በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የዱር እንስሳት ቋንቋ—የእንስሳት ቋንቋ ምሥጢሮች

የዱር እንስሳት ቋንቋ—የእንስሳት ቋንቋ ምሥጢሮች

የዱር እንስሳት ቋንቋ—የእንስሳት ቋንቋ ምሥጢሮች

ኬንያ የሚገኘው የንቁ! ዘጋቢ እንደጻፈው

ለሰው ልጅ ከተሰጡት ውድ ስጦታዎች አንዱ ሐሳብ ለሐሳብ የመለዋወጥ ችሎታ እንደሆነ አያጠራጥርም። በዚህ ችሎታችን ተጠቅመን በቃል፣ አለበለዚያም በአካላዊ መግለጫዎች መረጃዎችን ለሌሎች እናቀብላለን። እንዲያውም የመናገር ነጻነት በመላው ዓለም ከፍተኛ ተጋድሎ የተካሄደበት ጥያቄ ነው። በዚህ ምክንያት አንዳንዶች ሐሳብ ለሐሳብ የመገላለጥ ችሎታ ለሰው ልጅ ብቻ የተወሰነ ችሎታ ነው ብለዋል።

ይሁን እንጂ እንስሳትም ብዙውን ጊዜ የሰው ልጆች ሊረዱ ባልቻሏቸው የተራቀቁ ዘዴዎች የመረጃ ልውውጥ ያደርጋሉ። አዎን፣ በቃላት ባይሆንም እንኳን ጭራን እንደማወዛወዝ፣ ጆሮን እንደመነቅነቅና ክንፍ እንደማርገብገብ ባሉ የምልክት ቋንቋዎች “ይናገራሉ።” ሌሎች የሐሳብ መለዋወጫ ዘዴዎች እንደ ጩኸት፣ ማግሳት፣ መቆጣት ወይም እንደ ወፎች ዝማሬ ድምጽ ማሰማትን የሚጠይቁ ናቸው። አንዳንዶቹ “ቋንቋዎች” ለሰው ልጆች ግልፅ ሲሆኑ ሌሎቹ ግን መርምሮ ለመረዳት ብዙ ሳይንሳዊ ጥናት የሚጠይቁ ናቸው።

አዳኝ አራዊት!

የሐምሌ ወር አጋማሽ ነው። ታንዛንያ በሚገኘው ወጣ ገባ የበዛበት ሴሬንጌቲ ፓርክ በብዙ ሺህ የሚቆጠር የወንደቢ (wildebeest) መንጋ በስተ ሰሜን በኬንያ ውስጥ ወደሚገኘው ወደ ማሳይ የዱር አራዊት ጥብቅ ክልል ለምለም ግጦሽ ፍለጋ ሲጎርፍ ይታያል። በዚህ ዓመታዊ ፍልሰት ወቅት ሜዳው የወንደቢዎቹን የኮቴ ድምፅ ያስተጋባል። ይሁን እንጂ በመንገዳቸው ላይ የሚገጥማቸው ብዙ አደጋ አለ። መንገዱ እንደ አንበሳ፣ አቦሸማኔ፣ ጅብና ነብር ባሉ አዳኝ አራዊት የታጠረ ነው። ከዚህም በላይ ወንደቢዎቹ ሕይወታቸውን አደጋ ላይ ጥለው አዞዎች የሚርመሰመሱበትን የማራ ወንዝ ይሻገራሉ። ታዲያ ወንደቢዎች ራሳቸውን ከአዳኞቹ አራዊት የሚከላከሉት እንዴት ነው?

