በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

መበለቶችን በመከራቸው መርዳት

መበለቶችን በመከራቸው መርዳት

መበለቶችን በመከራቸው መርዳት

መበለቶችን በተመለከተ በሰፊው ከሚታወቁት ታሪኮች መካከል መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ሩትና ስለ አማቷ ኑኃሚን የሚናገረው ዘገባ ይገኝበታል። ሁለቱም ሴቶች መበለቶች ነበሩ። ይሁን እንጂ ኑኃሚን ባልዋን ብቻ ሳይሆን ሁለት ወንዶች ልጆቿንም አጥታለች፤ አንደኛው የሩት ባል ነበር። በአመዛኙ በወንዶች ላይ በሚመካ በግብርና በሚተዳደር ኅብረተሰብ ውስጥ የሚኖሩ በመሆናቸው ሁኔታቸው በጣም አስከፊ ነበር።​—⁠ሩት 1:​1-5, 20, 21

ሆኖም ኑኃሚን ከእሷ ላለመለየት የቆረጠች ግሩም ወዳጅና አጽናኝ ምራት ሩትን አግኝታለች። ከጊዜ በኋላ ሩት ለኑኃሚን በነበራት ጥልቅ ፍቅር ብቻ ሳይሆን ለአምላክም በነበራት ፍቅር የተነሳ ‘ለኑኃሚን ከሰባት ወንዶች ልጆች ይልቅ የምትሻል’ ሆና ተገኝታለች። (ሩት 4:​15) ኑኃሚን ሞዓባውያን ወደሆኑት ቤተሰቦቿና ወዳጆቿ እንድትመለስ ስትነግራት ሩት እስከዛሬ ድረስ ተመዝግበው ከሚገኙት የታማኝነት መግለጫዎች ሁሉ በጣም ልብ የሚነካ አነጋገር በመናገር መልስ ሰጥታለች:- “ወደምትሄጅበት እሄዳለሁና፣ በምታድሪበትም አድራለሁና . . . ሕዝብሽ ሕዝቤ፣ አምላክሽም አምላኬ ይሆናል፤ በምትሞችበትም ስፍራ እሞታለሁ፣ በዚያም እቀበራለሁ፤ ከሞት በቀር አንቺንና እኔን አንዳች ቢለየን እግዚአብሔር ይህን ያድርግብኝ እንዲሁም ይጨምርብኝ።”​—⁠ሩት 1:​16, 17

ሩት ያሳየችውን ባሕርይ ይሖዋ አምላክ አይቶላታል። ይሖዋ የኑኃሚንንና የሩትን ትንሹን ቤተሰብ የባረከ ሲሆን በመጨረሻም ሩት፣ ቦዔዝ የሚባል እስራኤላዊ አግብታለች። የኢየሱስ ክርስቶስ ቅድመ አያት የሆነውን የሩትንና የቦዔዝን ልጅ እንደ ራሷ ልጅ አድርጋ ተንከባክባ ያሳደገችው ኑኃሚን ነበረች። ይህ ታሪክ ይሖዋ ወደ እሱ የሚጠጉና በእሱ የሚታመኑ መበለቶችን ከፍ አድርጎ እንደሚመለከት የሚያሳይ ማስረጃ ነው። በተጨማሪም መጽሐፍ ቅዱስ ይሖዋ መበለቶችን በመከራቸው ፍቅራዊ በሆነ መንገድ ለሚረዱ ሰዎች ከፍ ያለ ግምት እንዳለው ይነግረናል። ታዲያ በዛሬው ጊዜ በመካከላችን ያሉትን መበለቶች መርዳት የምንችለው እንዴት ነው?​—⁠ሩት 4:​13, 16-22፤ መዝሙር 68:​5

