ለአምልኮ አንድ ላይ መሰብሰብ ያለብን ለምንድን ነው?
“አንድ ላይ ይሰበሰቡ . . . ነበር።”—ሥራ 2:42
መዝሙሮች፦ 20, 119
1-3. (ሀ) ክርስቲያኖች አንድ ላይ መሰብሰብን ከፍ አድርገው እንደሚመለከቱት ያሳዩት እንዴት ነው? (በመግቢያው ላይ ያለውን ፎቶግራፍ ተመልከት።) (ለ) በዚህ ርዕስ ውስጥ ምን እንመለከታለን?
ኮሪና የ17 ዓመት ልጅ እያለች እናቷ ተይዛ በሶቪየት ወደሚገኝ የጉልበት ሥራ ካምፕ ተላከች። በኋላ ላይ ደግሞ ኮሪና ራሷ፣ ከመኖሪያዋ በሺዎች የሚቆጠሩ ኪሎ ሜትሮች ርቆ ወደሚገኘው ወደ ሳይቤሪያ በግዞት ተወሰደች። በዚያም እንደ ባሪያ ትቆጠር የነበረ ሲሆን አንዳንድ ጊዜም በጣም ቀዝቃዛ በሆነው አየር በቂ ልብስ ሳትለብስ ደጅ ላይ እንድትሠራ ትገደድ ነበር። ኮሪና እና አንዲት ሌላ እህት እንዲህ ባለ በጣም አስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ ቢኖሩም በጉባኤ ስብሰባ ላይ ለመገኘት ቆርጠው ነበር።
2 ኮሪና እንዲህ ብላለች፦ “ምሽት ላይ ከሥራ ቦታችን ከወጣን በኋላ 25 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ወደሚገኝ ባቡር ጣቢያ በእግራችን ሄድን። ባቡሩ የተነሳው ከሌሊቱ ስምንት ሰዓት ሲሆን ጉዞው ስድስት ሰዓት ፈጀብን፤ ከባቡሩ ከወረድን በኋላ ደግሞ ወደ ስብሰባው ቦታ ለመድረስ 10 ኪሎ ሜትር በእግራችን ተጓዝን።” ታዲያ እንዲህ ያለ ጉዞ በማድረጋቸው ተጠቅመዋል? ኮሪና እንዲህ ብላለች፦ “በስብሰባው ላይ መጠበቂያ ግንብ ያጠናን ከመሆኑም ሌላ የመንግሥቱን መዝሙሮች ዘመርን። በዚህ ስብሰባ በጣም ታንጸናል፤ እምነታችንም ተጠናክሯል።” ኮሪና እና አብራት ያለችው እህት ወደ ሥራ ቦታቸው የተመለሱት ከሦስት ቀን በኋላ ቢሆንም የሚሠሩበት
እርሻ አስተዳዳሪ፣ አለመኖራቸውን እንኳ አላስተዋለም ነበር።3 ከጥንት ዘመን ጀምሮ የይሖዋ ሕዝቦች አንድ ላይ የሚሰበሰቡባቸውን አጋጣሚዎች ከፍ አድርገው ይመለከቷቸዋል። የክርስቲያን ጉባኤ እንደተቋቋመ የኢየሱስ ተከታዮች ‘አንድ ላይ መሰብሰብ’ ጀምረዋል። (ሥራ 2:42) አንተም ብትሆን ልክ እንደ እነሱ አዘውትረህ በጉባኤ ስብሰባዎች ላይ መገኘት እንደምትፈልግ የታወቀ ነው። ያም ቢሆን ሁሉም ክርስቲያኖች እንቅፋቶች ያጋጥሟቸዋል። በሰብዓዊ ሥራችን፣ ፕሮግራማችን የተጣበበ በመሆኑ አሊያም በዕለት ተዕለት እንቅስቃሴዎቻችን የተነሳ በመዛላችን በስብሰባዎች ላይ መገኘት አስቸጋሪ ሊሆንብን ይችላል። እነዚህን እንቅፋቶች አሸንፈን በስብሰባዎች ላይ አዘውትረን የመገኘት ልማድ ለማዳበር ምን ሊረዳን ይችላል? [1] የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶቻችንና ሌሎች ሰዎች በስብሰባዎች ላይ የመገኘትን አስፈላጊነት እንዲገነዘቡ ልንረዳቸው የምንችለው እንዴት ነው? በዚህ ርዕስ ውስጥ በስብሰባዎች ላይ እንድንገኝ የሚያነሳሱንን ስምንት ምክንያቶች እንመለከታለን። እነዚህን ምክንያቶች በሦስት ልንከፍላቸው እንችላለን፦ በስብሰባዎች ላይ መገኘትህ (1) አንተን የሚጠቅምህ እንዴት ነው? (2) ሌሎችን የሚጠቅመው እንዴት ነው? (3) ይሖዋን የሚያስደስተው ለምንድን ነው? [2]
አንተን የሚጠቅምህ እንዴት ነው?
