954 ማኒላ ደረስን።
በዚያም ሕዝቡን፣ አገሩንና ቋንቋውን ለመላመድ ጥረት ማድረግ ጀመርን። ይሁንና ሦስታችንም መጀመሪያ የተመደብነው ብዙዎቹ ነዋሪዎች እንግሊዝኛ መናገር በሚችሉበት በኬሶን ሲቲ ውስጥ ባለ ጉባኤ ነበር። በመሆኑም ስድስት ወር ካለፈ በኋላም እንኳ የምናውቀው ጥቂት የታጋሎግ ቃላት ብቻ ነበር። ቀጣዩ ምድባችን ግን ይህን ችግር ፈታው።
ግንቦት 1955 አንድ ቀን እኔና ወንድም ሊች ከአገልግሎት ወደ ቤት ስንመለስ ክፍላችን ውስጥ ደብዳቤዎች ተቀምጠው አገኘን። ደብዳቤዎቹን ስናነብ የወረዳ የበላይ ተመልካቾች ሆነን እንደተሾምን አወቅን። በወቅቱ ገና 22 ዓመቴ ቢሆንም ይህ ሥራ “ለሁሉም ዓይነት ሰዎች ሁሉንም ነገር” መሆን የምችልባቸውን አዳዲስ አጋጣሚዎች ከፈተልኝ።
ለምሳሌ ያህል፣ የወረዳ የበላይ ተመልካች ከሆንኩ በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ የሕዝብ ንግግር ያቀረብኩት በአንድ መንደር ውስጥ በሚገኝ መደብር ፊት ለፊት ነበር። በወቅቱ በፊሊፒንስ በነበረው ልማድ መሠረት የሕዝብ ንግግር የሚባለው በአደባባይ ይኸውም ብዙ ሰው በሚገኝባቸው ቦታዎች የሚሰጥ ንግግር እንደሆነ ብዙም ሳይቆይ ተገነዘብኩ። በወረዳው ውስጥ የሚገኙ የተለያዩ ጉባኤዎችን ስጎበኝ በመናፈሻዎች፣ በገበያ ቦታዎች፣ በማዘጋጃ ቤት አዳራሾች ፊት ለፊት፣ በቅርጫት ኳስ መጫወቻ ሜዳዎችና ብዙ ጊዜ ደግሞ በመንገድ ዳር ንግግር አቅርቤያለሁ። በአንድ ወቅት ሳን ፓብሎ ሲቲ ውስጥ የሚገኝ ጉባኤን ስጎበኝ ኃይለኛ ዝናብ በመዝነቡ ምክንያት በገበያ ቦታው ንግግር መስጠት አልቻልኩም፤ ስለሆነም ንግግሩ በመንግሥት አዳራሽ እንዲቀርብ ኃላፊነት ላላቸው ወንድሞች ሐሳብ አቀረብኩ። በኋላ ላይ ወንድሞች፣ ንግግሩ የቀረበው በአደባባይ ይኸውም ብዙ ሰው በሚገኝባቸው ቦታዎች ሳይሆን በመንግሥት አዳራሽ ውስጥ ከመሆኑ አንጻር እንደ ሕዝባዊ ስብሰባ ይቆጠር እንደሆነ ጠየቁኝ!
