መንፈስን እንደሚያድስ ጠል የሆኑ ወጣቶች
“ወደ እኔ ኑ፣ እኔም አሳርፋችኋለሁ”
መንፈስን እንደሚያድስ ጠል የሆኑ ወጣቶች
ኢየሱስ ክርስቶስ “ወደ እኔ ኑ፣ እኔም አሳርፋችኋለሁ” የሚለውን ግብዣ ያቀረበው ለወጣት ተከታዮቹም ጭምር እንደሆነ ምንም ጥርጥር የለውም። (ማቴዎስ 11:28) ሰዎች ትናንሽ ልጆቻቸውን ወደ ኢየሱስ ባመጡ ጊዜ ደቀ መዛሙርቱ ሊያከላክሏቸው ሞክረው ነበር። ኢየሱስ ግን “ሕፃናትን ወደ እኔ ይመጡ ዘንድ ተዉ አትከልክሉአቸው” አላቸው። እንዲያውም ኢየሱስ “አቀፋቸው እጁንም ጭኖ ባረካቸው።” (ማርቆስ 10:14-16) ኢየሱስ ልጆችን ውድ አድርጎ ይመለከታቸው እንደነበር ምንም አያጠያይቅም።
መጽሐፍ ቅዱስ አምላክን በማገልገል ረገድ ግሩም ምሳሌ ስለተዉልን ትናንሽ ልጆችና ታማኝ ስለሆኑ ወጣት ወንዶችና ሴቶች ይናገራል። የመዝሙር መጽሐፍ መንፈስን እንደሚያድስ ጠል ስለሆኑ “ወጣቶች” እንዲሁም የይሖዋን ስም ስለሚያወድሱ “ወጣት ወንዶች” እና “ደናግል” ይናገራል።—መዝሙር 110:3 NW ፤ 148:12, 13 አ.መ.ት
ለወጣቶች እድገት አመቺ የሆነ ቦታ
ጠል ከብልጽግናና ከበረከት ጋር የተያያዘ በመሆኑ ወጣቶች ከጠል ጋር መመሳሰላቸው ተገቢ ነው። (ዘፍጥረት 27:28) ጠል ደስ የሚያሰኝና መንፈስን የሚያድስ ነገር ነው። ክርስቶስ እየገዛ ባለበት በአሁኑ ወቅት ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ክርስቲያን ወጣቶች በፈቃደኝነትና በደስታ ራሳቸውን አቅርበዋል። ብዙ ወጣት ወንዶችና ሴቶች ይሖዋን በደስታ በማገልገልና ለእምነት ባልደረቦቻቸው ድጋፍ በመሆን መንፈስን እንደሚያድስ ጠል ሆነዋል።—መዝሙር 71:17
ክርስቲያን ወጣቶች የሌሎችን መንፈስ የሚያድሱ ከመሆናቸውም በተጨማሪ እነርሱ ራሳቸውም በአገልግሎታቸው እርካታ ያገኛሉ። የአምላክ ድርጅት እድገት ለማድረግ የሚያስችሏቸው ምቹ ሁኔታዎች ፈጥሮላቸዋል። ወጣት ወንዶችና ሴቶች ከፍተኛ ከሆኑት የሥነ ምግባር መሥፈርቶች ጋር ተስማምተው ስለሚኖሩ ከአምላክ ጋር የቀረበ ዝምድና አላቸው። (መዝሙር 119:9) በጉባኤ ውስጥም ጤናማ በሆኑ እንቅስቃሴዎች የመካፈልና ጥሩ ወዳጆች የማፍራት አጋጣሚ አላቸው። ይህም ዓላማ ያለውና እርካታ የሚያስገኝ ሕይወት ለመምራት ያስችላቸዋል።
‘ጤና እና ልምላሜ’
ክርስቲያን ወጣቶች ራሳቸው እንደ “ጠል” እንደሆኑ ይሰማቸዋልን? በጉባኤ ውስጥ በሚደረጉ እንቅስቃሴዎች በንቃት የምትሳተፈውንና በየወሩ በአገልግሎት ከ70 ሰዓት በላይ የምታሳልፈውን ታንየን እንደ ምሳሌ እንውሰድ። እንደዚህ በማድረጓ ምን ይሰማታል? እንዲህ ትላለች:- “መንፈሴ ይታደሳል እንዲሁም ይነቃቃል። ይሖዋና ምድራዊ ድርጅቱ ሕይወቴ ‘ጤናማ እንዲሆንና እንዲለመልም’ ረድተውኛል።”—ምሳሌ 3:8 አ.መ.ት
አሪኤል የተባለችው ሌላዋ ወጣት የሙሉ ጊዜ አገልጋይ በጉባኤ ውስጥ ለምታገኘው መንፈሳዊ ምግብ አመስጋኝ ናት። እንዲህ ብላለች:- “ወደ ክርስቲያናዊ ስብሰባዎች፣ የአውራጃ ስብሰባዎችና ያዕቆብ 2:23
