በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

መልክና ቁመናዬን ለማሳመር ቀዶ ሕክምና ማድረግ ይኖርብኛልን?

መልክና ቁመናዬን ለማሳመር ቀዶ ሕክምና ማድረግ ይኖርብኛልን?

የወጣቶች ጥያቄ . . .

መልክና ቁመናዬን ለማሳመር ቀዶ ሕክምና ማድረግ ይኖርብኛልን?

“አፍንጫዬ በቀዶ ሕክምና ከመስተካከሉ በፊት ሰዎች በጣም ያሾፉብኝ ነበር። ይህን ያደረግሁት እንዲስተካከልልኝ ብዬ እንጂ ለየት ያለ አፍንጫ እንዲኖረኝ ፈልጌ አይደለም። በተደረገልኝ ቀዶ ሕክምና ተደስቻለሁ፤ እንደገና ማድረግ ቢያስፈልገኝ እንኳን ዓይኔን ሳላሽ አደርገዋለሁ።”​—እሌኒ *

“ሰዎች ያወጡትን የቁንጅና መሥፈርት የምከተልበት ምን ምክንያት አለ? በቀዶ ሕክምና የተስተካከለ አካል የራሴ እንደሆነ ስለማይሰማኝ አርቴፊሻል የሆንኩ ይመስለኛል።”​—ማቲያስ

“እያንዳንዱ ሰው የራሱን ውሳኔ ማድረግ ይኖርበታል። በሌሎች ውሳኔ ጣልቃ መግባት በጣም ይከብዳል።”​—ማኑኤላ

“ሜካፕ የተቀባች ካልሆነች በስተቀር ከእኔ የምትበልጥ ቆንጆ አትገኝም።” በጀርመን መልካቸው ትንሽ እንከን እንዳለው የሚሰማቸው ሰዎች ይህንን ቀልድ አዘል አባባል ረዘም ላለ ጊዜ ሲጠቀሙበት ቆይተዋል። ዛሬ ዛሬ ግን በአንዳንድ አገሮች ይህ አባባል “ከእኔ የምትበልጥ ቆንጆ ሴት ካለች መልኳን ለማሳመር ቀዶ ሕክምና አድርጋለች ማለት ነው” ቢባል ሳይሻል አይቀርም። በእርግጥም መልክና ቁመናን ለማሳመር ቀዶ ሕክምና ማድረግ የተለመደ እየሆነ መጥቷል።

ኖዬ ሱርከር ሳይቱንግ የተባለው የስዊዝ ጋዜጣ “መልክና ቁመናን ለማሳመር የሚከናወን ቀዶ ሕክምና ሀብታሞች ብቻ የሚያደርጉት ነገር መሆኑ ቀርቷል” ሲል ዘግቧል። አክሎም እንዲህ ብሏል:- “ሁለት ዓይነት አዝማሚያዎች ብቅ ብለዋል:- መልክና ቁመናቸውን በቀዶ ሕክምና ለማሳመር የሚፈልጉ ወንዶች ቁጥር ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ ከመሆኑም በላይ . . . ከምን ጊዜውም ይበልጥ በዕድሜ ለጋ የሆኑ እንስቶች ይህንን ቀዶ ሕክምና እያደረጉ ነው።” በጀርመን ከ14 እስከ 29 ዓመት ባለው የዕድሜ ክልል ውስጥ በሚገኙ ወጣቶች ላይ የተደረገ አንድ ጥናት እንደሚያሳየው 20 በመቶ የሚያህሉት መልክና ቁመናቸውን ለማሳመር የሚያስችል ቀዶ ሕክምና (ኮስሜቲክ ሰርጀሪ ) አድርገዋል ወይም ሊያደርጉ አቅደዋል፤ አሊያም ቢያንስ ቢያንስ አስበውበታል። * ምናልባትም አንዳንድ ጓደኞችሽ፣ አብረውሽ የሚማሩ ልጆች ወይም ዘመዶችሽ እንደዚህ ዓይነት ቀዶ ሕክምና አድርገው ይሆናል። *