ወንደቢ ጠላቱን ግራ ለማጋባት ሲል ለአጭር ርቀት ወደፊት ሮጥ ካለ በኋላ መለስ በማለት ከጠላቱ ፊት ለፊት ይቆማል። በዚህ ጊዜ ሁሉ ራሱን ከግራ ወደ ቀኝ ያወዛውዛል። እንጣጥ፣ እንጣጥ እያለም እግሮቹን ወደ ላይ በመወርወር አስቂኝ ዓይነት እንቅስቃሴ ያሳያል። እንዲህ ያለውን እንግዳ እንቅስቃሴ የተመለከተ አዳኝ አውሬ ምን ያህል የቆረጠ ቢሆን በአድናቆት ቆም ማለቱ የማይቀር ነው። አሁንም አዳኙ ለመያዝ ጠጋ ካለ ይህንኑ ትርዒት ይደግማል። አዳኙ በዚህ እንቅስቃሴ ግራ ስለሚጋባ አደኑን ትቶ ለመሄድ ይገደዳል። ይህን በመሰለው ገልጃጃ ዳንስ ምክንያት ወንደቢ የሜዳው ቀልደኛ የሚል ቅጽል ስም አትርፏል።

የወንደቢ የቅርብ ዘመድ የሆኑት ቆርኬዎችም በከፍተኛ ዝላያቸው የታወቁ ናቸው። ይህ ዝላይ ለብዙዎች ቅልጥፍናንና ግርማን ከማመልከት ሌላ ምንም ትርጉም የሚኖረው አይመስልም። ይሁን እንጂ ቆርኬዎች ችግር ላይ በሚወድቁበት ጊዜ በዚህ የከፍታ ዝላይ አማካኝነት እግራቸውን አጥምዶ ሊይዛቸው ከፈለገ አዳኝ ያመልጣሉ። እስከ 9 ሜትር የሚደርስ ርዝመት ያለው ይህ ዝላይ ለማንኛውም አዳኝ አውሬ “ልትደርስብኝ ከቻልክ ተከተለኝ” የሚል ግልጽ መልእክት ያስተላልፋል። አንድን ቆርኬ ለመጣል ሲሉ ብቻ እንዲህ ካለው ልፋት ውስጥ ሊገቡ የሚፈልጉ አዳኞች በጣም ጥቂቶች ናቸው።

የምግብ ጊዜ

በዱር ውስጥ ብዙ አዳኝ አራዊት ጥሩ አዳኞች ለመሆን ከፈለጉ የማደን ችሎታቸውን ማራቀቅ ይኖርባቸዋል። ወጣት አራዊት ወላጆቻቸው የሚሰጧቸውን ማሠልጠኛ በትኩረት መከታተል ይኖርባቸዋል። በአንድ የአፍሪካ የዱር አራዊት መጠበቂያ ሳባ የተባለች አንዲት አቦሸማኔ ለቡችሎቿ አስፈላጊ የሆኑ ሥልጠና ስትሰጥ ታይቷል። ሣር ትግጥ የነበረችን አንዲት ድኩላ ለመያዝ ከአንድ ሰዓት በላይ ካደፈጠች በኋላ ዘልላ አነቀቻት። ሆኖም አልገደለቻትም። ከጊዜ በኋላ ሳባ በድንጋጤ የፈዘዘችውን ድኩላ በቡችሎቿ ፊት ጣለቻት። ቡችሎቿ ዘልለው ከማነቅ ይልቅ ወደኋላ አፈገፈጉ። እነዚህ ወጣት አቦሸማኔዎች እናታቸው በሕይወት ያለች እንስሳ ለምን ወደ እነርሱ እንዳመጣች ገብቷቸዋል። ድኩላ እንዴት መግደል እንደሚችሉ ልታስተምራቸው ፈልጋለች። ድኩላዋ ተነስታ ልትሮጥ በሞከረች ቁጥር አፍጥጠው የሚጠባበቁት ቡችሎች እየዘለሉ ይጥሉአታል። ድኩላዋ ተዳክማ ሕይወቷን ለማዳን የምታደርገውን ጥረት ታቆማለች። ከሩቅ ቆማ የምትመለከተው ሳባ በቡችሎቿ ድርጊት ደስ ትሰኛለች።