4. አንድ ላይ መሰብሰባችን ስለ ይሖዋ ለመማር የሚረዳን እንዴት ነው?
4 ስብሰባዎች ያስተምሩናል። በእያንዳንዱ የጉባኤ ስብሰባ ላይ ስለ አምላካችን ስለ ይሖዋ እንማራለን። ለምሳሌ ያህል፣ ወደ ይሖዋ ቅረብ የተባለው መጽሐፍ በአብዛኞቹ ጉባኤዎች ውስጥ ወደ ሁለት ዓመት ለሚጠጋ ጊዜ በጉባኤ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ላይ ተጠንቷል። በዚህ ዝግጅት አማካኝነት የአምላክን ባሕርያት ማጥናታችን እንዲሁም ወንድሞቻችንና እህቶቻችን የሰጧቸውን ከልብ የመነጩ ሐሳቦች መስማታችን በሰማይ የሚኖረውን አባታችንን ይበልጥ እንድንወደው አላደረገንም? በተጨማሪም በጉባኤ ለሚቀርቡ ንግግሮችና ሠርቶ ማሳያዎች እንዲሁም ለመጽሐፍ ቅዱስ ንባቡ ትኩረት መስጠታችን ስለ አምላክ ቃል ያለን እውቀት እንዲጨምር ያደርጋል። (ነህ. 8:8) ለምሳሌ ያህል፣ በየሳምንቱ ለሚቀርበው የመጽሐፍ ቅዱስ ንባብ ጎላ ያሉ ነጥቦች ስትዘጋጅና ስብሰባው ላይ ተገኝተህ ትምህርቱን ስታዳምጥ ስለምታገኛቸው መንፈሳዊ ዕንቁዎች እስቲ ቆም ብለህ አስብ!
5. ስብሰባዎች ከመጽሐፍ ቅዱስ የተማርከውን ነገር ተግባራዊ እንድታደርግና የምትሰብክበትን መንገድ እንድታሻሽል የረዱህ እንዴት ነው?
5 በስብሰባዎች ላይ የመጽሐፍ ቅዱስን መሠረታዊ ሥርዓቶች በሁሉም የሕይወታችን ዘርፎች ተግባራዊ ማድረግ የምንችለው እንዴት እንደሆነ እንማራለን። (1 ተሰ. 4:9, 10) ለምሳሌ ያህል፣ የመጠበቂያ ግንብ የጥናት ርዕሶች የሚዘጋጁት የአምላክ ሕዝቦች የሚያስፈልጓቸውን ነገሮች ግምት ውስጥ በማስገባት ነው። ግቦችህን መለስ ብለህ እንድትገመግም፣ የእምነት ባልንጀሮችህን ይቅር እንድትል ወይም የጸሎትህን ይዘት እንድታሻሽል ያነሳሳህ የመጠበቂያ ግንብ ጥናት አለ? በሳምንቱ መሃል በሚደረገው ስብሰባ ላይ ለአገልግሎታችን ሥልጠና እናገኛለን። ምሥራቹን መስበክና ቅዱስ ጽሑፋዊ መሠረታዊ ሥርዓቶችን ውጤታማ በሆነ መንገድ ማስተማር የምንችለው እንዴት እንደሆነ እንማራለን።—ማቴ. 28:19, 20
6. ስብሰባዎቻችን የሚያበረታቱንና የሚያጠናክሩን እንዴት ነው?
