የሽፋኑ ርዕሰ ጉዳይ
ውጥረትን መቆጣጠር የሚቻልበት መንገድ
“የትም ላትደርስ ነገር በሽክርክሪት ውስጥ የምትሮጥ አይጥ እንደሆንኩ ይሰማኛል። ብዙ ጊዜ በቀን 16 ሰዓት እሠራለሁ፤ ቅዳሜና እሁድ የማርፈው ከስንት አንዴ ነው። ቤት ስገባ ሕፃን ልጄ ተኝታ ስለማገኛት በራሴ እበሳጫለሁ። በውጥረት ምክንያት የጤና መቃወስ እያጋጠመኝ ነው።”—ካሪ፣ ፊንላንድ
በካሪ ላይ የደረሰው ሁኔታ ብዙዎችን የሚያጋጥም ነው። በዩናይትድ ኪንግደም የሚገኝ አንድ የአእምሮ ጤና ግብረ ሰናይ ድርጅት እንደገለጸው ከሆነ ከአምስት የብሪታንያ ሠራተኞች መካከል አንዱ በሥራ ዓለም ሳለ ባጋጠመው ውጥረት ምክንያት የጤና መቃወስ እንዳጋጠመው ሲናገር ከአራት ሰዎች መካከል አንዱ ደግሞ በሥራ ቦታ ሳለ በደረሰበት ጫና ምክንያት እንዳለቀሰ ተናግሯል። ለመንፈስ ጭንቀት የሚሰጡ መድኃኒቶች የኢኮኖሚ ውድቀት በደረሰበት በ2009 ከዚህ በፊት ታይቶ በማያውቅ መጠን በሐኪሞች ታዝዘዋል።
ውጥረት ያስከተለብህ ነገር ምንድን ነው?
ከገንዘብ ጋር የተያያዘ ወይም ሌላ ዓይነት ስጋት
ፋታ የማይሰጥ ሥራ
ከሰዎች ጋር አለመግባባት
አስደንጋጭ ገጠመኝ
ውጥረት ምን ተጽዕኖ አስከትሎብሃል?
የጤና መቃወስ
በስሜት መዛል
የእንቅልፍ ችግር
የመንፈስ ጭንቀት
ከሰዎች ጋር አለመስማማት
ሰውነታችን ድንገተኛ ሁኔታ ሲያጋጥመው ምላሽ የሚሰጥበት የራሱ የሆነ ሂደት አለው፤ ውጥረት ይህ ሂደት እንዲካሄድ ያደርጋል። በዚህ ጊዜ አተነፋፈስህ፣ የልብ ምትህና የደም ግፊትህ እንዲጨምር የሚያደርጉ ሆርሞኖች ይመነጫሉ። በተጨማሪም በመጠባበቂያነት የተቀመጡ የደም ሴሎችና ግሉኮስ ወደ ደማችን ውስጥ ይጎርፋሉ። ይህ ሁሉ ጋጋታ ውጥረት ያስከተለብህን ነገር ለመጋፈጥ እንድትዘጋጅ ያደርግሃል። ውጥረት ያስከተለብህ ነገር ካለፈ በኋላ ሰውነትህ ወደ ወትሮው ሁኔታ ይመለሳል። ውጥረት ያስከተለው ሁኔታ ከቀጠለ ግን ጭንቀትህ ወይም ስጋትህ ስለማይበርድ ሰውነትህ ለረጅም ጊዜ በኃይል እየሠራ እንደሚቀጥል ሞተር ይሆናል። ስለዚህ ውጥረትን ለመቆጣጠር ምን ማድረግ እንዳለብህ ማወቅህ ለአካላዊም ሆነ ለአእምሯዊ ጤንነትህ በጣም አስፈላጊ ነው።
ውጥረትን መቆጣጠር
ውጥረት በራሱ ሁልጊዜ ጎጂ አይደለም። የአሜሪካ የሥነ ልቦና ማኅበር የሚከተለውን ብሏል፦ “ውጥረት በሰዎች ላይ የሚያስከትለው ውጤት ቫዮሊን ሲቃኝ ከሚኖረው ሁኔታ ጋር ሊመሳሰል ይችላል። ጅማቱ በጣም ከላላ የሚወጣው ድምፅ ደካማና የታፈነ ይሆናል፤ በጣም ከከረረ ደግሞ ጆሮ የሚሰቀጥጥ ድምፅ ያወጣል፤ ወይም ክሩ ይበጠሳል። ከዚህ አንጻር ውጥረት የሞት መንስኤ አሊያም የሕይወት ቅመም ሊሆን ይችላል። ዋናው ነገር ውጥረትን መቆጣጠር ነው።”
