የሽፋኑ ርዕሰ ጉዳይ | ሐቀኛ መሆን ምን ጥቅም አለው?
ሐቀኛ አለመሆን ምን ጉዳት አለው?
“በመጠኑም ቢሆን ሐቀኝነትን በማጉደል ሊፈቱ የሚችሉ ችግሮች ሁልጊዜ ያጋጥሙናል።”—ሳማንታ፣ ደቡብ አፍሪካ
በዚህ አባባል ትስማማለህ? ልክ እንደ ሳማንታ፣ ሁላችንም በሕይወታችን ውስጥ በሆነ ወቅት ላይ አስቸጋሪ ሁኔታዎች አጋጥመውናል። ሐቀኝነት የጎደለው ድርጊት እንድንፈጽም የሚፈትን ሁኔታ ሲያጋጥመን ምላሽ የምንሰጥበት መንገድ በሕይወታችን ውስጥ ከፍ አድርገን የምናያቸው ነገሮች የትኞቹ እንደሆኑ ያሳያል። ለምሳሌ፣ ከምንም ነገር በላይ የሚያሳስበን ሰዎች ለእኛ ያላቸው አክብሮት ከሆነ ከኃፍረት ለመዳን ስንል ሐቀኝነት የጎደለው ድርጊት መፈጸምን እንደ አንድ አማራጭ ልናየው እንችላለን። ይሁንና እውነቱ ሲወጣ ሐቀኛ አለመሆናችን ብዙ መዘዝ ያስከትልብናል። እስቲ አንዳንድ መዘዞቹን እንመልከት።
ሐቀኝነትን ማጉደል መተማመንን ያጠፋል
ለማንኛውም ዝምድና መሠረቱ መተማመን ነው። ሁለት ሰዎች እርስ በርስ የሚተማመኑ ከሆነ የደኅንነትና የመረጋጋት ስሜት ይሰማቸዋል። ሆኖም መተማመን በአንድ ጀምበር የሚመጣ ነገር አይደለም። ሰዎች አብረው ጊዜ ሲያሳልፉ እርስ በርሳቸው እውነትን የሚነጋገሩ እንዲሁም አንዳቸው ለሌላው ራስ ወዳድነት የማይንጸባረቅበት ነገር የሚያደርጉ ከሆነ በመካከላቸው ያለው መተማመን እያደገ ይሄዳል። ይሁንና ሐቀኝነት የጎደለው አንድ ድርጊት መፈጸም ይህ መተማመን በአንዴ እንዲጠፋ ሊያደርግ ይችላል። አንዴ መተማመን ከጠፋ ደግሞ እንደገና መገንባት በጣም ከባድ ነው።
ወዳጄ ነው ብለህ ባሰብከው ሰው ተታልለህ ታውቃለህ? ከሆነ ምን ተሰማህ? ምናልባት ስሜትህ ተጎድቶ፣ ሌላው ቀርቶ እንደተከዳህ ተሰምቶህ ሊሆን ይችላል። እንዲህ የተሰማህ መሆኑ የሚያስገርም አይደለም። ሐቀኝነትን ማጉደል ከፍተኛ ዋጋ የምንሰጣቸውን ዝምድናዎች መሠረት ሊያናጋ እንደሚችል ጥርጥር የለውም።
ሐቀኝነት ማጉደል ይጋባል
በካሊፎርኒያ ዩኒቨርሲቲ የኢኮኖሚክስ ፕሮፌሰር የሆኑት ሮበርት ኢነስ ባደረጉት ጥናት ላይ “ሐቀኝነትን ማጉደል የሚጋባ ነገር እንደሆነ” ጠቁመዋል። በመሆኑም ሐቀኛ አለመሆንን ከቫይረስ ጋር ልናመሳስለው እንችላለን፤ አጭበርባሪ ከሆነ ሰው ጋር በተቀራረብክ መጠን በእምነት አጉዳይነት “የመጠቃት” አጋጣሚህ የዚያኑ ያህል እየጨመረ ይሄዳል።
ታዲያ ሐቀኝነት የጎደለው ድርጊት ከመፈጸም መቆጠብ የምትችለው እንዴት ነው? መጽሐፍ ቅዱስ በዚህ ረገድ ሊረዳህ ይችላል። እስቲ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚገኙ አንዳንድ መመሪያዎችን ተመልከት።