በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

በቀለማት ያሸበረቀው ዓሣ አመቴ

በቀለማት ያሸበረቀው ዓሣ አመቴ

በቀለማት ያሸበረቀው ዓሣ አመቴ

ማያዊ ቀለም ያለው አንድ ወፍ ውኃ ውስጥ ተወርውሮ ከገባ በኋላ በመንቆሩ ዓሣ ይዞ በፍጥነት ይወጣል። ከጠቅላላ አካሉ ጋር ሲወዳደር ትልቅ አናትና ረጅም መንቆር ያለው ይህ ወፍ ዓሣ አመቴ ይባላል፤ ብዙውን ጊዜ ሰዎች ይህንን በቀለማት ያሸበረቀ ወፍ ለመጀመሪያ ጊዜ የሚያዩት ከላይ በተገለጸው መንገድ ዓሣ ሲያድን ነው። እነዚህ ወፎች ዓሣ አመቴ ቢባሉም ዓሣ የሚመገቡት ሁሉም ዝርያዎች አይደሉም። አንዳንዶቹ ዝርያዎች ለመብልነት የሚመርጡት እንሽላሊትን፣ እባብን፣ ሸርጣንንና ሌሎች ነፍሳትን ነው፤ ብዙውን ጊዜ ነፍሳቱን የሚይዟቸው እየበረሩ እያሉ ነው። ከዚህም በላይ በዓለም ላይ ካሉት ዓሣ አመቴዎች መካከል ውኃ አካባቢ የሚኖሩት አንድ ሦስተኛ የሚሆኑት ብቻ ናቸው። እነዚህ አእዋፍ በሞቃታማ ቦታዎች በሚገኙ ጥቅጥቅ ያሉ ደኖች፣ በደሴቶችና በረሃማ በሆኑ አካባቢዎች ይኖራሉ። በበረሃማ አካባቢዎች ከሚገኙት ዓሣ አመቴዎች አንዱ ጀርባ ቀይ ዓሣ አመቴ ሲሆን የሚኖረው ደረቅ በሆነው የአውስትራሊያ ማዕከላዊ ክፍል ነው።

ዓሣ አዳኝ የሆኑት የዚህ ወፍ ዝርያዎች በዚህ ችሎታቸው እጅግ የተካኑ ናቸው። አብዛኛውን ጊዜ ወፉ ከላይ ሆኖ በማንዣበብ የሚያድነው ነገር እስኪያገኝ በትዕግሥት ይጠባበቃል። አንድ ዓሣ በሚያይበት ጊዜ ቁልቁል ለመወርወር ያቆበቁባል። ብርሃን ወደ ውኃ ሲገባ አቅጣጫውን ስለሚቀይር ዓሣው በውኃው ውስጥ የሚገኝበት አቅጣጫ ከላይ ከሚታየው የተለየ ይሆናል፤ ይሁንና ዓሣ አመቴው የዓሣውን ትክክለኛ አቅጣጫ ለመለየት የሚረዳውን በተፈጥሮው ያገኘው ችሎታ በመጠቀም አቅጣጫውን ያስተካክላል። ከዚያም ፍጥነት እንዲያገኝ ክንፎቹን በማርገብገብ ወደ ውኃው ተወርውሮ ይገባል። ዓሣው የሚገኘው በውኃው የላይኛ ክፍል ከሆነ ወፉ ወደ ውስጥ መግባት ሳያስፈልገው ለቀም አድርጎት ይሄዳል። ካልሆነ ግን ክንፎቹን ያጥፍና እንደ ቀስት በመምዘግዘግ ወደ ውኃ ይገባል። የአእዋፍ ሕይወት (እንግሊዝኛ) የተባለው መጽሐፍ ስለዚህ ክንውን ሲገልጽ “አላንዳች ማመንታት ወይም ስህተት የሚከናወን ብሎም እጅግ አስደናቂ ችሎታ የሚንጸባረቅበት ትእይንት ነው” ይላል። ዓሣ አመቴዎች በአንድ ጊዜ ከአንድ ዓሣ በላይ የመያዝ ችሎታ አላቸው! በቀዝቃዛ አካባቢዎች ደግሞ አንዳንድ ዓሣ አመቴዎች ስስ የሆነውን በረዶ ሰንጥቀው በመግባት ዓሣ ሲይዙ ታይተዋል። በአውስትራሊያ የሚገኙት አዙር የሚባሉት የዓሣ አመቴ ዝርያዎች ደግሞ ፕላቲፐስ በመባል የሚታወቁት የባሕር እንስሳት በወንዝ ውስጥ ምግባቸውን ሲፈልጉ በሚፈጥሩት ትርምስ የደነበሩትን ትናንሽ የባሕር እንስሳት ሲያድኑ ታይተዋል።

