በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ከአንባቢዎቻችን

ከአንባቢዎቻችን

ከአንባቢዎቻችን

የውኃን ችግር ለማስወገድ—ምን እየተደረገ ነው? (ጥር 2009) ይህ ርዕሰ ትምህርት ሐሳቡን የደመደመበት መንገድ ቅር አሰኝቶኛል። አንባቢዎቻችሁ የውኃ ጉድጓድ የሚሠሩ ሰዎችን እንዲያግዙ ወይም የውኃ ጥበቃ ፕሮግራሞችን እንዲደግፉ ከማበረታታት አሊያም የችግሩን ምንነት ይበልጥ እንዲያጠኑ ከማድረግ ይልቅ መጽሔቱ “የውኃን ችግር ለዘለቄታው የሚያስወግደው ሰው ሳይሆን አምላክ እንደሆነ” ከተናገረ በኋላ አምላክ ‘ሁሉን ነገር አዲስ የማድረግ’ ዓላማ እንዳለው ይገልጻል። (ራእይ 21:5) ይህ ሐሳብ የሚያበረታታ ቢሆንም እስከዚያው ድረስ ሰዎች የቻሉትን ያህል ጥረት እንዲያደርጉ ማበረታታቱ የተሻለ አይሆንም? በዚህ ዓለም ውስጥ በርካታ ችግሮች አሉ። አምላክ መፍትሔ ለማምጣት ዓላማ እንዳለው እርግጠኛ ብንሆንም ዲያብሎስ የፈለገውን ሲያደርግ እጃችንን አጣጥፈን መቀመጥ ያለብን አይመስለኝም።

ኤስ. ኤስ.፣ ዩናይትድ ስቴትስ

የንቁ! መጽሔት አዘጋጆች መልስ፦ ከላይ የተገለጸው ርዕስ ዓላማ ሰዎች በአሁኑ ጊዜ ያሉትን ችግሮች ለማስተካከል ጥረት የማድረግ ኃላፊነት የለባቸውም ለማለት አይደለም። በዚህ ርዕስ ውስጥ እንደተገለጸው “አምላክ ለሰው ልጆች ይህችን ምድር የመንከባከብ ኃላፊነት ሰጥቷቸዋል።” በመሆኑም መጽሔቶቻችን የምድርን ሀብት በቁጠባ በመጠቀምና አካባቢን በመጠበቅ ረገድ አንባቢዎቻችን የበኩላቸውን አስተዋጽኦ እንዲያደርጉ የሚያበረታቱ ሐሳቦችን ይዘው ወጥተዋል። የሚያሳዝነው ግን የአካባቢን ብክለት ከመከላከል ይልቅ ለኢኮኖሚ እድገት ትልቅ ቦታ የሚሰጡ ሕጎች እንዲሁም ፍጹም ያልሆኑት የሰው ልጆች የሚያሳዩት የስስትና የራስ ወዳድነት ዝንባሌ፣ ሰብዓዊው ኅብረተሰብ የምድርን ሀብት ለመጠበቅ ለሚያደርገው ጥረት ማነቆ ሆነዋል። ‘የውኃን ችግር ለዘለቄታው የሚያስወግደው አምላክ እንደሆነ’ የተናገርነው በዚህ ምክንያት ነው።

ለሕይወት አመቺ ሆና የተሠራችው ምድር (የካቲት 2009) መገናኛ ብዙኃን የምድር ሙቀት መጨመርን በተመለከተ ፍርሃት የሚለቅ ዘገባ ብቻ በሚዘግቡበት በዚህ ጊዜ ይህን የመሰለ ርዕስ ማንበቤ የአእምሮ ሰላም ሰጥቶኛል። የምድር የወደፊት ዕጣ ጨለማ እንዳልሆነ ከዚህ ይልቅ ቃል በቃል ወደ ገነትነት እንደምትለወጥ ብሎም ሰዎች ከአምላክ ጋር ሰላማዊ ግንኙነት ስለሚኖራቸው በመንፈሳዊ ገነት እንደምትሆን በማወቄም በጣም ተጽናንቻለሁ። ከልብ አመሰግናችኋለሁ።

ኤም. ኤች.፣ ጃፓን

ዲስሌክሲያ ግቤ ላይ ከመድረስ አላገደኝም (የካቲት 2009) እኔም ዲስሌክሲያ አለብኝ። የሚያሳዝነው ግን እኔና ባለቤቴ ሚስዮናዊ ሆነን በተመደብንበት አገር ሌላ ቋንቋ ለመማር እስከሞከርኩበት ጊዜ ድረስ የችግሬን ክብደት ሙሉ በሙሉ አልተረዳሁትም ነበር። ይህ ርዕስ በተለይ ደግሞ በገጽ 22 ላይ የሚገኘው ሣጥን የችግሩን ምንነት እንድገነዘብ ስለረዳኝ ትልቅ ማበረታቻ ሆኖልኛል። ማይካል ሄንቦ በርካታ ቋንቋዎችን በተሳካ መንገድ መማር የቻለው እንዴት እንደሆነ ማንበቤ አበረታቶኛል። በጣም አመሰግናችኋለሁ።

ኤም. ኤም.፣ ታንዛኒያ

የወጣቶች ጥያቄ . . . የመጽሐፍ ቅዱስ ንባቤን አስደሳች ማድረግ የምችለው እንዴት ነው? (ሚያዝያ 2009) ከፍተኛ የማየት ችግር ስላለብኝ ትምህርት ቤት የምጠቀመው በብሬል ነው። ጽሑፎቻችሁ ያሉብኝን በርካታ ችግሮች እንድቋቋም ስለረዱኝ በጣም እወዳቸዋለሁ። ብዙ ጊዜ ከመተኛቴ በፊት በካሴትና በሲዲ የተቀዱ ጽሑፎቻችሁን አዳምጣለሁ። ይህ ደግሞ ጥሩ ነገር እያሰብኩ እንድተኛ ረድቶኛል። ይህን ርዕስ ቢያንስ ለአምስት ጊዜ ያዳመጥኩት ሲሆን የግል ጥናቴን እንዴት ማሻሻል እንዳለብኝ የሚረዱ አንዳንድ ሐሳቦችን አግኝቼበታለሁ።

ኤስ. ኤች.፣ ፈረንሳይ