በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ወላጆቼን ማነጋገር የምችለው እንዴት ነው?

ወላጆቼን ማነጋገር የምችለው እንዴት ነው?

የወጣቶች ጥያቄ

ወላጆቼን ማነጋገር የምችለው እንዴት ነው?

“የተሰማኝን ነገር እንደምንም ብዬ ለወላጆቼ ለመንገር ሞክሬ ነበር፤ ሆኖም ሐሳቤን በደንብ መግለጽ አልቻልኩም። እነሱም ገና ሳልጨርስ አቋረጡኝ። ስሜቴን ለእነሱ ለመናገር የደፈርኩት በስንት ትግል ነበር፤ ግን ሳይሆንልኝ ቀረ!”—ሮሳ *

ትንሽ ልጅ ሳለህ ምክር ለመጠየቅ መጀመሪያ የምትሮጠው ወደ ወላጆችህ ሳይሆን አይቀርም። ትልቅም ይሁን ትንሽ ማንኛውንም ወሬ ትነግራቸው ነበር። ሐሳብህንና ስሜትህን ሳትፈራ ትገልጽላቸው ነበር፤ ደግሞም በሚሰጡት ምክር ትተማመን ነበር።

አሁን ግን ወላጆችህ ስሜትህን ሊረዱልህ እንደማይችሉ ይሰማህ ይሆናል። ኤዲ የተባለች አንዲት ወጣት እንዲህ ብላለች፦ “አንድ ቀን ራት እየበላን ሳለ ማልቀስ ጀመርኩ፤ ከዚያም ስሜቴን አውጥቼ [ለወላጆቼ] ነገርኳቸው። ወላጆቼ ቢያዳምጡኝም ስሜቴን የተረዱልኝ ግን አይመስሉም ነበር።” ታዲያ ኤዲ ምን ተሰማት? “ወደ መኝታ ክፍሌ ሄድኩና እንደገና አለቀስኩ!” ብላለች።

በሌላ በኩል ደግሞ አንዳንድ ጊዜ ስሜትህን አውጥተህ ለወላጆችህ አለመናገሩን ትመርጥ ይሆናል። ክሪስቶፈር የሚባል ልጅ “ከወላጆቼ ጋር ስለ ተለያዩ ጉዳዮች አወራለሁ” ይላል። “ይሁን እንጂ አንዳንድ ጊዜ የማስበውን ነገር ሁሉ አለማወቃቸው ደስ ይለኛል።”

አንዳንድ ነገሮችን ለሌሎች አለመናገርህ ስህተት ነው? ይህን ያደረግኸው ለማታለል ብለህ እስካልሆነ ድረስ ስህተት ላይሆን ይችላል። (ምሳሌ 3:32) ወላጆችህ እንደማይረዱህ ቢሰማህም ወይም ደግሞ ሐሳብህን አውጥተህ መናገር ባትፈልግም እንኳ ከወላጆችህ ጋር መነጋገር እንደሚያስፈልግህና እነሱም ሊሰሙህ እንደሚፈልጉ መረዳት ይኖርብሃል።

ከመናገር ወደኋላ አትበል!

ከወላጆችህ ጋር መነጋገር በአንዳንድ መንገዶች መኪና ከመንዳት ጋር ይመሳሰላል። መንገድ ላይ መሰናክል ቢያጋጥምህ ጉዞህን አታቋርጥም፤ ከዚህ ይልቅ ሌላ መንገድ ፈልገህ ጉዞህን ትቀጥላለህ። እስቲ አንዳንድ ምሳሌዎችን እንመልከት።

መሰናክል #1፦ መነጋገር ፈልገሃል፤ ይሁን እንጂ ወላጆችህ የሚያዳምጡህ አይመስሉም። “ከአባቴ ጋር መነጋገሩ አስቸጋሪ ሆኖብኛል” ትላለች ሊያ የምትባል ወጣት። “አንዳንድ ጊዜ አንድ ነገር ስነግረው ቆይቼ ‘ይቅርታ፣ ምን አልሽኝ?’ ይለኛል።”