ተጓዳኝ መፈለግና ቤት መሥራት

ዓሣ አመቴዎች ተጓዳኝ ሲፈልጉ መመልከት በጣም አዝናኝ ሊሆን ይችላል። አንዳንዶቹ ዝርያዎች ተጓዳኛቸውን የሚመርጡት አየር ላይ በመባረር ሲሆን ከዚያ በኋላ ወንዱ ጎጆ የመቆፈር ችሎታ እንዳለው ያሳያል። ተጓዳኝ የመምረጡ ሂደት ምግብ ማቅረብንም የሚጨምር ሊሆን ይችላል፤ በዚህ ወቅት ወንድየው ለሴቷ ግሩም የሆነ ምግብ በማቅረብ ትልቅ ቦታ እንድትሰጠው ለማድረግ ይጥራል።

ዓሣ አመቴዎች የሚሠሩት ጎጆ ከተለመደው ዓይነት የተለየ ነው። አንዳንዶቹ ጠጠር ለማውጣት የተቆፈሩ ጉድጓዶችን ወይም የቦዮችን ግድግዳ አሊያም በወንዝ ዳርቻ አካባቢ መሬቱን ከቦረቦሩ በኋላ በውስጠኛው ክፍል ላይ ቤታቸውን ይሠራሉ። ሌሎቹ ደግሞ ጥንቸሎች በቆፈሩት ጉድጓድ ውስጥ ወይም በዛፍ ግንድ ላይ በሚገኙ ቀዳዳዎች ውስጥ ይኖራሉ።

አንድ ዓሣ አመቴ አፈሩን ቦርቡሮ ቤት ለመሥራት አንድ ሜትር ያህል ርዝመት ያለው ቦይ ሊቆፍር ይችላል። ይሁን እንጂ ቁፋሮውን መጀመሩ አስቸጋሪ ነው። ብዙዎቹ ዝርያዎች ቁፋሮውን የሚጀምሩት መንቆራቸውን ወደፊት ቀስረው በቀጥታ አፈሩ ላይ እንደ ጦር በመሰካት ነው፤ ይህ ዓይነቱ ዘዴ ወፉ ራሱን ስቶ እንዲወድቅ ወይም እንዲሞት ሊያደርገው ስለሚችል አደገኛ ነው! በኒው ጊኒና በሰሜናዊ አውስትራሊያ በሞቃታማ አካባቢዎች በሚገኙት ደኖች ውስጥ የሚኖረው ፓራዳይዝ ዓሣ አመቴ አብዛኛውን ጊዜ የምስጥ ኩይሳዎችን በመቦርቦር ቤቱን ይሠራል። ምስጦቹም ይህ ወረራ የሚረብሻቸው አይመስሉም፤ ወፎቹ ጫጩቶቻቸውን አሳድገው ከሄዱ በኋላ ምስጦቹ በኩይሳቸው ላይ የደረሰውን ጉዳት ይጠግናሉ።

ጫጩቶቻቸውን ማሳደግም ለዓሣ አመቴዎች ከባድ ሥራ ሊሆንባቸው ይችላል። በአፍሪካ ውስጥ ሁለት ዓሣ አመቴዎች ራሳቸውን ከመመገብ በተጨማሪ በየቀኑ ከ60 እስከ 70 የሚያህሉ ዓሣዎችን ለአምስት ጫጩቶቻቸው እየተመላለሱ ሲመግቡ አንድ ሰው ተመልክቷል። በአንድ ወቅት ወንዱ ወፍ ጫጩቶቹ ከመፈልፈላቸው ከአራት ቀናት በፊት ተጓዳኙ ብትሞትበትም ብቻውን ሆኖ ጫጩቶቹን ማሳደግ ችሏል። አንዳንድ የዓሣ አመቴ ዝርያዎች ደግሞ እርስ በርስ ይተጋገዛሉ፤ ጫጩቶች የሌሏቸው ወፎች የሌሎቹን ወፎች እንቁላል በመታቀፍና እንቁላሎቹ ከተፈለፈሉ በኋላም ጫጩቶቹን በማሳደግ ይረዷቸዋል።

