ደስተኛ የይሖዋ አገልጋዮች
ደስተኛ የይሖዋ አገልጋዮች
‘በመንፈስ ድኾች የሆኑ ደስተኞች ናቸው።’—ማቴዎስ 5:3
1. እውነተኛ ደስታ ምንድን ነው? የምንስ ነጸብራቅ ነው?
የይሖዋ ሕዝቦች ለደስታቸው አስተዋጽኦ ለሚያደርጉ ነገሮች ትልቅ ግምት ይሰጣሉ። መዝሙራዊው ዳዊት ‘እግዚአብሔር አምላኩ የሆነ ሕዝብ ደስተኛ ነው’ በማለት ተናግሯል። (መዝሙር 144:15) ደስታ ከውስጣዊ እርካታ የሚመነጭ ስሜት ነው። እውነተኛ ደስታ ሊኖረን የሚችለው ይሖዋ እንደባረከን ሲሰማን ነው። (ምሳሌ 10:22) እንዲህ ያለው ደስታ በሰማይ ከሚኖረው አባታችን ጋር ጥሩ ወዳጅነት እንደመሠረትንና ፈቃዱን እያደረግን እንዳለን ያንጸባርቃል። (መዝሙር 112:1፤ 119:1, 2) ኢየሱስ ደስታ የሚያስገኙ ዘጠኝ ነጥቦችን ዘርዝሯል። በዚህና በሚቀጥለው ርዕስ ውስጥ እነዚህን ነጥቦች መመርመራችን ‘ደስተኛውን አምላክ’ ይሖዋን በታማኝነት በማገልገል እንዴት ደስታ ማግኘት እንደምንችል እንድንገነዘብ ይረዳናል።—1 ጢሞቴዎስ 1:11 NW
በመንፈሳዊ የሚጎድለንን መገንዘብ
2. ኢየሱስ ስለ ደስታ ንግግር ያቀረበው መቼ ነው? ንግግሩንስ የከፈተው ምን በማለት ነበር?
2 ኢየሱስ በ31 ከክርስቶስ ልደት በኋላ በታሪክ ውስጥ ዝነኛ ከሆኑት ንግግሮች መካከል አንዱን አቀረበ። ኢየሱስ ይህን ንግግር የሰጠው የገሊላን ባሕር ቁልቁል መመልከት ከሚያስችል ከፍታ ቦታ ላይ ሆኖ ስለነበር የተራራው ስብከት ተብሎ ይጠራል። የማቴዎስ ወንጌል እንዲህ ይላል፦ ‘ኢየሱስ ብዙ ሕዝብ እንደ ተሰበሰበ ባየ ጊዜ፣ ወደ ተራራ ወጣና ተቀመጠ፤ ደቀ መዛሙርቱም ወደ እርሱ መጡ። እንዲህም እያለ ያስተምራቸው ጀመር፤ በመንፈስ ድኾች የሆኑ ደስተኞች ናቸው፤ መንግሥተ ሰማይ የእነርሱ ናትና።’—ማቴዎስ 5:1-3
3. ትሑት መሆናችን ለደስታችን አስተዋጽኦ የሚያደርገው እንዴት ነው?
3 ኢየሱስ በዚህ የተራራ ስብከቱ አንድ ሰው በመንፈሳዊ የሚጎድለው ነገር እንዳለ ካልተገነዘበ ደስተኛ ሊሆን እንደማይችል ጠቁሟል። ትሑት የሆኑ ክርስቲያኖች ኃጢአተኞች መሆናቸውን በሚገባ የሚገነዘቡ ከመሆናቸውም በላይ ይሖዋ በክርስቶስ ቤዛዊ መሥዋዕት አማካኝነት ይቅር እንዲላቸው ይለምኑታል። (1 ዮሐንስ 1:9) በዚህም የተነሳ የአእምሮ ሰላምና እውነተኛ ደስታ አላቸው። ‘መተላለፉ ይቅር የተባለለት፣ ኀጢአቱም የተሸፈነለት፣ እንዴት ደስተኛ ነው!’—መዝሙር 32:1፤ 119:165
4. (ሀ) ስለ ራሳችንም ሆነ ስለ ሌሎች መንፈሳዊ ፍላጎት እንደምናስብ የምናሳይባቸው አንዳንድ መንገዶች የትኞቹ ናቸው? (ለ) ለመንፈሳዊ ፍላጎታችን ንቁዎች ከሆንን ደስታችን እንዲጨምር ምን እናደርጋለን?
