በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

 መጽሐፍ ቅዱስ ምን ይላል?

ማሰላሰል

ማሰላሰል

ማሰላሰል ምንድን ነው?

“ሥራህን ሁሉ አሰላስላለሁ፤ ድንቅ ሥራህን ሁሉ አውጠነጥናለሁ።”—መዝሙር 77:12

ሰዎች ምን ይላሉ?

ማሰላሰል ብዙ ዓይነት መልክ ሊኖረው ይችላል፤ ከእነዚህ ውስጥ ብዙዎቹ የመነጩት ከጥንት ምሥራቃውያን እምነቶች ነው። ስለዚህ ጉዳይ የጻፈ አንድ ሰው “አእምሮ አጥርቶ እንዲመለከት ከተፈለገ ባዶ መሆን አለበት” ብሏል። ይህ ሰው የተናገረው ሐሳብ፣ በተወሰኑ ቃላት ወይም ምስሎች ላይ በማተኮር አእምሮ ባዶ እንዲሆን ማድረግ ውስጣዊ ሰላምና የጠራ አስተሳሰብ ያስገኛል የሚለውን አመለካከት የሚደግፍ ነው።

መጽሐፍ ቅዱስ ምን ይላል?

መጽሐፍ ቅዱስ፣ ማሰላሰል በጣም አስፈላጊ እንደሆነ ይናገራል። (1 ጢሞቴዎስ 4:15) ይሁን እንጂ መጽሐፍ ቅዱስ እንድናደርገው የሚያበረታታን የማሰላሰል ዓይነት አእምሮን ባዶ ማድረግን ወይም የተወሰኑ ቃላትን ወይም ሐረጎችን መድገምን የሚጠይቅ አይደለም። ከዚህ ይልቅ በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተጠቀሰው ማሰላሰል፣ ጤናማ በሆኑ ርዕሰ ጉዳዮች ለምሳሌ በአምላክ ባሕርያት፣ በደንቦቹና በፍጥረታቱ ላይ ትርጉም ባለው መንገድ ማሰብን ያመለክታል። አንድ ታማኝ የአምላክ አገልጋይ “ሥራህንም ሁሉ አሰላሰልሁ፤ የእጅህንም ሥራ አውጠነጠንሁ” በማለት ጸልዮአል። (መዝሙር 143:5) በተጨማሪም “በመኝታዬ አስብሃለሁ፤ ሌሊቱንም ሁሉ ስለ አንተ አሰላስላለሁ” ብሏል።—መዝሙር 63:6

 ማሰላሰል ሊጠቅምህ የሚችለው እንዴት ነው?

“የጻድቅ ልብ፣ መልስ ከመስጠቱ በፊት ያሰላስላል።”—ምሳሌ 15:28 NW

መጽሐፍ ቅዱስ ምን ይላል?

ተገቢ የሆነ ማሰላሰል ብስለት፣ ስሜታችንን የመቆጣጠር ችሎታና የመንፈስ ጥንካሬ ይሰጠናል፤ እነዚህ ባሕርያት ደግሞ በንግግራችንና በምግባራችን ማስተዋል እንዲኖረን ይረዱናል። (ምሳሌ 16:23) በመሆኑም እንዲህ ያለው ማሰላሰል ደስተኛ እንድንሆንና አርኪ ሕይወት እንድንመራ ያስችለናል። መዝሙር 1:3 ስለ አምላክ አዘውትሮ የሚያሰላስል ሰው ምን ጥቅም እንደሚያገኝ ሲናገር “እርሱም በወራጅ ውሃ ዳር እንደ ተተከለች፣ ፍሬዋን በየወቅቱ እንደምትሰጥ፣ ቅጠሏም እንደማይጠወልግ ዛፍ ነው፤ የሚሠራውም ሁሉ ይከናወንለታል” ይላል።

በተጨማሪም ማሰላሰል የመረዳትና የማስታወስ ችሎታችንን እንድናሻሽል ይረዳናል። ለምሳሌ፣ ስለ አንድ የፍጥረት ሥራ ወይም የመጽሐፍ ቅዱስ ርዕሰ ጉዳይ ስናጠና ብዙ አስገራሚ እውነታዎችን እናውቃለን። በእነዚህ ነገሮች ላይ በምናሰላስልበት ጊዜ ደግሞ እውነታዎቹ እርስ በርሳቸውም ሆነ ከዚህ በፊት ከምናውቃቸው ነገሮች ጋር እንዴት እንደሚዛመዱ ማስተዋል እንችላለን። አንድ አናጺ የተለያዩ ቁሳቁሶችን ተጠቅሞ የሚያምር የቤት ዕቃ እንደሚሠራ ሁሉ ማሰላሰልም ያወቅናቸው የተለያዩ እውነታዎች እርስ በርስ እንዲያያዙና አንድ ላይ እንዲዋቀሩ ያስችላል።

በምናሰላስልበት ወቅት የምናስበውን ነገር መቆጣጠር አለብን?

“የሰው ልብ ከሁሉ ይልቅ ተንኰለኛ ነው፤ ፈውስም የለውም፤ ማንስ ሊረዳው ይችላል?”—ኤርምያስ 17:9

መጽሐፍ ቅዱስ ምን ይላል?

“ከውስጥ፣ ከሰው ልብ ክፉ ሐሳብ ይወጣል፦ ዝሙት፣ ሌብነት፣ ግድያ፣ ምንዝር፣ መጎምጀት፣ ክፋት፣ ማታለል፣ ብልግና፣ ምቀኝነት፣ . . . ሞኝነት።” (ማርቆስ 7:21, 22) በመሆኑም ማሰላሰል ልክ እንደ እሳት ቁጥጥር ሊደረግበት ይገባል። ካልሆነ ግን ተገቢ ያልሆኑ ሐሳቦች ከቁጥጥር ውጭ ሆነው ወደ ክፉ ድርጊት ሊመሩ የሚችሉ ጎጂ ፍላጎቶች በውስጣችን ሊያድጉ ይችላሉ።—ያዕቆብ 1:14, 15

በመሆኑም መጽሐፍ ቅዱስ ‘እውነት በሆነው፣ ጽድቅ በሆነው፣ ንጹሕ በሆነው፣ ተወዳጅ በሆነው፣ በመልካም በሚነሳው፣ በጎ በሆነው እና ምስጋና በሚገባው’ ነገር ላይ እንድናሰላስል ይመክረናል። (ፊልጵስዩስ 4:8, 9) እንደነዚህ ያሉትን ጥሩ ሐሳቦች በአእምሯችን ውስጥ ስንዘራ ግሩም የሆኑ ባሕርያትን እናፈራለን፤ አነጋገራችን ለዛ ያለው ይሆናል፤ ከሌሎችም ጋር ጥሩ ግንኙነት ይኖረናል።—ቆላስይስ 4:6