ከውጥረት ጋር በተያያዘ ሊነሳ የሚገባው ሌላው ጉዳይ ደግሞ የሰዎች ተፈጥሮና የጤና ሁኔታ የተለያየ መሆኑ ነው። በመሆኑም በአንድ ሰው ላይ ውጥረት የሚያስከትል ነገር በሌላው ላይ ምንም ለውጥ ላያመጣ ይችላል። ያም ሆኖ በዕለት ተዕለት እንቅስቃሴህ በጣም በመጨናነቅህ የተነሳ ዘና ማለት ካቃተህ ወይም ደግሞ የሚያጋጥሙህን ድንገተኛ ሁኔታዎችን መወጣት ከከበደህ ከመጠን ያለፈ ውጥረት አለብህ ማለት ነው።
አንዳንድ ሰዎች የሚደርስባቸውን ውጥረት ለመቋቋም ሲሉ አልኮል፣ ዕፅ፣ ወይም ትንባሆ ይወስዳሉ። ሌሎች ደግሞ ጤናማ ያልሆነ የአመጋገብ ልማድ ያዳብራሉ፤ አሊያም ቴሌቪዥን በማየት ወይም ኮምፒውተር በመጠቀም ረጅም ጊዜ ያሳልፋሉ፤ እነዚህ ልማዶች ችግሩን ከማስወገድ ይልቅ ያባብሱታል። ታዲያ የሚደርስብህን ውጥረት መቆጣጠር የምትችለው እንዴት ነው?
ብዙ ሰዎች በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚገኙ ጠቃሚ ምክሮችን ሥራ ላይ በማዋል የሚያጋጥማቸውን ውጥረት መቆጣጠር ችለዋል። ታዲያ ተፈትኖ የተረጋገጠው የመጽሐፍ ቅዱስ ምክር አንተንስ ሊረዳህ ይችላል? ለውጥረት መንስኤ የሚሆኑ አራት ነገሮችን በማንሳት የዚህን ጥያቄ መልስ ለማግኘት እንሞክር።
1 ስጋት
ማናችንም ብንሆን ከስጋት ሙሉ በሙሉ ነፃ አይደለንም። መጽሐፍ ቅዱስ እንደሚለው ሁላችንም “መጥፎ ጊዜና ያልተጠበቁ ክስተቶች” ያጋጥሙናል። (መክብብ 9:11 NW) ታዲያ ስጋትን ለመቋቋም ምን ሊረዳህ ይችላል? የሚከተሉትን ሐሳቦች ተግባራዊ ለማድረግ ሞክር።
ለምታምነው የቤተሰብህ አባል ወይም ለወዳጅህ የልብህን አውጥተህ ንገረው። ወዳጆቻችን የሚሰጡን ድጋፍ በውጥረት ምክንያት ከሚመጣ የጤና ቀውስ ብዙውን ጊዜ ሊጠብቀን እንደሚችል ጥናቶች አመልክተዋል። አዎ፣ “እውነተኛ ወዳጅ ምንጊዜም አፍቃሪ ነው፤ ደግሞም ለመከራ ቀን የተወለደ ወንድም ነው።”—ምሳሌ 17:17 NW
ሁልጊዜ ክፉውን ብቻ አታስብ። እንዲህ ያለው አስተሳሰብ ስሜታዊ ጥንካሬህን ከማዳከም ውጪ የሚፈይደው ነገር የለም። ደግሞም ይደርሳል ብለህ የፈራኸው ነገር ላይደርስ ይችላል። መጽሐፍ ቅዱስ “ስለ ነገ ፈጽሞ አትጨነቁ፤ ምክንያቱም ነገ የራሱ የሆኑ የሚያስጨንቁ ነገሮች አሉት” የሚለው ያለምክንያት አይደለም።—ማቴዎስ 6:34
