ገንዘብን በአግባቡ መጠቀም የምችለው እንዴት ነው?
መጽሐፍ ቅዱስ ምን ይላል?
ገንዘብን በአግባቡ መጠቀም የምችለው እንዴት ነው?
“ገቢዬ እያነሰ ሲሄድ ወጪዬ ግን እየጨመረ ነው። ለቤተሰቤ የሚያስፈልገውን ነገር እንዴት እንደማቀርብ ስጨነቅ ብዙውን ጊዜ እንቅልፍ በዓይኔ ሳይዞር አድራለሁ።”—ጄምስ
“መውጫ ቀዳዳ በሌለው ሁኔታ ውስጥ እንዳለሁ ሆኖ ተሰማኝ።”—ሼሪ
የኢኮኖሚ አለመረጋጋት በሚያጋጥምበት ወቅት እንዲህ ያሉ አስተያየቶችን መስማት የተለመደ ነገር ነው። የዓለም አቀፍ ሠራተኞች ድርጅት ዋና ዳይሬክተር የሆኑት ህዋን ሶማቪያ በቅርቡ ስለተከሰተው ዓለም አቀፍ የኢኮኖሚ ቀውስ አስተያየታቸውን ሲሰጡ ‘ይህ በዩናይትድ ስቴትስ የገንዘብ ተቋማት ላይ ብቻ የደረሰ ቀውስ አይደለም’ ካሉ በኋላ ‘ሁሉንም ሰው የሚነካ ዓለም አቀፍ ቀውስ ነው’ በማለት አክለው ተናግረዋል።
በድንገት ከሥራ መባረር ወይም ለቤተሰብ የሚያስፈልጉትን መሠረታዊ ነገሮች ለማቅረብ ገንዘብ ማጣት ለከፍተኛ ጭንቀት አልፎ ተርፎም ለተስፋ መቁረጥ ሊዳርግ ይችላል። መጽሐፍ ቅዱስን ከጻፉት ሰዎች አንዱ የሆነው ዳዊት በአንድ ወቅት በሕይወቱ ውስጥ እንደዚህ ተሰምቶት ነበር። ዳዊት “የልቤ መከራ በዝቶአል፤ ከጭንቀቴ ገላግለኝ” በማለት ጸልዮ ነበር። (መዝሙር 25:17) መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ዘመናችን ምን ይል ይሆን? ደግሞስ በዚህ መጽሐፍ ውስጥ የሚገኘው በመንፈስ መሪነት የተጻፈው ጥበብ ያዘለ ምክር የመረጋጋት ስሜትና ሰላም እንዲኖረን ሊረዳን ይችል ይሆን?
በዓይነቱ ልዩ ለሆነ ዘመን የሚሆን ጥበብ
መጽሐፍ ቅዱስ የዚህ ዓለም ‘የመጨረሻ ቀን ለመቋቋም የሚያስቸግር በዓይነቱ ልዩ የሆነ ዘመን’ እንደሚሆን እንዲሁም ‘ከምጥ ጣር’ ጋር እንደሚመሳሰል ትንቢት ተናግሯል። (2 ጢሞቴዎስ 3:1፤ ማቴዎስ 24:8) በዛሬው ጊዜ የእነዚህን ቃላት እውነተኝነት እየተመለከትን ነው! የምንኖረው በዓይነቱ ልዩ በሆነ ዘመን ውስጥ ቢሆንም ተስፋ አለን። አምላክ በቃሉ በመጽሐፍ ቅዱስ አማካኝነት የኢኮኖሚ አለመረጋጋት በነገሠበት በዚህ ዘመን እንኳ ችግሮችን ለመቋቋም የሚያስችለንን ጥበብ ይሰጠናል።
ለምሳሌ ያህል፣ መጽሐፍ ቅዱስ ለገንዘብ ትክክለኛ አመለካከት እንዲኖረን ይረዳናል። መክብብ 7:12 “ገንዘብ ጥላ ከለላ እንደ ሆነ ሁሉ፣ ጥበብም ጥላ ከለላ ነው፤ የዕውቀት ብልጫዋ ግን፣ ጥበብ የባለቤቷን ሕይወት መጠበቋ ነው” ይላል። አዎን፣ ገንዘብ በተወሰነ መጠን ጥላ ሊሆን ቢችልም በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የሚገኘው አምላካዊ ጥበብ ግን በየትኛውም ጊዜ የሚጠቅመንን እውነተኛ የመረጋጋት ስሜት ሊሰጠን ይችላል። እስቲ ጥቂት ምሳሌዎችን እንመልከት።