4 በመንፈሳዊ የሚጎድለን እንዳለ መገንዘባችን መጽሐፍ ቅዱስን ዘወትር እንድናነብ፣ ‘ታማኝና ልባም ባሪያ በጊዜው’ የሚያቀርብልንን መንፈሳዊ ምግብ በሚገባ እንድንመገብና በክርስቲያናዊ ስብሰባዎች ላይ አዘውትረን እንድንገኝ ይገፋፋናል። (ማቴዎስ 24:45 የ1954 ትርጉም፤ መዝሙር 1:1, 2፤ 119:111፤ ዕብራውያን 10:25) ለሰዎች ያለን ፍቅር እኛ ብቻ ሳንሆን ሌሎችም መንፈሳዊ ነገር እንደሚያስፈልጋቸው እንድንገነዘብ እንዲሁም የአምላክን መንግሥት ምሥራች በቅንዓት እንድንሰብክና እንድናስተምር ያነሳሳናል። (ማርቆስ 13:10፤ ሮሜ 1:14-16) የመጽሐፍ ቅዱስን እውነት ለሌሎች ማካፈል ደስታ ያስገኝልናል። (የሐዋርያት ሥራ 20:20, 35) አስደናቂ በሆኑት የመንግሥቱ ተስፋዎችና በረከቶች ላይ ባሰላሰልን መጠን ደስታችን የዚያኑ ያህል ይጨምራል። በዚህ ተስፋ መሠረት “ታናሽ መንጋ” ተብለው የተጠሩት ቅቡዓን ክርስቲያኖች የክርስቶስ መንግሥት ክፍል በመሆን በሰማይ የማይጠፋ ሕይወት ያገኛሉ። (ሉቃስ 12:32 የ1954 ትርጉም፤ 1 ቆሮንቶስ 15:50, 54) “ሌሎች በጎች” ደግሞ በአምላክ መንግሥት አማካኝነት ገነት በምትሆነው ምድር ላይ የዘላለም ሕይወት ያገኛሉ።—ዮሐንስ 10:16፤ መዝሙር 37:11፤ ማቴዎስ 25:34, 46
የሚያዝኑ ደስተኞች ሊሆኑ የሚችሉት እንዴት ነው?
5. (ሀ) “የሚያዝኑ” የሚለው አባባል ምን ማለት ነው? (ለ) እነዚህ ሰዎች የሚጽናኑት እንዴት ነው?
5 ኢየሱስ ደስታን በተመለከተ ቀጥሎ የተናገራቸው ቃላት እርስ በርስ የሚቃረኑ ይመስላሉ። ‘የሚያዝኑ ደስተኞች ናቸው፤ መጽናናትን ያገኛሉና’ ሲል ተናግሯል። (ማቴዎስ 5:4) አንድ ሰው አዝኖ እያለ እንዴት ደስተኛ ሊሆን ይችላል? የዚህን የኢየሱስ አባባል ትርጉም ለመረዳት ስለምን ዓይነት ሐዘን እንደተናገረ መመርመር ያስፈልገናል። ደቀ መዝሙሩ ያዕቆብ ኃጢአተኞች መሆናችን እንድናዝን ሊያደርገን እንደሚገባ ገልጿል። እንዲህ ሲል ጽፏል፦ “እናንተ ኀጢአተኞች እጃችሁን አንጹ፤ እናንተ በሁለት ሐሳብ የምትዋልሉ ልባችሁን አጥሩ። ተጨነቁ፤ እዘኑ፤ አልቅሱም። ሳቃችሁ ወደ ኀዘን፣ ደስታችሁም ወደ ትካዜ ይለወጥ። በጌታ ፊት ራሳችሁን አዋርዱ፣ እርሱም ከፍ ከፍ ያደርጋችኋል።” (ያዕቆብ 4:8-10) ኃጢአተኛ መሆናቸውን በመገንዘብ ከልብ የሚያዝኑ ሰዎች በክርስቶስ ቤዛዊ መሥዋዕት ካመኑና የይሖዋን ፈቃድ በማድረግ ንስሐ መግባታቸውን ካሳዩ ኃጢአታቸው ይቅር እንደሚባልላቸው ሲረዱ ይጽናናሉ። (ዮሐንስ 3:16፤ 2 ቆሮንቶስ 7:9, 10) ይህ ደግሞ ከይሖዋ ጋር የጠበቀ ወዳጅነት እንዲመሠርቱ የሚያስችላቸው ከመሆኑም በላይ ለዘላለም እርሱን እያገለገሉና እያወደሱ የመኖር ተስፋ ያስገኝላቸዋል። ይህም እውነተኛ ደስታ እንዲኖራቸው ያደርጋል።—ሮሜ 4:7, 8
6. አንዳንዶች የሚያዝኑት በምንድን ነው? የሚጽናኑትስ እንዴት ነው?