አንቺስ? በቀዶ ሕክምና መልክና ቁመናሽን ስለ ማሳመር አስበሽ ታውቂያለሽ? ጆሮሽ ትልቅ እንደሆነ፣ ጡቶችሽ በጣም ትልቅ ወይም በጣም ትንሽ እንደሆኑ፣ ቦርጫም እንደሆንሽ ወይም ዳሌሽ በጣም እንደሰፋ አሊያም ደግሞ አፍንጫሽ አስቀያሚ እንደሆነ ይሰማሻል? ከሆነ እንደዚህ የሚሰማሽ አንቺ ብቻ አይደለሽም። የሁለተኛ ደረጃ ተማሪዎች የሆኑ የተወሰኑ ልጃገረዶች በአንድ የጀርመን ጋዜጣ ላይ በወጣ ርዕስ ሥር እንደሚከተለው ሲሉ ጽፈዋል:- “በእኛ ዕድሜ ከሚገኙት ልጃገረዶች መካከል በሆነ ወቅት ላይ በሰውነቷ ቅር ሳትሰኝ ያለፈች አንድም ልጃገረድ የለችም ማለት ይቻላል።” ማራኪና ተወዳጅ ለመሆን መፈለግ ያለ ነገር ነው። ሆኖም ቀዶ ሕክምና ማድረግ መፍትሔ ይሆናልን?

ቀዶ ሕክምና ማድረግ መፍትሔ ይሆናልን?

እስቲ አንቺ የምታውቂያቸውን አንዳንድ ወጣቶች ለማሰብ ሞክሪ። አብዛኞቹ፣ ምናልባትም አንቺ ቆንጆ ናቸው የምትያቸውም ጭምር በመልካቸው ወይም በቁመናቸው እንደማይደሰቱ ብታውቂ ትገረሚ ይሆን? ሆኖም ብዙዎቹ እንደዚያ ይሰማቸዋል። ታዲያ እነዚህ ሁሉ ሰዎች መልክና ቁመናቸውን ለማሳመር ቀዶ ሕክምና ማድረግ የሚያስፈልጋቸው ይመስልሻል? ወይስ አብዛኞቹ ጥሩ ጎናቸውን በማየት ባላቸው መልክና ቁመና ረክተው ቢኖሩ በቂ ነው ትያለሽ? ይኸው መሠረታዊ መመሪያ ለአንቺም ይሠራ ይሆን?

እሌኒ ከሰጠችው ሐሳብ መመልከት እንደሚቻለው አንዳንድ ጊዜ ከሰዎች ፌዝና ትንኮሳ ለመገላገል ቀዶ ሕክምና ማድረግ እንደ አማራጭ ተደርጎ ሊወሰድ ይችላል። በሌላ በኩል ግን ይህ ለሁሉም ችግሮች መፍትሔ አይሆንም። ለአንድ ሰው አካላዊ ውበት የበለጠ አስተዋጽኦ የሚያደርገው ቀዶ ሕክምና ሳይሆን ጤናማ የአኗኗር ዘይቤ መሆኑ ምንም ጥርጥር የለውም። ከዚህም በላይ ምንም እንኳን አንድ ቀዶ ሐኪም መልክሽን ወይም ቁመናሽን ማስተካከል ቢችልም ስብዕናሽን መቀየር፣ ያለብሽን ጭንቀት ማስወገድ ወይም ደግሞ ለራስሽ ጥሩ ግምት እንዲኖርሽ ማድረግ አይችልም።

አንዳንድ ክሊኒኮችና ዶክተሮች ማድረግ የማይችሉትን ነገር እናደርጋለን እንደሚሉም አትዘንጊ። ደስተኛ እንደሚያደርጉሽ ቃል ይገቡ ይሆናል። ይሁን እንጂ ከአንቺ ደስታ ይበልጥ የሚያሳስባቸው የምትከፍያቸው ገንዘብ ነው። የሚያሳዝነው አንዳንድ ይሉኝታ የሌላቸው ሐኪሞች አንድ ሰው ገንዘብ ለመክፈል እስከተስማማ ድረስ አላስፈላጊ፣ ስኬታማ የመሆን ዕድላቸው በጣም የመነመነ ወይም አደገኛ የሆኑ ቀዶ ሕክምናዎችን ከማድረግ ወደ ኋላ አይሉም።