ጥያቄ፦ ሊያ መነጋገር የሚያስፈልገው አንድ ችግር አጋጥሟት ቢሆንስ? ቢያንስ ሦስት አማራጮች አሏት።

አማራጭ ሀ

በአባቷ ላይ መጮህ። ሊያ “ለምን አታዳምጠኝም? ቁም ነገር እኮ ነው የምነግርህ!” በማለት አባቷ ላይ ልትጮህበት ትችላለች።

አማራጭ ለ

ከአባቷ ጋር መነጋገሯን ማቆም። ሊያ ስለ ችግሯ ለወላጆቿ ለመናገር ጥረትማድረጓን ልትተወው ትችላለች።

አማራጭ ሐ

ሌላ አመቺ ጊዜ ጠብቃ ጉዳዩን እንደገና ማንሳት። ሊያ ስለ ችግሯ ከአባቷ ጋር ፊት ለፊት ልትነጋገር አሊያም ደብዳቤ ልትጽፍለት ትችላለች።

ሊያ መምረጥ ያለባት የትኛውን አማራጭ ይመስልሃል? ․․․․

እያንዳንዱ አማራጭ ምን ሊያስከትል እንደሚችል ለማወቅ እስቲ አማራጮቹን አንድ በአንድ እንመልከታቸው። የሊያ አባት ትኩረት ሰጥቶ አላዳመጣትም፤ በመሆኑም የተበሳጨችበትን ምክንያት አልተረዳላትም። ስለዚህ ሊያ አማራጭ ሀ ላይ እንደተጠቀሰው በአባቷ ላይ ብትጮኽበት እንዲህ ያደረገችበት ምክንያት ላይገባው ይችላል። ይህ አማራጭ አባቷ፣ ሊያ የምትናገረውን ነገር ለማዳመጥ እንዲነሳሳ ላያደርገው ይችላል፤ ከዚህም በላይ ሊያ ለወላጆቿ አክብሮት እንዳላት የሚያሳይ አይሆንም። (ኤፌሶን 6:2) በመሆኑም ይህ አማራጭ የሚፈለገውን ውጤት አያስገኝም።

አማራጭ ለ ከሁሉ የቀለለው መፍትሔ ሊሆን ቢችልም እንዲህ ያለውን አካሄድ መከተሉ ብልህነት አይደለም። ለምን? ምክንያቱም “ምክር ሲጓደል ዕቅድ ይፋለሳል፤ በብዙ አማካሪዎች ግን ይሳካል።” (ምሳሌ 15:22) ሊያ ችግሯን በተሳካ መንገድ ለመወጣት ከወላጆቿ ጋር መነጋገር ያስፈልጋታል፤ ወላጆቿ እርዳታ እንዲያደርጉላት ደግሞ በሕይወቷ ውስጥ ስላጋጠማት ነገር ማወቅ ይኖርባቸዋል። ከእነሱ ጋር መነጋገሯን ማቆሟ ምንም የሚፈይደው ነገር የለም።

ሊያ አማራጭ ሐ ላይ ያለውን መፍትሔ ብትከተል ግን በመንገዷ ላይ ያጋጠማት መሰናክል ጉዞዋን እንድታቋርጥ አያደርጋትም። በጉዳዩ ላይ ከወላጆቿ ጋር ሌላ ጊዜ ለመወያየት ጥረት ታደርጋለች። ለአባቷ ደብዳቤ በመጻፍ ስሜቷን ለመግለጽ ብትመርጥ ደግሞ ብስጭቷ ወዲያው ቀለል ሊልላት ይችላል። ደብዳቤ መጻፏ አባቷ በሚያዳምጣት ጊዜ ለመናገር የምትፈልገውን ነገር በትክክል ለመግለጽ ሊረዳት ይችላል። አባቷ ደብዳቤውን ሲያነበው ሊያ ልትነግረው የፈለገችውን ነገር ማወቅ ይችላል፤ ይህ ደግሞ የደረሰባትን ችግር በተሻለ ሁኔታ እንዲረዳላት ሊያደርገው ይችላል። ስለዚህ ሊያ አማራጭ ሐ ላይ ያለውን መፍትሔ መከተሏ ለእሷም ሆነ ለአባቷ ጥቅም አለው።

ሊያ ምን ሌሎች አማራጮች ሊኖሯት ይችላሉ? አማራጭ ሊሆን ይችላል ብለህ ያሰብከውን ከዚህ በታች ጻፈው። ከዚያም ያሰብከውን አማራጭ መከተሉ ምን ውጤት ሊያስገኝ እንደሚችል ጻፍ።