6 የኢየሱስ አባባል በዚህ ምድር ላይ በሚታዩ መጥፎ ነገሮች የሚያዝኑ ሰዎችንም ይጨምራል። ኢየሱስ በኢሳይያስ 61:1, 2 ላይ የሚገኘው ትንቢት በእርሱ ላይ እንደሚፈጸም ሲገልጽ እንዲህ ብሏል፦ “የጌታ የእግዚአብሔር መንፈስ በእኔ ላይ ነው፤ ለድኾች የምሥራች እንድሰብክ፣ እግዚአብሔር ቀብቶኛል። ልባቸው የተሰበረውን እንድጠግን፣ . . . የሚያለቅሱትን ሁሉ እንዳጽናና ልኮኛል።” ይህ ተልእኮ ገና በምድር ላይ ያሉትን ቅቡዓን ክርስቲያኖችም የሚመለከት ሲሆን እነርሱም አጋሮቻቸው በሆኑት “ሌሎች በጎች” በመታገዝ ተልእኳቸውን በመወጣት ላይ ናቸው። ሁሉም፣ ሕዝበ ክርስትናን በምታመለክተው በከሃዲዋ ኢየሩሳሌም ውስጥ “ስለ ተሠራው ጸያፍ ተግባር ሲያዝኑና ሲያለቅሱ በነበሩ ሰዎች” ግንባር ላይ ምልክት በማድረጉ ምሳሌያዊ ሥራ ይካፈላሉ። (ሕዝቅኤል 9:4) እነዚህ የሚያዝኑ ሰዎች ‘የመንግሥቱ ወንጌል’ ሲነገራቸው ይጽናናሉ። (ማቴዎስ 24:14) አሁን ያለው ክፉ የሰይጣን ሥርዓት በቅርቡ ይሖዋ በሚያመጣው ጽድቅ የሰፈነበት አዲስ ዓለም እንደሚተካ ሲያውቁ ይደሰታሉ።
የዋሆች ደስተኞች ናቸው
7. “የዋህ” ሲባል ምን ማለት አይደለም?
7 ኢየሱስ ‘የዋሆች ደስተኞች ናቸው፤ ምድርን ይወርሳሉና’ በማለት የተራራ ስብከቱን ቀጠለ። (ማቴዎስ 5:5) የዋህነት አንዳንድ ጊዜ የድክመት ምልክት እንደሆነ ተደርጎ ይታያል። ሃቁ ግን ይህ አይደለም። አንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ምሑር “የዋህ” ተብሎ የተተረጎመው ቃል የሚያስተላልፈውን መልእክት በሚመለከት እንዲህ ብለዋል፦ “የዋህ የሆነ ሰው በዋነኝነት የሚታወቀው ራሱን በመግዛት ችሎታው እንጂ ከልክ ባለፈ ገራገርነት፣ ቡቡነትና ቅልስልስነት አይደለም። ታምቆ የተያዘ ውስጣዊ ጥንካሬ ነው።” ኢየሱስ “እኔ በልቤ የዋህና ትሑት ነኝ” በማለት ስለራሱ ተናግሯል። (ማቴዎስ 11:29) ሆኖም ለጽድቅ መሠረታዊ ሥርዓቶች በመቆም ረገድ ቆራጥ ነበር።—ማቴዎስ 21:12, 13፤ 23:13-33
8. የዋህነት ከየትኛው ባሕርይ ጋር የቅርብ ተዛማጅነት አለው? ከሌሎች ጋር ባለን ግንኙነት የዋህነትን ማንጸባረቃችን አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው?