ሳይጫኑ ተግባራዊ እርዳታ መስጠት

አንዲትን መበለት በምትረዱበት ጊዜ ግልጽ መሆንና ስሜቷን ሳትጫኑ ልታደርጉላት የምትፈልጉትን ነገር በቀጥታ መጥቀስ የተሻለ ነው። “የሚያስፈልግሽ ነገር ካለ ንገሪኝ” እንደሚለው የመሳሰሉ ድፍንፍን ያሉ ሐሳቦች አትሰንዝሩ። እንዲህ ብሎ መናገር ለበረደውና ለራበው ሰው ምንም ሳያደርጉ እንዲሁ ብቻ ‘እሳት ሙቅ፣ ጥገብም’ ብሎ ከመናገር ተለይቶ አይታይም። (ያዕቆብ 2:​16) ብዙ ሰዎች አንድ የሚፈልጉት ነገር ሲኖር አፋቸውን አውጥተው እርዳታ ለመጠየቅ አይደፍሩም። ከዚህ ይልቅ ችግራቸውን አምቀው ይይዛሉ። እንደዚህ ያሉ ሰዎች የሚያስፈልጋቸውን ነገር ተገንዝቦ ለመርዳት ማስተዋል መጠቀም ይጠይቃል። በአንጻሩ ደግሞ ሁሉን ነገር እኔ ካላደረግኩት በማለት መፈናፈኛ ማሳጣት በተለይም የመበለቲቱን ሕይወት ለመቆጣጠር መሞከር የስሜት መጎዳት ወይም ግጭት ሊያስከትል ይችላል። በመሆኑም መጽሐፍ ቅዱስ ከሌሎች ጋር ባለን ግንኙነት ሚዛናዊ የመሆንን አስፈላጊነት ጠበቅ አድርጎ ይገልጻል። መጽሐፍ ቅዱስ ለሰዎች ራስ ወዳድነት የሌለበት ትኩረት እንድንሰጥ ቢያበረታታም እንኳ በሰዎች ጉዳይ እንዳንገባ ያሳስበናል።​—⁠ፊልጵስዩስ 2:​4፤ 1 ጴጥሮስ 4:​15

ሩት ለኑኃሚን ይህን የመሰለ ሚዛኑን የጠበቀ አያያዝ አድርጋለች። ሩት ከአማቷ ሳትለይ በታማኝነት ኖራለች፤ ሆኖም አልተጫነቻትም ወይም ነፃነትዋን አልነፈገቻትም። ሩት ለኑኃሚንም ሆነ ለራሷ ምግብ መፈለግን የመሳሰለ የአሳቢነት እርምጃ ወስዳለች። ሆኖም ኑኃሚን የምትሰጣትን መመሪያዎችም ታከብር ነበር።​—⁠ሩት 2:​2, 22, 23፤ 3:​1-6

እርግጥ ነው፣ መደረግ ያለበት ነገር እንደ ሰዉ ፍላጎት ሊለያይ ይችላል። ቀደም ሲል የተጠቀሰችው ሳንድራ “በሐዘኔ ወቅት በጣም የምወድዳቸውና አፍቃሪ የሆኑ ወዳጆቼ ከጎኔ ስለነበሩ የሚያስፈልገኝን ድጋፍ አግኝቻለሁ” ስትል ተናግራለች። በአንጻሩ ደግሞ ቀደም ሲል የተጠቀሰችው ኢሌን ለብቻዋ መሆን ፈልጋ ነበር። ስለዚህ እርዳታ ለመስጠት ፈቃደኛ መሆን ማለት የሌላውን ሰው ፍላጎት በማክበርና በአስፈላጊው ጊዜ እርዳታ ለመስጠት ራስን በማቅረብ መካከል ያለውን ልዩነት ማስተዋል እንዲሁም ሚዛናዊ መሆን ማለት ነው።

የቤተሰብ ድጋፍ

አሳቢና አፍቃሪ የሆነ ቤተሰብ ካለ አንዲት መበለት የገጠማትን ሁኔታ መወጣት እንድትችል ለማበረታታት ብዙ ሊያደርገው የሚችለው ነገር አለ። ምንም እንኳ አንዳንድ የቤተሰቡ አባላት ከሌሎቹ የበለጠ እርዳታ መስጠት ቢችሉም ሁሉም አስተዋጽኦ ማበርከት ይችላሉ። “ማንም ባልቴት ግን ልጆች ወይም የልጅ ልጆች ቢኖሩአት፣ እነርሱ አስቀድመው ለገዛ ቤተ ሰዎቻቸው እግዚአብሔርን መምሰል ያሳዩ ዘንድ፣ ለወላጆቻቸውም ብድራትን ይመልሱላቸው ዘንድ ይማሩ፤ ይህ በእግዚአብሔር ፊት መልካምና የተወደደ ነውና።”​—⁠1 ጢሞቴዎስ 5:​4