6 ስብሰባዎች ያበረታቱናል። ይህ ሥርዓት በአስተሳሰባችን፣ በስሜታችንና በመንፈሳዊነታችን ላይ ጫና ያሳድራል። ከዚህ በተቃራኒ የጉባኤ ስብሰባዎች ያበረታቱናል እንዲሁም ያጠናክሩናል። (የሐዋርያት ሥራ 15:30-32ን አንብብ።) በብዙዎቹ ስብሰባዎቻችን ላይ የመጽሐፍ ቅዱስን ትንቢቶች ፍጻሜ እንመረምራለን። ይህ ደግሞ ይሖዋ ስለ ወደፊቱ ጊዜ የሰጣቸው ተስፋዎችም እንደሚፈጸሙ ያለንን እምነት ያጠናክርልናል። እርግጥ ነው፣ ማበረታቻ የምናገኘው ከመድረክ ከሚቀርበው ትምህርት ብቻ አይደለም። በስብሰባዎች ላይ ሐሳብ የሚሰጡና ከልባቸው የሚዘምሩ የእምነት ባልንጀሮቻችንም ያንጹናል። (1 ቆሮ. 14:26) በተጨማሪም ከስብሰባዎቻችን በፊትና በኋላ ከወንድሞቻችንና ከእህቶቻችን ጋር ስንጨዋወት፣ ከልብ የሚወዱን ወዳጆች እንዳሉን ስለምንገነዘብ መንፈሳችን ይታደሳል።—1 ቆሮ. 16:17, 18
7. በስብሰባዎቻችን ላይ መገኘት በጣም አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው?
ራእይ 2:7) በእርግጥም ኢየሱስ የክርስቲያን ጉባኤን የሚመራው በመንፈስ ቅዱስ አማካኝነት ነው። ፈተናዎችን ለመቋቋም፣ ለአገልግሎት የሚያስፈልገንን ድፍረትና ሥልጠና ለማግኘት እንዲሁም ጥሩ ውሳኔዎችን ለማድረግ የመንፈስ ቅዱስ እርዳታ ያስፈልገናል። እንግዲያው የጉባኤ ስብሰባዎችን ጨምሮ፣ ይህን መንፈስ ማግኘት የምንችልበት ማንኛውም አጋጣሚ እንዲያመልጠን አንፍቀድ።
7 በስብሰባዎች ላይ መንፈስ ቅዱስ እናገኛለን። ክብር የተጎናጸፈው ኢየሱስ ክርስቶስ “መንፈስ ለጉባኤዎቹ የሚናገረውን ጆሮ ያለው ይስማ” ብሏል። (ሌሎችን የሚጠቅመው እንዴት ነው?
8. በስብሰባዎች ላይ መገኘታችን፣ ሐሳብ መስጠታችንና መዘመራችን ወንድሞቻችንን የሚጠቅማቸው እንዴት ነው? (“ምንጊዜም ከስብሰባው በኋላ የተሻለ ጤንነት ይሰማዋል” የሚለውን ሣጥንም ተመልከት።)
8 ስብሰባዎች ለወንድሞቻችን ፍቅራችንን ለመግለጽ አጋጣሚ ይሰጡናል። በጉባኤህ ያሉ አንዳንድ ወንድሞችና እህቶች የሚያጋጥሟቸውን ተፈታታኝ ሁኔታዎች ቆም ብለህ አስብ። ሐዋርያው ጳውሎስ “አንዳችን ለሌላው እናስብ” ብሎ መጻፉ የሚያስገርም አይደለም! ጳውሎስ በመቀጠል አሳቢነታችንን ማሳየት የምንችልበት አንዱ መንገድ ‘መሰብሰባችንን ቸል ባለማለት’ እንደሆነ ገልጿል። (ዕብ. 10:24, 25 ግርጌ) በስብሰባዎች ላይ መገኘትህ፣ ለወንድሞችህ ጊዜህንና ትኩረትህን መስጠት እንዲሁም አሳቢነት ማሳየት እንደምትፈልግ ያሳያል። በተጨማሪም የምትሰጠው ሐሳብ እንዲሁም ከልብ በመነጨ ስሜት መዘመርህ የእምነት ባልንጀሮችህን ያበረታታል።—ቆላ. 3:16
9, 10. (ሀ) በዮሐንስ 10:16 ላይ ኢየሱስ የተናገረው ሐሳብ ከወንድሞቻችን ጋር መሰብሰብ አስፈላጊ የሆነበትን ምክንያት ለመረዳት የሚያስችለን እንዴት ነው? አብራራ። (ለ) አዘውትረን በስብሰባዎች ላይ መገኘታችን የማያምን የቤተሰብ አባል ያላቸውን ክርስቲያኖች የሚጠቅመው እንዴት ነው?