ሁልጊዜም የማርፈው በወንድሞች ቤት ነበር። ቤታቸው ብዙ ነገር ባይኖረውም ምንጊዜም ንጹሕ ነው። አብዛኛውን ጊዜ የምተኛው ከጣውላ በተሠራው ወለል ላይ ምንጣፍ ተነጥፎልኝ ነበር። ሰውነቴን መታጠብ የምችለው ከቤት ውጭ ሰው ሁሉ ሊያየኝ በሚችል ቦታ ላይ ስለሆነ ገላዬን ደጅ መታጠብ ለመድኩ። ለመጓጓዣ በጂፕኒ (በፊሊፒንስ የሚገኙ ከጂፕ የተሠሩ አውቶቡሶች) እና በሌሎች አውቶቡሶች እንዲሁም ወደ አጎራባች ደሴቶች መሄድ ሲያስፈልገኝ ደግሞ በጀልባ እጠቀም ነበር። በአገልግሎት ባሳለፍኳቸው ዓመታት ሁሉ የራሴ መኪና ኖሮኝ አያውቅም።
በመስክ አገልግሎት መካፈሌና ጉባኤዎችን መጎብኘቴ የታጋሎግ ቋንቋን እንድማር ረድቶኛል። ቋንቋውን ለመማር መደበኛ ሥልጠና ባይሰጠኝም በመስክ አገልግሎትና በስብሰባዎች ላይ ወንድሞች ሲናገሩ በመስማት ይህን ቋንቋ መልመድ ቻልኩ። ወንድሞች ቋንቋውን እንድማር እርዳታ አበርክተውልኛል፤ ለትዕግሥታቸውና በሐቀኝነት ለሰጡኝ ሐሳብ አመስጋኝ ነኝ።
ጊዜ እያለፈ ሲሄድ አዳዲስ ኃላፊነቶች ተቀበልኩ፤ ይህ ደግሞ ተጨማሪ ማስተካከያዎች እንዳደርግ አነሳስቶኛል። በ1956 ወንድም ናታን ኖር ጎብኚ ሆኖ በተገኘበት ትልቅ ስብሰባ ላይ በሕዝብ ግንኙነት ቢሮ እንድሠራ ተመድቤ ነበር። ከዚህ በፊት እንዲህ ዓይነት ሥራ ሠርቼ
አላውቅም፤ በመሆኑም ወንድሞች ደስ እያላቸው ሥራውን አስተማሩኝ። ዓመት በማይሞላ ጊዜ ውስጥ ሌላ ትልቅ ስብሰባ ተዘጋጀ፤ በዚህ ጊዜ ደግሞ ወንድም ፍሬድሪክ ፍራንዝ ከዋናው መሥሪያ ቤት ሊጎበኘን መጥቶ ነበር። የስብሰባው የበላይ ተመልካች ሆኜ ስሠራ፣ ወንድም ፍራንዝ ከአገሩ ሰዎች ጋር ለመመሳሰል ከነበረው ፈቃደኝነት ትምህርት አግኝቻለሁ። የአገሪቱ ወንድሞች፣ ወንድም ፍራንዝ ባሮንግ ታጋሎግ የተባለውን የፊሊፒንስ ባሕላዊ ልብስ ለብሶ የሕዝብ ንግግሩን ሲሰጥ በማየታቸው ተደስተው ነበር።የአውራጃ የበላይ ተመልካች ሆኜ ስሾም ደግሞ ተጨማሪ ማስተካከያዎች ማድረግ አስፈልጎኝ ነበር። በወቅቱ ዘ ሃፒነስ ኦቭ ዘ ኒው ወርልድ ሶሳይቲ የተባለውን ቪዲዮ እናሳይ የነበረ ሲሆን አብዛኛውን ጊዜ ይህን የምናደርገው ከቤት ውጭ ሕዝብ በሚሰበሰብባቸው ቦታዎች ነበር። አንዳንድ ጊዜ ነፍሳት ያስቸግሩን ነበር። ከፕሮጀክተሩ የሚወጣውን መብራት ፈልገው ስለሚመጡ ፕሮጀክተሩ ላይ ይጣበቃሉ። ቪዲዮውን አሳይተን ከጨረስን በኋላ ፕሮጀክተሩን ማጽዳት ትልቅ ሥራ ነበር! ቪዲዮውን ለማሳየት ዝግጅት ማድረግ ቀላል ባይሆንም ሰዎች የይሖዋ ድርጅት ዓለም አቀፋዊ መሆኑን ሲያውቁ የሚሰጡትን ምላሽ ማየት ያስደስታል።
