በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

በትዳር ውስጥ አለመግባባት ሲፈጠር

በትዳር ውስጥ አለመግባባት ሲፈጠር

በትዳር ውስጥ አለመግባባት ሲፈጠር

ጤናማ አስተሳሰብ ያላቸው ባሎችም ሆኑ ሚስቶች በትዳራቸው ውስጥ ጠብ እንዲነሳ አይፈልጉም፤ ይሁን እንጂ እንዲህ ያለ ሁኔታ መከሰቱ የተለመደ ነው። ለምሳሌ ያህል አንድ ሰው የትዳር ጓደኛውን የሚያበሳጭ ነገር ይናገራል። ከዚያም መጯጯህና መቆጣት ይጀምራሉ፤ ይህም በስሜት ተነድተው ኃይለ ቃል እንዲናገሩ መንገድ ይከፍታል። ቀጥሎ ሁለቱም ይኮራረፉና ቤቱ በዝምታ ይዋጣል። ንዴታቸው በረድ ሲልላቸው ደግሞ ይቅርታ ይጠያየቁና ቢያንስ ቢያንስ ሌላ ግጭት እስከሚነሳ ድረስ ሰላም ይሰፍናል።

በትዳር ጓደኛሞች መካከል የሚፈጠረውን አለመግባባት በተመለከተ በርካታ ቀልዶች ይነገራሉ፤ እንዲሁም በዚህ ዙሪያ የሚያጠነጥኑ የቴሌቪዥን ፕሮግራሞች ይቀርባሉ። ይሁን እንጂ ነገሩ የሚያስቅ አይደለም። እንዲያውም አንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ምሳሌ “ግድ የለሽ ቃል እንደ ሰይፍ ይወጋል” ይላል። (ምሳሌ 12:18) አዎን፣ ሻካራ ንግግር ጠቡ ካበቃ በኋላ እንኳን ቶሎ የማይሽር የስሜት ጠባሳ ትቶ ሊያልፍ ይችላል። አልፎ ተርፎም ጭቅጭቅ ዓመጽ ወደ መፈጸም ሊመራ ይችላል።ዘፀአት 21:18

እርግጥ ነው፣ የሰው ልጆች ፍጹማን ባለመሆናቸው ምክንያት በትዳር ውስጥ የሚነሱትን ችግሮች ጨርሶ ማስወገድ አይቻልም። (ዘፍጥረት 3:16፤ 1 ቆሮንቶስ 7:28) ይሁን እንጂ ዘወትር ከባድ ጠብ የሚነሳ ከሆነ እንደ ቀላል ነገር መታየት የለበትም። በባልና ሚስት መካከል ዘወትር ጠብ የሚከሰት ከሆነ የኋላ ኋላ የመፋታታቸው አጋጣሚ ከፍ እንደሚል ባለሙያዎች ይናገራሉ። በመሆኑም አንተም ሆንክ የትዳር ጓደኛህ አለመግባባትን እንዴት ሰላማዊ በሆነ መንገድ መፍታት እንደምትችሉ መማራችሁ በጣም አስፈላጊ ነው።

ሁኔታውን ማጤን

ትዳርህ ጭቅጭቅ የማያጣው ከሆነ ብዙውን ጊዜ ወደዚህ ሁኔታ እንድትገቡ ምክንያት የሚሆነው ምን እንደሆነ ለማጤን ሞክር። a ለምሳሌ ያህል በአንድ ጉዳይ ላይ ከትዳር ጓደኛህ ጋር ባትስማሙ ምን ይፈጠራል? ወዲያውኑ ውይይታችሁ መልኩን ለውጦ ወደ ዘለፋና ውንጀላ ይቀየራል? እንዲህ ከሆነ ምን ማድረግ ትችላለህ?

በመጀመሪያ ደረጃ አንተ በግልህ ለችግሩ መነሳት ምን አስተዋጽኦ እንዳደረግክ በሐቀኝነት ራስህን መርምር። በቀላሉ ትቆጣለህ? መጨቃጨቅ ይቀናሃል? በዚህ ረገድ የትዳር ጓደኛህ ምን ትላለች? አንተና የትዳር ጓደኛህ ጭቅጭቅ ማለት ምን እንደሆነ የተለያየ አመለካከት ሊኖራችሁ ስለሚችል በመጨረሻው ጥያቄ ላይ ይበልጥ ማተኮሩ በጣም አስፈላጊ ነው።