ከአየርላንድ እስከ ሰለሞን ደሴቶች

የተለመደው ዓሣ አመቴ በስተ ሰሜን ምዕራብ ከምትገኘው አየርላንድ አንስቶ አውሮፓንና ሩሲያን በማካለል በስተ ደቡብ ምሥራቅ እስከሚገኙት የሰለሞን ደሴቶች ተሰራጭቶ ይገኛል። የመኖሪያ አካባቢው በቅዝቃዜው ወቅት በበረዶ የሚሸፈኑ ቦታዎችን ስለሚጨምር ራቅ ወዳሉ አካባቢዎች ከሚፈልሱት ጥቂት የአእዋፍ ዝርያዎች አንዱ ነው፤ አንዳንዶቹ ዓሣ አመቴዎች እስከ 3,000 ኪሎ ሜትር የሚያክል ርቀት ተጉዘው የቅዝቃዜውን ወራት በሌላ አካባቢ ያሳልፋሉ። የተለመደው ዓሣ አመቴ እንዲሁም ቡሬ ዓሣ አመቴና አንገተ ነጩ ዓሣ አመቴ በእስራኤል ምድር በዮርዳኖስ ወንዝ ዳርቻና በገሊላ ባሕር አካባቢ በብዛት ይታያሉ። ኢየሱስ ክርስቶስ እነዚህን የሚያማምሩ ወፎችና አኗኗራቸውን ሳያስተውል አልቀረም።— “የሰማይን ወፎች ልብ ብላችሁ ተመልከቱ” የሚለውን ሣጥን ማየት ትችላለህ።

በተለይ የአውስትራሊያው ሳቂታ ኩካቡራ ዓሣ አመቴ በስፋት ይታወቃል። ይህ ወፍ ርዝመቱ 43 ሴንቲ ሜትር የሚደርስ ሲሆን 8 ሴንቲ ሜትር ርዝመት ያለው ጠንካራ መንቆር አለው፤ አብዛኛውን ጊዜ ቡናማ ቀለም ያለው ሲሆን በስተ ደቡብ በምትገኘው በዚህች አገር በአትክልቶች አካባቢ አዘውትሮ የሚታይ ወፍ ነው። የማስካካት ዓይነት “ሳቅ” በማሰማት የሚታወቀው ኩካቡራ ዓሣ አመቴ እስከ አንድ ሜትር ርዝመት ያላቸውን እባቦች የሚበላ ደፋር አዳኝ ነው! *

ዓሣ አመቴዎች ብዙ የተፈጥሮ ጠላቶች የሌሏቸው ቢሆንም ወንዞች በሚበከሉበት ወይም ደኖች በሚራቆቱበት ጊዜ ቁጥራቸው በእጅጉ ይቀንሳል። እንዲያውም ወደ 25 የሚጠጉ የዓሣ አመቴ ዝርያዎች የመጥፋት አደጋ ከተጋረጠባቸውና ጨርሶ ሊጠፉ ከተቃረቡ የእንስሳት ዝርያዎች ውስጥ ተመድበዋል። እነዚህን የሚያማምሩና በአብዛኛው አዝናኝ የሆኑ ወፎች ከጥፋት ለመታደግ የሚደረገው ጥረት እንደሚሰምር ተስፋ እናደርጋለን።

[የግርጌ ማስታወሻ]

^ አን.11 በሰሜናዊ አውስትራሊያ የሚገኘው ባለ ሰማያዊ ክንፍ ኩካቡራ “የሳቅ” ዓይነት ድምፅ አያሰማም።

[በገጽ 17 ላይ የሚገኝ ሣጥን/ሥዕል]

 “የሰማይን ወፎች ልብ ብላችሁ ተመልከቱ”

ኢየሱስ ክርስቶስ ተፈጥሮን በትኩረት ይመለከት የነበረ ሲሆን ብዙውን ጊዜ ካስተዋላቸው ነገሮች በመነሳት ሥነ ምግባራዊና መንፈሳዊ እውነቶችን ለማስተማር የሚያስችሉ ጥሩ ምሳሌዎችን ይናገር ነበር። ለአብነት ያህል፣ ኢየሱስ እንዲህ ብሏል፦ “የሰማይን ወፎች ልብ ብላችሁ ተመልከቱ፤ እነሱ አይዘሩም፣ አያጭዱም ወይም በጎተራ አያከማቹም፤ ይሁንና በሰማይ ያለው አባታችሁ ይመግባቸዋል። ታዲያ እናንተ ከእነሱ አትበልጡም?” (ማቴዎስ 6:26) አምላክ ለሰብዓዊ ፍጥረታቱ ያለውን ፍቅር የሚያሳይ እንዴት ያለ ልብ የሚነካ ትምህርት ነው!

[በገጽ 16 ላይ የሚገኝ ሥዕል]