አንዳንድ አራዊት ምግባቸውን በሚፈልጉበት ጊዜ በጣም ከፍተኛ ጩኸት የማሰማት ልዩ ባሕርይ አላቸው። የጅቦች መንጋ የሚታደን አውሬ በሚያሳድዱበት ጊዜ ይጮሃሉ፣ ያጉረመርማሉ፣ ያሽካካሉ። የሚታደነው አውሬ ከተገደለ በኋላ ጅቦቹ “እያሽካኩ” ሌሎች ጅቦችን ይጋብዛሉ። ይሁን እንጂ ጅቦች ሁልጊዜ አድነው አይበሉም። ባገኙት ዘዴ ሁሉ ተጠቅመው አዳኝ አራዊትን ካስደነገጡ በኋላ አድነው የያዙትን ምግብ ስለሚነጥቁ በቀማኛነት የታወቁ ናቸው። አንበሶችን እንኳን ሳይቀር የማስደንበር ችሎታ እንዳላቸው ታውቋል! ይህን የሚያደርጉት እንዴት ነው? ሁከተኛ አራዊት በመሆናቸው ያደኑትን መብላት በጀመሩት አንበሶች ላይ ሽብር ይለቃሉ። አንበሶቹ ጩኸታቸውን ችላ ብለው መብላታቸውን ከቀጠሉ ከበፊቱ ይበልጥ ጩኸታቸውን ያቀልጡታል። በሁከት ሰላማቸውን ያጡት አንበሶች የጣሉትን ግዳይ ትተው አካባቢውን ለቅቀው ይሄዳሉ።

የንቦች ምግብ ፍለጋ በጣም የተወሳሰበ ሥርዓት የሚከናወንበት ነው። በጣም በተራቀቁ ሳይንሳዊ ጥናቶች እንደተረጋገጠው ንቦች በሚያደርጉት የዳንስ እንቅስቃሴ በቀፎው ውስጥ ላሉ ሌሎች ንቦች የተገኘውን ምግብ ዓይነት፣ ቦታና የምግቡን ጥራት ሳይቀር ያሳውቃሉ። አንዲት ንብ ያገኘችውን ምግብ የአበባ ማርም ይሁን የአበባ ዱቄት ናሙና በሰውነቷ ይዛ በቀፎው ውስጥ ላሉ ሌሎች ንቦች ታሳያለች። በምታደርገው የስምንት ቁጥር ቅርጽ ያለው ዳንስ ምግቡ የሚገኝበትን ቦታ ብቻ ሳይሆን በምን ያህል ርቀት ላይ እንደሚገኝ ጭምር ትጠቁማለች። ጠንቀቅ በል! ከላይህ የምታንዣብበው ንብ ወደ ቤትዋ ይዛ የምትሄደው በጣም አስፈላጊ የሆነ መረጃ በማጠናከር ላይ ልትሆን ትችላለች። ሽቶ ተቀብተህ እንደሆነ ምግቧን ያገኘች መስሏት ልትታለል ትችላለች!

እንዳይጠፋፉ ማድረግ

ጭር ባለ ሌሊት እንደ አንበሳ ግሣት በጣም አስደናቂ ድምፅ የለም። አንበሳ ይህን ድምፅ የሚያሰማበትን ምክንያት በተመለከተ የተለያዩ ሐሳቦች ተሰንዝረዋል። የወንዱ አንበሳ ግሣት በአካባቢው አንበሳ ስላለ በሕይወትህ ቆርጠህ ግባ የሚል ማስጠንቀቂያ ያስተላልፋል። ይሁን እንጂ አንበሳ ማኅበራዊ ኑሮ የሚወድ እንስሳ በመሆኑ ከመንጋው ሌሎች አባላት እንዳይጠፋፋ ሲልም የግሣት ድምፅ ያሰማል። ይኸኛው ግሣት ግን አብዛኛውን ጊዜ ለስለስ ያለ ነው። በአንድ ምሽት አንድ አንበሳ የጠፋበት ዘመዱ ካለበት ሩቅ ቦታ ሆኖ ድምፅ እስኪያሰማ ድረስ በየ15 ደቂቃ ሲያገሣ ተሰምቷል። ከዚያም በኋላ እስኪገናኙ ድረስ ለተጨማሪ 15 ደቂቃ “ሲጠራሩ” ቆይተዋል። ከዚያም ግሣቱ አቆመ።

