የሕይወት ታሪክ
የቀድሞዎቹ መነኮሳት እውነተኛ መንፈሳዊ እህትማማቾች ሆኑ
“በቃሽ፣ አቁሚ። ከዚህ በኋላ ስለ አንቺ ሃይማኖት ምንም ነገር መስማት አልፈልግም። በጣም ያበሳጨኛል። አንቺ ራስሽ አስጠልተሽኛል!” አሁን 91 ዓመቴ ቢሆንም ታናሽ እህቴ አራሴሊ የተናገረቻቸው እነዚህ ቃላት ምን ያህል ጎድተውኝ እንደነበር ዛሬም ድረስ አልረሳውም። ይሁንና “የአንድ ነገር ፍጻሜ ከጅማሬው ይሻላል” የሚለውን የመክብብ 7:8 ጥቅስ እውነተኝነት በእኛ ሕይወት አይተነዋል።—ፌሊሳ
ፌሊሳ፦ ቤተሰባችን በጣም ሃይማኖተኛ ነበር። ከዘመዶቻችን መካከል 13 የሚሆኑት ወይ ቀሳውስት ናቸው አሊያም በካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ ያገለግላሉ። እንዲያውም በአንድ የካቶሊክ ትምህርት ቤት አስተማሪ የነበረው የእናቴ የአክስት ልጅ፣ ቅዱስ እንዲባል ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዳግማዊ ጆን ፖል ሐሳብ አቅርበው ነበር። የቤተሰባችን ኑሮ ዝቅተኛ ነበር። አባቴ ቀጥቃጭ ሲሆን እናቴ በእርሻ ላይ ትሠራ ነበር። በቤተሰባችን ውስጥ ካሉት ስምንት ልጆች መካከል የመጀመሪያዋ እኔ ነኝ።
የ12 ዓመት ልጅ ሳለሁ የስፔኑ የእርስ በርስ ጦርነት ፈነዳ። ከጦርነቱ በኋላ አባቴ ወህኒ ወረደ፤ አባቴ የነበረው የለዘብተኝነት አቋም በወቅቱ ያለውን አምባገነናዊ መንግሥት አላስደሰተውም። እናታችን፣ ቤተሰባችን የሚያስፈልገውን ማቅረብ በጣም ስለከበዳት አራሴሊ፣ ላውሪ እና ራሞኒ የተባሉትን ሦስቱን ታናናሽ እህቶቼን በቢልባው፣ ስፔን ወደሚገኝ የሴቶች ገዳም እንድትልካቸው አንድ ጓደኛዋ ሐሳብ አቀረበችላት። እዚያ ከሆኑ ቢያንስ የሚበሉት አያጡም።
አራሴሊ፦ በወቅቱ ገና የ14, የ12 እና የ10 ዓመት ልጆች ስለነበርን ከቤተሰባችን መለየት በጣም ከበደን። በቢልባው የጽዳት ሥራ እንሠራ ነበር። ከሁለት ዓመት በኋላ መነኮሳቱ፣ ዛራጎዛ ወደሚገኝ አረጋውያን የሚጦሩበት ትልቅ የሴቶች ገዳም አዛወሩን። ሥራችን ማዕድ ቤት ማጽዳት ሲሆን በአሥራዎቹ ዕድሜ ላይ ለምንገኝ ልጆች ይህ በጣም አድካሚ ነበር።
ፌሊሳ፦ እህቶቼ ወደ ዛራጎዛ ሲሄዱ እናቴና ቄስ የሆነው አጎቴ፣ እኔም እዚያው ገዳም ሄጄ ብሠራ እንደሚሻል ወሰኑ። ወደዚያ መሄዴ በአካባቢያችን ካለ አንድ የሚወደኝ ወጣት እንድርቅ እንደሚያደርገኝ ተሰምቷቸው ነበር። አጥባቂ ሃይማኖተኛ ስለነበርኩ በገዳም ውስጥ ለተወሰነ ጊዜ መቆየቴ አስደሰተኝ። በየዕለቱ ቅዳሴ ላይ የምገኝ ሲሆን በአፍሪካ
