በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ጽኑ አቋማቸውን በድፍረት የጠበቁ ምሥክሮች የናዚን ስደት በድል ተወጡ

ጽኑ አቋማቸውን በድፍረት የጠበቁ ምሥክሮች የናዚን ስደት በድል ተወጡ

ጽኑ አቋማቸውን በድፍረት የጠበቁ ምሥክሮች የናዚን ስደት በድል ተወጡ

“ልጄ ሆይ፣ ጠቢብ ሁን፣ ልቤንም ደስ አሰኘው፣ ለሚሰድበኝ መልስ መስጠት ይቻለኝ ዘንድ።” (ምሳሌ 27:​11) ይህ ፍቅራዊ ማሳሰቢያ የማሰብ ችሎታ ያላቸው ፍጡራን ለእርሱ የታመኑ ሆነው በመገኘት የይሖዋን ልብ ደስ ማሰኘት እንደሚችሉ ያሳያል። (ሶፎንያስ 3:​17) ይሁን እንጂ ከሳሽ የሆነው ሰይጣን የይሖዋ አገልጋዮች ያላቸውን ጽኑ አቋም ለማላላት ቆርጦ ተነስቷል።​—⁠ኢዮብ 1:​10, 11

በተለይ ከሰማይ ወደ ምድር ከተጣለበት ከ20ኛው መቶ ዘመን መግቢያ ጀምሮ ሰይጣን በከፍተኛ ቁጣ በይሖዋ ሕዝቦች ላይ ተነስቷል። (ራእይ 12:​10, 12) ሆኖም እውነተኛ ክርስቲያኖች ‘ምሉዓን በመሆንና ጽኑ እምነት’ በመያዝ ለአምላክ ያላቸውን ጽኑ አቋም ጠብቀዋል። (ቆላስይስ 4:​12 NW ) እስቲ ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት በፊትና ጦርነቱ እየተካሄደ በነበረበት ወቅት እንዲህ ያለውን ጽኑ አቋም በማሳየት ረገድ ግሩም ምሳሌ የሚሆኑንን በጀርመን የሚገኙ የይሖዋ ምሥክሮች ታሪክ በአጭሩ እንመልከት።

ቅንዓት የተሞላበት እንቅስቃሴ በአቋም ጽናት ላይ ፈተና አስከተለ

በ1920ዎቹና በ1930ዎቹ መጀመሪያ ላይ ቢቤልፎርሸር (የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎች) ተብለው ይጠሩ የነበሩት በጀርመን የሚገኙ የይሖዋ ምሥክሮች ብዛት ያላቸውን መጽሐፍ ቅዱሳዊ ጽሑፎች አሰራጭተዋል። እነዚህ ምሥክሮች ከ1919 እስከ 1933 በነበሩት ዓመታት በጀርመን ለሚገኘው ለእያንዳንዱ ቤተሰብ በአማካይ ስምንት መጻሕፍት፣ ቡክሌቶች ወይም መጽሔቶች አበርክተዋል።

ጀርመን፣ በወቅቱ የክርስቶስ ቅቡዓን ተከታዮች በብዛት ይገኙባቸው ከነበሩት አገሮች መካከል አንዷ ስትሆን እንዲያውም በ1933 በዓለም ዙሪያ በተከበረው የጌታ እራት ላይ ከተካፈሉት 83, 941 ሰዎች መካከል ወደ 30 በመቶ የሚጠጉት በጀርመን የሚኖሩ ነበሩ። ብዙም ሳይቆይ እነዚህ የጀርመን ምሥክሮች በአቋም ጽናታቸው ላይ ጭካኔ የተሞላበት ፈተና ይደርስባቸው ጀመር። (ራእይ 12:​17፤ 14:​12) ከሥራ በማፈናቀል፣ ቤታቸውን በማሰስ፣ ከትምህርት ቤት በማባረር የጀመረው ስደት ወደ ድብደባ፣ እሥርና ወኅኒ ተለወጠ። (ሥዕል 1) በመሆኑም ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት በፊት ባሉት ዓመታት በማጎሪያ ካምፖች ውስጥ ከነበሩት ሰዎች መካከል ከ5 እስከ 10 በመቶ የሚሆኑት የይሖዋ ምሥክሮች ነበሩ።

