ሞት የሰው ልጆች መጨረሻ ነው?
ሞት የሰው ልጆች መጨረሻ ነው?
የኩላሊት ችግር ያለባቸው አንድ የ85 ዓመት አረጋዊ በየካቲት 1987 ዘወትር ይደረግላቸው የነበረውን ኪድኒ ዳያሊሲስ የተባለ ሕክምና ለማቋረጥ ወሰኑ። በሕይወት መቀጠላቸው የተመካው በዚህ ሕክምና ላይ ስለነበር ሕክምናውን ካቋረጡ ከሁለት ሳምንት በኋላ አንድያ ልጃቸው አጠገባቸው እንዳለ በሞት አሸለቡ።
አባትና ልጅ ለመጨረሻ ጊዜ አብረው ያሳለፉት ያ ጊዜ ከዚያ በፊት ተወያይተውበት በነበረው “ከመቃብር ወጥቶ እንደገና መኖር ይቻላል?” በሚለው ርዕስ ላይ ለማሰላሰል አጋጣሚ ሰጥቷቸዋል። አባትየው በጣም የተማሩ ሰው ሲሆኑ ተጠራጣሪም ነበሩ። የዝግመተ ለውጥ ትምህርት በአስተሳሰባቸው ላይ ተጽእኖ ያሳደረባቸው ከመሆኑም በላይ ሃይማኖታዊ ግብዝነት አንገሽግሿቸው ነበር። እኚህ ሰው አምላክ ስለመኖሩ ምንም ማረጋገጫ መስጠት አይቻልም የሚል እምነት ስለነበራቸው ራሳቸውን አግኖስቲክ እንደሆኑ አድርገው ይቆጥሩ ነበር።
ልጁ አባቱን ለማጽናናትና ተስፋቸውን ለማለምለም ሲል ከመቃብር ወጥቶ እንደገና መኖር የሚቻል መሆኑ የተረጋገጠ ሐቅ የሆነበትን ምክንያት አስረዳቸው። አባትየው መሞቻቸው ሲቃረብ ጤንነታቸው ተመልሶና ጉልበታቸው ታድሶ እንደገና መኖር ቢችሉ ደስ እንደሚላቸው ሳይሸሽጉ ተናግረዋል።
ሞት ሲጋረጥብን መጽናኛ ማግኘት
ሁሉም ሰው ባይሆንም እንኳ አብዛኞቹ ሰዎች ጤንነታቸው እስከተመለሰና ጉልበታቸው እስከታደሰ ድረስ ሰላም በሰፈነበት ዓለም ውስጥ እንደገና ቢኖሩ ደስ ይላቸዋል። ሰዎች መጽሐፍ ቅዱስ “አእምሮ የሌላቸው” ወይም “በደመ ነፍስ የሚመሩ ፍጥረታት” ብሎ ከሚጠራቸው እንስሳት ፍጹም የተለዩ ናቸው። (2 ጴጥሮስ 2:12 ኒው ኢንተርናሽናል ቨርሽን) እኛ ሰዎች ሙታኖቻችንን እንቀብራለን። ስለ ወደፊቱ ጊዜ እናስባለን። ማርጀት፣ መታመምም ሆነ መሞት አንፈልግም። ሆኖም እነዚህ ነገሮች በሁሉም ሰው ላይ የሚደርሱ የገሃዱ ዓለም ገጠመኞች ናቸው።
የራሳችንም ሆነ የምንወደው ሰው ሞት ሲቃረብ እናዝናለን። ይሁን እንጂ መጽሐፍ ቅዱስ “ወደ ግብዣ ቤት ከመሄድ፣ ወደ ሐዘን ቤት መሄድ ይሻላል” በማለት ሞትን በድፍረት እንድንጋፈጥ ያበረታታናል። አክሎም “ሕያው የሆነም ይህን ልብ ማለት ይገባዋል” ይላል። (መክብብ 7:2) አንድ ሰው ሟች መሆኑን ልብ ማለት ወይም ስለ ሞት በጥልቅ ማሰብ የሚያስፈልገው ለምንድን ነው?
አንዱ ምክንያት ሰላምና ደኅንነት በሰፈነበት ሁኔታ ሕይወትን የማጣጣም ተፈጥሯዊ ፍላጎት ስላለን ነው። ማንም ሰው ቢሆን መሞት ወይም ከሕልውና ውጭ መሆን አይፈልግም። ሞትን አምኖ መቀበል ፈጽሞ አይቻልም ባይባልም እንኳ በጣም ከባድ ነገር መሆኑ ግልጽ ነው። መጽሐፍ ቅዱስ ይህ የሆነበትን ምክንያት ሲገልጽ ‘አምላክ በሰዎች ልብ ዘላለማዊነትን አኖረ’ በማለት ይናገራል። (መክብብ 3:11) የምንፈልገው መሞት ሳይሆን መኖር ነው። እስቲ አስበው ፈጣሪያችን ለዘላለም እንድንኖር ዓላማ ባይኖረው ኖሮ እንዲህ ያለ ከፍተኛ ፍላጎት ይኖረን ነበር? ደግሞስ ለዘላለም ፍጹም ጤንነትና ደስታ አግኝቶ እንደገና መኖር ይቻላል?