․․․․․

መሰናክል #2፦ ወላጆችህ ሊያነጋግሩህ ፈልገዋል፤ አንተ ግን አልፈለግህም። ሣራ የተባለች አንዲት ወጣት፣ በትምህርት ቤት መጥፎ ቀን ካሳለፈች በኋላ ከወላጆቿ ጋ እንደተገናኘች በጥያቄ ሲያፋጥጧት በጣም እንደምትበሳጭ ገልጻለች። “ስለ ትምህርት ቤት እንዲነሳብኝ አልፈልግም፤ ወላጆቼ ግን ገና ሲያገኙኝ ‘ውሎሽ እንዴት ነበር? ያጋጠመሽ ችግር ነበር እንዴ?’ እያሉ መጠየቅ ይጀምራሉ።” የሣራ ወላጆች እንዲህ ዓይነት ጥያቄዎች የሚያቀርቡላት ለእሷ በማሰብ እንደሆነ ጥርጥር የለውም። ያም ሆኖ ሣራ “ሰውነቴ ዝሎና አእምሮዬ ውጥር ብሎ ባለበት ሰዓት ላይ ስለ ትምህርት ቤት ማውራት ከባድ ነው” በማለት በምሬት ትናገራለች።

ጥያቄ፦ ሣራ እንዲህ ባለው ሁኔታ ውስጥ ምን ማድረግ ትችላለች? ቀደም ባለው ምሳሌ ላይ እንደተጠቀሰው ሣራም ቢያንስ ሦስት አማራጮች አሏት።

አማራጭ ሀ

ለመናገር ፈቃደኛ አለመሆን። “አሁን ማውራት አልፈልግም። በቃ ተዉኝ!” ትል ይሆናል።“

አማራጭ ለ

ባትፈልግም መናገር። ሣራ ውጥረት ስለተሰማት ማውራት ባያሰኛትም ወላጆቿ የሚጠይቋትን ጥያቄዎች ደስ ሳይላት መመለስ ትችላለች።

አማራጭ ሐ

“ስለ ትምህርት ቤት” መነጋገሩን ለሌላ ጊዜ ማስተላለፍና በሌላ ርዕስ ላይ ጭውውቱን መቀጠል። ሣራ ስለ ትምህርት ቤት ሌላ ጊዜ አእምሮዋ ሲረጋጋ እንዲወያዩ ሐሳብ ማቅረብ ትችላለች። ከዚያም ከልቧ እንደምታስብላቸው በሚያሳይ መንገድ “እስቲ እናንተ ስለ ውሏችሁ ንገሩኝ። ጥሩ ቀን አሳለፋችሁ?” በማለት ልትጠይቃቸው ትችላለች።

ሣራ መምረጥ ያለባት የትኛውን አማራጭ ይመስልሃል? ․․․․

እስቲ እያንዳንዱ አማራጭ ምን ውጤት እንደሚያስከትል እንመርምር።

ሣራ አማራጭ ሀ ላይ ያለውን መፍትሔ ከመምረጧ በፊትም ቢሆን ውጥረት ስለተሰማት ማውራት አልፈለገችም። ይህን አማራጭ ከመረጠች በኋላም ከውጥረቱ አልተገላገለችም፤ በዚያ ላይ ደግሞ በወላጆቿ ላይ በመጮዃ የጥፋተኝነት ስሜት ይሰማታል።—ምሳሌ 29:11

የሣራ ወላጆች በቁጣ መልስ መስጠቷም ሆነ ከዚያ በኋላ ዝም ማለቷ ሊያሳዝናቸው ይችላል። ሣራ አንድ የደበቀችው ነገር እንዳለ ሊጠረጥሩ ይችላሉ። ስሜቷን አውጥታ እንድትነግራቸው ከበፊቱ ይበልጥ ይወተውቷት ይሆናል፤ ይህ ደግሞ ሣራን የባሰ እንደሚያበሳጫት የታወቀ ነው። በመሆኑም ይህ አማራጭ መፍትሔ አያስገኝም።