እንዲህ ያለው ግንኙነት ዝምድና እንዲጠናከር ከማድረጉ ሌላ ከባድ የአየር ሁኔታ ለውጦችን ለመቋቋም ያስችላሉ። አንዲት ዶሮ የተለያዩ መልእክቶች የሚያስተላልፉ የተለያዩ ድምፆች ታሰማለች። በጣም ተለይቶ የሚታወቀው ግን ምሽት ላይ ጫጩቶቿን ልትታቀፋቸው መምጣትዋን የምታሳውቀበት ድምፅ ነው። ጫጩቶቹም የእናታቸውን ጥሪ ተቀብለው በክንፎችዋ ሥር ይሰባሰቡና የሌሊቱን እንቅልፍ ይጀምራሉ።​—⁠ማቴዎስ 23:​37

ተጓዳኝ ፍለጋ

የወፎች ዝማሬ በድንገት ትኩረትህን ስቦት ያውቃል? የተለያዩ ዜማዎችን በማሰማት ችሎታቸው አልተደነቅህም? ይሁን እንጂ ይህን ሁሉ ዝማሬ የሚያሰሙት አንተን ለማዝናናት ብለው እንዳልሆነ ታውቃለህ? መዝሙሮቻቸው አስፈላጊ የሆኑ መልእክቶችን የሚያስተላልፉባቸው ዘዴዎች ናቸው። ክልላቸውን ለማስከበር ሲሉ ዝማሬ የሚያሰሙበት ጊዜ ቢኖሩም አብዛኛውን ጊዜ ግን የሚዘምሩት ተጓዳኝ ለመሳብ ሲሉ ነው። ዘ ኒው ቡክ ኦቭ ኖውሌጅ እንደሚለው ወንዱና ሴቷ አንዴ ከተገናኙ በኋላ “የመዝሙሩ መጠን እስከ 90 በመቶ ድረስ ይቀንሳል።”

ይሁን እንጂ ተጓዳኝ ለመማረክ ጥሩ መዝሙር ብቻ በቂ የማይሆንበት ጊዜ አለ። አንዳንድ እንስት ወፎች በተባዕቱ ከመሸነፋቸው በፊት “ጥሎሽ” እንዲጣልላቸው ይፈልጋሉ። ስለዚህ ዊቨርበርድ የተባለው ወፍ በጥያቄው ከመ​ግፋቱ በፊት ጎጆ የመሥራት ችሎታውን ማስመስከር ይኖርበታል። ሌሎች ተባዕት የአእዋፍ ዝርያዎች ደግሞ እንስቷን ቃል በቃል በመቀለብ ለቤተሰባቸው መተዳደሪያ የማቅረብ ችሎታቸውን ማስመስከር ይኖርባቸዋል።

እንስሳት ሐሳብ ለሐሳብ የሚግባቡባቸው መንገዶች አካላዊ ፍላጎቶቻቸውን ከማሟላት አልፈው ብዙ ጠብ እንዳይፈጠር በማድረግ በዱር ውስጥ ሰላም እንዲሰፍን ያደርጋሉ። በእንስሳት የሐሳብ ልውውጥ ላይ የሚደረገው ምርምር እየቀጠለ በሄደ መጠን ስለ “ዱር አራዊት ጭውውት” የምናውቀው ብዙ ነገር ይኖረናል። ሙሉ በሙሉ ባንረዳውም እንኳ ለፈጠራቸው አምላክ ለይሖዋ ውዳሴና ክብር የሚያመጣ ይሆናል።

[በገጽ 18 እና 19 ላይ የሚገኝ ሣጥን/ሥዕሎች]