በአብዛኛዎቹ ሁኔታዎች የገንዘብ እርዳታ ወይም ‘ብድራት መመለስ’ አያስፈልግ ይሆናል። አንዳንድ መበለቶች የሚያስፈልጋቸውን ነገር ለማግኘት በቂ ገንዘብ ያላቸው ሲሆን ሌሎች ደግሞ መንግሥት የገንዘብ ድጎማ በሚያደርግባቸው በአንዳንድ አገሮች ከዝግጅቱ ተጠቃሚ ለመሆን መሥፈርቱን ያሟሉ ናቸው። ሆኖም የገንዘብ ችግር ያለባቸውን መበለቶች የቤተሰቡ አባላት ሊረዷቸው ይገባል። ቅዱሳን ጽሑፎች አንዲት መበለት ሊረዳት የሚችል የቅርብ ዘመድ ከሌላት ወይም ዘመዶቿ የመርዳት አቅም ከሌላቸው የእምነት ጓደኞቿ እርዳታ እንዲያደርጉላት ማበረታቻ ይሰጣሉ:- “ንጹሕ የሆነ ነውርም የሌለበት አምልኮ በእግዚአብሔር አብ ዘንድ ይህ ነው፤ ወላጆች የሌላቸውን ልጆች ባልቴቶችንም በመከራቸው መጠየቅ።”​—⁠ያዕቆብ 1:​27

እነዚህን የመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓቶች በተግባር የሚያውሉ ሰዎች በእርግጥ ‘ባልቴቶችን ያከብራሉ።’ (1 ጢሞቴዎስ 5:​3) አንድን ሰው ማክበር በሌላ አባባል ለሰውየው ልዩ ግምት መስጠት ማለት ነው። በአክብሮት የተያዙ ሰዎች ተፈላጊ እንደሆኑ፣ እንደሚወደዱና እንደሚከበሩ ይሰማቸዋል። ሌሎች እነሱን የሚረዷቸው ግዴታ ስለሆነባቸው ብቻ ነው የሚል ስሜት አያድርባቸውም። ምንም እንኳ ሩት ለተወሰነ ጊዜ መበለት የነበረች ቢሆንም የኑኃሚን ሥጋዊና ስሜታዊ ፍላጎቶች መሟላታቸውን በደስታና ፍቅራዊ በሆነ መንገድ በመከታተል ከልብ አክብራታለች። እንዲያውም ሩት ያሳየችው ዝንባሌ በአጭር ጊዜ ውስጥ መልካም ስም አትርፎላታል። ከዚህም የተነሳ በኋላ ባልዋ የሆነው ሰው “በአገሬ ያሉ ሕዝብ ሁሉ ምግባረ መልካም ሴት እንደ ሆንሽ ያውቃሉ” ብሏታል። (ሩት 3:​11) ከዚህ በተጨማሪ ኑኃሚን ለአምላክ የነበራት ፍቅር፣ ለተደረገላት ነገር አመስጋኝ መሆንዋ እና ሩት ለዋለችላት ውለታ የነበራት ጥልቅ አድናቆት ሩት እሷን በደስታ ለመርዳት እንድትነሳሳ አድርጓታል። ኑኃሚን በዛሬው ጊዜ ላሉ መበለቶች ምንኛ ግሩም ምሳሌ ነች!