8 የዋህነት ራስን ከመግዛት ጋር የቅርብ ተዛማጅነት ያለው ባሕርይ ነው። እርግጥ ነው፣ ሐዋርያው ጳውሎስ ‘የመንፈስ ፍሬን’ ሲዘረዝር ሁለቱንም በዝርዝሩ ውስጥ አካቷቸዋል። (ገላትያ 5:22, 23) የዋህነት ለማዳበር የግድ የመንፈስ ቅዱስ እርዳታ ያስፈልገናል። በጉባኤ ውስጥ ካሉም ሆነ የይሖዋ ምሥክሮች ካልሆኑ ሰዎች ጋር ሰላማዊ ግንኙነት እንዲኖረን የሚረዳ ክርስቲያናዊ ባሕርይ ነው። ጳውሎስ “ርኅራኄን፣ ቸርነትን፣ ትሕትናን፣ የዋህነትን፣ ትዕግሥትን ልበሱ፤ እርስ በርሳችሁ ትዕግሥትን አድርጉ፣ . . . ይቅር ተባባሉ” ሲል ጽፏል።—ቆላስይስ 3:12, 13 የ1954 ትርጉም
9. (ሀ) የዋህነት የሚጠቅመን ከሰዎች ጋር ባለን ግንኙነት ብቻ አይደለም የምንለው ለምንድን ነው? (ለ) ገሮች ወይም የዋሆች ‘ምድርን የሚወርሱት’ እንዴት ነው?
9 ይሁን እንጂ፣ የዋህነት የሚጠቅመን ከሰዎች ጋር ባለን ግንኙነት ብቻ አይደለም። ለይሖዋ ሉዓላዊነት ራሳችንን በፈቃደኝነት በማስገዛት የዋህ መሆናችንን ማሳየት እንችላለን። እዚህ ምድር ላይ በነበረበት ወቅት የዋህነትን ያንጸባረቀውና ለአባቱ ፈቃድ ራሱን ሙሉ በሙሉ ያስገዛው ኢየሱስ ክርስቶስ በዚህ ረገድ ግንባር ቀደም ምሳሌያችን ነው። (ዮሐንስ 5:19, 30) ኢየሱስ በምድር ላይ ገዥ ሆኖ ስለተሾመ ምድርን በመውረስ ረገድ የመጀመሪያው እርሱ ነው ሊባል ይችላል። (መዝሙር 2:6-8፤ ዳንኤል 7:13, 14) እርሱ ደግሞ ይህን መብት ‘አብረውት ለሚወርሱት’ ‘በምድር ላይ እንዲነግሱ’ ከሰዎች መካከል ለተመረጡት 144,000 ሰዎች ያካፍላል። (ሮሜ 8:17፤ ራእይ 5:9, 10፤ 14:1, 3, 4፤ ዳንኤል 7:27) ክርስቶስና ተባባሪ ገዥዎቹ “ገሮች ግን ምድርን ይወርሳሉ፤ በታላቅ ሰላምም ሐሤት ያደርጋሉ” የሚለው ትንቢታዊ መዝሙር ፍጻሜ የሚያገኝባቸውን በሚሊዮን የሚቆጠሩ በግ መሰል ወንዶችና ሴቶች ያስተዳድራሉ።—መዝሙር 37:11፤ ማቴዎስ 25:33, 34, 46
ጽድቅን የሚራቡ ደስተኞች ናቸው
10. ‘ጽድቅን የሚራቡና የሚጠሙ ሰዎች’ የሚጠግቡት እንዴት ነው?
