ከዓለም አካባቢ
በጀርመን በ2010 ከተወለዱት ሕፃናት መካከል 33 በመቶ የሚሆኑት ከጋብቻ ውጭ የተወለዱ ናቸው፤ በ1993 ከጋብቻ ውጭ የተወለዱት ሕፃናት 15 በመቶ ብቻ ነበሩ። —ኤርጽቴ ጻይቱንግ እና ዘ ሎካል፣ ጀርመን
የ2010 የሕዘብ ቆጠራ መረጃ እንደሚያሳየው በዩናይትድ ስቴትስ 69.4 በመቶ የሚሆኑ ልጆች የሚኖሩት ከሁለቱም ወላጆቻቸው ጋር ሲሆን 23.1 በመቶ የሚሆኑት ከእናታቸው ጋር ብቻ እንዲሁም 3.4 በመቶ የሚሆኑት ከአባታቸው ጋር ብቻ ይኖራሉ። ከወላጆቻቸው ጋር የማይኖሩት ደግሞ 4.1 በመቶ ናቸው።—የዩናይትድ ስቴትስ የሕዝብ ቆጠራ ቢሮ፣ ዩናይትድ ስቴትስ
በ2011 የተፈጥሮ አደጋዎች በዓለም ኢኮኖሚ ላይ 380 ቢልዮን የአሜሪካ ዶላር እንደሚደርስ የሚገመት ኪሳራ አስከትለዋል። የጃፓኑ የምድር መናወጥ “ታይቶ የማይታወቅ ከፍተኛ ኪሳራ ያስከተለ ሲሆን በፉኩሺማ የተከሰተውን የኑክሌር አደጋ ሳይጨምር አደጋው የ210 ቢልዮን የአሜሪካ ዶላር ኪሳራ አስከትሏል።”—ኒው ሳይንቲስት፣ ብሪታንያ
በዓለም አቀፍ ደረጃ በብዛት በመሰረቅ ረገድ የአንደኝነት ቦታ የያዘው የምግብ ምርት ቺዝ ነው። በየዓመቱ በመላው ዓለም ለችርቻሮ ከሚቀርበው ቺዝ ውስጥ ከ3 በመቶ በላይ የሚሆነው በሸማቾች እና በሱቅ ሠራተኞች ይሰረቃል።—የችርቻሮ ምርምር ማዕከል፣ ብሪታንያ
ኳስ በቴስታ መምታት የሚያስከትለው አደጋ
በእግር ኳስ ጨዋታ ላይ ኳስን በቴስታ መምታት የተለመደ ነው። ይሁን እንጂ የተራቀቁ የራጅ መሣሪያዎችንና የአእምሮ ችሎታ መፈተሻ ዘዴዎችን በመጠቀም በቅርቡ የተደረጉ ጥናቶች እንደሚያመለክቱት ኳስን በተደጋጋሚ በቴስታ መምታት አደገኛ ሊሆን ይችላል። በኒው ዮርክ፣ ዩናይትድ ስቴትስ የአልበርት አንስታይን የሕክምና ኮሌጅ ተመራማሪዎች እንደሚሉት ይህ ድርጊት “በአንጎል ላይ ጉዳት እንዲደርስና የማሰብ ችሎታ እንዲያሽቆለቁል አስተዋጽኦ ሊያደርግ ይችላል።” በዓመት ውስጥ ከ1,000 እስከ 1,500 ጊዜ (ለአንድ መደበኛ ተጫዋች በቀን ጥቂት ምቶች ብቻ ሊሆን ይችላል) ኳስ በቴስታ በሚመቱ ጀማሪ ተጫዋቾች ላይ ጉልህ የሆነ ጉዳት ታይቷል።
ኤሌክትሪክንና ነዳጅን የሚጠቀሙ ተሽከርካሪዎች ለእግረኞች ይበልጥ አደገኛ ናቸው
“ኤሌክትሪክንና ነዳጅን የሚጠቀሙ ተሽከርካሪዎች በእግረኞች ላይ የሚያደርሱት አደጋ እንዳሳሰባቸው የሚገልጹ ወገኖች አሉ” በማለት የዩናይትድ ስቴትስ የትራንስፖርት ሚኒስቴር ያወጣው ሪፖርት ገልጿል። “እንዲህ ዓይነት ተሽከርካሪዎች በአንጻራዊ ሁኔታ ብዙም ድምፅ ስለማያሰሙ እግረኞችና ብስክሌተኞች በመንገድ ሲጓዙ ወይም ማቋረጫ ቦታዎች ላይ ሲደርሱ ተሽከርካሪ መምጣቱን ሰምተው የጥንቃቄ እርምጃ መውሰድ አይችሉም።” በእርግጥም ሪፖርቱ እንደገለጸው እንዲህ ያሉት ተሽከርካሪዎች ከመደበኛዎቹ ተሽከርካሪዎች ጋር ሲወዳደሩ አንዳንድ እንቅስቃሴዎችን በሚያደርጉበት ወቅት “እግረኞችን የመግጨት አጋጣሚያቸው በሁለት እጥፍ ከፍ ያለ ነው።” በዚህ ምክንያት ብሔራዊ የጎዳና ደኅንነት አስተዳደር፣ እነዚህ መኪኖች ዝግ ባለ ፍጥነት በሚጓዙበት ጊዜ ድምፅ እንዲያሰሙ የሚያደርግ ደንብ እንዲወጣ ሐሳብ አቅርቧል።