ለምሳሌ ያህል የትዳር ጓደኛህ በተወሰነ መጠን ቁጥብ ስትሆን አንተ ግን ሐሳብህን በግልጽና በስሜት ትናገራለህ እንበል። እንዲህ ትል ይሆናል:- “ያደግኩት ሁሉም የቤተሰብ አባላት እንዲህ ባለ መንገድ በሚነጋገሩበት ቤት ውስጥ ነው። መጨቃጨቄ አይደለም!” ምናልባት አንተ እንደ ተጨቃጨቅህ አይሰማህ ይሆናል። በግልጽ ተናገርኩ ያልከው ነገር የትዳር ጓደኛህን የሚጎዳና ለጠብ የሚጋብዝ ሊሆን ይችላል። አንተና የትዳር ጓደኛህ ሐሳባችሁን የምትገልጹበት መንገድ የተለያየ መሆኑን መገንዘብህ ብቻ አለመግባባት እንዳይፈጠር ለመከላከል ይረዳሃል።

ጭቅጭቅ ሁልጊዜ በጩኸት ይገለጻል ማለት እንደማይቻል አስታውስ። ጳውሎስ “ጩኸትም መሳደብም . . . ከእናንተ ዘንድ ይወገድ” በማለት ለክርስቲያኖች ጽፎላቸዋል። (ኤፌሶን 4:31 የ1954 ትርጉም) “ጩኸት” ማለት ድምፅን ከፍ አድርጎ መናገር ሲሆን “መሳደብ” የተባለው ደግሞ የንግግሩን ይዘት ያመለክታል። ከዚህ አንጻር ስንመለከት ዝግ ባለ ድምፅ የሚነገሩ ቃላት ሌላውን ወገን የሚያበሳጩ ወይም የሚያቃልሉ እስከሆኑ ድረስ ከጭቅጭቅ ተለይተው አይታዩም።

ቀደም ብሎ የተጠቀሰውን ሐሳብ በአእምሮህ ያዝና ከትዳር ጓደኛህ ጋር አለመግባባት ሲፈጠር እንዴት እንደምትፈታው ራስህን ገምግም። ተጨቃጫቂ ነህ? በአብዛኛው የዚህን ጥያቄ ትክክለኛ መልስ ለማግኘት የሚያስችልህ የትዳር ጓደኛህ ያላት አመለካከት እንደሆነ ቀደም ሲል ተመልክተናል። የትዳር ጓደኛህ በቀላሉ የምትከፋ እንደሆነች በማሰብ አመለካከቷን ከማጣጣል ይልቅ ራስህን በእርሷ ዓይን ለመመልከት ሞክር፤ እንዲሁም አስፈላጊውን ማስተካከያ አድርግ። ጳውሎስ “እያንዳንዱ ሰው የባልንጀራውን ጥቅም እንጂ የራሱን ብቻ አይፈልግ” በማለት ጽፏል።1 ቆሮንቶስ 10:24

“እንዴት እንደምትሰሙ ተጠንቀቁ”

ኢየሱስ “እንዴት እንደምትሰሙ ተጠንቀቁ” ሲል የተናገረው ሐሳብ፣ አለመግባባትን መፍታት የሚቻልበትን ሌላውን መንገድ ይጠቁመናል። (ሉቃስ 8:18) ኢየሱስ እዚህ ላይ በትዳር ጓደኛሞች መካከል ስላለው የሐሳብ ግንኙነት እየተናገረ እንዳልሆነ የተረጋገጠ ነው። የሆነ ሆኖ መሠረታዊ ሥርዓቱ በትዳርም ላይ ይሠራል። የትዳር ጓደኛችሁን ምን ያህል በጥሞና ታዳምጣላችሁ? እንደው ሲናገሩስ ጆሯችሁን ትሰጣላችሁ? ወይስ ንግግራቸውን ሳይጨርሱ ጣልቃ ገብታችሁ ሙሉ ለሙሉ ላልተረዳችሁት ችግር ብዙም ያልታሰበበት የመፍትሄ ሐሳብ ትናገራላችሁ? መጽሐፍ ቅዱስ “ከማዳመጡ አስቀድሞ የሚመልስ፣ ቂልነትና ዕፍረት ይሆንበታል” ይላል። (ምሳሌ 18:13) አለመግባባት በሚነሳበት ጊዜ ከትዳር ጓደኛችሁ ጋር በጥሞና በጉዳዩ ላይ ተወያዩበት፤ እንዲሁም ከልብ ተደማመጡ።