እንደሚያገለግለው የአክስቴ ልጅ ሚስዮናዊ ለመሆን አስቤ ነበር።በገዳሙ ውስጥ ያሉት መነኮሳት ወደ ሌላ አገር ሄጄ አምላክን ለማገልገል እንደምፈልግ ስነግራቸው ብዙም አላበረታቱኝም፤ የገዳም ሕይወት እስር ቤት ሆነብኝ። በመሆኑም ከአንድ ዓመት በኋላ፣ ቄስ የሆነውን አጎቴን ለመንከባከብ ወደ ቤት ተመለስኩ። የቤት ውስጥ ሥራ ከመሥራት በተጨማሪ ሁልጊዜ ማታ ላይ ከአጎቴ ጋር በመቁጠሪያ እንጸልይ ነበር። ከዚህም ሌላ የቤተ ክርስቲያኑን አበቦች ማስተካከል እንዲሁም የድንግል ማርያምንና “የቅዱሳንን” ምስሎች ማሰማመር እወድ ነበር።
አራሴሊ፦ ውሎ አድሮ በገዳም ውስጥ ያለን ሕይወት ተለወጠ። ቃለ መሃላ ከፈጸምኩ በኋላ መነኮሳቱ እኔንና እህቶቼን ለያዩን። ራሞኒ እዚያው ዛራጎዛ ቀረች፤ ላውሪ ወደ ቫሌንሲያ እኔ ደግሞ ወደ ማድሪድ ተላክን፤ በማድሪድ ሳለሁ ሁለተኛውን ቃለ መሃላ ፈጸምኩ። በማድሪድ ያለው ገዳም ለተማሪዎች፣ ለአረጋውያንና ለሌሎች ጎብኚዎች ማረፊያ ስለሚያዘጋጅ በገዳሙ ውስጥ በጣም ብዙ ሥራ ነበር። እኔ የምሠራው ለአረጋውያንና ለታመሙ ሰዎች እርዳታ በሚሰጥበት ክፍል ውስጥ ነበር።
እውነቱን ለመናገር፣ የመነኮሳት ሕይወት ይበልጥ አስደሳች እንደሚሆን ጠብቄ ነበር። መጽሐፍ ቅዱስን ለማንበብና ለመረዳት እጓጓ ነበር። ይሁንና ስለ አምላክም ሆነ ስለ ኢየሱስ ጨርሶ የማይነሳ ከመሆኑም ሌላ በመጽሐፍ ቅዱስም አንጠቀምም። በገዳሙ ውስጥ የላቲንን ቋንቋ በተወሰነ መጠን ከመማር፣ ስለ “ቅዱሳን” ከማጥናትና ማርያምን ከማምለክ ውጭ ያተረፍኩት ነገር ከባድ የጉልበት ሥራ መሥራት ብቻ ነው።
ነገሩ ስላስጨነቀኝ እመምኔቷን (የገዳሙን አስተዳዳሪ መነኩሲት) አነጋገርኳቸው። ቤተሰቤ የእኔ እርዳታ እያስፈለጋቸው እኔ ግን ሌሎች ኪሳቸውን እንዲያደልቡ መልፋቴ ትርጉም እንዳልሰጠኝ ለእመምኔቷ ገለጽኩላቸው። እመምኔቷም ሐሳቤን ለማስቀየርና ገዳሙን ትቼ እንዳልወጣ ለማድረግ ሲሉ አንድ ክፍል ውስጥ ቆለፉብኝ።
በሦስት የተለያዩ ጊዜያት መነኮሳቱ ከክፍሉ ቢያስወጡኝም ከገዳሙ የመውጣት ሐሳቤን እንዳልቀየርኩ ሲያውቁ ግን መልሰው ይቆልፉብኝ ነበር። በአቋሜ መጽናቴን ሲገነዘቡ “የምወጣው ከአምላክ ይልቅ ሰይጣንን ማምለክ ስለፈለግኩ ነው” ብዬ በጽሑፍ እንዳሰፍር ነገሩኝ። ይህም በእጅጉ አስደነገጠኝ፤ ከገዳሙ ለመውጣት በጣም ብፈልግም እንደዚያ ብዬ ለመጻፍ ግን ፈቃደኛ አልሆንኩም። በመጨረሻም አንድ ቄስ ማነጋገር እንደምፈልግ ገለጽኩላቸው፤ ከዚያም ለቄሱ ሁኔታውን ነገርኩት። እሱም በዛራጎዛ ወደሚገኘው ቀደም ሲል ወደነበርኩበት ገዳም እንድዛወር ዝግጅት አደረገ። በዚያ ለተወሰኑ ወራት ከቆየሁ በኋላ ከገዳሙ እንድወጣ ተፈቀደልኝ። ከዚያ ብዙም ሳይቆይ ላውሪ እና ራሞኒም ከነበሩበት ገዳም ወጡ።
