በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ቃለ ምልልስ | ፋን ዩ

አንድ የሶፍትዌር ንድፍ አውጪ ስለሚያምኑበት ነገር ምን ይላሉ?

አንድ የሶፍትዌር ንድፍ አውጪ ስለሚያምኑበት ነገር ምን ይላሉ?

ዶክተር ፋን ዩ የሒሳብ ተመራማሪነት ሙያቸውን የጀመሩት በቤጂንግ አቅራቢያ በሚገኘው የቻይና የአቶሚክ ኢነርጂ ኢንስቲትዩት ውስጥ ነው። በወቅቱ በአምላክ መኖር የማያምኑ ከመሆናቸውም ሌላ በዝግመተ ለውጥ ፅንሰ ሐሳብ ያምኑ ነበር። በአሁኑ ጊዜ ግን ዶክተር ዩ፣ ሕይወት ንድፍ አውጪ እንዳለውና ሕይወት ያላቸውን ነገሮች የፈጠረው አምላክ እንደሆነ ያምናሉ። ንቁ! መጽሔት ለእኚህ ሰው ስለሚያምኑበት ነገር ቃለ መጠይቅ አድርጎላቸዋል።

እስቲ ስለ አስተዳደግዎ በጥቂቱ ይንገሩን።

የተወለድኩት በ1959 በፉጆ ሲቲ፣ ጂያንግሺ ግዛት፣ ቻይና ውስጥ ነው። የስምንት ዓመት ልጅ ሳለሁ በአሁኑ ወቅት ‘የባሕል አብዮት’ እየተባለ የሚጠራው እንቅስቃሴ በአገሪቱ ላይ አንዳንድ ለውጦችን ማምጣት ጀምሮ ነበር። የሲቪል መሐንዲስ የነበረው አባቴ ርቆ በሚገኝ በረሃማ አካባቢ የባቡር ሃዲድ እንዲዘረጋ ተመደበ። በዚህ ሥራ ላይ በነበረባቸው በርካታ ዓመታት ውስጥ፣ ሊጠይቀን የሚመጣው በዓመት አንድ ጊዜ ብቻ ነበር። በወቅቱ የምኖረው የአንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት መምህርት ከነበረችው ከእናቴ ጋር ነበር። የምንኖረው እዚያው እናቴ የምታስተምርበት ትምህርት ቤት ውስጥ ነበር። በ1970 ሊዮፋንግ ወደምትባል አንዲት የገጠር መንደር ተዛወርን፤ በዚያን ጊዜ ሊዮፋንግ የምግብ እጥረት የነበረባት ድሃ መንደር ነበረች።

ስለ ቤተሰቦችዎ እምነት ሊነግሩን ይችላሉ?

አባቴ ስለ ሃይማኖትም ሆነ ስለ ፖለቲካ ግድ አልነበረውም። እናቴ ደግሞ ቡዲስት ነበረች። በትምህርት ቤት፣ ሕይወት ያላቸው ነገሮች በሂደት ተሻሽለው እንደመጡ ተምረን ነበር፤ እኔም አስተማሪዎቼ ባስተማሩኝ ነገር አምን ነበር።

ሒሳብ ለማጥናት የመረጡት ለምንድን ነው?

ሒሳብ እውነትን ምክንያታዊ በሆነ መንገድ መፈለግን የሚጠይቅ ሂደት ስለሆነ ይህ ትምህርት ይማርከኛል። የአብዮቱ መሪ ማኦ ሴቱንግ በ1976 ከሞቱ ብዙም ሳይቆይ ዩኒቨርሲቲ ገባሁ። በዋነኝነት ለማጥናት የመረጥኩት የሒሳብ ትምህርት ነው። የማስትሬት ዲግሪዬን እንዳገኘሁ የያዝኩት ሥራ የኑክሌር ማብላያ ንድፍ ለማውጣት የሒሳብ ምርምር ማድረግን የሚጠይቅ ነበር።

መጀመሪያ ላይ ስለ መጽሐፍ ቅዱስ ምን አመለካከት ነበርዎት?

