በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

‘ዘመኑን እየዋጀህ’ ነውን?

‘ዘመኑን እየዋጀህ’ ነውን?

‘ዘመኑን እየዋጀህ ’ ነውን?

ሐዋርያው ጳውሎስ በመጀመሪያው መቶ ዘመን በኤፌሶን የነበሩትን ክርስቲያኖች እንዲህ ሲል መክሯቸዋል:- “እንግዲህ እንደ ጥበበኞች እንጂ ጥበብ እንደሌላቸው ሳይሆን እንዴት እንድትመላለሱ በጥንቃቄ ተጠበቁ፤ ቀኖቹ ክፉዎች ናቸውና ዘመኑን ዋጁ።” (ኤፌሶን 5:​15, 16) ይህ ምክር አስፈላጊ የነበረው ለምንድን ነው? ይህንን ጥያቄ ለመመለስ በዚያች ጥንታዊ ከተማ ይኖሩ የነበሩት ክርስቲያኖች ስለተጋፈጧቸው ፈተናዎች በቂ ግንዛቤ ማግኘቱ አስፈላጊ ይሆናል።

ኤፌሶን በከፍተኛ ብልጽግናዋ፣ ጸያፍ በሆነው ሥነ ምግባሯ፣ በተስፋፉት የወንጀል ድርጊቶቿና በተለያዩ አጋንንታዊ ተግ​ባሮቿ በሰፊው የምትታወቅ ከተማ ነበረች። ከዚህም በተጨማሪ እዚያ የነበሩት ክርስቲያኖች ጊዜን አስመልክቶ ከሰፈነው ፍልስፍና ጋር መታገል ነበረባቸው። በኤፌሶን የሚኖሩት ክርስቲያን ያልሆኑ ግሪካውያን ጊዜ በአንድ አቅጣጫ ይጓዛል ብለው አያምኑም ነበር። የግሪክ ፍልስፍና ሕይወት ማቆሚያ የሌለው የዑደት ድግግሞሽ እንደሆነ አስተምሯቸው ነበር። ጊዜውን በአንድ ዓይነት የሕይወት ዑደት ውስጥ ያባከነ ሰው ያንኑ ጊዜውን በሌላ ዑደት መልሶ ሊያገኘው ይችላል። እንዲህ ያለው አስተሳሰብ የኤፌሶን ክርስቲያኖች ይሖዋ መለኮታዊ ፍርድ የሚያስፈጽምበትን ጊዜ ጨምሮ ለነገሮች ያወጣውን የጊዜ ሠሌዳ በተመለከተ የግድየለሽነት ዝንባሌ እንዲያዳብሩ ሊያደርጋቸው ይችል ነበር። ስለዚህ ጳውሎስ “ዘመኑን ዋጁ” የሚል ምክር መስጠቱ ተገቢ ነበር።

እዚህ ላይ ጳውሎስ እንዲሁ ስለ ጊዜ መናገሩ አልነበረም። የተጠቀመበት የግሪክኛ ቃል ለአንድ ለተለየ ዓላማ አመቺ የሆነን ወይም የተወሰነን ጊዜ ያመለክታል። ጳውሎስ የመጀመሪያው መቶ ዘመን ክርስቲያኖች መለኮታዊ ምህረት ማግኘትና ከተዘረጋላቸው የመዳን ዝግጅት መጠቀም የሚችሉበት ጊዜ ከማለቁ በፊት ያገኙትን ምቹ ጊዜ ወይም የሞገስ ዘመን በጥበብ እንዲጠቀሙበት መምከሩ ነበር።​—⁠ሮሜ 13:​11-13፤ 1 ተሰሎንቄ 5:​6-11

እኛም በተመሳሳይ ምቹ በሆነ ጊዜ ውስጥ እንገኛለን። ክርስቲያኖች ዓለም የሚያቀርባቸውን ጊዜያዊ ደስታ የሚያስገኙ ነገሮች በመከታተል ይህንን ፈጽሞ የማይደገም የሞገስ ዘመን ከማባከን ይልቅ ጊዜያቸውን ‘ለአምላክ ማደራቸውን የሚያሳዩ ሥራዎች’ ለመሥራትና ፈጣሪ ከሆነው ከይሖዋ አምላክ ጋር ያላቸውን ዝምድና ለማጠንከር ከተጠቀሙበት ጥበበኞች ናቸው።​—2 ጴጥሮስ 3:​11፤ መዝሙር 73:​28፤ ፊልጵስዩስ 1:​9, 10