በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

መጽሐፍ ቅዱስ ማጥናት ይጠቅምሃልን?

መጽሐፍ ቅዱስ ማጥናት ይጠቅምሃልን?

መጽሐፍ ቅዱስ ማጥናት ይጠቅምሃልን?

“ቄስ በሌለበት የማይነበብ።” ይህ ማስጠንቀቂያ በካቶሊኮች እጅ በሚገኙ በአንዳንድ መጽሐፍ ቅዱሶች የመጀመሪያ ገጽ ላይ ሰፍሮ ይገኛል። “እኛ ካቶሊኮች መጽሐፍ ቅዱስን የማንበብ ልማድ አልነበረንም፤ አሁን ግን ሁኔታው እየተለወጠ ነው” በማለት ሎስ አንጀለስ በሚገኘው የካቶሊክ የመጽሐፍ ቅዱስ ተቋም ውስጥ የሚሠሩት ኬ መርዲ ተናግረዋል። ካቶሊኮች ቅዱሳን ጽሑፎች ሕይወታቸውን እንዴት ሊነኩት እንደሚችሉ አንዴ ከተገነዘቡ በኋላ “ለመጽሐፍ ቅዱስ የራሳቸው የሆነ ጉጉትና ጥማት ያዳብራሉ” ሲሉ እኚሁ ሴት አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።

ይህንን ለውጥ በተመለከተ ዩ ኤስ ካቶሊክ የተባለው መጽሔት አንድ የሃይማኖታዊ ትምህርት አስተባባሪ የሆኑ ሰው የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርቶች በሚሰጡባቸው ክፍሎች ውስጥ ገብተው የተማሩ ካቶሊኮችን አስመልክተው የተናገሩትን በመጥቀስ እንዲህ ብሏል:- “ካቶሊኮች ብዙ ነገር እንደቀረባቸውና መጽሐፍ ቅዱስ መንፈሳዊ ሃብት እንዳዘለ ሆኖ ይሰማቸዋል። በመሆኑም እንዳጡት ሆኖ የሚሰማቸውን ይህንን መንፈሳዊ ሃብት በተወሰነ መጠን ለማግኘት ይፈልጋሉ።”

ያም ሆነ ይህ አንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ሊያገኘው የሚችለው “መንፈሳዊ ሃብት” ምንድን ነው? የሚከተሉትን ጥያቄዎች ተመልከት:- በየቀኑ የሚያጋጥሙህን የኑሮ ጭንቀቶች መቋቋም የምትችልበትን መንገድ ማወቅ ትፈልጋለህ? በቤተሰብህ መካከል ሰላም እንዲሰፍን ማድረግ የምትችለው እንዴት ነው? ጥላቻና ለኅብረተሰብ ጠንቅ የሆነ ጠባይ በብዛት የሚታየው ለምንድን ነው? ዛሬ ባሉት ወጣቶች ዘንድ ለተስፋፋው ዓመፅ መንስኤው ምንድን ነው? የአምላክ ቃል መጽሐፍ ቅዱስ ለእነዚህና ለሌሎች አሳሳቢ ጥያቄዎች አስተማማኝ መልስ ይሰጣል። በእርግጥም እነዚህ መልሶች ለካቶሊኮች ወይም ለፕሮቴስታንቶች ብቻ ሳይሆን ለቡድሃ፣ ለሂንዱና ለሺንቶ እምነት ተከታዮች፣ ለሙስሊሞች እንዲሁም አምላክ የለም ወይም ስለ እርሱ ማወቅ አይቻልም ብለው ለሚያምኑ ሁሉ “መንፈሳዊ ሃብት” ሊሆኑ ይችላሉ። ሁኔታው ልክ መዝሙራዊው እንዳስቀመጠው ነው። ‘ሕጉ ለእግሩ መብራት፣ ለመንገዱም ብርሃን ሆኖለት ነበር።’ ለአንተም እንዲሁ ሊሆንልህ ይችላል።​—⁠መዝሙር 119:​105