አርቆ ማሰብም በጣም አስፈላጊ ነው። ለምሳሌ ያህል በ16 ዓመትሽ አስቀያሚ እንደሆነ አድርገሽ የምታስቢውን የሰውነትሽ ክፍል 21 ዓመት ሲሆንሽ በተለየ መንገድ ትመለከችው ይሆናል። የኮስሜቲክ ቀዶ ሕክምና ባለሙያ የሆኑት ዶክተር ኡርስ ቦሽ እንዲህ ብለዋል:- “በአጠቃላይ ሲታይ በአሥራዎቹ ዕድሜ ውስጥ የሚገኙ ወጣቶች መልክና ቁመናቸውን ለማስተካከል ቀዶ ሕክምና ማድረግ የለባቸውም። በዚህ ዕድሜ የአንድ ወጣት የሰውነት ቅርጽና ወጣቱ ስለ ሰውነቱ ያለው ግንዛቤ ይቀየራል።” በተጨማሪም ብዙውን ጊዜ ወጣቶች ከትላልቅ ሰዎች የበለጠ ተከታታይ ቀዶ ሕክምና ማድረግ ይጠይቅባቸዋል። ከዚህም በላይ ሰውነትሽ እያደገ ሲሄድ ቀዶ ሕክምናው የተወው ጠባሳም እየሰፋ ሊሄድ ይችላል።

ኪሳራውን አስዪ

መጽሐፍ ቅዱስ አንድ ከበድ ያለ እርምጃ ከመውሰዳችን በፊት ኪሳራውን እንድናሰላ ይመክረናል። (ሉቃስ 14:28) መልክና ቁመናን ለማሳመር የሚደረግ ቀዶ ሕክምና ከፍተኛ ወጪ የሚጠይቅ በመሆኑ ለብዙ ወጣቶች ጨርሶ ሊታሰብ የሚችል ነገር አይደለም። ከቀዶ ሕክምናው በኋላ ደግሞ ተከታታይ ምርመራዎችንም ሆነ አስፈላጊ በሚሆንበት ጊዜ ተጨማሪ ማስተካከያዎችን ለማድረግ ሌላ ክፍያ ያስፈልግ ይሆናል።

የዚህ ዓይነት ቀዶ ሕክምና ያደረጉ ብዙ ሰዎች ገንዘባቸውን ብቻ ሳይሆን ጤናቸውንም ጭምር አጥተዋል። የአሜሪካ የፕላስቲክ ቀዶ ሕክምና ማኅበር እንደሚለው እንዲህ ዓይነቱ ቀዶ ሕክምና ጊዜያዊ እብጠት፣ የዕድሜ ልክ ጠባሳ፣ የመደንዘዝ ስሜትና ጡት የማጥባት ችሎታ ማጣትን የመሳሰሉ የጤና እክሎች ሊያስከትልና ከፍተኛ መጠን ያለው ደም እንዲፈስስ ሊያደርግ ይችላል። ለምሳሌ ያህል አና በሆዷ አካባቢ ያለውን የስብ መጠን ለመቀነስ ተብሎ በተደረገላት ቀዶ ሕክምና ሕይወቷን ልታጣ ምንም ያህል አልቀራትም ነበር። አና “አሁን ሆዴ ላይ የሚዘገንን ጠባሳና ስርጉድ አለብኝ” ስትል ቅሬታዋን ገልጻለች። አንድ የጀርመን ጋዜጣ በሰውነት ውስጥ ያለውን የስብ መጠን ለመቀነስ ተብሎ ስለሚደረግ ቀዶ ሕክምና ሲናገር “ከባድ ችግሮችና ሞትም ሳይቀር እንዳስከተለ የሚገልጹ ዘገባዎች እየተበራከቱ ነው” ብሏል። አፖቴከን ኡምሻው የተባለው የጤና መጽሔት እንደገለጸው “የትኛውም ዓይነት ቀዶ ሕክምና ቢሆን ምን ጊዜም አደጋ እንዳለው” ማስታወስ ይገባል። እንግዲያው ማንኛውንም ዓይነት ቀዶ ሕክምና ለማድረግ ከመወሰንሽ በፊት (በተለይ በጤና እክል ምክንያት ካልሆነ) ተያይዞ የሚመጣውን ችግር በሚገባ አስቢበት።

ራስሽን እንዲህ እያልሽ ጠይቂ:- ‘እንደዚህ ማድረጌ በሰዎች ላይ ምን ዓይነት ስሜት ሊያሳድር ይችላል? ለውጫዊ መልኬ ከሁሉ የላቀ ቦታ እንደምሰጥ አድርገው ያስቡ ይሆን? ውሳኔዬ በእኩዮቼ ወይም በታናናሽ ወንድሞቼና እህቶቼ ላይ ምን ተጽዕኖ ይኖረዋል?’ *

ቀዶ ሕክምና እንድታደርጊ የገፋፋሽ ምንድን ነው?