9 ስብሰባዎች ከእምነት ባልንጀሮቻችን ጋር አንድነት እንዲኖረን ይረዱናል። (ዮሐንስ 10:16ን አንብብ።) ኢየሱስ ራሱን ከእረኛ፣ ተከታዮቹን ደግሞ ከበግ መንጋ ጋር አመሳስሏል። አንድ ምሳሌ እንመልከት፦ ሁለት በጎች አንድ ኮረብታ ላይ፣ ሌሎች ሁለት በጎች ሸለቆ ውስጥ፣ አንድ ሌላ በግ ደግሞ ብቻውን ነጠል ብሎ ሲግጥ ብታይ እነዚህ አምስት በጎች አንድ መንጋ እንደሆኑ ታስባለህ? በተለምዶ አንድ መንጋ የሚባሉት፣ በእረኛቸው ሥር አንድ ላይ ያሉ በጎች ናቸው። በተመሳሳይ እኛም ሆን ብለን ራሳችንን ከመንጋው የምናገልል ከሆነ እረኛችንን መከተል አንችልም። ‘በአንድ እረኛ’ ሥር ያለው “አንድ መንጋ” አባላት መሆን ከፈለግን ከሌሎች ክርስቲያኖች ጋር መሰብሰብ ይኖርብናል።
10 በስብሰባ ላይ ስንገኝ ለወንድማማች ማኅበራችን አንድነት አስተዋጽኦ እናደርጋለን። (መዝ. 133:1) አንዳንድ የእምነት ባልንጀሮቻችንን፣ ወላጆቻቸው ወይም ወንድሞቻቸውና እህቶቻቸው አግልለዋቸዋል። ያም ሆኖ ኢየሱስ፣ የሚወዳቸውና የሚንከባከባቸው መንፈሳዊ ቤተሰብ እንደሚሰጣቸው ቃል ገብቷል። (ማር. 10:29, 30) አዘውትረን በስብሰባዎች ላይ ስንገኝ ለእነዚህ ውድ ክርስቲያኖች እንደ አባት፣ እናት፣ ወንድም ወይም እህት መሆን እንችላለን! ታዲያ ይህን ማወቃችን በሁሉም ስብሰባዎች ላይ ለመገኘት የምንችለውን ያህል ጥረት እንድናደርግ አያነሳሳንም?
ይሖዋን የሚያስደስተው ለምንድን ነው?
11. በስብሰባዎች ላይ ስንገኝ ለይሖዋ የሚገባውን የምንሰጠው እንዴት ነው?
11 በስብሰባዎች ላይ ስንገኝ ለይሖዋ የሚገባውን እንሰጣለን። ይሖዋ ፈጣሪያችን እንደመሆኑ መጠን ውዳሴ፣ ግርማ፣ ምስጋና እና ክብር ሊሰጠው ይገባል። (ራእይ 7:12ን አንብብ።) በስብሰባዎቻችን ላይ ስንጸልይ፣ ስንዘምርና ስለ ይሖዋ ስንናገር ለእሱ የሚገባውን ነገር ይኸውም አምልኮ እያቀረብን ነው። በጣም ብዙ ነገር ላደረገልን አምላክ ክብር የመስጠት አጋጣሚያችንን ከፍ አድርገን እንመለከታለን።
12. ይሖዋ በስብሰባዎች ላይ እንድንገኝ የሰጠንን መመሪያ ስንታዘዝ ምን ይሰማዋል?
12 ይሖዋን ልንታዘዘውም ይገባል። በተለይ አሁን ባለንበት የመጨረሻው ጊዜ መሰብሰባችንን ቸል እንዳንል አዞናል። ይህን መመሪያ በፈቃደኝነት ስንታዘዝ ይሖዋ ይደሰታል። (1 ዮሐ. 3:22) በእያንዳንዱ ስብሰባ ላይ ለመገኘት የምናደርገውን ጥረት ይመለከታል፤ እንዲሁም ትልቅ ቦታ ይሰጠዋል።—ዕብ. 6:10
13, 14. በስብሰባዎች ላይ መገኘታችን ወደ ይሖዋና ወደ ኢየሱስ ለመቅረብ የሚረዳን እንዴት ነው?