ለማመን የሚያስችል ምክንያት
በአሜሪካ ጡረተኞች ማኅበር የሚታተመው ኤ ኤ አር ፒ ዘ ማጋዚን የተሰኘው መጽሔት ባለፈው ዓመት “ከሞት በኋላ ሕይወት” የሚል ርዕስ ይዞ ወጥቶ ነበር። ዕድሜያቸው ከ50 ዓመት በላይ ከሆኑ በርካታ ሰዎች ጋር የተደረገው ቃለ ምልልስ እንዳመለከተው “ወደ ሦስት አራተኛ የሚጠጉት (73 በመቶ የሚሆኑት) ‘ከሞት በኋላ ሕይወት እንዳለ አምናለሁ’ በሚለው ሐሳብ ይስማማሉ።” በሌላ በኩል ደግሞ አንድ አራተኛ የሚሆኑት “ሞት የሕይወቴ ፍጻሜ እንደሆነ አምናለሁ” በሚለው ሐሳብ እንደሚስማሙ መጽሔቱ ዘግቧል። ይሁን እንጂ ሰዎች ለማመን የሚፈልጉት በእርግጥ ይህንን ነው?
ከላይ በተጠቀሰው መጽሔት ላይ የወጣው ጽሑፍ በኒው ዮርክ የሚኖር ቶም የሚባል የካቶሊክ ሃይማኖት ተከታይ እንዲህ እንዳለ ዘግቦ ነበር:- “ይገርምሃል፣ [የሃይማኖት ሰዎች] ከሞት በኋላ ሕይወት አለ ብለው ይሰብካሉ። እኔ ግን ሰዎች ይህን ጉዳይ በተመለከተ የሚሰብኩት ነገር የተለያየ እንደሆነ ይሰማኛል። ስለዚህ ማመን የምትፈልገውን ነገር አንተ ራስህ መወሰን አለብህ። ሥርዓተ ቅዳሴ ላይ እገኛለሁ። አኗኗሬ ከሞት በኋላ ሕይወት አለ ብዬ የማምን
ያስመስለኝ ይሆናል፤ እኔ ግን እንዲህ ያለ እምነት የለኝም። ከሞት በኋላ ሕይወት ካለም እሰየው ነው።”እንደ ቶምና በዚህ ርዕስ መጀመሪያ ላይ እንደተጠቀሱት ሰውዬ ሁሉ ብዙ ሰዎች ዳግም በሕይወት መኖር ይቻላል የሚለውን ሐሳብ ይጠራጠራሉ። እኚህ ሰው ልጃቸውን ብዙ ጊዜ “የሞትን አይቀሬነት መቀበል የሚከብዳቸው ሰዎች አንድ ሃይማኖት ቢይዙ ይሻላቸዋል” ይሉት ነበር። ሆኖም እሳቸውም ሆኑ ሌሎች ተጠራጣሪዎች ለመቀበል እንደተገደዱት፣ ሰዎች እጅግ ታላቅ ኃይል ያለው ፈጣሪ መኖሩን አምነው መቀበላቸው እንደ ተአምር የሚቆጠሩና ለመረዳት የሚያዳግቱ ነገሮች የሚፈጸሙበትን መንገድ ለመረዳት ቀላል ያደርግላቸዋል።
ለምሳሌ ያህል፣ አንድ ጽንስ በተጸነሰ በሦስተኛው ሳምንት የአንጎል ሴሎች መፈጠር ይጀምራሉ። እነዚህ ሴሎች አስደናቂ በሆነ ፍጥነት ሊባዙ አንዳንድ ጊዜም በደቂቃ እስከ ሩብ ሚሊዮን የሚደርሱ አዳዲስ ሴሎች ሊጨመሩ ይችላሉ! ከዘጠኝ ወራት በኋላ ሕፃኑ አስገራሚ የመማር ችሎታ ያለው አንጎል ኖሮት ይወለዳል። ሞለኪዩላር ባዮሎጂስት የሆኑት ጄምስ ዋትሰን የሰውን አንጎል “በጽንፈ ዓለሙ ውስጥ ካገኘናቸው ነገሮች ሁሉ በውስብስብነቱ ወደር የማይገኝለት” በማለት ጠርተውታል።
ብዙ ሰዎች እንዲህ ስላሉት ተአምራዊ ነገሮች ሲያስቡ በከፍተኛ የአድናቆት ስሜት ይዋጣሉ፤ አንተስ ተመሳሳይ ስሜት ይሰማሃል? እንዲህ ባሉት ነገሮች ላይ ማሰላሰልህ በጥንት ዘመን የኖረ አንድ ሰው ላነሳው “ሰው ከሞተ በኋላ ተመልሶ በሕይወት ይኖራል?” ለሚለው ጥያቄ መልስ እንድታገኝ አስችሎሃል? ይህ ሰው በእርግጠኝነት ስሜት “ትጠራኛለህ፤ እኔም እመልስልሃለሁ፤ የእጅህንም ሥራ ትናፍቃለህ” በማለት ለአምላክ መልስ ሰጥቷል።—ኢዮብ 14:14, 15
በእርግጥም ከሞት በኋላ እንደገና በሕይወት መኖር ይቻላል ብለን እንድናምን የሚያበቁንን ማስረጃዎች መመርመራችን ጠቃሚ ነው።