ጸሎት ያለውን ኃይል አቅልለህ አትመልከት። በመሆኑም ‘የሚያስጨንቅህን ነገር ሁሉ በአምላክ ላይ ጣል’፤ ምክንያቱም 1 ጴጥሮስ 5:7 እንደሚናገረው ‘እሱ ስለ አንተ ያስባል።’ አምላክ ውስጣዊ ሰላም በመስጠት፣ እንደሚያስብልን ያሳየናል፤ በተጨማሪም በችግር ጊዜ ማጽናኛና እርዳታ ፈልገው ወደ እሱ የሚጮኹትን ሁሉ ‘ፈጽሞ እንደማይተዋቸው’ ማረጋገጫ ሰጥቷል።—ዕብራውያን 13:5፤ ፊልጵስዩስ 4:6, 7
2 ፋታ የማይሰጥ ሥራ
ሥራ፣ ትምህርት፣ ልጆች ማሳደግ ወይም አረጋዊ ወላጆችን መንከባከብ አሊያም ለሥራ ረጅም ጉዞ ማድረግ ለውጥረት ሊዳርግ ይችላል። በሌላ በኩል ደግሞ እነዚህን እንቅስቃሴዎች ማቆም የማይታሰብ ነገር ሊሆን ይችላል። (1 ጢሞቴዎስ 5:8) ታዲያ ምን ማድረግ ይቻላል?
ዘና የምትልበትን ጊዜ በመመደብ በቂ እረፍት ለማግኘት ሞክር። መጽሐፍ ቅዱስ “ብዙ በመልፋትና ነፋስን በማሳደድ ከሚገኝ ሁለት እፍኝ ይልቅ ጥቂት እረፍት በማድረግ የሚገኝ አንድ እፍኝ ይሻላል” ይላል።—መክብብ 4:6 NW
ቅድሚያ ሊሰጣቸው የሚገቡ ነገሮችን ለይ፤ ልከኛ የሆነ ኑሮ ለመኖር ጥረት አድርግ። (ፊልጵስዩስ 1:10) ኑሮህን ቀላል ለማድረግ ሞክር፤ ምናልባትም ወጪዎችህን ወይም በሥራ የምታሳልፈውን ጊዜ በመቀነስ ይህን ማድረግ ትችላለህ።
ቀደም ሲል የተጠቀሰው ካሪ ሕይወቱን መለስ ብሎ ተመለከተ። “አኗኗሬ ራስ ወዳድነት የሚንጸባረቅበት እንደሆነ ተገነዘብኩ” ሲል ጽፏል። ሱቁን ሸጠና ከቤተሰቡ ጋር የበለጠ ጊዜ ለማሳለፍ የሚያስችለውን ሥራ ጀመረ። እንዲህ ብሏል፦ “የኑሮ ደረጃችን በመጠኑ ቀንሷል፤ ይሁን እንጂ በአሁኑ ጊዜ እኔና ባለቤቴ ውጥረት ከበዛበት ሕይወት ነፃ ወጥተናል። ከቤተሰቦቻችንና ከወዳጆቻችን ጋር የበለጠ ጊዜ ማሳለፍ ችለናል። አሁን ያለኝን ውስጣዊ ሰላም በሚከፈቱልኝ የንግድ አጋጣሚዎች መለወጥ አልፈልግም።”
3 ከሰዎች ጋር አለመግባባት
ከሌሎች በተለይም በሥራ ቦታ ከምታገኛቸው ሰዎች ጋር መጋጨት ከፍተኛ ውጥረት ሊያስከትልብህ ይችላል። እንዲህ ያለ ችግር ካጋጠመህ ሊረዱህ የሚችሉ የተለያዩ አማራጮች አሉ።
አንድ ሰው ሲያናድድህ ራስህን ለማረጋጋት ሞክር። እሳቱ ላይ ጭድ ከመጨመር ተቆጠብ። ምሳሌ 15:1 “የለዘበ መልስ ቍጣን ያበርዳል፤ ክፉ ቃል ግን ቍጣን ይጭራል” ይላል።
አለመግባባት ሲፈጠር ግለሰቡን ለብቻው በአክብሮት ለማነጋገር ጥረት አድርግ፤ እንዲህ ማድረግህ ለግለሰቡ አክብሮት እንዳለህ ያሳያል።—ማቴዎስ 5:23-25
