በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የዓለማችን ትንሿ የሌሊት ወፍ

የዓለማችን ትንሿ የሌሊት ወፍ

የዓለማችን ትንሿ የሌሊት ወፍ

ወቅቱ 1973 ሲሆን የታይላንድ ተወላጅ የሆነው ባዮሎጂስቱ ኪቲ ቶንክሎንግያ እና የሥራ ባልደረቦቹ በታይላንድ ሴ ዮክ ፏፏቴ አቅራቢያ በሚገኙት ዋሻዎች ውስጥ ዝርያቸው ተለይቶ ያልታወቀ ከ50 የሚበልጡ የሌሊት ወፎችን ሰበሰቡ። ከዚያም ኪቲ፣ ለናሙና እንዲሆን ጥቂት የሌሊት ወፎችን በለንደን በሚገኘው የብሪታንያ የተፈጥሮ ታሪክ ሙዚየም ውስጥ ወደሚሠሩት ወደ ዶክተር ጆን ሂል ላከ። የሚያሳዝነው ግን ኪቲ አዲስ የሌሊት ወፍ ዝርያ ማግኘቱን ሳያውቅ ሞተ፤ ዶክተር ሂል እነዚህን የሌሊት ወፎች ለኪቲ መታሰቢያ እንዲሆኑ በማለት ክሬሲዮኒክተሪስ ቶንክሎንግያይ ብለው ሰየሟቸው። የዚህች የሌሊት ወፍ የተለመደው መጠሪያዋ ባለ አሳማ አፍንጫዋ የኪቲ የሌሊት ወፍ የሚል ነው።

ባለ አሳማ አፍንጫዋ የኪቲ የሌሊት ወፍ ርዝመቷ 3 ሴንቲ ሜትር ገደማ ሲሆን ክንፎቿ ሙሉ በሙሉ ሲዘረጉ ከጫፍ እስከ ጫፍ ወደ 13 ሴንቲ ሜትር የሚጠጋ ርዝመት አላቸው፤ በመሆኑም እስካሁን ከሚታወቁት የሌሊት ወፍ ዝርያዎች መካከል በጣም ትንሿ ስትሆን እጅግ በጣም አነስተኛ ከሆኑት አጥቢ እንስሳት አንዷ ነች። እንዲያውም በጣም ትንሽ ከመሆኗ የተነሳ ትልቅ በሆነው የንብ ዝርያ ማለትም በባምብልቢ ስም የምትጠራበት ጊዜ አለ። በተጨማሪም ይህች የሌሊት ወፍ ጅራት አልባ ብሎም የአሳማ ዓይነት አፍንጫ (ስሟን ያገኘችው ከዚህ ነው) እንዲሁም ያበጠ የሚመስል ጉጢት (የጆሮ ቀዳዳ ሽፋን) ያላቸው ትልልቅ ጆሮዎች ያሏት መሆኗ ለየት ከሚያደርጓት ሌሎች ነገሮች መካከል አንዳንዶቹ ናቸው።

ብዙ ቦታ የማትገኝ የሌሊት ወፍ

እነዚህ የሌሊት ወፍ ዝርያዎች የሚገኙት ታይላንድ ውስጥ ባለው በሴ ዮክ ብሔራዊ ፓርክና አጎራባች በሆኑት የምያንማር ግዛቶች ብቻ ነው። ባለ አሳማ አፍንጫዋ የኪቲ የሌሊት ወፍ እንደ ሌሎቹ የሌሊት ወፍ ዝርያዎች ሁሉ ነፍሳትን የምታድነው የምታወጣው ድምፅ ነፍሳቱ ላይ ነጥሮ በሚመለስላት የድምፅ ሞገድ በመመራት ነው። ይህች አጥቢ እንስሳ ከሰውነቷ መጠን ጋር ሲነጻጸር ትልቅ ክንፍ ያላት መሆኑ በአየር ላይ ወዲያ ወዲህ ሳትል አንድ ቦታ ላይ ለመንሳፈፍ ይረዳታል፤ ይህ ደግሞ በዛፍ ቅጠሎች ላይ የሚገኙ ነፍሳትን ለቀም ለማድረግ ያስችላታል። ይህች እንስሳ ለማረፍ የምትመርጠው ጣሪያቸው ከፍ ባለና ብዙ ክፍሎች ባሏቸው የኖራ ድንጋይ ዋሻዎች ውስጥ ሲሆን የምትንጠላጠልባቸው የዋሻዎቹ ከፍ ያሉ ስፍራዎች ሞቃታማ ናቸው። የሌሊት ወፎቹ እንዲህ ያሉ ዋሻዎችን መምረጣቸው ራሳቸውን ከአደጋ ለመጠበቅና ብዙ ሙቀት ከሰውነታቸው እንዳይወጣ ለማድረግ ይረዳቸዋል። ፈጣሪ ለእነዚህ አስገራሚ ትናንሽ ፍጥረታት የሰጠው ጥበብና ችሎታ ምንኛ አስደናቂ ነው!—ራእይ 4:11

ባለ አሳማ አፍንጫዋ የኪቲ የሌሊት ወፍ ዝርያዎች በተወሰኑ አካባቢዎች ላይ ብቻ የሚገኙና በጣም አናሳ ቁጥር ያላቸው በመሆኑ ሁኔታው ካልተሻሻለ በቀር እስከነጭራሹ እንዳይጠፉ ያሰጋል። የተሻለ ጥበቃ እንዲኖር ለማስቻል ጥረቶች እየተደረጉ ቢሆንም የደን መራቆት፣ ለንግድ ሲሉ ዛፎችን የሚቆርጡ ሰዎች፣ የመንገድ ሥራና ቱሪዝም ስጋት መፍጠራቸው አልቀረም። ይህች አነስተኛ አጥቢ እንስሳ በቀላሉ ሊጠፋ በሚችለው የመኖሪያ አካባቢዋ ላይ የሰው ልጆች የሚያደርሱትን ጉዳት ተቋቁማ በሕይወት መዝለቅ መቻል አለመቻሏ ገና ወደፊት የሚታይ ነገር ይሆናል።

[በገጽ 21 ላይ የሚገኝ ሣጥን/ሥዕል]

በጣም ትልቁና በጣም ትንሿ

ከአንድ ሺህ የሚበልጡ የሌሊት ወፍ ዝርያዎች ሲኖሩ ከአጥቢ እንስሳት መካከል መብረር የሚችሉት እነሱ ብቻ ናቸው። ከሌሊት ወፍ ዝርያዎች በትልቅነቱ ተወዳዳሪ የሌለው (1) በራሪ ቀበሮ የሚባለው ነው፤ ይህ የሌሊት ወፍ ክንፎቹን ሲዘረጋ ከጫፍ እስከ ጫፍ ያለው ርዝመት ከ1 ሜትር ተኩል የሚበልጥ ሲሆን ክብደቱም አንድ ኪሎ ግራም ያህላል። በተቃራኒው ደግሞ (2) ባለ አሳማ አፍንጫዋ የኪቲ የሌሊት ወፍ የክንፎቿ ርዝመት ከጫፍ እስከ ጫፍ 13 ሴንቲ ሜትር አካባቢ ሲሆን ክብደቷ ከሁለት ግራም አይበልጥም።

[በገጽ 21 ላይ የሚገኝ የሥዕል ምንጭ]

ፎቶ፦ © Merlin D. Tuttle, Bat Conservation International, www.batcon.org