ይህን ያውቁ ኖሯል?
በጥንቷ ባቢሎን ፍርስራሾች መካከል የተገኙት ጡቦችና የተሠሩበት መንገድ የመጽሐፍ ቅዱስን ዘገባ የሚደግፈው እንዴት ነው?
የአርኪኦሎጂ ባለሙያዎች የጥንቷ ባቢሎን በምትገኝበት ቦታ ባደረጉት ቁፋሮ ከተማዋን ለመገንባት ያገለገሉ ብዙ የተተኮሱ ጡቦች አግኝተዋል። ሮበርት ኮልደቢ የተባሉት የአርኪኦሎጂ ባለሙያ እንደተናገሩት እነዚህ ጡቦች የሚተኮሱባቸው እቶኖች የሚገኙት ከከተማዋ ውጭ ነበር፤ “ከከተማዋ ውጭ መሆኑ ጥቅሙ ጭቃው ጥሩ ነው፤ ማገዶውም . . . እንደ ልብ ይገኛል።”
የጥንት መዛግብት እንደሚጠቁሙት ባቢሎናውያን ባለሥልጣናት እቶናቸውን ለመጥፎ ዓላማ ይጠቀሙበት ነበር። በቶሮንቶ ዩኒቨርሲቲ የአሦር ጥናት ፕሮፌሰር የሆኑት ፖል አላን ቦልዩ እንዲህ ብለዋል፦ “በርካታ ባቢሎናውያን ምንጮች . . . እንደዘገቡት በዓመፅ ወይም ቅዱስ ነገሮችን በማርከስ የተወነጀሉ ሰዎች በንጉሡ ትእዛዝ ይቃጠሉ ነበር።” በንጉሥ ናቡከደነጾር ዘመን የተጻፈ አንድ ጥንታዊ ጽሑፍ እንዲህ የሚል ሐሳብ ይዟል፦ “አጥፏቸው፣ አቃጥሏቸው፣ ለብልቧቸው፣ . . . ወደ ምድጃው ጣሏቸው . . . ጭሳቸው እየተትጎለጎለ እንዲወጣ በሚንበለበለው እሳት አጋዩአቸው።”
ይህ ግኝት የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎችን የሚያስታውሳቸው አንድ ታሪክ አለ፤ ይህም በዳንኤል ምዕራፍ 3 ላይ የሚገኘው ታሪክ ነው። ታሪኩ እንደሚገልጸው ንጉሥ ናቡከደነጾር ከባቢሎን ከተማ ውጭ በዱራ ሜዳ ላይ አንድ ትልቅ የወርቅ ምስል አቆመ። ሲድራቅ፣ ሚሳቅና አብደናጎ የተባሉት ሦስት ዕብራውያን ወጣቶች ለምስሉ ለመስገድ ፈቃደኞች አልሆኑም። ናቡከደነጾር በዚህ በጣም ስለተቆጣ ወደሚንበለበለው የእቶን እሳት እንዲጥሏቸው አዘዘ። የእቶኑም እሳት “ከወትሮው ይበልጥ ሰባት እጥፍ እንዲነድ አዘዘ።” አንድ ኃያል መልአክ ግን ወጣቶቹን ከሞት ታደጋቸው።—ዳን. 3:1-6, 19-28
በባቢሎን የተገኙት ጡቦች ራሳቸው የመጽሐፍ ቅዱስን ዘገባ እውነተኝነት ያረጋግጣሉ። ለምሳሌ ያህል፣ ንጉሡን የሚያወድስ ጽሑፍ የተቀረጸባቸው ብዙ ጡቦች አሉ። አንደኛው ጽሑፍ እንዲህ ይላል፦ “ናቡከደነጾር፣ የባቢሎን ንጉሥ . . . ቤተ መንግሥቱ፣ ለግርማዬ ክብር የገነባሁት መኖሪያ . . . ከአብራኬ የሚከፈሉት ልጆቼ ለዘላለም ይግዙበት።” ይህ ጽሑፍ ዳንኤል 4:30 ላይ ከሚገኘው ሐሳብ ጋር በጣም ይመሳሰላል፤ ጥቅሱ ላይ ናቡከደነጾር እንዲህ ሲል በጉራ ተናግሯል፦ “ይህች፣ ንጉሣዊ መኖሪያ እንድትሆን ለግርማዬ ክብር፣ በገዛ ብርታቴና ኃይሌ የገነባኋት ታላቂቱ ባቢሎን አይደለችም?”