13 በስብሰባዎች ላይ ስንገኝ ወደ ይሖዋና ወደ ልጁ መቅረብ እንደምንፈልግ እናሳያለን። በስብሰባዎቻችን ላይ ታላቁ አስተማሪያችን ይሖዋ፣ በቃሉ በመጽሐፍ ቅዱስ አማካኝነት መመሪያ ይሰጠናል። (ኢሳ. 30:20, 21) በስብሰባዎቻችን ላይ የሚገኙ የማያምኑ ሰዎች እንኳ “አምላክ በእርግጥ በመካከላችሁ ነው” የሚል መደምደሚያ ላይ ሊደርሱ ይችላሉ። (1 ቆሮ. 14:23-25) ይሖዋ ስብሰባዎችን በቅዱስ መንፈሱ የሚመራ ሲሆን መንፈሳዊ ትምህርት የሚሰጠን እሱ ነው። በመሆኑም በስብሰባዎቻችን ላይ የይሖዋን ድምፅ የምንሰማ ከመሆኑም ሌላ ፍቅራዊ እንክብካቤ እንደሚያደርግልን እናስተውላለን። ይህም ወደ እሱ እንድንቀርብ ያደርገናል።
14 ኢየሱስ “ሁለት ወይም ሦስት ሆነው በስሜ በሚሰበሰቡበት በዚያ በመካከላቸው እገኛለሁ” ብሏል። (ማቴ. 18:20) ኢየሱስ የተናገረው ነገር ከስብሰባዎቻችን ጋር በተያያዘም ይሠራል። ክርስቶስ የጉባኤው ራስ እንደመሆኑ መጠን የአምላክን ሕዝቦች ባቀፉት ጉባኤዎች ‘መካከል ይመላለሳል።’ (ራእይ 1:20 እስከ 2:1) እስቲ አስበው! ይሖዋና ኢየሱስ በክርስቲያናዊ ስብሰባዎች አማካኝነት ያበረታቱናል። ይሖዋ ወደ እሱና ወደ ልጁ ለመቅረብ ምን ያህል እንደምንጓጓ ሲመለከት ምን የሚሰማው ይመስልሃል?
15. በስብሰባዎች ላይ መገኘታችን አምላክን ለመታዘዝ እንደምንፈልግ የሚያሳየው እንዴት ነው? አብራራ።
15 በስብሰባዎች ላይ ስንገኝ የአምላክን ሉዓላዊነት እንደምንደግፍ እናሳያለን። ይሖዋ በስብሰባዎች ላይ እንድንገኝ ያዘዘን ቢሆንም ይህን እንድናደርግ አያስገድደንም። (ኢሳ. 43:23) በመሆኑም ይሖዋን ከልባችን እንደምንወደውና የእሱን አገዛዝ አጥብቀን እንደምንደግፍ ማሳየት የእኛ ፋንታ ነው። (ሮም 6:17) ለምሳሌ ያህል፣ አሠሪያችን ብዙ እንድንሠራ ስለሚጠብቅብን አዘውትረን በስብሰባ ላይ መገኘት አስቸጋሪ ቢሆንብን ምን እናደርጋለን? አሊያም ደግሞ የመንግሥት ባለሥልጣናት ለአምልኮ መሰብሰባችንን ካልተውን እንደሚቀጡን፣ እንደሚያስሩን ወይም ከዚያ የከፋ ነገር እንደሚያደርጉብን ያስፈራሩን ይሆናል። በሌላ በኩል ደግሞ በስብሰባዎች ላይ መገኘታችንን ትተን ለመዝናናት እንፈተን ይሆናል። ከላይ ከተጠቀሱት ሁኔታዎች ጋር በተያያዘ ‘የምናገለግለው ማንን ነው?’ ለሚለው ጥያቄ መልስ መስጠት አለብን። (ሥራ 5:29) የይሖዋን ሉዓላዊነት ለመደገፍ ስንመርጥ ልቡን ደስ እናሰኛለን።—ምሳሌ 27:11
አንድ ላይ ለመሰብሰብ ጥረት ማድረጋችሁን ቀጥሉ
16, 17. (ሀ) በመጀመሪያው መቶ ዘመን የነበሩ ክርስቲያኖች ለስብሰባዎች ትልቅ ቦታ ይሰጡ እንደነበር እንዴት እናውቃለን? (ለ) ወንድም ጆርጅ ጋንጋስ ስለ ክርስቲያናዊ ስብሰባዎች ምን ተሰምቶታል?