ከባድ የኢኮኖሚ ችግርን መቋቋም
ታታሪ ሁን። መጽሐፍ ቅዱስ “ሰነፍ አጥብቆ ይመኛል፤ አንዳችም አያገኝም፤ የትጉዎች ምኞት ግን ይረካል” በማለት ይናገራል። (ምሳሌ 13:4) ከዚህ የምናገኘው ትምህርት ምንድን ነው? ‘ሐቀኛና ትጉሕ ሠራተኛ ነው’ የሚል ስም አትርፍ። ጥሩ ሠራተኞች በአሠሪዎች ዘንድ የሚወደዱ ሲሆን ሥራ ለመቀጠር ቅድሚያ ሊሰጣቸው እንዲሁም ከሥራ የመባረር አጋጣሚያቸውም እጅግ አነስተኛ ሊሆን ይችላል።—ኤፌሶን 4:28
ሉቃስ 14:28) ምንም እንኳ ኢየሱስ ይህን ምሳሌ የተጠቀመው የእሱ ተከታይ መሆን የሚጠይቀውን ወጪ ማስላት አስፈላጊ ስለመሆኑ ለመግለጽ ቢሆንም የተናገራቸው ቃላት ቃል በቃልም እንደሚሠሩ ግልጽ ነው። ስለዚህ የግድ የሚያስፈልጉህን ነገሮች ከነዋጋቸው በመዘርዘር ባጀት አውጣ።
ከመግዛትህ በፊት ወጪህን አስላ። ኢየሱስ “ከእናንተ መካከል፣ ግንብ ለመገንባት ፈልጎ ለመጨረስ የሚያስችል በቂ ገንዘብ እንዳለው ለማወቅ በመጀመሪያ ተቀምጦ ወጪውን የማያሰላ ማን ነው?” በማለት ተናግሮ ነበር። (ለመጥፎ ልማዶች ገንዘብ አታባክን። እንደ ቁማር፣ ማጨስ፣ መድኃኒቶችን አላግባብ እንደ መጠቀም እንዲሁም ዕፆችን እንደ መውሰድና አልኮል መጠጦችን ከልክ በላይ እንደ መጠጣት የመሳሰሉት ልማዶች በአምላክ ፊት መጥፎ ናቸው።—ምሳሌ 23:20, 21፤ ኢሳይያስ 65:11፤ 2 ቆሮንቶስ 7:1
“ከገንዘብ ፍቅር” ተጠበቅ። (ዕብራውያን 13:5) ገንዘብን የሚወዱ ሰዎች ‘ሁለንተናቸውን በብዙ ሥቃይ የወጉ’ ያህል ሐዘንና ግራ መጋባት ያጋጥማቸዋል። (1 ጢሞቴዎስ 6:9, 10) ከዚህም በላይ ለማይረካ ፍላጎት ባሪያዎች ስለሚሆኑ የቱንም ያህል ገንዘብ ቢኖራቸው በቃኝ አይሉም።—መክብብ 5:10
ረክቶ መኖርን ተማር። መጽሐፍ ቅዱስ እንዲህ ይላል፦ “ወደ ዓለም ያመጣነው ምንም ነገር የለም፤ ምንም ነገር ይዘን መሄድም አንችልም። ስለዚህ ምግብ እንዲሁም ልብስና መጠለያ ካለን በእነዚህ ነገሮች ረክተን መኖር ይገባናል።” (1 ጢሞቴዎስ 6:7, 8) በጥቂት ነገሮች ረክተው የሚኖሩ ሰዎች የኢኮኖሚ ማሽቆልቆል በሚከሰትበት ጊዜ ከልክ በላይ ከመጨነቅ ሊጠበቁ ይችላሉ። በመሆኑም ባሉህ ነገሮች ረክቶ መኖርን ተማር።—በቀኝ በኩል የሚገኘውን ሣጥን ተመልከት።
ማናችንም ብንሆን ነገ የሚሆነውን አናውቅም። ሁላችንንም “መጥፎ ጊዜና ያልተጠበቁ ክስተቶች” ሊያጋጥሙን እንደሚችሉ መክብብ 9:11 [NW] ይናገራል። ስለዚህ ጠቢባን፣ ‘ተስፋቸውን አስተማማኝነት በሌለው ሀብት ላይ ሳይሆን በአምላክ ላይ ይጥላሉ፤’ ምክንያቱም አምላክ ለታማኝ አገልጋዮቹ “ፈጽሞ አልተውህም፣ በምንም ዓይነት አልጥልህም” በማለት ቃል ገብቷል።—1 ጢሞቴዎስ 6:17፤ ዕብራውያን 13:5
ይህን አስተውለኸዋል?