10 ኢየሱስ በገሊላ ተራራ ስብከቱ ላይ ለደስታ አስተዋጽኦ ያደርጋል ብሎ የጠቀሰው ሌላው ነገር የሚከተለው ነው፦ ‘ጽድቅን የሚራቡና የሚጠሙ ደስተኞች ናቸው፤ ይጠግባሉና።’ (ማቴዎስ 5:6) ለክርስቲያኖች የጽድቅ መሥፈርት የሚያወጣላቸው ይሖዋ ነው። በመሆኑም ጽድቅን የሚራቡና የሚጠሙ ሰዎች መለኮታዊ መመሪያ ይራባሉ እንዲሁም ይጠማሉ ማለት ነው። እንደነዚህ ያሉ ሰዎች ኃጢአተኞች መሆናቸውን ስለሚገነዘቡ በይሖዋ ፊት ሞገስ ለማግኘት ይናፍቃሉ። ንስሐ ከገቡና በክርስቶስ ቤዛዊ መሥዋዕት አማካኝነት አምላክ ይቅር እንዲላቸው ከለመኑ እርሱ እንደ ጻድቃን እንደሚቆጥራቸው ከቃሉ ሲማሩ በጣም ይደሰታሉ!—የሐዋርያት ሥራ 2:38፤ 10:43፤ 13:38, 39፤ ሮሜ 5:19
11, 12. (ሀ) ቅቡዓን ክርስቲያኖች ጻድቃን የሚሆኑት እንዴት ነው? (ለ) የቅቡዓኑ ደጋፊዎች የጽድቅ ጥማታቸው የሚረካላቸው እንዴት ነው?
11 ኢየሱስ ጽድቅን የሚራቡ ሰዎች ደስ የሚላቸው ‘ስለሚጠግቡ’ እንደሆነ ገልጿል። (ማቴዎስ 5:6) በሰማይ ከክርስቶስ ጋር ‘እንዲነግሡ’ የተጠሩት ቅቡዓን ክርስቲያኖች ‘እንደ ጻድቃን’ ተቆጥረዋል። (ሮሜ 5:1, 9, 16-18) ይሖዋ እንደ መንፈሳዊ ልጆቹ አድርጎ ይቀበላቸዋል። ከክርስቶስ ጋር አብረው የሚወርሱ ሲሆን በሰማያዊው መንግሥት ነገሥታትና ካህናት እንዲሆኑ ተጠርተዋል።—ዮሐንስ 3:3፤ 1 ጴጥሮስ 2:9
12 የቅቡዓኑ ደጋፊዎች የሆኑት ሌሎች በጎች ገና ሙሉ በሙሉ እንደ ጻድቃን አልተቆጠሩም። ይሁን እንጂ፣ ይሖዋ በፈሰሰው የክርስቶስ ደም ላይ ያላቸውን እምነት መሠረት በማድረግ በተወሰነ ደረጃ እንደ ጻድቃን ያያቸዋል። (ያዕቆብ 2:22-25፤ ራእይ 7:9, 10) በዚህም የተነሳ የይሖዋ ወዳጅ በመሆን “ከታላቁ መከራ” በሕይወት የመትረፍ አጋጣሚ ያገኛሉ። (ራእይ 7:14) ‘በአዲሱ ሰማይ’ የሚተዳደረው ‘ጽድቅ የሚሰፍንበት’ አዲስ ምድር ክፍል በሚሆኑበት ጊዜ የጽድቅ ጥማታቸው ሙሉ በሙሉ ይረካል።—2 ጴጥሮስ 3:13፤ መዝሙር 37:29
ምሕረት የሚያደርጉ ደስተኞች ናቸው
13, 14. መሐሪዎች መሆናችንን ማሳየት የምንችልባቸው አንዳንድ መንገዶች የትኞቹ ናቸው? ይህስ ምን ጥቅሞች ያስገኝልናል?