ወደ አምላክ ተጠጉ

እርግጥ ነው፣ የቤተሰብ አባላትና ወዳጆች የትዳር ጓደኛ ሞት የሚፈጥረውን ክፍተት መድፈን አይችሉም። ስለሆነም ሐዘን ላይ የወደቀችው መበለት በተለይ ‘የርኅራኄ አባት የመጽናናትም ሁሉ አምላክ ወደሆነው በመከራችን ሁሉ ወደሚያጽናናን’ አምላክ መጠጋቷ በጣም ወሳኝ ነው። (2 ቆሮንቶስ 1:​3, 4) ኢየሱስ በተወለደበት ጊዜ የ84 ዓመት ሴት የነበረችውን ለአምላክ ያደረች መበለት የሐናን ምሳሌ ተመልከት።

ሐና ባልዋ ገና በተጋቡ በሰባት ዓመታቸው ሲሞት ማጽናኛ ለማግኘት ወደ ይሖዋ ዞረች። “በጾምና በጸሎትም ሌሊትና ቀን እያገለገለች ከመቅደስ አትለይም ነበር።” (ሉቃስ 2:​36, 37) ይሖዋ፣ ሐና ላሳየችው ለአምላክ የማደር ባሕርይ ምላሽ ሰጥቷልን? አዎን! ሲያድግ ለዓለም ቤዛ የሚሆነውን ሕፃን የማየት አጋጣሚ እንድታገኝ በማድረግ ይሖዋ ለእሷ ያለውን ፍቅር እጅግ ልዩ በሆነ መንገድ አሳይቷል። ይህ ሐናን ምንኛ አስደስቷትና አጽናንቷት ይሆን! የመዝሙር 37:​4ን ትክክለኛነት በራሷ ሕይወት እንዳየች ግልጽ ነው:- “በእግዚአብሔር ደስ ይበልህ፣ የልብህንም መሻት ይሰጥሃል።”

አምላክ በክርስቲያን ባልንጀሮቻችን በኩል ድጋፍ ይሰጣል

ኢሌን እንዲህ ትላለች:- “ከዴቪድ ሞት በኋላ ጎኔን በስለት የተወጋሁ ያህል ለረጅም ጊዜ ያመኝ ነበር። የምግብ አለመፈጨት እንደሆነ ይሰማኝ ነበር። አንድ ቀን በጣም ሲያመኝ ሐኪም ቤት ብሄድ ሳይሻል አይቀርም ብዬ አሰብኩ። አስተዋይ የሆነች አንዲት መንፈሳዊ እህቴና ጓደኛዬ መንስዔው ያደረብኝ ሐዘን ሊሆን እንደሚችል በመጠቆም ይሖዋን እርዳታና ማጽናኛ እንድጠይቀው አበረታታችኝ። ምክሯን ተቀብዬ ወዲያው ይሖዋ ሐዘኔን መቋቋም እንድችል እንዲያበረታኝ በመጠየቅ በውስጤ ልባዊ ጸሎት አቀረብኩ። እሱም ብርታት ሰጠኝ!” ኢሌን ጥሩ ስሜት ይሰማት ጀመር፤ ከዚያ ብዙም ሳይቆይ ያደረባት ሕመም ተወገደ።

በተለይ የጉባኤ ሽማግሌዎች በሐዘን ላይ ላሉ መበለቶች ደግነት በተሞላበት ሁኔታ ወዳጅነት ሊያሳዩዋቸው ይችላሉ። ሽማግሌዎች ቋሚ መንፈሳዊ ድጋፍ እንዲሁም ጥበብና ማስተዋል በተሞላበት መንገድ ማጽናኛ በመስጠት መበለቶች መከራ ቢኖርባቸውም እንኳ ይሖዋን የሙጥኝ ብለው እንዲኖሩ ሊረዷቸው ይችላሉ። አስፈላጊ ሲሆን ደግሞ ቁሳዊ እርዳታ የሚያገኙበትን ዝግጅት በማመቻቸት መርዳት ይችላሉ። እንዲህ ያሉ ሩኅሩኅና አስተዋይ ሽማግሌዎች በእርግጥ “ከነፋስ እንደ መሸሸጊያ” ይሆናሉ።​—⁠ኢሳይያስ 32:​2፤ ሥራ 6:​1-3