የዝሆኖች “የዝምታ ድምፅ”

በጣም ሞቃት በሆነ ከሰዓት በኋላ፣ በኬንያ በሚገኘው የአምቦሴሊ ብሔራዊ ፓርክ የተንጣለለ ሜዳ ላይ የሠፈረው በጣም ትልቅ የዝሆኖች መንጋ በመኖሪያ አካባቢው ላይ እየደረሰ ያለው ወረራ ያሳሰበው አይመስልም። ይሁን እንጂ አየሩ ከሚያስገመግም ወፍራም ጉርምርምታ እስከ መለከት ድምፅ በሚደርሱ የተለያዩ “የዝሆን ንግግሮች” ተሞልቷል። ዝሆኖቹ ከሚጠራሩባቸው ደምፆች አንዳንዶቹ ለሰው ጆሮ የማይሰሙ ይሁኑ እንጂ በርካታ ኪሎ ሜትሮች ርቆ ለሚገኝ ዝሆን ሊሰማ የሚችል ከፍተኛ ኃይል ያላቸው ናቸው።

የእንስሳትን ባሕርይ የሚያጠኑ ሊቃውንት ዝሆኖች በጣም አስፈላጊ የሆኑ መልእክቶችን በሚያስተላልፉባቸው የረቀቁ ዘዴዎች በጣም ተደንቀዋል። ጆይስ ፑል የአፍሪካ ዝሆኖች እርስ በርሳቸው የሚነጋገሩባቸውን ዘዴዎች ለ20 ዓመታት ያህል አጥንተዋል። እነዚህ በጣም ተፈላጊ በሆነው ጥርሳቸው ምክንያት በሠፊው ሊታወቁ የቻሉት ግዙፍ እንስሳት በጥቂት እንስሳት ላይ ብቻ የሚታይ ስሜት እንደሚታይባቸው ተገንዝበዋል። “አንድ ቤተሰብ የሆኑ ወይም የሚዛመዱ ዝሆኖች በሚገናኙበት ጊዜ የሚያደርጉትን የሰላምታ ልውውጥ ወይም አዲስ የቤተሰብ አባል የሚሆን ሕፃን በሚወለድበት ጊዜ የሚከናወነውን ሥነ ሥርዓት የተመለከተ ሰው . . . ደስታ፣ ተድላ፣ ፍቅር፣ የወዳጅነት ስሜት፣ ፈንጠዝያ፣ ርህራሄና አክብሮት ሊባሉ የሚችሉ ጠንካራ ስሜቶች የሏቸውም ሊል አይችልም” ብለዋል።

ለረዥም ጊዜ ተለያይተው ቆይተው በሚገናኙበት ጊዜ ራሳቸውን ቀና አድርገውና ጆሮቻቸውን ቀልብሰው እያውለበለቡ አንዳቸው ወደ ሌላው በሚሯሯጡበት ጊዜ ከፍተኛ ትርምስ ይፈጠራል። እንዲያውም አንደኛው ዝሆን ኩንቢውን ሌላኛው አፍ ውስጥ የሚጨምርበት ጊዜ ይኖራል። የሰላምታው ልውውጥ ዝሆኖቹ “እንደገና መገናኘት መቻላችን ምንኛ የሚያስደስት ነው!” የሚሉ ያህል ከፍተኛ ደስታ የተሰማቸው መሆኑን ያሳያል! ይህ ዓይነቱ ዝምድናና ትስስር ለሕልውናቸው በጣም አስፈላጊ የሆነውን እርስ በርስ የመደጋገፍ መንፈስ ያድሳል።