16 የጥንቶቹ ክርስቲያኖች በ33 ዓ.ም. በዋለው የጴንጤቆስጤ በዓል ላይ ከተፈጸመው አስደናቂ ተአምር በኋላ አንድ ላይ ይሰበሰቡ የነበረው ለተወሰነ ጊዜ ብቻ አይደለም። መጽሐፍ ቅዱስ “የሐዋርያቱንም ትምህርት በትኩረት መከታተላቸውን ቀጠሉ፤ . . . በየዕለቱም በአንድ ልብ ሆነው በቤተ መቅደሱ አዘውትረው ይገኙ ነበር” ይላል። (ሥራ 2:42, 46) “አዘውትረው ይገኙ ነበር” ተብሎ የተተረጎመው የግሪክኛ ሐሳብ በአንድ ነገር መጽናትን የሚያመለክት ሲሆን ይህም ከፍተኛ ጥረት ማድረግን ይጠይቃል። በሮም አገዛዝ ሥር ለሚኖሩትና በጊዜው ከነበሩት የሃይማኖት መሪዎች ተቃውሞ ለሚደርስባቸው ለእነዚያ ክርስቲያኖች በስብሰባዎች ላይ መገኘት ቀላል አልነበረም። ያም ቢሆን በስብሰባዎች ላይ አዘውትረው ይገኙ ነበር።
17 በዛሬው ጊዜ የሚገኙ በርካታ የይሖዋ አገልጋዮች ለክርስቲያናዊ ስብሰባዎች ጥልቅ አድናቆት እንዳላቸው አሳይተዋል። ከ22 ለሚበልጡ ዓመታት የበላይ አካል አባል ሆኖ ያገለገለው ወንድም ጆርጅ ጋንጋስ እንዲህ ብሏል፦ “ከወንድሞች ጋር መሰብሰብ ማለት ለእኔ፣ በሕይወቴ ውስጥ ትልቅ ደስታና ማበረታቻ ከሚሰጡኝ ነገሮች አንዱ ነው። በተቻለ መጠን ወደ መንግሥት አዳራሽ ቀድመው ከሚደርሱትና መጨረሻ ከሚወጡት ሰዎች መካከል መሆን እፈልጋለሁ። ከአምላክ ሕዝቦች ጋር ስነጋገር ውስጣዊ እርካታ ይሰማኛል። ከእነሱ ጋር ስሆን ልክ ቤቴ ውስጥ ከቤተሰቤ ጋር እንዳለሁ እንዲሁም በመንፈሳዊ ገነት ውስጥ እንደሆንኩ ይሰማኛል።” አክሎም “የኮምፓስ ቀስት ሁልጊዜ ወደ ሰሜን እንደሚያመለክት ሁሉ የእኔም የዘወትር ሐሳብና ፍላጎት በስብሰባዎች ላይ መገኘት ነው” ብሏል።
18. ስለ ስብሰባዎቻችን ምን ይሰማሃል? ምን ለማድረግስ ቆርጠሃል?
18 አንተስ ይሖዋን ለማምለክ አንድ ላይ ስለ መሰብሰብ እንዲህ ይሰማሃል? ከሆነ በስብሰባዎች ላይ አዘውትረህ ለመገኘት የምታደርገውን ልባዊ ጥረት ግፋበት። በዚህ መንገድ የንጉሥ ዳዊት ዓይነት ስሜት እንዳለህ ታሳያለህ፤ ዳዊት እንዲህ ብሏል፦ “ይሖዋ ሆይ፣ የምትኖርበትን ቤት . . . እወዳለሁ።”—መዝ. 26:8
^ [1] (አንቀጽ 3) አንዳንድ የእምነት ባልንጀሮቻችን፣ ከባድ ሕመምን የመሳሰሉ ከአቅማቸው በላይ የሆኑ ችግሮች ስላሉባቸው አዘውትረው በስብሰባዎች ላይ መገኘት አይችሉም። እነዚህ ክርስቲያኖች ይሖዋ ሁኔታቸውን እንደሚረዳላቸውና በሙሉ ነፍስ የሚያቀርቡትን አምልኮ ከፍ አድርጎ እንደሚመለከተው እርግጠኛ መሆን ይችላሉ። ሽማግሌዎች፣ አቅማቸው ውስን የሆነው እነዚህ ክርስቲያኖች በስብሰባዎች ላይ ከሚቀርቡት መንፈሳዊ ፕሮግራሞች እንዲጠቀሙ ለመርዳት ዝግጅት ሊያደርጉ ይችላሉ፤ ለምሳሌ፣ ስብሰባውን በስልክ እንዲከታተሉ ወይም ተቀድቶ እንዲያዳምጡት ማድረግ ይቻላል።
^ [2] (አንቀጽ 3) “መሰብሰብ የሚያስፈልገን ለምንድን ነው?” የሚለውን ሣጥን ተመልከት።