“የተከለከለው” መጽሐፍ አለመግባባት ፈጠረ
ፌሊሳ፦ ከጊዜ በኋላ ትዳር መሠረትኩና ወደ ካንታብሪያ፣ ስፔን ሄድኩ። በዚያም አዘውትሬ ቅዳሴ ላይ መገኘቴን አልተውኩም፤
አንድ እሁድ ዕለት ቄሱ ከመድረክ የተናገረው ማስታወቂያ አስገረመኝ። ቄሱ ወደ ዘላለም ሕይወት የሚመራው እውነት የተባለውን መጽሐፍ እያመለከተ “ይህን መጽሐፍ እዩት!” ሲል በቁጣ ተናገረ። አክሎም “ይህን መጽሐፍ አንድ ሰው ሰጥቷችሁ ከሆነ ለእኔ ስጡኝ አሊያም ጣሉት!” አለ።በወቅቱ መጽሐፉ ባይኖረኝም ይህን መጽሐፍ ለማግኘት ጓጓሁ። የሚገርመው ከጥቂት ቀናት በኋላ ሁለት የይሖዋ ምሥክሮች በሬን አንኳኩና “የተከለከለውን” መጽሐፍ ሰጡኝ። መጽሐፉን የዚያኑ ዕለት አንብቤው አደርኩ፤ ከዚያም ሴቶቹ ተመልሰው ሲመጡ መጽሐፍ ቅዱስን ከእነሱ ጋር ለማጥናት ተስማማሁ።
ብዙም ሳይቆይ እውነት ወደ ልቤ ጠልቆ ገባ። ቀድሞውንም ሃይማኖተኛ ነበርኩ፤ እውነትን ሳውቅ ደግሞ ለይሖዋ ጥልቅ ፍቅር ያደረብኝ ከመሆኑም ሌላ አገልግሎቱን በቅንዓት ማከናወን ጀመርኩ። በ1973 ተጠመቅኩ። እውነትን ለቤተሰቦቼ ለመንገር ብዙ አጋጣሚዎች ባይኖሩኝም ይህን ለማድረግ የቻልኩትን ያህል እጥር ነበር። በመግቢያው ላይ እንደጠቀስኩት ቤተሰቤ በተለይም እህቴ አራሴሊ እምነቴን አጥብቃ ተቃወመች።
አራሴሊ፦ በገዳሙ ውስጥ ያጋጠሙኝ መጥፎ ነገሮች ምሬት እንዲያድርብኝ አድርገውኝ ነበር። ሆኖም እሁድ እሁድ የቅዳሴ ሥርዓት ላይ የምገኝ ሲሆን በየዕለቱ በመቁጠሪያዬ እጸልይ ነበር። መጽሐፍ ቅዱስን ለመረዳት ከፍተኛ ፍላጎት ስለነበረኝ አምላክ እንዲረዳኝ ጸለይኩ። ይሁንና እህቴ ፌሊሳ ስለ አዲሱ እምነቷ በግለት ስትነግረኝ አክራሪ እንደሆነች ተሰማኝ። በመሆኑም አጥብቄ ተቃወምኳት።
ከተወሰኑ ዓመታት በኋላ ለሥራ ወደ ማድሪድ ሄድኩ፤ እዚያም ትዳር መሠረትኩ። እያደር በጣም ተጠራጣሪ ሆንኩ። ቅዳሴ ላይ አዘውትረው የሚገኙ ሰዎች በወንጌሎች ላይ ያሉትን ትምህርቶች በሕይወታቸው ውስጥ ተግባራዊ እንደማያደርጉ አስተዋልኩ። በመሆኑም ቤተ ክርስቲያን መሄዴን አቆምኩ። “በቅዱሳን፣” በኑዛዜ ወይም በገሃነመ እሳት ማመን ተውኩ። አልፎ ተርፎም ያሉኝን ምስሎች በሙሉ አስወገድኩ። የወሰድኩት እርምጃ ትክክል ይሁን አይሁን የማውቀው ነገር አልነበረም። በጣም አዝኜ ነበር፤ ያም ሆኖ አምላክን “ላውቅህ እፈልጋለሁ። እርዳኝ!” ብዬ መለመኔን አልተውኩም። የይሖዋ ምሥክሮች በተለያዩ ወቅቶች ቤቴ እንደመጡ ትዝ ይለኛል፤ በሩን ከፍቼላቸው ግን አላውቅም። በማንኛውም ሃይማኖት ላይ እምነት አልነበረኝም።
