በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ከዓለም አካባቢ | እስያ

የዜናው ትኩረት—እስያ

የዜናው ትኩረት—እስያ

እስያ በዓለም ላይ ካሉ ሌሎች አህጉራት ይበልጥ ብዙ ሕዝብ የሚኖርባት አህጉር ናት። በቻይናና በሕንድ ብቻ እንኳ ከምድር ሕዝብ መካከል ከአንድ ሦስተኛ በላይ የሚሆነው ይኖራል። ታዲያ እስያ ውስጥ ያሉ አገሮች ሕዝባቸውን በማስተማርና በመጠበቅ ረገድ ምን ተፈታታኝ ሁኔታ ተጋርጦባቸዋል?

ልጆችን ማስተማር ከጥቃት ይጠብቃቸዋል

ወላጆች ፆታን በተመለከተ ለልጆቻቸው ገና ከሕፃንነታቸው ሥልጠና ካልሰጧቸው ልጆቹ ለጥቃት የመጋለጣቸው አጋጣሚ ሰፊ እንደሚሆን የቻይና የሕግ ባለሙያዎች ይናገራሉ። በቻይና የሚገኙ አቃቤ ሕጎች፣ ባለፉት አራት ዓመታት ውስጥ 8,000 የሚያህሉ በልጆች ላይ ከተፈጸሙ የፆታ ጥቃቶች ጋር የተያያዙ ክሶችን ተመልክተዋል። በቤይጂንግ ኖርማል ዩኒቨርሲቲ የሕግ ፕሮፌሰር የሆኑ አንድ ሰው ልጆች “ለጥቃት የተጋለጡና በቀላሉ የወንጀል ዒላማ ሊሆኑ የሚችሉ ናቸው። የፆታ ጥቃትን ለመከላከል ቁልፉ ማስተማር ነው” ብለዋል።

መጽሐፍ ቅዱስ ምን ይላል? ጥበበኛ የሆኑ ወላጆች ልጆቻቸውን ‘ጠማማ ነገር ከሚናገሩ ሰዎች’ ራሳቸውን እንዴት መጠበቅ እንደሚችሉ ያስተምራሉ።​—ምሳሌ 2:1, 10-12

ኃይለኛ አውሎ ነፋስ ከተከሰተ በኋላ የሚሞቱ ሕፃናት

አንድ ጥናት እንዳመለከተው በፊሊፒንስ ኃይለኛ አውሎ ነፋስ ከተከሰተ በኋላ በነበረው አንድ ዓመት ውስጥ የሞቱት ሴት ሕፃናት ቁጥር ነፋስ በቀላቀለው ጎርፍ ከሞቱት ሰዎች ቁጥር በ15 እጥፍ ይበልጣል። ለእነዚህ ሕፃናት ሞት በምክንያትነት ከሚጠቀሱት ነገሮች መካከል አውሎ ነፋሱ ያስከተለው ሥራ አጥነት፣ ከተማዋን መልሶ ለመገንባት የወጣው ወጪ እንዲሁም ከምግብና ከጤና ጋር በተያያዘ ለሴት ሕፃናት የሚያስፈልጉት ነገሮች አለመሟላታቸው ይገኙበታል።

መጽሐፍ ቅዱስ ምን ይላል? ‘ምግብህን ለተራበው አካፍል፤ ድሆችንና ቤት የሌላቸውን ወደ ቤትህ አስገባ፤ የተራቆተ ሰው ስታይ አልብሰው።’​—ኢሳይያስ 58:7

በደቡብ ኮሪያ ራሳቸውን የሚያጠፉ አረጋውያን

በ2011 በደቡብ ኮሪያ ራሳቸውን ካጠፉ ሰዎች መካከል ከአንድ አራተኛ በላይ የሚሆኑት ከ65 ዓመት በላይ የሆኑ አረጋውያን ናቸው። አንዳንድ ተመራማሪዎች ለዚህ ምክንያቱ ለአረጋውያን እንክብካቤ ማድረግን በተመለከተ የአመለካከት ለውጥ መኖሩ እንዲሁም ያሉበት የኢኮኖሚ ሁኔታ ዝቅተኛ መሆኑ እንደሆነ ይናገራሉ፤ በደቡብ ኮሪያ ከሚኖሩ አረጋውያን መካከል ከግማሽ በላይ የሚሆኑት በአንጻራዊ ሁኔታ በድህነት ይኖራሉ። በአሁኑ ጊዜ በደቡብ ኮሪያ ከሚኖሩ ሰዎች መካከል ልጆች አረጋውያን ወላጆቻቸውን መጦር እንደሚገባቸው የሚያስቡት ከግማሽ ያነሱ ናቸው።

መጽሐፍ ቅዱስ ምን ይላል? “አባትህንና እናትህን አክብር።”—ኤፌሶን 6:2