በ1987 በቴክሳስ ኤ ኤንድ ኤም ዩኒቨርሲቲ የዶክትሬት ዲግሪዬን ለመከታተል ወደ ዩናይትድ ስቴትስ መጣሁ። አሜሪካ ውስጥ ብዙ ሰዎች በአምላክ እንደሚያምኑና መጽሐፍ ቅዱስን እንደሚያነቡ አውቅ ነበር። እንዲሁም መጽሐፍ ቅዱስ ብዙ ጥበብ ያዘሉ ምክሮችን እንደያዘ እሰማ ነበር፤ ስለዚህ መጽሐፍ ቅዱስን ማንበብ እንዳለብኝ ተሰማኝ።

በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ያሉትን ትምህርቶች ጠቃሚ ሆነው ባገኛቸውም የተወሰኑ የመጽሐፍ ክፍሎችን መረዳት ከብዶኝ ነበር። በመሆኑም ብዙም ሳይቆይ መጽሐፍ ቅዱስን ማንበብ ተውኩ።

ስለ መጽሐፍ ቅዱስ የማወቅ ፍላጎትዎ በድጋሚ እንዲቀሰቀስ ያደረገው ምንድን ነው?

‘ፈጣሪ አለ’ የሚለው ሐሳብ ለእኔ አዲስ ነገር ነበር፤ በመሆኑም በጉዳዩ ላይ የራሴን ምርምር ለማድረግ ወሰንኩ

በ1990 አንዲት የይሖዋ ምሥክር ቤቴ መጥታ የሰው ልጆች ያላቸውን አስደሳች የወደፊት ተስፋ በተመለከተ መጽሐፍ ቅዱስ ምን እንደሚል አሳየችኝ። ከዚያም አንድ ባልና ሚስት መጥተው መጽሐፍ ቅዱስን እንዲያስተምሩኝ ዝግጅት አደረገች። በቻይና በሚገኝ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ውስጥ ፊዚክስ ታስተምር የነበረችው ባለቤቴ ሊፒንግም ከጊዜ በኋላ መጽሐፍ ቅዱስን ማጥናት ጀመረች፤ እሷም እንደ እኔ አምላክ የለሽ ነበረች። መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ሕይወት አመጣጥ ምን እንደሚያስተምር ተረዳን። ‘ፈጣሪ አለ’ የሚለው ሐሳብ ለእኔ አዲስ ነገር ነበር፤ በመሆኑም በጉዳዩ ላይ የራሴን ምርምር ለማድረግ ወሰንኩ።

ታዲያ ምርምሩን ያደረጉት እንዴት ነው?

የሒሳብ ባለሙያ እንደመሆኔ መጠን ነገሮች ሊከናወኑ የሚችሉበትን አጋጣሚ በስሌት ማስቀመጥ ስለሚቻልበት መንገድ ተምሬያለሁ። በተጨማሪም ሕይወት በራሱ እንዲመጣ ከተፈለገ ፕሮቲኖች አስቀድመው ሊኖሩ እንደሚገባ አውቅ ነበር። ስለዚህ ፕሮቲኖች በራሳቸው ሊመጡ የሚችሉበት አጋጣሚ ምን ያህል እንደሆነ ለማስላት ሞከርኩ። ፕሮቲኖች እስካሁን ከተደረሰባቸው በጣም ውስብስብ የሚባሉ ሞለኪዩሎች መካከል ይመደባሉ፤ ሕይወት ያላቸው ሴሎች ደግሞ እርስ በርሳቸው ልዩ በሆነ መንገድ የሚቀናጁ በሺዎች የሚቆጠሩ የተለያዩ ፕሮቲኖች አሏቸው። በመሆኑም አንዳንዶች የደረሱበት መደምደምያ ላይ ደረስኩ፤ ፕሮቲኖች በራሳቸው ሊገኙ የሚችሉበት አጋጣሚ በጣም አናሳ ከመሆኑ የተነሳ ጨርሶ ሊሆን የማይችል ነገር ነው ሊባል ይችላል! ስለ ዝግመተ ለውጥ ጽንሰ ሐሳብ በሚናገሩ ጽሑፎች ውስጥ፣ ፕሮቲኖች ተቀናጅተው ሕይወት ያላቸውን ነገሮች ሊያስገኙ የቻሉት እንዴት እንደሆነ ይቅርና በጣም ውስብስብ የሆኑት ፕሮቲኖች ራሳቸውም እንኳ ራሳቸውን ሊፈጥሩ የቻሉት እንዴት እንደሆነ የሚገልጽ አጥጋቢ ማብራሪያ ላገኝ አልቻልኩም። ስለዚህ ማስረጃዎቹ በፈጣሪ መኖር እንዳምን አደረጉኝ።

መጽሐፍ ቅዱስ የአምላክ ቃል መሆኑን እንዲያምኑ ያደረግዎት ምንድን ነው?

ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር መጽሐፍ ቅዱስን መማሬን ስቀጥል በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ፍጻሜያቸውን ያገኙ ዝርዝር ሐሳቦችን የያዙ በርካታ ትንቢቶች እንዳሉ ተረዳሁ። እንዲሁም የመጽሐፍ ቅዱስን መመሪያዎች ተግባራዊ ማድረግ የሚያስገኘውን ጥቅም በገዛ ሕይወቴ ተመለከትኩ። ‘በሺዎች ከሚቆጠሩ ዓመታት በፊት የኖሩ የመጽሐፍ ቅዱስ ጸሐፊዎች በዛሬው ጊዜም እንኳ ተግባራዊ ሊሆኑ የሚችሉ ጥበብ ያዘሉ ሐሳቦችን ሊያሰፍሩ የቻሉት እንዴት ነው?’ ብዬ አሰብኩ። ቀስ በቀስ መጽሐፍ ቅዱስ የአምላክ ቃል እንደሆነ እየተገነዘብኩ ሄድኩ።

በፈጣሪ መኖር ላይ ያለዎትን እምነት የሚያጠናክሩ ምን ተጨማሪ ማስረጃዎች አግኝተዋል?

በተፈጥሮ ላይ የሚታዩትን የተለያዩ ነገሮች ሳስብ ‘ፈጣሪ አለ’ የሚል መደምደሚያ ላይ ለመድረስ እገደዳለሁ። በአሁኑ ወቅት የኮምፒውተር ሶፍትዌሮችን ንድፍ ከማውጣት ጋር የተያያዘ ሥራ በመሥራት ላይ እገኛለሁ፤ አንጎላችን ከኮምፒውተር ፕሮግራሞች ምን ያህል የላቀ ችሎታ እንዳለው ስመለከት በጣም እደመማለሁ። ለምሳሌ ያህል፣ አንጎላችን ያለው የሰዎችን ንግግር የመለየት ችሎታ በጣም አስደናቂ ነው። የሰዎች ንግግር ያላለቀ ዓረፍተ ነገር ያለበት ቢሆን፣ ሳቅ ወይም ሳል ቢቀላቀልበት፣ መንተባተብም ሆነ ለየት ያለ ቅላጼ ቢኖረው፣ ከጀርባው የሚረብሽ ድምፅ ቢኖር ሌላው ቀርቶ ሰዎቹ እያናገሩን ያሉት በስልክ ቢሆንም እንኳ አብዛኞቻችን ንግግራቸውን ለመረዳት አንቸገርም። ‘ታዲያ ይህ ምን ያስደንቃል?’ ብለህ ታስብ ይሆናል። የሶፍትዌር ንድፍ አውጪዎች ግን ይህ ምን ያህል ከባድ እንደሆነ ይገባቸዋል። እስከዛሬ ድረስ ከተሠሩት ንግግር መለየት የሚችሉ ሶፍትዌሮች መካከል በጣም ምርጥ የሚባለው እንኳ ከሰው አንጎል ጋር ሲወዳደር እዚህ ግባ የሚባል አይደለም።

በጣም ውስብስብ ከሚባሉት ኮምፒውተሮች በተለየ መልኩ አንጎላችን የሰዎችን ስሜት መረዳት፣ የንግግር ቅላጼዎችን መለየት እንዲሁም ከድምፃቸው በመነሳት የሰዎችን ማንነት ማወቅ ይችላል። የሶፍትዌር ንድፍ አውጪዎች፣ የሰው አንጎል ያለውን ንግግር የመለየት ችሎታ መኮረጅ የሚችሉ ኮምፒውተሮችን ለመሥራት ምርምር እያደረጉ ነው። እነዚህ ሰዎች ይህን ጥናት ሲያደርጉ የአምላክን የእጅ ሥራ እያጠኑ እንደሆነ ግልጽ ነው።