በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ፍቱን መድኃኒት

ፍቱን መድኃኒት

በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ሰዎች ቀደም ባሉት ርዕሶች ላይ የተጠቀሱትን ምክሮች ተግባራዊ ማድረጋቸው ጭፍን ጥላቻን በማስወገድ ረገድ ትልቅ ስኬት እንዲያገኙ ረድቷቸዋል። እንደ እውነቱ ከሆነ ግን በራሳችን ጥረት ጭፍን ጥላቻን ሙሉ በሙሉ ማስወገድ አንችልም። ታዲያ ጭፍን ጥላቻ ሊወገድ አይችልም ማለት ነው?

መፍትሔ የሚያመጣ መንግሥት

ሰብዓዊ መንግሥታት ጭፍን ጥላቻን በማስወገድ ረገድ እንዳልተሳካላቸው ታይቷል። ይህ ሲባል ታዲያ ጭፍን ጥላቻን ሊያስወግድ የሚችል መንግሥት የለም ማለት ነው?

አንድ መንግሥት ጭፍን ጥላቻን እንዲያስወግድ ከተፈለገ

  1. 1. ሰዎች ለሌሎች ያላቸውን አመለካከትና ስሜት እንዲለውጡ ሊያደርግ ይገባል።

  2. 2. ሰዎች ጭፍን ጥላቻ እንዲያድርባቸው የሚያደርገውን ስሜታዊ ቁስል ሊፈውስ ይገባል።

  3. 3. እያንዳንዱን ዜጋ በእኩል ዓይን የሚመለከቱ ጥሩ ገዢዎች ሊኖሩት ይገባል።

  4. 4. ሁሉንም ዓይነት ሰዎች አንድ ሊያደርግ ይገባል።

መጽሐፍ ቅዱስ አምላክ እንዲህ ዓይነት መንግሥት እንዳቋቋመ ይናገራል። ይህ መንግሥት ‘የአምላክ መንግሥት’ በመባል ይታወቃል።—ሉቃስ 4:43

የአምላክ መንግሥት ምን ነገሮችን እንደሚያስገኝ እንመልከት።

1. የላቀ ትምህርት

“የምድሪቱ ነዋሪዎች ስለ ጽድቅ ይማራሉ።”—ኢሳይያስ 26:9

“የእውነተኛ ጽድቅ ውጤት ሰላም፣ የእውነተኛ ጽድቅ ፍሬም ዘላቂ ጸጥታና ደህንነት ይሆናል።”—ኢሳይያስ 32:17

ይህ ምን ማለት ነው? የአምላክ መንግሥት ትክክል የሆነው ነገር ምን እንደሆነ ለሰዎች ያስተምራል። ሰዎች ትክክልና ስህተት ማለትም ፍትሐዊ ስለሆነውና ስላልሆነው ነገር ሲማሩ አንዳቸው ለሌላው ያላቸው አመለካከት ይለወጣል። እያንዳንዱ ሰው ሁሉንም ዓይነት ሰው መውደድ እንዳለበት ይገነዘባል።

2. ፈውስ

አምላክ “እንባን ሁሉ ከዓይናቸው ያብሳል፤ ከእንግዲህ ወዲህ ሞት አይኖርም፤ ሐዘንም ሆነ ጩኸት እንዲሁም ሥቃይ ከእንግዲህ ወዲህ አይኖርም። ቀድሞ የነበሩት ነገሮች አልፈዋል።”—ራእይ 21:4

ይህ ምን ማለት ነው? የአምላክ መንግሥት የፍትሕ መዛባት ያስከተለውን ሥቃይ በሙሉ ያስወግዳል። ቀደም ሲል ኢፍትሐዊ ድርጊት የተፈጸመባቸው ሰዎች ጥላቻ እንዲያድርባቸው የሚያደርግ ምንም ምክንያት አይኖርም።

3. መልካም አስተዳደር

“ዓይኑ እንዳየ አይፈርድም ወይም ጆሮው በሰማው ነገር ላይ ብቻ ተመሥርቶ አይወቅስም። ለችግረኞች በትክክል ይፈርዳል፤ በምድር ላሉ የዋሆች ጥቅም ሲል ሌሎችን ፍትሐዊ በሆነ መንገድ ይወቅሳል።”—ኢሳይያስ 11:3, 4

ይህ ምን ማለት ነው? በሰማይ ያለው የአምላክ መንግሥት ንጉሥ የሆነው ኢየሱስ ክርስቶስ ምድርን ፍትሐዊና ከአድልዎ ነፃ በሆነ መንገድ ያስተዳድራል። ኢየሱስ አንዱን ብሔር ከሌላው የማያስበልጥ ከመሆኑም ሌላ በዓለም ዙሪያ ያሉ ሰዎች በሙሉ የእሱን የጽድቅ መሥፈርቶች እንዲታዘዙ ማድረግ ይችላል።

4. አንድነት

የአምላክ መንግሥት፣ ሰዎች ‘ፍጹም አንድነት ኖሯቸውና አንድ ዓይነት አስተሳሰብ ይዘው በአንድ ሐሳብና በአንድ ፍቅር መኖር’ የሚችሉበትን መንገድ ያስተምራል።—ፊልጵስዩስ 2:2

ይህ ምን ማለት ነው? በአምላክ መንግሥት ዜጎች መካከል የሚኖረው አንድነት እንዲሁ ከላይ ከላይ የሚታይ ብቻ አይሆንም። አንዳቸው ሌላውን ከልብ ስለሚወዱ “ፍጹም አንድነት” ይኖራቸዋል።