አዲሱ የምድር ንጉሥ የሚያመጣው ዘላቂ ማጽናኛ

ከሁለት ሺህ ዓመት ገደማ በፊት፣ በዕድሜ የገፋችው ሐና በማየቷ ደስ የተሰኘችበት ሕፃን አሁን የአምላክ ሰማያዊ መንግሥት መሲሐዊ ንጉሥ ሆኗል። በቅርቡ ይህ መስተዳድር ሞትን ጨምሮ ለሐዘን ምክንያት የሆኑትን ነገሮች በሙሉ ያስወግዳል። በዚህ ረገድ ራእይ 21:​3, 4 እንዲህ ይላል:- “እነሆ፣ የእግዚአብሔር ድንኳን በሰዎች መካከል ነው . . . እንባዎችንም ሁሉ ከዓይኖቻቸው ያብሳል፣ ሞትም ከእንግዲህ ወዲህ አይሆንም፣ ኀዘንም ቢሆን ወይም ጩኸት ወይም ሥቃይ ከእንግዲህ ወዲህ አይሆንም፣ የቀደመው ሥርዓት አልፎአልና ብሎ ሲናገር ሰማሁ።” ይህ ጥቅስ ስለ ‘ሰዎች’ እንደሚናገር አስተዋላችሁ? አዎን፣ ሰዎች ከሞት እንዲሁም ሞት ከሚያስከትለው ኀዘንና ጩኸት ሁሉ ይገላገላሉ።

ሆኖም ሌላም ምሥራች አለ! መጽሐፍ ቅዱስ የሙታን ትንሣኤም እንደሚኖር ተስፋ ይሰጣል። ‘በመቃብር ያሉት ሁሉ የኢየሱስን ድምፅ ሰምተው የሚወጡበት ሰዓት ይመጣል።’ (ዮሐንስ 5:​28, 29) ኢየሱስ ከሞት እንዳስነሣው እንደ አልዓዛር ሁሉ እነሱም መንፈሳዊ ፍጡር ሆነው ሳይሆን ሥጋ ለብሰው ይነሳሉ። (ዮሐንስ 11:​43, 44) ትንሣኤ ካገኙ በኋላ ‘መልካም የሚያደርጉ’ ሰዎች ሰብዓዊ ፍጽምና የሚላበሱ ሲሆን ይሖዋ ‘እጁን ከፍቶ ሕይወት ላለው ሁሉ መልካምን ሲያጠግብ’ በግለሰብ ደረጃ አባታዊ እንክብካቤውን ያያሉ።​—⁠መዝሙር 145:​16

የሚወዱትን ሰው በሞት ያጡና እርግጠኛ በሆነው በትንሣኤ ተስፋ ላይ እምነት የሚያሳድሩ ሰዎች ከፍተኛ መጽናኛ ያገኙበታል። (1 ተሰሎንቄ 4:​13) ስለዚህ መበለት ከሆንሽ በየዕለቱ የሚያጋጥሙሽን የተለያዩ ጫናዎች ለመወጣት የሚያስችልሽን ማጽናኛና እርዳታ ለማግኘት ‘ሳታቋርጪ ጸልዪ።’ (1 ተሰሎንቄ 5:​17፤ 1 ጴጥሮስ 5:​7) እንዲሁም አምላክ ከተናገራቸው ነገሮች ማጽናኛ ለማግኘት የአምላክን ቃል በየዕለቱ ለማንበብ ጊዜ መድቢ። እነዚህን ነጥቦች ሥራ ላይ ካዋልሽ መበለት በመሆንሽ በርካታ ችግሮችና ፈተናዎች ቢገጥሙሽም እንኳ ይሖዋ የአእምሮ ሰላም እንዲኖርሽ በእርግጥ ሊረዳሽ እንደሚችል መገንዘብ ትችያለሽ።

[በገጽ 5 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

አንድን ሰው ለመርዳት ፈቃደኛ መሆን ማለት የግለሰቡን ፍላጎት በማክበርና አስፈላጊ በሚሆንበት ጊዜ ራስን በማቅረብ ረገድ ሚዛናዊ መሆን ማለት ነው

[በገጽ 7 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

አምላክ አረጋዊቷን መበለት ሐናን ባርኳታል