ይህን ያውቁ ኖሯል?
የጥንት እስራኤላውያን ለሙዚቃ ምን ያህል ቦታ ይሰጡ ነበር?
በጥንት እስራኤላውያን ባሕል ውስጥ ሙዚቃ ጉልህ ቦታ ነበረው። መጽሐፍ ቅዱስ፣ የሙዚቃ መሣሪያ ስለሚጫወቱና መዝሙር ስለሚዘምሩ ሰዎች በብዙ ቦታዎች ላይ ይናገራል። አንድ አሥረኛ የሚሆነውን የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል የያዙት መዝሙሮች ናቸው፤ ከእነዚህ መካከል የመዝሙር መጽሐፍ፣ መኃልየ መኃልይ እና ሰቆቃወ ኤርምያስ በዋነኝነት ይጠቀሳሉ። ሚዩዚክ ኢን ቢብሊካል ላይፍ የተባለው መጽሐፍ እንደሚገልጸው፣ መጽሐፍ ቅዱስ “እስራኤላውያን በዕለት ተዕለት ሕይወታቸው ሙዚቃን ይጠቀሙ እንደነበር በግልጽ ያሳያል።”
ሙዚቃ በዕለት ተዕለት ሕይወት ውስጥ። እስራኤላውያን ስሜታቸውን ለመግለጽ ሙዚቃን ይጠቀሙ ነበር። (ኢሳ. 30:29) ሴቶች በነገሥታት የሹመት ሥነ ሥርዓት፣ በበዓላትና በድል ወቅት አታሞ እየመቱ በደስታ ይዘፍኑና ይጨፍሩ ነበር። (መሳ. 11:34፤ 1 ሳሙ. 18:6, 7፤ 1 ነገ. 1:39, 40) በተጨማሪም እስራኤላውያን በሐዘን ወቅት ስሜትን የሚገልጹ ሙሾዎችን ያወርዱ ነበር። (2 ዜና 35:25) በግልጽ ማየት እንደሚቻለው እስራኤላውያን ሙዚቃ በጣም ይወዱ ነበር።
ሙዚቃ በቤተ መንግሥት ውስጥ። የእስራኤል ነገሥታት ሙዚቃ መስማት ያስደስታቸው ነበር። ንጉሥ ሳኦል ሙዚቃ እንዲጫወትለት ዳዊትን ወደ ቤተ መንግሥቱ አስጠርቶታል። (1 ሳሙ. 16:18, 23) ዳዊት ራሱ ንጉሥ ከሆነ በኋላ ደግሞ የሙዚቃ መሣሪያዎችን ፈልስፏል፤ ደስ የሚሉ መዝሙሮችን አቀናብሯል፤ እንዲሁም በይሖዋ ቤተ መቅደስ ውስጥ የሚጫወቱ የሙዚቀኞች ቡድኖችን አደራጅቷል። (2 ዜና 7:6፤ አሞጽ 6:5) ንጉሥ ሰለሞንም በቤተ መንግሥቱ ውስጥ ወንድና ሴት ዘፋኞች ነበሩት።—መክ. 2:8
ሙዚቃ በአምልኮ ውስጥ። በዋነኝነት ደግሞ እስራኤላውያን ሙዚቃን ለይሖዋ አምልኮ ይጠቀሙበት ነበር። እንዲያውም በኢየሩሳሌም ባለው ቤተ መቅደስ ውስጥ የሚጫወቱ 4,000 ሙዚቀኞች ነበሩ። (1 ዜና 23:5) ሲምባል፣ ባለ አውታር መሣሪያዎችና በገና ይጫወቱ እንዲሁም መለከት ይነፉ ነበር። (2 ዜና 5:12) ሆኖም በሙዚቃ ተጠቅመው ይሖዋን ያመልኩ የነበሩት እነዚህ የሠለጠኑ ሙዚቀኞች ብቻ አይደሉም። በርካታ እስራኤላውያን ዓመታዊ በዓላትን ለማክበር ወደ ኢየሩሳሌም በሚሄዱበት ወቅት “ወደ ላይ የመውጣት መዝሙር” ተብለው የሚጠሩትን መዝሙሮች ይዘምሩ እንደነበር ከሁኔታዎች መረዳት ይቻላል። (መዝ. 120–134) በተጨማሪም አንዳንድ የአይሁድ መዛግብት እንደሚገልጹት እስራኤላውያን የፋሲካን ራት በሚበሉበት ወቅት የሃሌል መዝሙሮችን a ይዘምሩ ነበር።
በዛሬው ጊዜም ቢሆን የአምላክ ሕዝቦች ለሙዚቃ ትልቅ ቦታ ይሰጣሉ። (ያዕ. 5:13) መዝሙር መዘመር የአምልኳችን ክፍል ነው። (ኤፌ. 5:19) ሙዚቃ ከእምነት አጋሮቻችን ጋር ያቀራርበናል። (ቆላ. 3:16) በተጨማሪም በመከራ ውስጥ ስንሆን ያጠናክረናል። (ሥራ 16:25) ሙዚቃ በይሖዋ ላይ ያለንን እምነትና ለእሱ ያለንን ፍቅር የምናሳይበት ግሩም መንገድ ነው።
a አይሁዳውያን ይሖዋን ለማወደስ የሚዘመሩትን ከመዝሙር 113 እስከ 118 ያሉትን መዝሙሮች “የሃሌል መዝሙሮች” ብለው ይጠሯቸዋል።