ናዚዎች ምሥክሮቹን ያሳደዱበት ምክንያት

የናዚ መንግሥት በይሖዋ ምሥክሮች ላይ በቁጣ እንዲነሳ ያደረገው ነገር ምንድን ነው? የታሪክ ፕሮፌሰር የሆኑት ኢያን ካርሻ ሂትለር​—⁠1889-1936:- ሁብሪስ በተባለው መጽሐፋቸው ላይ ምሥክሮቹን የስደት ዒላማ ያደረጋቸው “የናዚ መንግሥት የጠየቀውን ሁሉ ለማሟላት” ፈቃደኞች ባለመሆናቸው እንደሆነ ገልጸዋል።

የታሪክ ፕሮፌሰር ሮበርት ፒ ኤሪክሰን እና የአይሁዶች ጥናት ፕሮፌሰር ሱዛና ሄሽል ቢትሬያል​—⁠ጀርመን ቸርችስ ኤንድ ዘ ሆሎከስት በተባለው መጽሐፋቸው ላይ እንዳብራሩት ምሥክሮቹ “በዓመፅ ድርጊት ለመካፈልም ሆነ በጦር ኃይሎች ውስጥ ለመሳተፍ እምቢ ብለዋል። . . . ምሥክሮቹ በፖለቲካ ጉዳዮች ገለልተኛ በመሆን ስለሚያምኑ ለሂትለር ድጋፍም ሆነ ሰላምታ አይሰጡም ነበር።” ይኸው ምንጭ አክሎ ሲናገር ይህ አቋማቸው የናዚን ቁጣ ከማነሳሳቱም በላይ “ብሔራዊ ሶሺያሊዝም እንዲህ ያለውን አቋም በዝምታ ስለማያልፍ” ምሥክሮቹን ለጥቃት ዳረጋቸው።

ዓለም ዓቀፍ ተቃውሞና መጠነ ሰፊ ጥቃት

በዚህ ወቅት በሥራው ግንባር ቀደም ሆኖ ያገለግል የነበረው ጆሴፍ ኤፍ ራዘርፎርድ በልዩ መልእክተኛው አማካኝነት የካቲት 9, 1934 ናዚ እያካሄደ ያለውን ተግባር እንደሚቃወም የሚገልጽ ደብዳቤ ላከ። (ሥዕል 2) ከዚያም የራዘርፎርድን ደብዳቤ ተከትሎ ጥቅምት 7, 1934 በጀርመንና በሌሎች 50 አገሮች ውስጥ የሚገኙ የይሖዋ ምሥክሮች 20, 000 የሚያክሉ የተቃውሞ ደብዳቤዎችንና የቴሌግራም መልእክቶችን ላኩ።

ሆኖም ናዚ ይባስ ብሎ ስደቱን አቀጣጠለው። ሚያዝያ 1, 1935 የምሥክሮቹ ሥራ በመላው አገሪቱ ታገደ። እንዲሁም ነሐሴ 28, 1936 ጌስታፖ ያለ የሌለ ኃይሉን በማስተባበር በይሖዋ ምሥክሮች ላይ የከረረ ጥቃት ሰነዘረ። ይሁን እንጂ ምሥክሮቹ “ፓምፍሌቶችን ማሰራጨታቸውንም ሆነ በእምነታቸው ጽኑ ሆነው መኖራቸውን ቀጥለው ነበር” በማለት ቢትሬያል​—⁠ጀርመን ቸርችስ ኤንድ ዘ ሆሎከስት የተባለው መጽሐፍ ገልጿል።