13 ኢየሱስ የተራራ ስብከቱን በመቀጠል ‘ምሕረት የሚያደርጉ ደስተኞች ናቸው፤ ምሕረትን ያገኛሉና’ ሲል ተናገረ። (ማቴዎስ 5:7) ምሕረት ከሕግ አንጻር ሲታይ አንድ ዳኛ በአንድ ጥፋተኛ ላይ ሕጉ የሚጠይቀውን ሙሉ ቅጣት ሳይበይንበት ከቀረ ምሕረት እንዳደረገለት ይቆጠራል። ይሁን እንጂ፣ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ “ምሕረት” ተብለው የተተረጎሙት የዕብራይስጥና የግሪክኛ ቃላት አብዛኛውን ጊዜ ችግር ላይ የወደቁ ሰዎችን በአሳቢነት ወይም በአዘኔታ ተነሳስቶ መርዳትን ያመለክታሉ። በመሆኑም መሐሪ የሆኑ ሰዎች ርኅሩኅ ናቸው። ኢየሱስ ስለ ደጉ ሳምራዊ የተናገረው ምሳሌ ችግር ላይ ለወደቀ ግለሰብ ‘ምሕረት የሚያደርግ’ ሰው ምን ዓይነት እንደሆነ ጥሩ አድርጎ ይገልጻል።—ሉቃስ 10:29-37 የ1954 ትርጉም
14 መሐሪ በመሆን ደስታ ለማግኘት ከፈለግን ችግር ላይ የወደቁ ሰዎችን በደግነት ተነሳስተን መርዳት ይኖርብናል። (ገላትያ 6:10) ኢየሱስ ለሰዎች ያዝን ነበር። መጽሐፍ ቅዱስ “እረኛ እንደሌላቸው በጎች ስለ ነበሩም አዘነላቸው፤ ብዙ ነገርም ያስተምራቸው ጀመር” በማለት ይናገራል። (ማርቆስ 6:34) ኢየሱስ ሰዎች ከምንም በላይ የሚያስፈልጋቸው መንፈሳዊ ነገር መሆኑን ተገንዝቦ ነበር። እኛም ለሰዎች በጣም የሚያስፈልገውን ‘የመንግሥቱን ወንጌል’ በመስበክ ርኅሩኆችና መሐሪዎች መሆናችንን ማሳየት እንችላለን። (ማቴዎስ 24:14) በተጨማሪም በዕድሜ የገፉ ክርስቲያኖችን፣ መበለቶችን፣ ወላጆች የሌላቸውን ልጆች መጠየቅና መርዳት እንዲሁም ‘የተጨነቁትን ማጽናናት’ እንችላለን። (1 ተሰሎንቄ 5:14 NW፤ ምሳሌ 12:25፤ ያዕቆብ 1:27) እንዲህ ማድረጋችን ለራሳችን ደስታ የሚያስገኝልን ከመሆኑም በላይ የይሖዋን ምሕረት እንድናገኝ በር ይከፍትልናል።—የሐዋርያት ሥራ 20:35፤ ያዕቆብ 2:13
ልበ ንጹሖችና ሰላማውያን ደስተኞች ናቸው
15. ልበ ንጹሕና ሰላማዊ መሆን የምንችለው እንዴት ነው?
15 ኢየሱስ ‘ልባቸው ንጹሕ የሆነ ደስተኞች ናቸው፤ እግዚአብሔርን ያዩታልና። ሰላምን የሚያወርዱ ደስተኞች ናቸው፤ የእግዚአብሔር ልጆች ተብለው ይጠራሉና’ በማለት ለደስታ አስተዋጽኦ የሚያደርጉ ሌሎች ሁለት ነገሮችን ጠቅሷል። (ማቴዎስ 5:8, 9) ልበ ንጹሕ የሚለው አነጋገር ሥነ ምግባራዊ ንጽሕናን ብቻ ሳይሆን በመንፈሳዊ አለመርከስንና ባልተከፋፈለ ልብ አምላክን ማገልገልን ይጨምራል። (1 ዜና መዋዕል 28:9፤ መዝሙር 86:11) ሰላማዊ የሆኑ ክርስቲያኖች ከእምነት ወንድሞቻቸውና እህቶቻቸውም ሆነ ከሌሎች ሰዎች ጋር በተቻለ መጠን በሰላም ለመኖር ይጥራሉ። (ሮሜ 12:17-21) ‘ሰላምን ይፈልጋሉ፤ ይከተሉትማል።’—1 ጴጥሮስ 3:11
16, 17. (ሀ) ቅቡዓን ክርስቲያኖች “የእግዚአብሔር ልጆች” የተባሉት ለምንድን ነው? ‘እግዚአብሔርንስ የሚያዩት’ እንዴት ነው? (ለ) “ሌሎች በጎች” ‘እግዚአብሔርን የሚያዩት’ እንዴት ነው? (ሐ) ሙሉ በሙሉ “የእግዚአብሔር ልጆች” የሚሆኑትስ እንዴትና መቼ ነው?