በፈረንሳይ የምትኖረው ላውሪ እና በስፔን የምትኖረው ራሞኒ በ1980ዎቹ መጀመሪያ አካባቢ ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር መጽሐፍ ቅዱስን ማጥናት ጀመሩ። እንደ ፌሊሳ ሁሉ እነሱም እንደተታለሉ ተሰማኝ። ከጊዜ በኋላ አንጀሊነስ ከተባለች ጎረቤቴ ጋር ወዳጅነት መሠረትኩ። እሷም የይሖዋ ምሥክር ናት። አንጀሊነስ እና ባለቤቷ መጽሐፍ ቅዱስን እንዳጠና በተደጋጋሚ ጊዜ ይጠይቁኝ ነበር። በሃይማኖት ላይ እምነት እንደሌለኝ ብናገርም የመጽሐፍ ቅዱስን እውነት እንደተጠማሁ መገንዘብ ችለው ነበር። በመጨረሻም “እሺ። ሆኖም ከእናንተ ጋር የማጠናው የራሴን መጽሐፍ ቅዱስ የምጠቀም ከሆነ ብቻ ነው” አልኳቸው፤ ይህን ስል ናካር ኮሉንጋ የተባለውን የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉም ማለቴ ነበር።
በመጨረሻ መጽሐፍ ቅዱስ አስማማን
ፌሊሳ፦ በ1973 በተጠመቅኩበት ወቅት የካንታብሪያ ግዛት ዋና ከተማ በሆነችው በሳንታንደር 70 የሚያህሉ የይሖዋ ምሥክሮች ነበሩ። ክልላችን በጣም ሰፊ በመሆኑ በአውቶቡስ፣ በኋላ ላይ ደግሞ በመኪና እየተጓዝን በሁሉም የግዛቱ ክፍል ለመስበክ እንጥር ነበር። በዚህ ግዛት ውስጥ የሚገኙትን በመቶዎች የሚቆጠሩ መንደሮች እስክናዳርስ ድረስ ወደ እያንዳንዱ መንደር ሄደናል።
በእነዚህ ሁሉ ዓመታት ብዙ ሰዎችን መጽሐፍ ቅዱስ የማስጠናት መብት ያገኘሁ ሲሆን ከመካከላቸው 11ዱ ተጠምቀዋል። አብዛኞቹ ካቶሊኮች ነበሩ። እኔ ራሴ በአንድ ወቅት አጥባቂ ካቶሊክ ስለነበርኩ ታጋሽ መሆንና ሁኔታቸውን መረዳት እንዳለብኝ አውቃለሁ። አጥብቀው የሚያምኑባቸውን ነገሮች ለመተው ጊዜ እንደሚያስፈልጋቸው ተገንዝቤአለሁ፤ በተጨማሪም እውነትን ለይተው ማወቅ እንዲችሉ መጽሐፍ ቅዱስና የይሖዋ ቅዱስ መንፈስ ልባቸውን ሊነኩት እንደሚገባ አስተዋልኩ። (ዕብ. 4:12) ፖሊስ የነበረው ባለቤቴ ብዬንቬኒዶ በ1979 ተጠመቀ፤ እናቴም ከመሞቷ ትንሽ ቀደም ብላ መጽሐፍ ቅዱስን ማጥናት ጀምራ ነበር።
አራሴሊ፦ ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር መጽሐፍ ቅዱስን ማጥናት ስጀምር በጣም ተጠራጣሪ ነበርኩ። ሳምንት አልፎ ሳምንት ሲተካ ግን በውስጤ የነበረው ምሬት እየጠፋ መሆኑን አስተዋልኩ። ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር በተያያዘ ያስገረመኝ፣ የሚሰብኩትን ነገር ተግባራዊ የሚያደርጉት መሆኑ ነው። ጥርጣሬዬ ተወግዶ እምነት ማዳበር ስጀምር ይበልጥ ደስተኛ ሆንኩ። አንዳንድ ጎረቤቶቼ እንኳ “አራሴሊ፣ የመረጥሽውን ጎዳና እንዳትተዪ!” አሉኝ።