የወረዳ ስብሰባዎች ስሄድ ከይሖዋ መንፈሳዊ ማዕድ ስለምመገብ በመንፈሳዊ እታደሳለሁ። በዓለም ዙሪያ አብረውኝ የሚሠሩ የሥራ ባልደረቦች እንዳሉኝ ማወቄም ያበረታታኛል።” ከሁሉ የላቀ እረፍት ከየት እንደሚገኝ ስትናገርም “ይህ ሥርዓት በሰዎች ላይ የሚያሳድረውን መጥፎ ተጽዕኖ ስሰማ ወይም ስመለከት ከይሖዋ ጋር ባለኝ ወዳጅነት የበለጠ እደሰታለሁ” ብላለች።—የ20 ዓመቱ አቢሻይ የሙሉ ጊዜ ወንጌላዊና የጉባኤ አገልጋይ ነው። እንዲህ ሲል ስሜቱን ይገልጻል:- “ዛሬ በወጣቶች ፊት የተደቀኑትን በርካታ ችግሮች እንዴት መወጣት እንደምችል ስለማውቅ እረፍት እንዳገኘሁ ሆኖ ይሰማኛል። የመጽሐፍ ቅዱስ እውነት ይሖዋን በሙሉ ነፍሴ ማገልገል እችል ዘንድ ምን ማድረግ እንዳለብኝ እንዳስብ አድርጎኛል።”
አንትዋን በአሥራዎቹ ዕድሜው መጀመሪያ ላይ በነበረበት ወቅት ግልፍተኛ ነበር። አንድ ጊዜ አብሮት የሚማረውን ልጅ በወንበር መቶታል፤ በሌላ ጊዜ ደግሞ ሌላውን ልጅ በእርሳስ ወጋው። በግልጽ ለማየት እንደሚቻለው አንትዋን እረፍት የሚሰጥ ልጅ አልነበረም! ሆኖም ከመጽሐፍ ቅዱስ ያገኘው ትምህርት ባሕርዩን ለወጠው። አሁን 19 ዓመት የሆነው አንትዋን በጉባኤ ውስጥ አገልጋይ ከመሆኑም በላይ በሙሉ ጊዜ አገልግሎት በመካፈል ላይ ነው። እንዲህ ይላል:- “ይሖዋ ስለ እሱ እንዳውቅ ስለፈቀደና ራሴን መቆጣጠር እንዳለብኝ ተገንዝቤ ባሕርዬን እንድቀይር ስለረዳኝ አመሰግነዋለሁ። እንደዚህ በማድረጌ ከብዙ ችግሮች ማምለጥ ችያለሁ።”
ወጣት ክርስቲያኖች የሚያሳዩትን መንፈስን የሚያድስ ጠባይ ሌሎች ሰዎች ማስተዋላቸው አይቀርም። ማቴኦ በኢጣሊያ የሚኖር ወጣት የይሖዋ ምሥክር ነው። መምህሩ በክፍል ውስጥ ካሉት ተማሪዎች መካከል ጸያፍ ቃላት የሚናገር ማንኛውም ልጅ አነስተኛ የሆነ የገንዘብ ቅጣት እንዲከፍል ትወስናለች። ከጥቂት ጊዜ በኋላ ልጆቹ “መጥፎ ቃላትን ሙሉ በሙሉ ማስወገድ የማይቻል ነገር ስለሆነ” ሕጉ ይቀየርልን ብለው ይጠይቃሉ። “ሆኖም መምህርዋ ይህ የማይቻል ነገር አለመሆኑን ከተናገረች በኋላ እኔን እንደ ምሳሌ አድርጋ ጠቀሰችኝ። ከዚያም መጥፎ ቃላት ስለማልጠቀም በክፍሉ ተማሪዎች ፊት አመሰገነችኝ” ይላል ማቴኦ።
በታይላንድ ረባሽ ተማሪዎች ባሉበት አንድ ክፍል ውስጥ አስተማሪዋ የ11 ዓመቱን ራትያን በክፍሉ ተማሪዎች ፊት እንዲቆም ካደረገች በኋላ ስለ መልካም ፀባዩ እንዲህ በማለት አመሰገነችው:- “ለምን ሁላችሁም የሱን ምሳሌ አትከተሉም? በትምህርቱ ጎበዝ ከመሆኑም በላይ ሥርዓታማ ነው።” ቀጥላም ለተማሪዎቹ እንዲህ አለቻቸው:- “ባሕርያችሁን ለማሻሻል ምናልባት እንደ ራትያ የይሖዋ ምሥክር መሆን ሳያስፈልጋችሁ አይቀርም።”
በሺዎች የሚቆጠሩ ክርስቲያን ወጣቶች ስለ ይሖዋ ያላቸው እውቀት እያደገ ሲሄድና ፈቃዱን ሲያደርጉ ማየት የሚያስደስት ነው። እነዚህ መልካም ወጣቶች ከዕድሜያቸው በላይ ጠቢባን እንደሆኑ እያሳዩ ነው። አምላክ የአሁኑ ሕይወታቸው የተሳካ እንዲሆን ከመርዳትም አልፎ በመጪው አዲስ ሥርዓት ውስጥ አስደሳች ሕይወት ይሰጣቸዋል። (1 ጢሞቴዎስ 4:8) በመንፈሳዊ ሁኔታ እንደ በረሃ በሆነውና እርካታ በሌላቸውና ተስፋ በቆረጡ ወጣቶች በተሞላው በዚህ ሥርዓት ውስጥ እንደዚህ ዓይነት ወጣቶች መኖራቸው መንፈስን የሚያድስ ነው!