16 ልባቸው ንጹሕ የሆኑ ሰላማዊ ሰዎች ‘የእግዚአብሔር ልጆች ተብለው እንደሚጠሩና እግዚአብሔርን እንደሚያዩ’ ቃል ተገብቶላቸዋል። ቅቡዓን ክርስቲያኖች ገና ምድር ላይ እያሉም እንኳ በመንፈስ የተወለዱ የይሖዋ “ልጆች” ናቸው። (ሮሜ 8:14-17) ትንሣኤ አግኝተው በሰማይ ከክርስቶስ ጋር ሲሆኑ ደግሞ ይሖዋን የማየትና የማገልገል አጋጣሚ ያገኛሉ።—1 ዮሐንስ 3:1, 2፤ ራእይ 4:9-11
17 ሰላማውያን የሆኑ “ሌሎች በጎች” ደግሞ ወደፊት ‘የዘላለም አባታቸው’ በሚሆነው በመልካሙ እረኛ በክርስቶስ ኢየሱስ ሥር በመሆን ይሖዋን ያገለግላሉ። (ዮሐንስ 10:14, 16፤ ኢሳይያስ 9:6) በሺህ ዓመቱ የክርስቶስ ግዛት መጨረሻ ላይ የሚኖረውን ፈተና የሚያልፉ ሁሉ የይሖዋ ምድራዊ ልጆች በመሆን ‘ለእግዚአብሔር ልጆች ወደሆነው ወደ ከበረው ነጻነት ይደርሳሉ።’ (ሮሜ 8:21፤ ራእይ 20:7, 9) ይህ ተስፋ የሚፈጸምበትን ጊዜ በጉጉት ይጠባበቃሉ፤ ሆኖም ይሖዋ ሕይወት ሰጪያቸው መሆኑን በመቀበል ራሳቸውን ለእርሱ ስለወሰኑ አሁንም እንኳ ቢሆን አባታችን ብለው ይጠሩታል። (ኢሳይያስ 64:8) ጥንት እንደነበሩት እንደ ኢዮብና ሙሴ ሁሉ እነርሱም በእምነት ዓይናቸው ‘እግዚአብሔርን ያዩታል።’ (ኢዮብ 42:5፤ ዕብራውያን 11:27) ‘በልባቸው ዓይኖችና’ ከአምላክ በሚያገኙት ትክክለኛ እውቀት አማካኝነት የይሖዋን ድንቅ ባሕርያት ያያሉ፤ እንዲሁም ፈቃዱን በማድረግ እርሱን ለመምሰል ይጥራሉ።—ኤፌሶን 1:18፤ ሮሜ 1:19, 20፤ 3 ዮሐንስ 11
18. ኢየሱስ ለደስታ አስተዋጽኦ ያደርጋሉ ብሎ በዘረዘራቸው ሰባት ነጥቦች መሠረት በዛሬው ጊዜ እውነተኛ ደስታ የሚያገኙት እነማን ናቸው?
18 በመንፈሳዊ የሚጎድላቸው እንዳለ የሚታወቃቸው፣ የሚያዝኑ፣ የዋሆች፣ ጽድቅን የሚራቡና የሚጠሙ፣ መሐሪዎች፣ ልበ ንጹሖች እንዲሁም ሰላም ወዳዶች ይሖዋን በማገልገል እውነተኛ ደስታ እንደሚያገኙ ተመልክተናል። ሆኖም እንዲህ ያሉ ሰዎች ብዙውን ጊዜ ተቃውሞ አልፎ ተርፎም ስደት ይደርስባቸዋል። ታዲያ ይህ ደስታቸውን ይሰርቅባቸው ይሆን? የዚህ ጥያቄ መልስ በሚቀጥለው ርዕስ ውስጥ ይብራራል።
ለክለሳ ያህል
• በመንፈሳዊ የሚጎድላቸው ነገር እንዳለ የሚገነዘቡ ሰዎች ምን ደስታ ያገኛሉ?
• የሚያዝኑ ሰዎች የሚጽናኑባቸው አንዳንድ መንገዶች ምንድን ናቸው?
• የዋህነት ማሳየት የምንችለው እንዴት ነው?
• መሐሪዎች፣ ልበ ንጹሖችና ሰላማውያን መሆን የሚገባን ለምንድን ነው?
[የአንቀጾቹ ጥያቄዎች]
[በገጽ 10 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
‘በመንፈስ ድኾች የሆኑ ደስተኞች ናቸው’
[በገጽ 10 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
‘ምሕረት የሚያደርጉ ደስተኞች ናቸው’
[በገጽ 10 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
‘ጽድቅን የሚራቡና የሚጠሙ ደስተኞች ናቸው’