በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ንድፍ አውጪ አለው?

ከትልፊሽ—የባሕር ውስጥ እስስት

ከትልፊሽ—የባሕር ውስጥ እስስት

ከትልፊሽ የተባለው የዓሣ ዝርያ ቀለሙን መቀያየርና ከአከባቢው ጋር በመመሳሰል ከእይታ መሰወር ይችላል። አንድ ጥናት እንዳመለከተው ከሆነ ከትልፊሽ የተባሉት የባሕር ውስጥ ፍጥረታት “እጅግ ብዙ ዓይነት ቅርጽ ያላቸው ከመሆኑም ሌላ በቅጽበት ከአንዱ ቅርጽ ወደ ሌላው መቀየር ይችላሉ።” ይህን የሚያደርጉት እንዴት ነው?

እስቲ የሚከተለውን አስብ፦ ከትልፊሽ ቀለሙን እንዲቀይር የሚያስችለው ከቆዳው ሥር የሚገኝ ክሮማቶፎር የሚባል ልዩ የሆነ ሴል ነው። ክሮማቶፎር የተባሉት ሴሎች ቀለም የተሞሉ ከረጢት መሰል ነገሮችን የያዙ ሲሆን ቀጫጭን በሆኑ ጡንቻዎች ተከበዋል። ከትልፊሽ ራሱን መደበቅ ሲፈልግ አንጎሉ በከረጢቶቹ ዙሪያ ያሉት ጡንቻዎች እንዲኮማተሩ ትእዛዝ ያስተላልፋል። በዚህ ጊዜ ከረጢቶቹም ሆኑ በውስጣቸው የያዙት ቀለም ስለሚለጠጥ ይህ ፍጥረት ቀለሙንና ቅርጹን በቅጽበት ይቀይራል። ከትልፊሽ ይህን ችሎታውን የሚጠቀምበት ራሱን ለመደበቅ ብቻ ሳይሆን ተጓዳኙን ለመማረክና ለመግባባት ጭምር ነው።

በእንግሊዝ ብሪስትል ዩኒቨርሲቲ ውስጥ የሚገኙ መሐንዲሶች ሰው ሠራሽ የከትልፊሽ ቆዳ መሥራት ችለዋል። እንደ ከትልፊሽ ጡንቻ በሚሠሩ ትናንሽ መሣሪያዎች መካከል ከጥቁር ጎማ የተሠሩ ዲስኮችን ከተቱ። ተማራማሪዎቹ ቆዳው ላይ የኤሌክትሪክ ንዝረት በሚለቁበት ጊዜ መሣሪያዎቹ ተለጥጠው ጠፍጣፋ ሆኑ፤ በዚህ ጊዜ ዲስኮቹ የተለጠጡ ከመሆኑም በላይ የሰው ሠራሽ ቆዳው ቀለም ይበልጥ እየደመቀና እየተቀየረ ሄደ።

መሐንዲስ የሆኑት ጆናታን ሮሲተር “ተፈጥሮ ያስገኘቻቸው ስስ የአካል ክፍሎች” በማለት በጠሯቸው የከትልፊሽ ጡንቻዎች ላይ የሚደረገው ምርምር ቀለማቸውን በቅጽበት ሊቀያይሩ የሚችሉ ልብሶችን ለመሥራት ያስችላል። በተጨማሪም ሮሲተር፣ ሰዎች ከትልፊሽን በመኮረጅ የሚሠሯቸውን ልብሶች ከእይታ ለመሰወር ወይም እንዲሁ ለመዘነጥ ሊጠቀሙባቸው እንደሚችሉ ገልጸዋል።

ታዲያ ምን ይመስልሃል? ከትልፊሽ ያለው ቀለምን የመቀያየር ችሎታ በዝግመተ ለውጥ የተገኘ ነው? ወይስ ንድፍ አውጪ አለው?