በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

መጽሐፍ ቅዱስን ማጥናት ይበልጥ ውጤታማና አስደሳች እንዲሆንልህ ማድረግ

መጽሐፍ ቅዱስን ማጥናት ይበልጥ ውጤታማና አስደሳች እንዲሆንልህ ማድረግ

ኢያሱ ከባድ ፈተና ተጋርጦበታል። ትላልቅ መሰናክሎችን አልፎ የእስራኤልን ብሔር እየመራ ወደ ተስፋይቱ ምድር ማስገባት ይጠበቅበታል። ይሁንና ይሖዋ ስኬታማ እንደሚሆን ማረጋገጫ የሰጠው ከመሆኑም ሌላ እንዲህ በማለት አበረታቶታል፦ ‘ደፋርና ብርቱ ሁን፤ ሕጌን ፈጽም። በውስጡ የተጻፈውን በጥንቃቄ መፈጸም እንድትችል ቀንም ሆነ ሌሊት አንብበው፤ እንዲህ ካደረግክ መንገድህ ይቃናልሃል፤ እንዲሁም ማንኛውንም ነገር በጥበብ ማከናወን ትችላለህ።’—ኢያሱ 1:7, 8

እኛም የምንኖረው “ለመቋቋም [በሚያስቸግር] በዓይነቱ ልዩ የሆነ ዘመን” ውስጥ ስለሆነ ከባድ ፈተናዎች ያጋጥሙናል። (2 ጢሞ. 3:1) ይሖዋ ለኢያሱ የሰጠውን ምክር ተግባራዊ የምናደርግ ከሆነ ልክ እንደ ኢያሱ ስኬታማ መሆን እንችላለን። መጽሐፍ ቅዱስን አዘውትረን ማንበብ እንዲሁም ፈተናዎች ሲያጋጥሙን በውስጡ የሚገኙትን መሠረታዊ ሥርዓቶች በጥንቃቄ ተግባራዊ ማድረግ ይኖርብናል።

እንደ እውነታው ከሆነ ግን አብዛኞቻችን ጥሩ የጥናት ልማድ የለንም፤ ወይም ማጥናት ያን ያህል አያስደስተንም። ሆኖም መጽሐፍ ቅዱስን ማጥናት በጣም አስፈላጊ ነገር ስለሆነ “ የሚከተሉትን ምክሮች ተግባራዊ ለማድረግ ሞክር” በሚለው ሣጥን ውስጥ የቀረቡትን ጥናታችንን ይበልጥ ውጤታማና አስደሳች ለማድረግ የሚረዱ ነጥቦች መከለሳችን ጠቃሚ ነው።

መዝሙራዊው “በትእዛዛትህ መንገድ ምራኝ፤ በእሱ ደስ እሰኛለሁና” በማለት ዘምሯል። (መዝ. 119:35) የአምላክን ቃል ማጥናትህ ከፍተኛ ደስታ ያስገኝልሃል። መንፈሳዊ ዕንቁዎችን ለማግኘት የምታደርገው ጥረት መልሶ እንደሚክስህ እርግጠኛ ሁን።

እርግጥ ነው፣ አንተ እንደ ኢያሱ አንድን ብሔር የመምራት ኃላፊነት ባይጣልብህም በግለሰብ ደረጃ የምትጋፈጣቸው ተፈታታኝ ሁኔታዎች እንዳሉብህ የታወቀ ነው። በመሆኑም ልክ እንደ ኢያሱ፣ አምላክ ለአንተ ጥቅም ሲል ያጻፈውን ቃሉን ማጥናትህና በጥንቃቄ መፈጸምህ አስፈላጊ ነው። እንዲህ ካደረግክ አንተም መንገድህ ሊቃናልህና ማንኛውንም ነገር በጥበብ ልታከናውን ትችላለህ።