ቀዶ ሕክምናውን ለማድረግ የተነሳሳሽበት ዓላማም በሚገባ ሊታሰብበት ይገባል። ምናልባትም እንዲህ ለማድረግ የገፋፋሽን ነገር በግልጽ አልተገነዘብሽው ይሆናል። ለምሳሌ ያህል፣ እንዲህ እያልሽ ራስሽን ልትጠይቂ ትችያለሽ:- ‘ቀዶ ሕክምናውን ማድረግ የፈለግሁት ሰዎች ስለሚያሾፉብኝ ነው? ወይስ ስለ መልክና ቁመናዬ ከሚገባ በላይ ስለምጨነቅ? መልኬን በቀዶ ሕክምና ለማስተካከል የፈለግሁት እኩዮቼ፣ ማራኪ የሆኑ ማስታወቂያዎች ወይም ታዋቂ ተዋንያን ተጽዕኖ ስላሳደሩብኝ ነው? ዛሬ በመገናኛ ብዙኃን የውበት መጨረሻ እንደሆነ ተደርጎ የሚነገርለትን መሥፈርት ለማሟላት እየጣርኩ ይሆን?’

አንዳንዶች አካላዊ ውበት የትዳር ጓደኛ ወይም ጥሩ ሥራ የማግኘት አጋጣሚያቸውን ከፍ እንደሚያደርገው ይሰማቸዋል። ይሁን እንጂ ሐቁን እንነጋገር ከተባለ ያገቡ ሰዎች ሁሉ ቆንጆዎች ናቸው? በሥራው ዓለም ያሉ ሰዎችስ ቢሆኑ? እነዚህን ነገሮች ማግኘትሽ በአካላዊ ውበትሽ ላይ ብቻ የተመካ አይደለም። ደግሞስ ከውስጣዊ ባሕርያትሽ ይልቅ ለአካላዊ ውበትሽ የበለጠ ትኩረት ለሚሰጥ የትዳር ጓደኛ ወይም ቀጣሪ ስትይ ያን ያህል ወጪ ማውጣትና ቀዶ ሕክምና ሊያስከትለው ለሚችለው አደገኛ ሁኔታ ራስሽን ማጋለጥ ተገቢ ይሆናልን?

ቀዶ ሕክምናውን ለማድረግ የተነሳሳሽበትን ዓላማ በጥንቃቄ በምትመረምሪበት ወቅት የሚሰማሽን ነገር ከወላጆችሽ ወይም ከአንዲት የጎለመሰች ወዳጅሽ ጋር ተወያዪበት። አንድ የተወሰነ የሰውነትሽ ክፍል በእርግጥ እንከን እንዳለው ከተሰማሽ ሐቀኝነት የተሞላበት አስተያየታቸውን እንዲሰጡሽ ጠይቂያቸው። ራስሽ በመስተዋት ውስጥ ያየሽው ነገር በፈጠረብሽ ስሜት ብቻ ተገፋፍተሽ ውሳኔ ላይ ለመድረስ አትቸኩዪ። ስለ ራሳችን አካላዊ ጉድለቶች የሚኖረንን አመለካከት በተመለከተ ናና እንዲህ ብለዋል:- “ያለብንን ጉድለት ለየት ባለ መንገድ ስለምንመለከተው ከሌላው ሰው ይበልጥ አክብደን እናየዋለን።” በጀርመን በላንዳው ዩኒቨርሲቲ የሚሠሩ ተመራማሪዎች እንደገለጹት ብዙውን ጊዜ መልክና ቁመናን ለማሳመር የሚደረጉ ቀዶ ሕክምናዎች የሚከናወኑት “አንድ የሰውነት ክፍል የተበላሸ መልክ ስለያዘ ሳይሆን ግለሰቡ የተበላሸ መስሎ ስለሚታየው ነው።”

ውሳኔ ለማድረግ ከመቸኮል ይልቅ ሁኔታዎቹን በሙሉ በጥንቃቄ መርምሪ። በቀዶ ሕክምና የተስተካከለ ማንኛውም የሰውነትሽ ክፍል ተመልሶ እንደነበረ ሊሆን እንደማይችል አድርገሽ አስቢ። የትኛውንም ዓይነት ቀዶ ሕክምና ብታደርጊ ለተወሰነ ጊዜም ቢሆን ውሳኔሽ ያስከተለውን ውጤት ተቀብለሽ መኖርሽ የግድ ነው።

