በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

 ንድፍ አውጪ አለው?

የአርክቲኩ የመሬት አደሴ ቁኒ አስገራሚ አንጎል

የአርክቲኩ የመሬት አደሴ ቁኒ አስገራሚ አንጎል

በበረዷማ አካባቢ የሚኖሩ እንስሳት የቅዝቃዜውን ወራት በእንቅልፍ በሚያሳልፉበት ጊዜ የሰውነታቸው ሙቀት በጣም ይቀንሳል። የሰውነታቸው ሙቀት ምን ያህል ሊቀንስ ይችላል? በዚህ ረገድ አንዳንድ የአርክቲክ የመሬት አደሴ ቁኒዎች (Squirrel) * ከዚህ ቀደም ታይቶ የማይታወቅ ደረጃ ላይ ደርሰዋል፤ እነዚህ እንስሳት የሰውነታቸው ሙቀት ከዜሮ በታች እስከ 2.9 ዲግሪ ሴንቲ ግሬድ ዝቅ ያለበት ወቅት ተመዝግቧል! ሰውነታቸው ይህን ያህል ሲቀዘቅዝ አንጎላቸው ሥራውን እንደሚያቆም እንጠብቅ ይሆናል። ታዲያ በአርክቲክ የሚኖረው የመሬት አደሴ ቁኒ ቅዝቃዜውን ተቋቁሞ በሕይወት መትረፍ የሚችለው እንዴት ነው?

እስቲ የሚከተለውን አስብ፦ የአርክቲኩ የመሬት አደሴ ቁኒ የቅዝቃዜውን ወራት በእንቅልፍ በሚያሳልፍበት ወቅት በየሁለት ወይም በየሦስት ሳምንቱ ሰውነቱ ወደ ትክክለኛው የሙቀት መጠኑ (36.4 ዲግሪ ሴንቲ ግሬድ) ይመለሳል፤ ከዚያም ከ12 እስከ 15 ሰዓት ያህል እንደገና ሳይቀዘቅዝ ይቆያል። ሰውነቱ ሞቅ የሚልበት ይህ አጭር ጊዜ አንጎሉ እንዳይሞት አስተዋጽኦ እንደሚያደርግ ተመራማሪዎች ይገልጻሉ። ከዚህም በላይ በእንቅልፍ በሚያሳልፋቸው ጊዜያት ሁሉ ጭንቅላቱ ከሌላው የአካሉ ክፍል በትንሹም ቢሆን የሚበልጥ ሙቀት ይኖረዋል። በቤተ ሙከራ ውስጥ እንደታየው የእነዚህ እንስሳት አንገት ሙቀት ከ0.7 ዲግሪ ሴንቲ ግሬድ ፈጽሞ አይወርድም።

እነዚህ አደሴ ቁኒዎች የሰውነታቸው ሙቀት ቀዝቅዞ የሚቆዩበት ጊዜ ሲያበቃ አንጎላቸው ሁለት ሰዓት በሚያህል ጊዜ ውስጥ እንደ ቀድሞው ሥራውን ማከናወን ይጀምራል። እንዲያውም አንድ ጥናት እንዳመለከተው አደሴ ቁኒዎች በእንቅልፍ ከሚያሳልፉት ጊዜ በኋላ አንጎላቸው በተሻለ ቅልጥፍና ይሠራል! ሊቃውንቱ ይህ አስደናቂ ሁኔታ እንቆቅልሽ ሆኖባቸዋል። ደን ከተቃጠለ በኋላ በጥቂት ቀናት ውስጥ ዕፅዋቱ እንደገና ሲያቆጠቁጡ የሚኖረው ሁኔታ ከዚህ ክንውን ጋር እንደሚመሳሰል ይገልጻሉ።

ተመራማሪዎች በአርክቲኩ የመሬት አደሴ ቁኒ ላይ የሚያደርጉት ጥናት የሰውን አንጎል ችሎታ ይበልጥ ለመረዳት እንደሚያስችላቸው ተስፋ ያደርጋሉ። ግባቸው በአንጎላችን ውስጥ ያሉ ሕዋሶች እንደ አልዛይመርስ ባሉ የአንጎል ሕመሞች ምክንያት እንዳይጎዱ መከላከል ወይም የተጎዱት እንኳ እንደገና ሥራቸውን በአግባቡ ማከናወን እንዲችሉ ማድረግ ስለሚቻልበት መንገድ ተጨማሪ እውቀት ማግኘት ነው።

ታዲያ ምን ይመስልሃል? የአርክቲኩ የመሬት አደሴ ቁኒ አስገራሚ አንጎል በዝግመተ ለውጥ የተገኘ ነው? ወይስ ንድፍ አውጪ አለው?

^ አን.3 አደሴ ቁኒ የሚባለው እንስሳ ሙጭጭላ ወይም ሸለውለዊት ተብሎም ይጠራል።