በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የሽፋኑ ርዕሰ ጉዳይ | ሐቀኛ መሆን ምን ጥቅም አለው?

ሐቀኝነት ጊዜ ያለፈበት ነገር ነው?

ሐቀኝነት ጊዜ ያለፈበት ነገር ነው?

ሂቶሺ በጃፓን በሚገኝ አንድ ሥራ አስቀጣሪ ድርጅት ውስጥ በሒሳብ ክፍል ውስጥ ይሠራ ነበር። ከአለቃው ጋር ሆኖ የሒሳብ መዝገብ በሚመረምሩበት ጊዜ አለቃው የሐሰት ሪፖርት እንዲያዘጋጅ አዘዘው። ሂቶሺ እንደዚህ ዓይነት ሐቀኝነት የጎደለው ሥራ ለመሥራት ሕሊናው እንደማይፈቅድለት ለአለቃው ነገረው። በመሆኑም አለቃው ከሥራ እንደሚያባርረው አስጠነቀቀው፤ በመጨረሻም ሂቶሺ ሥራውን አጣ።

በቀጣዮቹ ወራት ሂቶሺ ሥራ ለመቀጠር ያደረገው ጥረት ባለመሳካቱ ተስፋ ቆረጠ። ለምሳሌ ያህል፣ ለአንድ የሥራ ቃለ መጠይቅ በቀረበበት ወቅት ሐቀኝነት የጎደለው ሥራ ለመሥራት ፈቃደኛ እንዳልሆነ ተናገረ። ቃለ መጠይቅ ያደርግለት የነበረው ሰው “የምታስብበት መንገድ ግራ ይገባል!” አለው። ምንም እንኳ ቤተሰቦቹና ወዳጆቹ ሐቀኛ ለመሆን ያደረገውን ቁርጥ ውሳኔ ደግፈው በአቋሙ እንዲጸና ቢያበረታቱትም ሂቶሺ የያዘውን አቋም በተመለከተ ጥርጣሬ አድሮበት ነበር። ሂቶሺ “በእምነቴ ምክንያት እንዲህ ያለ አቋም መያዜ ትክክል ነው የሚለውን ነገር መጠራጠር ጀምሬ ነበር” በማለት ተናግሯል።

በሂቶሺ ላይ የደረሰው ነገር ሐቀኝነትን ከፍ አድርጎ የሚመለከተው ሁሉም ሰው እንዳልሆነ የሚያሳይ አሳዛኝ እውነታ ነው። እንዲያውም አንዳንዶች በንግዱ ዓለም ውስጥ ሐቀኛ መሆን የሚያዋጣ ነገር እንዳልሆነ ይሰማቸዋል። በደቡብ አፍሪካ የምትኖር አንዲት ሴት በሥራ ቦታዋ ስለሚያጋጥማት ነገር ስትናገር “ብዙ ሰዎች ሐቀኛ አይደሉም፤ በመሆኑም አንዳንድ ጊዜ የእነሱ ዓይነት አካሄድ እንድከተል ጫና ይደረግብኛል” ብላለች።

በአሁኑ ጊዜ ከምናያቸው ሐቀኝነት የጎደላቸው ድርጊቶች መካከል በተለየ ሁኔታ ተስፋፍቶ የሚገኘው ውሸት ነው። ከጥቂት ዓመታት በፊት በማሳቹሴትስ ኤምኸርስት ዩኒቨርሲቲ የሥነ ልቦና ባለሞያ የሆኑት ሮበርት ፌልድማን ያደረጉት አንድ ጥናት እንዳሳየው 60 በመቶ የሚሆኑት አዋቂዎች በ10 ደቂቃ ውስጥ ቢያንስ አንዴ ይዋሻሉ። ፌልድማን እንዲህ ብለዋል፦ “ጥናቱ ያሳየው ውጤት በጣም የሚገርም ነው። ውሸት የሕይወታችን አንዱ ክፍል እስኪመስል ድረስ እንደዚህ ተስፋፍቷል ብለን አልጠበቅንም ነበር።” ብዙ ሰዎች፣ ሌሎች ሲዋሿቸው ደስ ባይላቸውም እነሱ ራሳቸው የሚዋሹ መሆናቸው የሚገርም ነው።

ውሸት፣ ስርቆት እና ሌሎች ሐቀኝነት የጎደላቸው ድርጊቶች ይህን ያህል የተስፋፉት ለምንድን ነው? ሐቀኝነት የጎደለው ድርጊት በማኅበረሰቡ ላይ ምን ተጽዕኖ ይኖረዋል? ከሁሉ በላይ ደግሞ እንዲህ ባሉ ሐቀኝነት የጎደላቸው ድርጊቶች ከመካፈል ለመቆጠብ ምን ማድረግ እንችላለን?