ለምሳሌ ያህል ታኅሣሥ 12, 1936 ወደ 3, 500 የሚጠጉ ምሥክሮች ይደርስባቸው ስለነበረው በደል የሚገልጹ በአሥር ሺህ የሚቆጠሩ የአቋም መግለጫዎች በጌስታፖዎች አፍንጫ ሥር ሆነው አሰራጭተዋል። ይህንን ዘመቻ አስመልክቶ መጠበቂያ ግንብ እንደሚከተለው በማለት ሪፖርት አድርጓል:- “ዘመቻው ታላቅ ድል ያጎናጸፈና ለጠላት የጎን ውጋት የነበረ ሲሆን ለታማኝ ሠራተኞቹ ይህ ነው የማይባል ደስታ አምጥቶላቸዋል።”​—⁠ሮሜ 9:​17

ስደቱ ቆመ!

ናዚ የይሖዋ ምሥክሮችን ማደኑን በመቀጠል በ1939 ስድስት ሺህ የሚያክሉትን እስር ቤት ያስገባ ሲሆን ሌሎች በሺህ የሚቆጠሩትን ደግሞ ወደ ማጎሪያ ካምፖች ልኳል። (ሥዕል 3) በሁለተኛው የዓለም ጦርነት መገባደጃ ላይ ሁኔታው ምን መልክ ይዞ ነበር? በእስር ላይ የነበሩት 2, 000 የሚያክሉ ምሥክሮች የሞቱ ሲሆን ከእነዚህ ውስጥ 250 የሚያክሉት የሞቱት የሞት ቅጣት ተበይኖባቸው ነው። ዳሩ ግን “የይሖዋ ምሥክሮች በአስቸጋሪ ሁኔታዎች ውስጥም እያሉ እምነታቸውን አጥብቀው ይዘዋል” በማለት ፕሮፌሰር ኤሪክሰንና ሄሻል ጽፈዋል። በመጨረሻ የሂትለር አገዛዝ ሲገረሰስ ከሺህ የሚበልጡ ምሥክሮች በድል አድራጊነት ከካምፖቹ ወጥተዋል።⁠—⁠ሥዕል 4፤ ሥራ 5:​38, 39፤ ሮሜ 8:​35-37

የይሖዋ ሕዝቦች በስደት እንዲጸኑ ያደረጋቸውን ጥንካሬ ያገኙት ከማን ነው? ከማጎሪያ ካምፕ የተረፈው አዶልፍ አርኖልድ እንዲህ በማለት ያብራራል:- “ኃይልህ ሁሉ ተሟጥጦ እንዳለቀብህ ሆኖ በሚሰማህ ጊዜ እንኳን ይሖዋ ያይሃል። በምን ዓይነት ሁኔታ ሥር እንዳለህ ያውቃል። በመሆኑም ያለህበትን ሁኔታ መቋቋም እንድትችልና ታማኝነትህን ጠብቀህ እንድትቆይ የሚያስፈልግህን ጥንካሬ ይሰጥሃል። እጁ አጭር አይደለም።”

የነቢዩ ሶፎንያስ ቃላት በእነዚህ ታማኝ ክርስቲያኖች ላይ ምንኛ ይሠራሉ! ነቢዩ እንዲህ ብሏል:- “አምላክሽ እግዚአብሔር በመካከልሽ ታዳጊ ኃያል ነው፤ በደስታ በአንቺ ደስ ይለዋል።” (ሶፎንያስ 3:​17) በዛሬው ጊዜ የምንገኝ የእውነተኛው አምላክ አምላኪዎች የሆንን ሁላችን የናዚን ስደት በጽናት በመቋቋም የይሖዋን ልብ ደስ ያሰኙትን የእነዚህን ታማኝ ምሥክሮች እምነት የምንኮርጅ እንሁን።​—⁠ፊልጵስዩስ 1:​12-14

[በገጽ 8 ላይ የሚገኝ ሥዕል ምንጭ]

Państwowe Muzeum Oświȩcim-Brzezinka, courtesy of the USHMM Photo Archives