በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ብቃት ያለው አመራር ለማግኘት የሚደረገው ጥረት

ብቃት ያለው አመራር ለማግኘት የሚደረገው ጥረት

ብቃት ያለው አመራር ለማግኘት የሚደረገው ጥረት

“መንበሩን ልቀቅና ውረድ፤ የአንተ ነገር በቅቶናል። በፈጣሪ ስም እለምንሃለሁ፣ ሂድልን!”—የብሪታንያ ፓርላማ አባል የነበሩት ሊየፖልድ አሜሪ የኦሊቨር ክሮምዌልን አባባል ጠቅሰው የተናገሩት

ሁለተኛው የዓለም ጦርነት ከተጀመረ ስምንት ወራት ያስቆጠረ ሲሆን በዚህ ጊዜ ውስጥ ከፍተኛ ውድመት አድርሷል። አዝማሚያው ሲታይ ብሪታንያና ተባባሪዎቿ በጦርነቱ ድል ማድረግ የሚችሉ አይመስልም። ሊየፖልድ አሜሪና በሥልጣን ላይ የሚገኙ ሌሎችም የአመራር ለውጥ እንደሚያስፈልግ ተሰምቷቸዋል። በዚህም ምክንያት ግንቦት 7, 1940 ሚስተር አሜሪ ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ኔቭል ቼምበርሊን በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ውስጥ ከላይ ያሉትን ቃላት ተናገሩ። ከሦስት ቀናት በኋላ ሚስተር ቼምበርሊን ሥልጣናቸውን የለቀቁ ሲሆን ዊንስተን ቸርችል በእርሳቸው እግር ተተኩ።

ከሰው ልጅ መሠረታዊ ፍላጎቶች አንዱ ጥሩ አመራር ማግኘት ቢሆንም ብቃቱን የሚያሟሉት ግን ሁሉም መሪዎች አይደሉም። በቤተሰብ ክልል ውስጥም እንኳ አንድ አባት ሚስቱና ልጆቹ ደስተኞች እንዲሆኑ ጥሩ መሪ መሆን አለበት። ከዚህ አንጻር የአንድ አገር ወይም የዓለም መሪ መሆን ምን ያህል ከፍተኛ ብቃት እንደሚጠይቅ መገመት ይቻላል! በመሆኑም ብቃት ያላቸው መሪዎች ማግኘት በጣም አስቸጋሪ መሆኑ ምንም አያስገርምም።

በዚህም ምክንያት በሺዎች ለሚቆጠሩ ዓመታትና ቁጥር ሥፍር ለሌላቸው ጊዜያት ነገሥታት ዘውድ ሲጭኑ፣ አብዮታዊ እንቅስቃሴና የመንግሥት ግልበጣ ሲካሄድ፣ መሪዎች ሲሾሙ፣ ምርጫ ሲደረግ፣ በሥልጣን ላይ ያሉ ሰዎች ሲገደሉ እንዲሁም የአገዛዝ ለውጥ ሲደረግ ቆይቷል። ነገሥታት፣ ጠቅላይ ሚኒስትሮች፣ ልዑላን፣ ፕሬዚዳንቶች፣ ዋና ጸሐፊዎች እንዲሁም አምባገነን መሪዎች የሥልጣን እርካብ ላይ ሲፈናጠጡና ሲወርዱ ኖረዋል። ኃያል የሚባሉት መሪዎችም እንኳ ባልተጠበቁ ለውጦች ሳቢያ ከሥልጣናቸው ተፈናቅለዋል። (በገጽ 5 ላይ የሚገኘውን “በድንገት ከሥልጣን መውረድ” የሚለውን ሣጥን ተመልከት።) ያም ሆኖ ብቃት ያለውና ዘላቂ የሆነ አመራር ማግኘት አዳጋች ሆኗል።

“ያለውን ተቀብለን መኖር” ወይስ ሌላ አማራጭ አለ?

በመሆኑም ብቃት ያለው መሪ የማግኘቱ ጉዳይ ለብዙዎች ተስፋ አስቆራጭ መሆኑ አያስገርምም። በአንዳንድ አገሮች ሕዝቡ በተለይ በምርጫ ወቅት የግዴለሽነትና የተስፋ መቁረጥ ስሜት ይታይበታል። በአፍሪካ የሚገኝ ጄፍ ሂል የተባለ አንድ ጋዜጠኛ እንዲህ ብሏል፦ “ሰዎች በሥቃይ የተሞላ ሕይወታቸውን ለመለወጥ ምንም ማድረግ እንደማይችሉ ሲሰማቸው ቸልተኛ ይሆናሉ ወይም [በምርጫ ከመሳተፍ] ይታቀባሉ። . . . በአፍሪካ ውስጥ ሕዝቡ በምርጫ የማይካፈለው ባለው አገዛዝ ስለረካ ብቻ ላይሆን ይችላል። አብዛኛውን ጊዜ ችግራቸውን የሚረዳላቸው ወገን እንደሌለ የሚሰማቸው ሰዎች እርዳታ እንደሚፈልጉ የሚገልጹበት መንገድ ነው።” በተመሳሳይም በዩናይትድ ስቴትስ የሚኖር አንድ የጋዜጣ ዘጋቢ እየቀረበ ስላለ የምርጫ ወቅት ሲጽፍ “ሙሉ በሙሉ ብቁ የሆነ እጩ ቢወዳደር ደስ ይለኝ ነበር” ብሏል። አክሎም “እንደዚህ ያለ ተወዳዳሪ ግን የለም። ከአሁን በፊትም ኖሮ አያውቅም። ያለውን ተቀብለን መኖር አለብን” በማለት ተናግሯል።

በእርግጥ፣ ፍጹም ያልሆኑ መሪዎችን አገዛዝ ‘ተቀብለን ከመኖር’ የተሻለ ምርጫ የለንም ማለት ነው? ሰብዓዊ መሪዎች የዜጎቻቸውን ፍላጎቶች ማሟላት አለመቻላቸው ብቃት ያለው አመራር ፈጽሞ ማግኘት እንደማይቻል የሚጠቁም ነው? አይደለም። ከሁሉ የላቀ ብቃት ያለው አመራር አለ። የሚቀጥለው ርዕስ ለሰው ዘር ብቃት ያለው መሪ ማን እንደሆነና የዚህ መሪ አገዛዝ አንተን ጨምሮ በሚሊዮን የሚቆጠሩ የተለያዩ ሰዎችን የሚጠቅመው እንዴት እንደሆነ ያብራራል።

[በገጽ 3 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ከላይ በስተግራ፦ ኔቭል ቼምበርሊን

ከላይ በስተቀኝ፦ ሊየፖልድ አሜሪ

ከታች፦ ዊንስተን ቸርችል

[ምንጭ]

ቼምበርሊን፦ Photo by Jimmy Sime/Central Press/Getty Images; አሜሪ፦ Photo by Kurt Hutton/Picture Post/Getty Images; ቸርችል፦ The Trustees of the Imperial War Museum (MH 26392)