አገሮችና ሕዝቦች
ኒው ዚላንድን እንጎብኝ
የማኦሪ ጎሳዎች በሺዎች የሚቆጠሩ ኪሎ ሜትሮችን በውቅያኖስ ላይ ተጉዘው በኒው ዚላንድ የሰፈሩት ከ800 ዓመታት ገደማ በፊት ሳይሆን አይቀርም። እዚያ ሲደርሱ ያገኙት መልክዓ ምድር፣ ትተዋቸው ከመጧቸው ሞቃታማ የአየር ጠባይ ያላቸው የፖሊኔዥያ ደሴቶች ፈጽሞ የተለየ ነበር። ይህ ምድር ግግር በረዶ ያለባቸው አካባቢዎችና ተራሮች የሞሉበት እንዲሁም ፍል ውኃ የሚፈልቅባቸው ምንጮች በብዛት የሚገኙበት ነበር። ከ500 ዓመታት ገደማ በኋላ ደግሞ ሌላ ዝርያ ያላቸው ሰዎች ርቆ ከሚገኘው ከአውሮፓ መጥተው በዚህ አካባቢ ሰፈሩ። በዛሬው ጊዜ አብዛኞቹ ኒው ዚላንዳውያን ከአንግሎ ሳክሰንና ከፖሊኔዥያ የተወረሱ ባሕሎችንና ወጎችን ይከተላሉ። ዘጠና በመቶ ገደማ የሚሆኑት ኒው ዚላንዳውያን የከተማ ነዋሪዎች ናቸው። የዌሊንግተን ከተማ በዓለማችን ደቡባዊ ጫፍ ላይ የምትገኝ ዋና ከተማ በመሆን ትታወቃለች።
ኒው ዚላንድ በአንጻራዊ ሁኔታ ርቃ የምትገኝ አገር ብትሆንም ካላት የተለያየ መልክዓ ምድራዊ አቀማመጥና ውብ ተፈጥሯዊ ገጽታ አንጻር በየዓመቱ ሦስት ሚሊዮን በሚያክሉ ቱሪስቶች የምትጎበኝ መሆኗ አያስገርምም።
ኒው ዚላንድ እንግዳ የሆኑ የዱር እንስሳት የሚገኙባት አገር ስትሆን መብረር በማይችሉ አእዋፍ ዝርያዎች ብዛት ረገድ የትኛውም የዓለም ክፍል አይወዳደራትም። ቱዋታራ በመባል የሚታወቀው እንሽላሊት መሰል እንስሳም የሚገኘው በኒው ዚላንድ ነው፤ ይህ በደረቱ የሚሳብ ፍጡር እስከ መቶ ዓመት ድረስ ሊኖር ይችላል! በአገሪቱ ውስጥ ካሉት አጥቢ እንስሳት መካከል በሌላ በየትኛውም አገር የማይገኙት፣ የተወሰኑ የሌሊት ወፍ ዝርያዎችና እንደ ዓሣ ነባሪዎችና ዶልፊኖች ያሉ አንዳንድ ትላልቅ የባሕር አጥቢዎች ብቻ ናቸው።
የይሖዋ ምሥክሮች ላለፉት 120 የሚጠጉ ዓመታት በኒው ዚላንድ ሲሰብኩ ቆይተዋል። መጽሐፍ ቅዱስን ቢያንስ በ19 ቋንቋዎች ያስተምራሉ፤ ከእነዚህ መካከል እንደ ኒዩየን፣ ራሮቶንግኛ፣ ሳሞአንና ቶንጋኛ ያሉ የፖሊኔዥያ ቋንቋዎች ይገኙበታል።