በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

መጽሐፍ ቅዱስ ምን ይላል?

ሥራ

ሥራ

መጽሐፍ ቅዱስ ከተጻፈ ረጅም ዘመን ያስቆጠረ ቢሆንም በውስጡ ያሉት መመሪያዎች ጊዜ የማይሽራቸው ናቸው። መጽሐፍ ቅዱስ ሥራን አስመልክቶ የሚሰጣቸው ምክሮች በተጻፉበት ወቅት ጠቃሚ የነበሩትን ያህል ዛሬም ይጠቅማሉ።

ስለ ሥራ ሊኖረን የሚገባው ትክክለኛ አመለካከት ምንድን ነው?

አንዳንዶች ምን ይላሉ?

ፉክክር በነገሠበት በሥራው ዓለም ተወዳዳሪ ሆነህ ለመቀጠል ከምንም ነገር በላይ ለሥራህ ቅድሚያ መስጠት ይኖርብሃል። ይህ አመለካከት አንዳንዶች ቤተሰባቸውንም ሆነ ጤንነታቸውን ችላ እስኪሉ ድረስ በሥራቸው ላይ ብቻ እንዲያተኩሩ አድርጓቸዋል።

መጽሐፍ ቅዱስ ምን ይላል?

መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ሥራ ሚዛናዊ አመለካከት እንዲኖረን ይመክራል። ታታሪነትን የሚያበረታታ ሲሆን ስንፍናን ደግሞ ያወግዛል። (ምሳሌ 6:6-11፤ 13:4) በሌላ በኩል ግን መጽሐፍ ቅዱስ በሥራ ሱስ እንዳንጠመድ ያስጠነቅቃል። እንዲያውም ዘና የምንልበት ጊዜ እንዲኖረን ያበረታታል። መክብብ 4:6 “ብዙ በመልፋትና ነፋስን በማሳደድ ከሚገኝ ሁለት እፍኝ ይልቅ ጥቂት እረፍት በማድረግ የሚገኝ አንድ እፍኝ ይሻላል” ይላል። በመሆኑም ቤተሰባችንንና ጤንነታችንን ችላ እስክንል ድረስ በሥራ መወጠር የሚያስገኘው ጥቅም የለም!

“ሰው ከመብላትና ከመጠጣት እንዲሁም ተግቶ በመሥራት እርካታ ከማግኘት የሚሻለው ነገር የለም።”መክብብ 2:24

የምንመርጠው የሥራ ዓይነት ለውጥ ያመጣል?

አንዳንዶች ምን ይላሉ?

ሥራው ምንም ይሁን ምን ክፍያው ጥሩ ከሆነ መሥራት ይኖርብሃል። እንዲህ ያለው አመለካከትና በአቋራጭ የመክበር ፍላጎት አንዳንዶችን ሐቀኝነት በጎደላቸው የንግድ ሥራዎች እንዲካፈሉ አልፎ ተርፎም ሕገ ወጥ በሆኑ ሥራዎች እንዲሰማሩ አነሳስተዋቸዋል።

ሌሎች ደግሞ መሥራት የሚፈልጉት እነሱን የሚያስደስታቸውን ሥራ ብቻ ነው። ‘ለዚያ ሥራ የተፈጠሩ ናቸው’ ካልተባለላቸው ወይም ሥራው የሚመስጣቸው ዓይነት ካልሆነ አሰልቺ ይሆንባቸዋል። በዚህም የተነሳ ለሥራቸው አሉታዊ አመለካከት የሚኖራቸው ሲሆን በሥራቸውም ይለግማሉ። አልፎ ተርፎም ለእነሱ እንደማይመጥኑ ከተሰማቸው ጥሩ የሥራ አጋጣሚዎችን እንኳ ከመቀበል ወደኋላ ይላሉ።

መጽሐፍ ቅዱስ ምን ይላል?