በተጨማሪም ዝሆኖች ቀልድ የሚያውቁ ይመስላል። ፑል ዝሆኖች የአፋቸውን የግራና ቀኝ ጠርዝ ወደኋላ ሸሸት በማድረግና ራሳቸውን በመነቅነቅ ደስ መሰኘታቸውን የሚያሳይ የሚመስል እንቅስቃሴ ሲያደርጉ መመልከታቸውን ገልጸዋል። አንድ ጊዜ እንስሳቱን እንዳጫወቷቸውና ለ15 ደቂቃ ያህል ሁሉም እንደቦረቁ ተናግረዋል። ከሁለት ዓመት በኋላ በጨዋታው ተካፍለው ከነበሩት ዝሆኖች አንዳንዶቹ ዳግመኛ ሲመለከቷቸው፣ ጨዋታውን አስታውሰው ሳይሆን አይቀርም፣ “ፈገግ” ብለውላቸዋል። ዝሆኖች እርስ በርሳቸው በመጨዋወት ከመደሰት በተጨማሪ ድምፆችን የመኮረጅ ችሎታም አላቸው። ፑል ባከናወኑት አንድ የጥናት ፕሮጀክት ከተለመደው የዝሆኖች ጥሪ የተለየ ድምፅ ሰምተዋል። ድምፁ በሚመረመርበት ጊዜ ዝሆኖች ባጠገባቸው ያልፍ የነበረን የጭነት መኪና ድምፅ መኮረጃቸው እንደሆነ ሊታወቅ ተችሏል። ይህን ያደርጉ የነበረው ለጨዋታ ሲሉ እንደሆነ ግልጽ ነው! ዝሆኖች ባገኙት አጋጣሚ ሁሉ ለመፈንጠዝና ለመጫወት የሚፈልጉ ይመስላል።

በአንድ የቤተሰብ አባል ላይ ጉዳት በሚደርስበት ጊዜ ዝሆኖች እንዴት እንደሚያዝኑ ብዙ ተብሏል። አንድ ጊዜ ፑል ሞታ በተወለደች ግልገሏ አጠገብ ዞር ሳትል ለሦስት ቀናት የቆየች ዝሆን ተመልክተው ያዩትን እንዲህ በማለት ገልጸዋል። “ፊትዋ በሐዘን የተመታና በትካዜ የተዋጠን ሰው ፊት ይመስላል። ራስዋና ጆሮችዋ ወደታች ተንጠልጥለዋል። የአፉዋ ጠርዞች ወደታች ተዘርግተዋል።”

ዝሆኖችን ለጥርሳቸው ሲሉ የሚገድሉ ሰዎች እናታቸው ስትገደል በተመለከቱ ግልገሎች ላይ ምን ያህል ‘የሥነ ልቦና ቁስል’ እንደሚያደርሱ አያስቡም። እነዚህ ግልገሎች የመጀመሪያዎቹን ጥቂት ቀናት ወላጆቻቸውን ያጡ እንስሳት በሚጠለሉባቸው ቦታዎች ተጠብቀው የደረሰባቸውን “ሐዘን” ለመርሳት ይጣጣራሉ። አንድ ጠባቂ ግልገሎቹ ማለዳ ላይ “ሲጮሁ” መስማቱን ተናግሯል። ከግድያው ከበርካታ ዓመታት በኋላ እንኳን ሐዘኑ ሲያገረሽባቸው ታይቷል። ዝሆኖቹ ለዚህ ሁሉ ሥቃይ የሚዳርጋቸው የሰው ልጅ መሆኑን ማወቅ እንደሚችሉ ፑል ተናግረዋል። ሰውና እንስሳ በሰላም አብረው የሚኖሩበትን ጊዜ በታላቅ ጉጉት እንጠባበቃለን።​—⁠ኢሳይያስ 11:​6-9

[በገጽ 12 እና 13 ላይ የሚገኙ ሥዕሎች]

ኬፕ ጋነትስ ሰላምታ ሲለዋወጡ

[በገጽ 13 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ወንደቢ ጠላቱን ግራ ለማጋባት ቅጥ የሌለው ጭፈራ ሲጨፍር

[በገጽ 13 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

የጅብ “ሳቅ”

[ምንጭ]

© Joe McDonald

[በገጽ 14 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

የንብ ዳንስ