“ይሖዋ፣ ተስፋ ቆርጠህ ስላልተውከኝ እንዲሁም ስፈልገው የነበረውን ነገር ይኸውም የመጽሐፍ ቅዱስን ትክክለኛ እውቀት እንዳገኝ ብዙ አጋጣሚዎችን ስለከፈትክልኝ አመሰግንሃለሁ” ብዬ እንደጸለይኩ አስታውሳለሁ። እህቴን ፌሊሳን ስሜቷን የሚጎዳ ነገር ተናግሬያት ስለነበር ይቅር እንድትለኝ ጠየቅኳት። እንደ ድሮው መከራከራችን ቀረና አስደሳች የመጽሐፍ ቅዱስ ውይይት እናደርግ ጀመር። በ1989 በ61 ዓመቴ ተጠመቅኩ።
ፌሊሳ፦ አሁን 91 ዓመቴ ሲሆን ባለቤቴም ሞቷል፤ የቀድሞው ጥንካሬ የለኝም። ያም ቢሆን በየዕለቱ መጽሐፍ ቅዱስን አነባለሁ፤ ጤንነቴ በሚፈቅደው መጠን በስብሰባዎች ላይ እገኛለሁ፤ እንዲሁም የቻልኩትን ያህል በአገልግሎት መካፈል ያስደስተኛል።
አራሴሊ፦ በአገልግሎት ለማገኛቸው ቀሳውስትና መነኮሳት ሁሉ መስበክ ደስ ይለኛል፤ ይህን የማደርገው መነኩሲት ስለነበርኩ ሳይሆን አይቀርም። ለእነዚህ ሰዎች በርካታ ጽሑፎችን ያበረከትኩላቸው ከመሆኑም ሌላ አስደሳች ውይይቶችን አድርገናል። አንድ ቄስ ለተወሰነ ጊዜ ካነጋገርኩት በኋላ እንዲህ አለኝ፦ “አራሴሊ፣ በምትይው ነገር ሁሉ እስማማለሁ፤ ሆኖም በዚህ ዕድሜዬ ወዴት እሄዳለሁ? ምዕመኖቼና ቤተሰቦቼ ምን ይሉኛል?” እኔም “አምላክስ ምን ይላል?” አልኩት። ጭንቅላቱን በመነቅነቅ በተናገርኩት ነገር መስማማቱን ገለጸ፤ እንዳዘነም ያስታውቅ ነበር፤ ሆኖም በወቅቱ እውነትን ለመፈለግ ድፍረት አልነበረውም።
ባለቤቴ አብሮኝ ስብሰባ መሄድ እንደሚፈልግ ለመጀመሪያ ጊዜ የተናገረበትን ቀን መቼም አልረሳውም። በሕይወቴ ትልቅ ቦታ ከምሰጣቸው ትዝታዎች መካከል አንዱ ነው። በወቅቱ 80 ዓመት አልፎት የነበረ ቢሆንም ከዚያ ቀን ወዲህ ስብሰባ ቀርቶ አያውቅም። ባለቤቴ መጽሐፍ ቅዱስን አጥንቶ ያልተጠመቀ አስፋፊ ሆነ። አብረን አገልግሎት የወጣንባቸውን አስደሳች ጊዜያት መቼም ቢሆን አልረሳቸውም። ሊጠመቅ ሁለት ወር ሲቀረው በሞት አንቀላፋ።
ፌሊሳ፦ በሕይወቴ ውስጥ በጣም ከምደሰትባቸው ነገሮች አንዱ፣ ይቃወሙኝ የነበሩት ሦስቱ ታናናሽ እህቶቼ፣ በመንፈሳዊም እህቶቼ መሆናቸውን ማየቴ ነው። አብረን መሆን እንዲሁም ስለምንወደው አምላካችን ስለ ይሖዋና ስለ ቃሉ ማውራት በጣም ያስደስተናል! በመጨረሻ እኔና እህቶቼ በመንፈሳዊ አንድ ሆንን። *
^ አን.29 የ87 ዓመቷ አራሴሊ፣ የ91 ዓመቷ ፌሊሳ እና የ83 ዓመቷ ራሞኒ አሁንም ይሖዋን በቅንዓት እያገለገሉ ነው። ላውሪ ለይሖዋ ታማኝነቷን እንደጠበቀች በ1990 በሞት አንቀላፍታለች።