የካቶሊክ ቄሶች፣ ትላልቅ ስብሰባዎች ለማድረግ ፈቃድ እንዳይሰጡን አንዳንድ ባለሥልጣናትን ይገፋፏቸው ነበር። ወይም ደግሞ ንግግሮቹ የሚቀርቡት በእነሱ ቤተ ክርስቲያን አካባቢ ከሆነ የቤተ ክርስቲያኑን ደወል በማጮኽ ንግግሩ እንዳይሰማ ለማድረግ ይሞክሩ ነበር። ያም ቢሆን ሥራው የቀጠለ ከመሆኑም ሌላ በእነዚያ
አካባቢዎች የሚኖሩ ብዙ ሰዎች የይሖዋ አምላኪዎች ሆነዋል።ተጨማሪ ማስተካከያ የሚጠይቁ ኃላፊነቶች
በ1959 በቅርንጫፍ ቢሮው እንዳገለግል መመደቤን የሚገልጽ ደብዳቤ ደረሰኝ። ይህም ትምህርት ማግኘት የምችልባቸውን ተጨማሪ አጋጣሚዎች ከፈተልኝ። ከጊዜ በኋላ ደግሞ የዞን የበላይ ተመልካች ሆኜ ሌሎች አገሮችን እንድጎበኝ ተጠየቅኩ። ከእነዚህ ጉብኝቶች በአንዱ ላይ በታይላንድ ከምታገለግል ጃኔት ዱሞንድ የምትባል ሚስዮናዊት ጋር ተዋወቅኩ። ለተወሰነ ጊዜ ስንጻጻፍ ከቆየን በኋላ ተጋባን። ከጃኔት ጋር ለ51 ዓመታት በአገልግሎት አስደሳችና አርኪ ሕይወት አሳልፈናል።
በድምሩ በ33 አገሮች የሚገኙ የይሖዋ ሕዝቦችን የመጎብኘት መብት አግኝቻለሁ። ቀደም ሲል የተቀበልኳቸው ኃላፊነቶች፣ የተለያዩ አገር ሕዝቦችን ስጎበኝ ለሚያጋጥሙኝ ለየት ያሉ ተፈታታኝ ሁኔታዎች አዘጋጅተውኛል፤ ለዚህም አመስጋኝ ነኝ! የተለያዩ አገሮችን መጎብኘቴ አመለካከቴን ያሰፋልኝ ከመሆኑም ሌላ ይሖዋ ሁሉንም ዓይነት ሰዎች እንደሚወድና እንደሚቀበል እንዳስተውል ረድቶኛል።—ሥራ 10:34, 35
ማስተካከያ ማድረጌን ቀጥያለሁ
በፊሊፒንስ ከሚገኙ ወንድሞቻችን ጋር ማገልገል ምንኛ አስደሳች ነው! በአሁኑ ጊዜ በፊሊፒንስ የሚገኙት አስፋፊዎች ቁጥር እኔ እዚያ ማገልገል ስጀምር ከነበረው በአሥር እጥፍ ገደማ ጨምሯል። እኔና ጃኔት በኬሶን ሲቲ በሚገኘው የፊሊፒንስ ቅርንጫፍ ቢሮ እያገለገልን ነው። በውጭ አገር ማገልገል ከጀመርኩ ከ60 ዓመት በላይ ቢሆነኝም እንኳ ይሖዋ የሚጠይቅብኝን ለመፈጸም አሁንም ማስተካከያዎችን ለማድረግ ፈቃደኛ መሆን ያስፈልገኛል። በቅርቡ የተደረጉ ድርጅታዊ ለውጦች ለይሖዋና ለወንድሞቻችን ከምናቀርበው አገልግሎት ጋር በተያያዘ ለውጥ ለማድረግ ፈቃደኛ መሆንን ጠይቀውብናል።
የይሖዋ ፈቃድ እንደሆነ የተረዳነውን ማንኛውንም ነገር ለመቀበል ጥረት ስናደርግ ኖረናል፤ ይህ ደግሞ ከሁሉ በላይ እርካታ ያለው ሕይወት ለመምራት አስችሎናል። በተጨማሪም አስፈላጊ የሆኑ ማስተካከያዎችን ለማድረግና ወንድሞቻችንን በሚገባ ለማገልገል ጥረት አድርገናል። አዎ፣ ይሖዋ እስከፈቀደው ጊዜ ድረስ “ለሁሉም ዓይነት ሰዎች ሁሉንም ነገር” መሆናችንን ለመቀጠል ቁርጥ ውሳኔ አድርገናል።