የሌላውን ሰው ስሜትና አመለካከት ለመረዳት ሞክር። ይህን ማስተዋልህ ራስህን በሌላው ሰው ቦታ አድርገህ እንድታይ ስለሚያስችል ‘ከቍጣ ያዘገይሃል።’ (ምሳሌ 19:11 የ1954 ትርጉም) በተጨማሪም በሌላው ሰው መነጽር ራስህን እንድታይ ሊረዳህ ይችላል።
ይቅር ባይ ሁን። ይቅር ማለት መልካም ምግባር ከመሆኑም በላይ ጥሩ መድኃኒት ነው። በ2001 የተደረገ አንድ ጥናት እንዳሳየው “ቂም መያዝ” የደም ግፊትና የልብ ምት “እንዲጨምሩ” የሚያደርግ ሲሆን ይቅር ማለት ግን ውጥረትን ይቀንሳል።—ቆላስይስ 3:13
4 አስደንጋጭ ገጠመኝ
በካምቦዲያ የምትኖረው ኒየንግ በመከራ ላይ መከራ ተደራርቦባታል። በ1974 በአንድ የአውሮፕላን ማረፊያ ቦምብ ሲፈነዳ ከባድ ጉዳት ደረሰባት። በቀጣዩ ዓመት ሁለት ልጆቿ፣ እናቷና ባሏ ሞቱባት። በ2000 ቤት ንብረቷ በእሳት የወደመ ሲሆን ከሦስት ዓመት በኋላ ደግሞ ሁለተኛ ባሏ ሞተ። በዚህ ጊዜ ራሷን ማጥፋት ፈለገች።
“ብዙ በመልፋት . . . ከሚገኝ ሁለት እፍኝ ይልቅ ጥቂት እረፍት በማድረግ የሚገኝ አንድ እፍኝ ይሻላል”
ይህን እንጂ ኒየንግ ሐዘኗን መቋቋም የምትችልበትን መንገድ አገኘች። እንደ ካሪ ሁሉ እሷም መጽሐፍ ቅዱስን በመመርመሯ ብዙ ተጠቅማለች፤ በምላሹም እሷ ያገኘችውን ጥቅም ሌሎች እንዲያገኙ በመርዳቱ ሥራ አብዛኛውን ጊዜዋን ማሳለፍ ጀመረች። የእሷ ታሪክ የብሪታንያ ተመራማሪዎች በ2008 ያደረጉትን ጥናት ያስታውሰናል። እነዚህ ተመራማሪዎች የደረሱበት መደምደሚያ እንደሚያሳየው “ውጥረትን ለመቋቋም የሚያስችል አቅም ለማግኘት” ከሚረዱ መንገዶች አንዱ “ለሰዎች በሆነ መንገድ በጎ ተግባር መፈጸም” ነው፤ ይህ ደግሞ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሰፈረ ጥንታዊ ምክር ነው።—የሐዋርያት ሥራ 20:35
በተጨማሪም ኒየንግ ወደፊት የተሻለ ጊዜ እንደሚመጣ ይኸውም ዛሬ የሰው ልጆችን ቀስፈው የያዙት ችግሮች በሙሉ እንደሚወገዱ የሚገልጽ አስተማማኝ ተስፋ አገኘች። ይህ ተስፋ በሚፈጸምበት ጊዜ “ሰላም ይበዛል።”—መዝሙር 72:7, 8
እውነተኛ ተስፋና ውጥረትን ለመቋቋም የሚያስችል ጥበብ ማግኘት በዋጋ ሊተመን የማይችል ሀብት ነው፤ ሁለቱንም ቢሆን ከመጽሐፍ ቅዱስ ማግኘት ይቻላል። በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች ከዚህ አስደናቂና ልዩ የሆነ መጽሐፍ ጥቅም አግኝተዋል። አንተም ከእነሱ አንዱ ልትሆን ትችላለህ።