አማራጭ ለ ከአማራጭ ሀ የተሻለ እንደሚሆን ግልጽ ነው። ቢያንስ ሣራና ወላጆቿ ይነጋገራሉ። ይሁን እንጂ ጭውውቱ ከልብ ስለማይሆን ሣራም ሆነች ወላጆቿ ውይይታቸው እንደሚፈልጉት አይሆንላቸውም፤ በሌላ አባባል፣ ዘና ባለ መንፈስ የውስጣቸውን አውጥተው አይነጋገሩም።

ሣራ አማራጭ ሐ ላይ ያለውን መፍትሔ ብትከተል ግን “ስለ ትምህርት ቤት” መነጋገሩ ለሌላ ጊዜ ስለተላለፈ ጥሩ ስሜት ሊሰማት ይችላል። ወላጆቿም ቢሆኑ ውይይቱ እንዲቀጥል ጥረት በማድረጓ ደስ ይላቸዋል። ይህ አማራጭ ጥሩ ውጤት የማስገኘት አጋጣሚው ሰፊ ነው፤ ምክንያቱም ሁለቱም ወገኖች በፊልጵስዩስ 2:4 (አ.መ.ት.) ላይ ያለውን “እያንዳንዳችሁ ሌሎችን የሚጠቅመውንም እንጂ፣ ራሳችሁን የሚጠቅመውን ብቻ አትመልከቱ” የሚለውን መሠረታዊ ሥርዓት በሥራ ላይ እያዋሉ ናቸው።

www.watchtower.org/ype በሚለው ድረ ገጽ ላይ “Young People Ask” በሚል አምድ ሥር ተጨማሪ ርዕሶችን ማግኘት ይቻላል።

[የግርጌ ማስታወሻ]

^ አን.3 አንዳንዶቹ ስሞች ተቀይረዋል።

ሊታሰብባቸው የሚገቡ ነጥቦች

▪ ጥሩ ውይይት ለማድረግ አመቺ ጊዜ መምረጥ ምን ያህል አስፈላጊ ነው?—ምሳሌ 25:11

▪ ከወላጆችህ ጋር ለመነጋገር ጥረት ማድረግህ ጠቃሚ ነው የምንለው ለምንድን ነው?—ኢዮብ 12:12

[በገጽ 18 ላይ የሚገኝ ሣጥን/ሥዕል]

በሌላ መንገድ ይረዱሃል?

ከወላጆችህ ጋር ለመነጋገር ተቸግረሃል? ምናልባት የምትናገረውን ነገር በሌላ መንገድ እየተረዱት ይሆናል።

አንተ . . .

“ስለዚህ ጉዳይ መነጋገር አልፈልግም” ስትል

ወላጆችህ . . .

“ለጓደኞቼ ሐሳቤንና ስሜቴን ሳልሸማቀቅ እነግራቸዋለሁ፤ እናንተ ግን በሕይወቴ ውስጥ ያን ያህል ትልቅ ቦታ ስለሌላችሁ ልነግራችሁ አልፈልግም” ያልክ ይመስላቸዋል።

አንተ . . .

“ብነግራችሁ አይገባችሁም” ስትል

ወላጆችህ . . .

“እናንተ አርጅታችኋል፤ የእኛ ዘመን ስለማይገባችሁ የምነግራችሁን ለመረዳት ባትሞክሩ ይሻላችኋል” ያልክ ይመስላቸዋል።

[በገጽ 21 ላይ የሚገኝ ሣጥን/ሥዕሎች]

እኩዮችህ ምን ይላሉ?

“በትምህርት ቤት ስለገጠመኝ አንድ ችግር ለወላጆቼ ነገርኳቸው፤ ምን ያህል ትኩረት ሰጥተው እንዳዳመጡኝ ስመለከት ተገረምኩ። በእነሱ እርዳታ ችግሩን በቀላሉ ማሸነፍ ቻልኩ!”—ናታሊ

“ከወላጆችህ ጋር መነጋገር ሁልጊዜ ቀላል ባይሆንም ስሜትህን አውጥተህ ስታወያያቸው አንድ ከባድ ነገር ከላይህ ላይ የተነሳልህ ያህል ቅልል ይልሃል።”—ዴቨኒ

[በገጽ 21 ላይ የሚገኝ ሣጥን]