መጽሐፍ ቅዱስ ሐቀኝነት በጎደለው ወይም በሆነ መንገድ ሰዎችን በሚጎዳ ሥራ መካፈልን ያወግዛል። (ዘሌዋውያን 19:11, 13፤ ሮም 13:10) ጥሩ ሥራ ሌሎች ሰዎችን የሚጠቅም ከመሆኑም በላይ የሚሠራው ሰውም “ጥሩ ሕሊና” እንዲኖረው ያደርጋል።—1 ጴጥሮስ 3:16

በተጨማሪም መጽሐፍ ቅዱስ ሥራ የምንሠራበት ዋነኛ ዓላማ ውስጣዊ እርካታ ማግኘት ሳይሆን ራሳችንንና ቤተሰባችንን ለማስተዳደር የሚያስችል ገቢ ማግኘት እንደሆነ ያስተምራል። ሰብዓዊ ሥራ በመሥራት መደሰት ስህተት ባይሆንም በሕይወታችን ውስጥ ትልቅ ቦታ የሚሰጠው ነገር ሊሆን ግን አይገባም።

“አባቴ ሥራ በጣም ይበዛበታል። ከሰብዓዊ ሥራው በተጨማሪ የይሖዋ ምሥክሮች እንደመሆናችን መጠን በጉባኤያችን ውስጥ የተለያዩ ኃላፊነቶች አሉበት። ሆኖም አባቴ ጥሩ የሥራ ልማድ አለው። መሥራት ያለበትን ነገሮች ይሠራል፤ እንደዚያም ሆኖ ለእኔ፣ ለእህቴና ለእናቴ የሚሆን ጊዜ አያጣም። ብዙ የሚሠራቸው ነገሮች ቢኖሩትም ሁሉንም ሚዛናዊ በሆነ መንገድ ያከናውናል።”—አላና

የዋጋ ግሽበትና የኑሮ ውድነት ገቢያችንን ከወጪያችን ጋር አብቃቅተን ለመኖር የምናደርገውን ጥረት ከባድ ሊያደርጉብን እንደሚችሉ ግልጽ ነው፤ ያም ቢሆን መጽሐፍ ቅዱስ ልከኛ እንድንሆን ይመክረናል። እንዲህ ይላል፦ “ምግብና ልብስ ካለን በእነዚህ ነገሮች ረክተን መኖር ይገባናል።” (1 ጢሞቴዎስ 6:8) ይህ ሲባል ግን መጽሐፍ ቅዱስ የመናኝ ዓይነት ኑሮ እንድንመራ ያስተምራል ማለት አይደለም። ከዚህ ይልቅ ከገንዘብ ጋር በተያያዘ አቅማችንን ግምት ውስጥ ማስገባት እንዲሁም እንዲኖረን በምንፈልገው ቁሳዊ ነገር ረገድ ምክንያታዊ መሆን ይኖርብናል ማለት ነው።—ሉቃስ 12:15

ሥራ ለአንተ ምን ትርጉም አለው?

ታታሪ ሠራተኛ ሁን። ሥራህን የማከናወን ልባዊ ፍላጎት ይኑርህ። ሥራው አሰልቺ ቢሆንብህ ወይም የምትመኘው ዓይነት ባይሆን እንኳ በሥራው የተካንክ ለመሆን ጥረት አድርግ። ታታሪ ሠራተኛ መሆንህ አንድ ነገር በማከናወን የሚገኘውን ደስታ እንድትቀምስ ያስችልሃል፤ በሙያው ስትካን ደግሞ ከሥራው የምታገኘው እርካታ ሊጨምር ይችላል።

ሚዛናዊ መሆን እንዳለብህም አትርሳ። አልፎ አልፎ ለማረፍና ዘና ለማለት ሞክር። በትጋት ከሠሩ በኋላ ዘና ማለት ደስታ ያስገኛል። በተጨማሪም ሥራ ሠርተን የሚያስፈልጉንን ነገሮች ማሟላት መቻላችን ለራሳችን ያለን ግምት ከፍ እንዲል የሚያደርግ ከመሆኑም በላይ የቤተሰባችንን አባላት ጨምሮ የሰዎችን አክብሮት እንድናተርፍ ያደርጋል።—2 ተሰሎንቄ 3:12

“‘ምን እንበላለን?’ ወይም ‘ምን እንጠጣለን?’ አሊያም ‘ምን እንለብሳለን?’ ብላችሁ ፈጽሞ አትጨነቁ። . . . በሰማይ የሚኖረው አባታችሁ እነዚህ ሁሉ እንደሚያስፈልጓችሁ ያውቃል።”ማቴዎስ 6:31, 32