ይህን ያውቁ ኖሯል?
ከዮናስ ዘመን በኋላ ነነዌ ምን ደረሰባት?
በሰባተኛው መቶ ዘመን ዓ.ዓ. የአሦር መንግሥት በዓለም ላይ ካሉት መንግሥታት ሁሉ ሰፊውን ግዛት ይዞ ነበር። የብሪትሽ ሙዚየም ድረ ገጽ እንደሚገልጸው ግዛቱ “በስተ ምዕራብ ከቆጵሮስ አንስቶ በስተ ምሥራቅ እስከ ኢራን ይደርስ ነበር። እንዲያውም በአንድ ወቅት ግብፅንም ጭምር ያካትት ነበር።” የአሦር መዲና የሆነችው ነነዌ በዓለም ላይ ካሉት ከተሞች ሁሉ ትልቋ ነበረች። በከተማዋ ውስጥ ግዙፍ ሐውልቶች፣ አስደናቂ የአትክልት ስፍራዎች፣ የተንቆጠቆጡ ቤተ መንግሥቶች እና ትላልቅ ቤተ መጻሕፍቶች ይገኙ ነበር። በጥንቷ ነነዌ የተገኙ በግድግዳ ላይ የተቀረጹ ጽሑፎች እንደሚያሳዩት ንጉሥ አሹርባኒፓል እንደ ሌሎቹ የአሦር ነገሥታት ራሱን “የዓለም ንጉሥ” በማለት ይጠራ ነበር። በወቅቱ አሦር እና ነነዌ ማንም ሊነካቸው የሚችል አይመስሉም ነበር።
ያም ቢሆን አሦር እጅግ ኃያል በነበረበት ዘመን፣ የይሖዋ ነቢይ የሆነው ሶፎንያስ እንዲህ የሚል ትንቢት ተናገረ፦ “[ይሖዋ አሦርን] ያጠፋል፤ ነነዌንም ባድማና እንደ በረሃ ደረቅ ያደርጋታል።” በተጨማሪም የይሖዋ ነቢይ የሆነው ናሆም እንዲህ የሚል ትንቢት ተናግሯል፦ “ብሩን ዝረፉ፤ ወርቁን ዝረፉ! . . . ከተማዋ ባዶና ወና እንዲሁም ባድማ ሆናለች! . . . አንቺን የሚያይ ሁሉ ከአንቺ ይሸሻል፤ ደግሞም ‘ነነዌ ወድማለች! . . .’ ይላል።” (ሶፎ. 2:13፤ ናሆም 2:9, 10፤ 3:7) ሰዎች እነዚህን ትንቢቶች ሲሰሙ ‘ይህ በእርግጥ ሊፈጸም ይችላል? በእርግጥ ታላቁ አሦር ድል ሊደረግ ይችላል?’ ብለው አስበው ይሆናል። ይህ ጨርሶ ሊሆን የማይችል ይመስል ነበር።
ይሁንና ያልተጠበቀው ነገር ተፈጸመ! በሰባተኛው መቶ ዘመን ዓ.ዓ. መገባደጃ ላይ አሦር በባቢሎናውያን እና በሜዶናውያን ድል ተደርጎ ነበር። ከጊዜ በኋላ ነነዌ ባድማ ሆነች፤ እንዲሁም ጨርሶ ተረሳች! በኒው ዮርክ የሚገኘው ዘ ሜትሮፖሊታን ሙዚየም ኦቭ አርት ያዘጋጀው ጽሑፍ እንደሚገልጸው “በመካከለኛው መቶ ዘመን ከተማዋ ተቀብራ ነበር። ስለ ነነዌ የሚገልጽ ዘገባም የሚገኘው በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ብቻ ነበር።” ቢብሊካል አርኪኦሎጂ ሶሳይቲ ኦንላይን አርካይቭ እንደሚገልጸው “በ1800ዎቹ መጀመሪያ ላይ ታላቋ የአሦር መዲና በእርግጥ በታሪክ ውስጥ መኖሯን የሚያውቅ እንኳ አልነበረም።” ሆኖም የአርኪኦሎጂ ባለሙያ የሆኑት ኦስተን ሄንሪ ላየርድ፣ ነነዌ ትገኝ በነበረበት ቦታ ላይ በ1845 ቁፋሮ ማካሄድ ጀመሩ። በቁፋሮ የተገኙት ነገሮች ነነዌ በእርግጥም ታላቅ ከተማ እንደነበረች ይመሠክራሉ።
ስለ ነነዌ የሚገልጹት ትንቢቶች በትክክል መፈጸማቸው፣ በዛሬው ጊዜ ያሉት መንግሥታት እንደሚጠፉ የሚገልጹት የመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢቶችም ፍጻሜያቸውን እንደሚያገኙ ያለንን እምነት ያጠናክርልናል።—ዳን. 2:44፤ ራእይ 19:15, 19-21