● መጽሐፍ ቅዱስ ዘመናችንን የሚገልጸው እንዴት ነው?—2 ጢሞቴዎስ 3:1-5
● በዛሬው ጊዜ እምነት የሚጣልበት መመሪያ ማግኘት የሚቻለው ከየት ነው?—መዝሙር 19:7
● ቤተሰቤ አስተማማኝ ሕይወት እንዲኖረው ማድረግ የምችለው እንዴት ነው?—መክብብ 7:12
[በገጽ 19 ላይ የሚገኝ ሣጥን/ሥዕል]
ገንዘብ መቆጠብ የሚቻልባቸው መንገዶች
ገበያ፦ የምትገዛቸውን ዕቃዎች ዝርዝር አዘጋጅ። በዕቅድህ ውስጥ የሌሉ ነገሮችን ከመግዛት ተቆጠብ። ቅናሽ ዋጋ ፈልግ፤ ለምሳሌ፣ ኩፖኖችን ተጠቀም ወይም በቅናሽ ሊሸጥልህ የሚችል ደንበኛ አብጅ። የምትፈልጋቸው ነገሮች በቅናሽ ዋጋ የሚሸጡበትን ወቅት ጠብቀህ ግዛ። ከቻልክ በጅምላ ግዛ።
የቤት ወጪዎች፦ ቅጣት ከመክፈል ለመዳን ክፍያዎችህን ጊዜያቸው ሳያልፍ አጠናቅቅ። ምግብና መጠጦችን ቤት ውስጥ አዘጋጅ፤ እንዲሁም በምግብና በአልኮል አወሳሰድህ ረገድ ልከኛ ሁን። የመብራት ፍጆታህን ለመቀነስ ሰው በሌለባቸው ክፍሎች ውስጥ መብራቶችን አጥፋ፤ እንዲሁም የማትገለገልባቸውን በኤሌክትሪክ የሚሠሩ መሣሪያዎች ሶኬት ንቀል። ከተቻለ ኃይል ቆጣቢ አምፑሎችንና ዕቃዎችን ተጠቀም። ቤትህን በምታሞቅበት ጊዜ ሙቀቱ እንዳይወጣ ለማድረግ የተለያዩ ዘዴዎችን ተጠቀም። አነስተኛ ቤት ውስጥ ስለመኖር አስብ።
መጓጓዣ፦ መኪና የሚያስፈልግህ ከሆነ አስተማማኝና ነዳጅ ቆጣቢ መኪና ግዛ። እርግጥ ነው፣ መኪናው አዲስ መሆን የለበትም። በአንድ አካባቢ ልትፈጽማቸው የምትችላቸው ነገሮች በሙሉ እዚያው አካባቢ ለመጨረስ ሞክር፤ የሚቻል ከሆነ ከሌሎች ጋር በአንድ መኪና ተጠቀም። አለበለዚያም በሕዝብ መጓጓዣ ተገልገል፣ በእግርህ ሂድ ወይም ብስክሌት ተጠቀም። ለሽርሽር የምትወጣ ከሆነ የዋጋ ቅናሽ በሚኖርበት ወቅት ወይም ቅርብ ወደሆነ አካባቢ ሂድ።
ስልክና መዝናኛ፦ የቤት ስልክና ሞባይል ያስፈልግሃል? ልጆችህ ሞባይል ስልክ ካላቸው በቁጠባ ሊጠቀሙ ይችላሉ? አሊያም ስልክ ባይኖራቸው የተሻለ ይሆን? የቴሌቪዥን አገልግሎት ለማግኘት ከተመዘገብህ የጣቢያዎቹን ቁጥር በመቀነስ ወጪህን መቆጠብ ትችል ይሆን? * መጻሕፍትንና ፊልሞችን ከመግዛት ይልቅ ተዋስ።
[የግርጌ ማስታወሻ]
^ አን.26 ተጨማሪ ሐሳቦችን ለማግኘት በመጋቢት 2009 ንቁ! መጽሔት ላይ የወጣውን “ጥሩ የገንዘብ አጠቃቀም ችሎታ አዳብር” እንዲሁም በሰኔ 2006 ንቁ! መጽሔት ላይ የወጣውን “የወጣቶች ጥያቄ . . . አባካኝ ከመሆን መቆጠብ የምችለው እንዴት ነው?” የሚሉትን ርዕሶች ተመልከት።