ከሁሉ የላቀው ውበት

ደስታ ማግኘትሽ የተመካው በመልክሽ ላይ አይደለም። መልክና ቁመናሽ ለራስሽ ያለሽን ግምት ከፍ ሊያደርገው ወይም ሊያሳንሰው ቢችልም የበለጠ ሊያሳስብሽ የሚገባው ግን ባሕርይሽና አመለካከትሽ ነው። አና ሕይወቷን ሊያሳጣት የነበረውን ቀዶ ሕክምና ካደረገች በኋላ “ውበት ከውጫዊ ገጽታችን ጋር ምንም ግንኙነት እንደሌለው ተምሬያለሁ” ብላለች።

መጽሐፍ ቅዱስ ምንም እንኳን አካላዊ ውበትን ቢያደንቅም ከመንፈሳዊ ውበት ጋር ሲወዳደር ግን ሁለተኛ ደረጃ የሚሰጠው መሆኑን እንዲህ በማለት ይገልጻል:- “ውበት ሐሰት ነው፣ ደም ግባትም ከንቱ ነው፤ እግዚአብሔርን የምትፈራ ሴት ግን እርስዋ ትመሰገናለች።” (ምሳሌ 31:30፤ 1 ሳሙኤል 16:7) የዚህ ዓይነት አመለካከት ማዳበርሽ በሰውነትሽ ላይ እንከን እንዳለ ቢሰማሽም እንኳን ውስጣዊ ሰላም እንዲኖርሽ ያስችልሻል።

ውሳኔሽ ምንም ይሁን ምን በዛሬው ጊዜ እንከን የለሽ መልክና ፍጹም የሆነ ደስታ ሊገኝ እንደማይችል አትዘንጊ። በዚያም ሆነ በዚህ ሁሉም ሰው ጉድለቶች አሉት። (ሮሜ 3:23) ይህንን መለወጥ አትችይም። መለወጥ የምትችይው መጽሐፍ ቅዱስ “የተሰወረ የልብ ሰው” ብሎ የሚጠራውን ውስጣዊ ማንነትሽን ነው። (1 ጴጥሮስ 3:3, 4) በአምላክ ዓይን ውብ የሆኑ ባሕርያትን በማዳበር ራስሽን ማስዋብ ትችያለሽ። ይህ አደጋም ሆነ የገንዘብ ወጪ የሌለው ከመሆኑም በላይ እንደዚህ በማድረግ ወደር የሌለው በረከት ታጭጃለሽ!

[የግርጌ ማስታወሻዎች]

^ አን.3 አንዳንዶቹ ስሞች ተቀይረዋል።

^ አን.7 ኮስሜቲክ ሰርጀሪ የሚባለው ጤናማ የሆኑ የሰውነት ክፍሎችን የበለጠ ለማሳመር ተብሎ የሚደረግ ሕክምና ነው። ሪኮንስትራክቲቭ ሰርጀሪ ደግሞ በአደጋ ወይም በበሽታ ምክንያት የተበላሹ የሰውነት አካላትን አሊያም አንድ ሰው ሲወለድ ጀምሮ ያለበትን ችግር ለማስተካከል ተብሎ የሚደረግ ቀዶ ሕክምና ነው። ሁለቱም የፕላስቲክ ቀዶ ሕክምና ዘርፎች ናቸው።

^ አን.7 ይህ ርዕስ በሴቶች ላይ ያተኮረ ቢሆንም መሠረታዊ ሥርዓቱ ግን ለወንዶችም ይሠራል።

^ አን.17 በይሖዋ ምሥክሮች በተዘጋጀው ወጣቶች የሚጠይቋቸው ጥያቄዎችና ተግባራዊ መሆን የሚችሉ መልሶች በተባለው መጽሐፍ ላይ የወጣውን “መልክ ምን ያህል አስፈላጊ ነው?” የሚለውን ምዕራፍ ተመልከቺ።

[በገጽ 19 ላይ የሚገኝ የተቀነጨበ ሐሳብ]

“መስተካከል አለበት” የምትይው ነገር በእርግጥ መስተካከል የሚያስፈልገው ነው ወይስ መስተካከል ያለበት ስለ ራስሽ ያለሽ አመለካከት ነው?