የትዳር ጓደኛህን አመለካከት አቅልለህ ከመመልከት ይልቅ “የሌላው መከራ ለእናንተ እንደሚሆን አድርጉ” የሚለውን ምክር በሥራ ላይ ለማዋል ጥረት አድርግ። (1 ጴጥሮስ 3:8 የ1954 ትርጉም) ጥቅሱ መጀመሪያ በተጻፈበት በግሪክኛ ቋንቋ ይህ አባባል ሌላ ሰው ሲሰቃይ አብሮ መሰቃየትን ያመለክታል። የትዳር ጓደኛህ በሆነ ምክንያት ከተጨነቀች አብረሃት መጨነቅ አለብህ። ጉዳዩን በእርሷ ቦታ ሆነህ ለማየት ጥረት አድርግ።

ለአምላክ አክብሮት የነበረው ይስሐቅ የሚስቱን አመለካከት ይረዳላት እንደነበር ከታሪካቸው ማየት ይቻላል። የይስሐቅ ሚስት ርብቃ ከልጅዋ ከያዕቆብ ጋር በተያያዘ በጣም የረበሻት አንድ የቤተሰብ ጉዳይ እንደነበር መጽሐፍ ቅዱስ ይናገራል። ርብቃ “ዔሳው ባገባቸው በኬጢያውያን ሴቶች ምክንያት መኖር አስጠልቶኛል፤ ያዕቆብም ከዚሁ አገር ከኬጢያውያን ሴቶች ሚስት የሚያገባ ከሆነ፣ ሞቴን እመርጣለሁ” በማለት ለይስሐቅ ነገረችው።—ዘፍጥረት 27:46

ርብቃ ከጭንቀቷ የተነሳ ጉዳዩን ማጋነኗ እሙን ነው። በእርግጥ ሕይወቷን ጠልታ ነበር? ልጅዋ ከኬጢያውያን መካከል ሚስት ከሚያገባ ይልቅ ሞትን ትመርጥ ነበር? ላይሆን ይችላል። ቢሆንም ይስሐቅ የርብቃን ስሜት አቅልሎ አልተመለከተም፤ ከዚህ ይልቅ ጭንቀቷ ተገቢ እንደሆነ በማመን አስፈላጊውን እርምጃ ወስዷል። (ዘፍጥረት 28:1) አንተም ወደፊት የትዳር ጓደኛህ የሚያስጨንቅ ሁኔታ ካጋጠማት ተመሳሳይ ነገር አድርግ። ጉዳዩ የሚረባ እንዳልሆነ በማሰብ ችላ ከማለት ፈንታ የትዳር ጓደኛህን ስማ፣ አመለካከቷን አክብርላት፣ እንዲሁም ስሜቷን እንደተረዳህላት በሚያሳይ መንገድ እርምጃ ውሰድ።

የማዳመጥና የማስተዋል ጥቅም

አንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ምሳሌ “የቊጣን ስሜት መቆጣጠር አስተዋይነት ነው” ይላል። (ምሳሌ 19:11 የ1980 ትርጉም) በጭቅጭቁ መሃል አንደኛው የትዳር ጓደኛ ለሚሰነዝራቸው ጎጂ ቃላት ሁሉ ተቻኩሎ መልስ መስጠት በጣም ቀላል ነው። ይሁን እንጂ ብዙውን ጊዜ እንዲህ ማድረጉ ንትርኩ እየተባባሰ እንዲሄድ መንገድ ይከፍታል። ስለዚህ የትዳር ጓደኛህ በምትናገርበት ጊዜ የምትሰነዝራቸውን ቃላት ከማዳመጥ በተጨማሪ ከንግግሯ በስተ ጀርባ ያለውንም ስሜት ለማጤን ቁርጥ ውሳኔ አድርግ። እንዲህ ያለው ማስተዋል በሚያናድደው ጉዳይ ላይ እንዳታተኩርና ለችግሩ መሠረት የሆነውን ነገር እንድትመለከት ያስችልሃል።