ለወላጆች የቀረበ ሐሳብ

የልጆችህ ጉዳይ የሚያሳስብህ ወላጅ እንደመሆንህ መጠን ‘ልጆቼ እኔን ማነጋገር ከባድ ይሆንባቸው ይሆን’ ብለህ ማሰብህ አይቀርም። አንዳንድ ወጣቶች ወላጆቻቸውን ከማነጋገር ወደኋላ የሚሉት ለምን እንደሆነ ለንቁ! መጽሔት የሰጡትን ሐሳብ ተመልከት። ከዚያም በቀረቡት ጥያቄዎች መሠረት ራስህን ፈትሽ፤ እንዲሁም ጥቅሶቹን ከመጽሐፍ ቅዱስ አውጥተህ አንብብ።

አባቴ በሥራ ቦታም ሆነ በጉባኤ ውስጥ ብዙ የሚያከናውናቸው ነገሮች ስላሉት እሱን ማነጋገር አስቸጋሪ ነው። በፍጹም እሱን ማነጋገር የሚቻልበት አመቺ ጊዜ ያለ አይመስልም።—አንድሩ

‘ሳይታወቀኝ ልጆቼ ጊዜ እንደሌለኝ ሆኖ እንዲሰማቸው እያደረግኩ ይሆን? ከሆነ፣ እኔን መቅረብ ቀላል እንዲሆንላቸው ማድረግ የምችለው እንዴት ነው? ከልጆቼ ጋር የማወራበት ቋሚ ጊዜ ለመመደብ ተስማሚ የሆነው ሰዓት የትኛው ነው?’—ዘዳግም 6:7

በትምህርት ቤት ከልጆች ጋር የተጨቃጨቅንበትን ጉዳይ አንስቼ ለእናቴ እያለቀስኩ ነገርኳት። ታጽናናኛለች ብዬ ሳስብ እሷ ግን ተቆጣችኝ። ከዚያን ጊዜ ወዲህ ስለሚያሳስበኝ ነገር ምንም ነግሬያት አላውቅም።—ከንጂ

‘ልጆቼ ችግራቸውን ሲነግሩኝ መልስ የምሰጣቸው እንዴት ነው? እርማት መስጠት አስፈላጊ ቢሆንም እንኳ ምክር ከመስጠቴ በፊት ረጋ ብዬ በርኅራኄ ማዳመጥን መማር ያስፈልገኝ ይሆን?’—ያዕቆብ 1:19

ወላጆች ልጆቻቸው የተሰማቸውን ነገር ቢነግሯቸው እንደማይቆጧቸው ሁልጊዜ የሚናገሩ ቢሆንም መበሳጨታቸው የሚቀር አይመስለኝም። በዚህ ጊዜ ልጆቹ እንደተታለሉ ይሰማቸዋል።”—ሬቸል

‘ልጄ አንድ የሚያናድድ ነገር ቢነግረኝ ቶሎ እንዳልበሳጭ ስሜቴን መቆጣጠር የምችለው እንዴት ነው?’—ምሳሌ 10:19

ብዙ ጊዜ ለእናቴ ሚስጥሬን አውጥቼ ስነግራት ወዲያውኑ ለጓደኞቿ ትነግራቸዋለች። ለረጅም ጊዜ በእሷ ላይ እምነት መጣል አልቻልኩም።—ቻንቴል

‘ልጄ የነገረኝን ሚስጥር ለሌሎች ባለመናገር ለስሜቱ እንደምጠነቀቅ አሳያለሁ?’—ምሳሌ 25:9

ከወላጆቼ ጋር መነጋገር የምፈልገው ብዙ ነገር አለኝ። ይሁንና ጭውውቱን እነሱ ቢጀምሩልኝ ደስ ይለኛል።—ኮርትኒ

‘ከልጄ ጋር ጭውውት ለመጀመር ቅድሚያውን መውሰድ እችላለሁ? ለመነጋገር አመቺ የሚሆነው ጊዜ መቼ ነው?’—መክብብ 3:7

[በገጽ 19 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

መንገድ ላይ መሰናክል ቢያጋጥማችሁ ሌላ መንገድ እንደምትፈልጉ ሁሉ ከወላጆቻችሁ ጋር ለመነጋገር ስትፈልጉ እንቅፋት ቢያጋጥማችሁም ሐሳባችሁን ለመግለጽ የሚያስችላችሁ አማራጭ ማግኘት ትችላላችሁ!