ለምሳሌ ያህል ባለቤትህ “ከእኔ ጋር ምንም ጊዜ አታሳልፍም!” አለችህ እንበል። በዚህ ጊዜ ልትበሳጭና ከዚህ በፊት ያደረግሃቸውን ነገሮች በግዴለሽነት መንፈስ በመናገር ክሱን ለማስተባበል ትሞክር ይሆናል። “ባለፈው ወር አንድ ቀን ሙሉ አብረን አልዋልንም?” ብለህ መልስ ትሰጣት ይሆናል። ልብ ብለህ ብታዳምጣት ግን ሚስትህ ተጨማሪ ሰዓት ወይም ደቂቃዎች አብረሃት እንድታሳልፍ እየጠየቀችህ እንዳልሆነ ልትገነዘብ ትችላለህ። ከዚህ ይልቅ ችላ እንዳልካትና እንደማትወዳት እንደተሰማት መናገሯ እንዲሁም ቀርበህ ስሜትህን እንድትገልጽላት መጠየቋ ሊሆን ይችላል።

ሚስት ከሆንሽ ደግሞ ባለቤትሽ በቅርቡ አንዳንድ ነገሮችን ለመግዛት ያወጣሽው ገንዘብ ጉዳይ እንዳሳሰበው ገለጸልሽ እንበል። “እንዴት ይህን ያህል ገንዘብ ታጠፊያለሽ?” በማለት ነገሩን ማመን እንዳቃተው ይነግርሻል። በዚህ ጊዜ የቤተሰባችሁን የገንዘብ አቅም በመንገር ወይም ደግሞ ያወጣሽውን ወጪ ከእርሱ ወጪ ጋር በማወዳደር ምንም ጥፋት እንደሌለብሽ ለማስረዳት ትሞክሪ ይሆናል። ሆኖም የማስተዋል ችሎታ ባለቤትሽ እየተናገረ ያለው ስለ ብርና ሳንቲሞች ላይሆን እንደሚችል እንድትገነዘቢ ይረዳሻል። ከዚህ ይልቅ ከበድ ያለ ወጪ ለማድረግ በፈለግሽበት ጊዜ ስላላማከርሽው ተበሳጭቶ ይሆናል።

እርግጥ ነው፣ ባልና ሚስት አብረው የሚያሳልፉትን ጊዜና የቤት ወጪያቸውን በተመለከተ የሚያደርጉት ውሳኔ ከትዳር ትዳር ሊለያይ ይችላል። አለመግባባት በሚከሰትበት ጊዜ ንዴትን ለመቆጣጠርና የችግሩን ትክክለኛ መንስኤ ለማወቅ ማስተዋል ትልቁን ሚና እንደሚጫወት መገንዘብ ይገባል። ስሜታዊ የሆነ እርምጃ ከመውሰድ ይልቅ “ሰው ሁሉ ለመስማት የፈጠነ፣ ለመናገር የዘገየ፣ ለቊጣም የዘገየ ይሁን” በማለት የመጽሐፍ ቅዱስ ጸሐፊ የሆነው ያዕቆብ የሰጠውን ምክር ተከተል።—ያዕቆብ 1:19

የትዳር ጓደኛህን በምታነጋግርበት ወቅት አነጋገርህ ትልቅ ለውጥ እንደሚያመጣ አትዘንጋ። መጽሐፍ ቅዱስ “የጠቢብ አንደበት . . . ፈውስን ያመጣል” ይላል። (ምሳሌ 12:18) በትዳር ጓደኛሞች መካከል ግጭት በሚፈጠርበት ጊዜ ሁለቱም ‘የምናገራቸው ቃላት የሚያቆስሉ ናቸው ወይስ የሚፈውሱ? ለእርቅ መሰናክል ይፈጥራሉ ወይስ መንገድ ይጠርጋሉ?’ ብለው ራሳቸውን መጠየቅ ይኖርባቸዋል። ቀደም ብለን እንደተመለከትነው በንዴት ወይም በችኮላ የሚሰጡ መልሶች ጠብን ይጭራሉ።—ምሳሌ 29:22

አለመግባባቱ ወደ ቃላት ጦርነት ካመራ ከዋናው ጉዳይ ላለመውጣት ጥረት አድርጉ። በችግሩ መንስዔ ላይ ትኩረት አድርግ እንጂ በትዳር ጓደኛህ ላይ ጣትህን አትቀስር። ይበልጥ ሊያሳስብህ የሚገባው ‘ትክክለኛው ማን ነው’ የሚለው ሳይሆን ‘ትክክል የሆነው ነገር ምንድን ነው’ የሚለው መሆን አለበት። የምትናገራቸው ቃላት ንትርኩን የሚያባብሱ እንዳይሆኑ ጥንቃቄ አድርግ። መጽሐፍ ቅዱስ “ክፉ ቃል . . . ቁጣን ይጭራል” ይላል። (ምሳሌ 15:1) አዎን፣ የምትናገረው ነገርና የምትናገርበት መንገድ የትዳር ጓደኛህን ድጋፍ ማግኘት ወይም አለማግኘትህ ላይ ትልቅ ለውጥ ያመጣል።

ዓላማህ አለመግባባቱን መፍታት እንጂ መርታት አይሁን

አለመግባባቶችን ለማስወገድ በምንጥርበት ጊዜ ግባችን መፍትሄ ማግኘት እንጂ በክርክሩ ድል መንሳት መሆን የለበትም። መፍትሄ ማግኘት የምትችለው እንዴት ነው? በእርግጠኝነት ችግርን ለመፍታት የሚያስችለው መንገድ የመጽሐፍ ቅዱስን ምክር መፈለግና በሥራ ላይ ማዋል ነው፤ በተለይ ባሎች በዚህ ረገድ ቀዳሚ መሆን አለባቸው። በወቅቱ የተነሱትን ጉዳዮች ወይም ችግሮች በተመለከተ ያለህን ጥብቅ አቋም ለመናገር ከመቸኮል ይልቅ ለምን ነገሩን ከይሖዋ አመለካከት አንጻር ለማየት አትሞክርም? ወደ ይሖዋ ጸልይ፤ እንዲሁም ልብህንና አሳብህን የሚጠብቀውን የአምላክን ሰላም ለማግኘት ተጣጣር። (ኤፌሶን 6:18፤ ፊልጵስዩስ 4:6, 7) ለራስህ ብቻ ሳይሆን ለትዳር ጓደኛህም ጥቅም ትኩረት ለመስጠት ጥረት አድርግ።—ፊልጵስዩስ 2:4

ቅሬታ እና ከቁጥጥር ውጪ የሆኑ ስሜቶች አስተሳሰብህንና ድርጊትህን እንዲቆጣጠሩት ከፈቀድክ ብዙውን ጊዜ ሁኔታው እየተባባሰ ይሄዳል። በሌላ በኩል ደግሞ የአምላክ ቃል በሚሰጠው ምክር መሠረት ለመስተካከል ፈቃደኛ መሆን ሰላም፣ ስምምነትና የይሖዋን በረከት ያስገኛል። (2 ቆሮንቶስ 13:11 NW) ‘ከሰማይ በሆነችው ጥበብ’ በመመራትና አምላካዊ ባሕርያትን በማንጸባረቅ ‘ሰላምን የሚያደርጉ’ ሰዎች የሚያገኟቸውን ጥቅሞች ቅመስ።—ያዕቆብ 3:17, 18

የግል ፍላጎትን መሥዋዕት ማድረግ የሚጠይቅ ቢሆንም እንኳ ሁሉም ሰው አለመግባባትን እንዴት በሰላም መፍታት እንደሚቻል ማወቅ እንደሚኖርበት የተረጋገጠ ነው። (1 ቆሮንቶስ 6:7) “ቍጣን፣ ንዴትን፣ ስድብን፣ ሐሜትንና አሳፋሪ ንግግርን . . . አስወግዱ፤ አሮጌውን ሰው ከሥራው ጋር አውልቃችሁ ስለ ጣላችሁ . . . አዲሱን ሰው ለብሳችኋል” የሚለውን የጳውሎስን ምክር በሥራ ላይ አውል።—ቆላስይስ 3:8-10

እርግጥ አንዳንድ ጊዜ በኋላ የሚቆጭህን ነገር ትናገር ይሆናል። (ያዕቆብ 3:8) እንዲህ ዓይነት ሁኔታ ሲከሰት የትዳር ጓደኛህን ይቅርታ ጠይቅ። ለወደፊቱ ላለመድገምም ጥረት አድርግ። በጊዜ ሂደት ሁለታችሁም አለመግባባቶችን በመፍታት ረገድ ትልቅ መሻሻል እንዳደረጋችሁ ትገነዘባላችሁ።

[በገጽ 22 ላይ የሚገኝ ሣጥን/ሥዕል]

ጭቅጭቅን ማብረድ የሚቻልባቸው ሦስት እርምጃዎች

• የትዳር ጓደኛችሁን አዳምጡ።—ምሳሌ 10:19

• ለትዳር ጓደኛችሁ አመለካከት አክብሮት ይኑራችሁ።—ፊልጵስዩስ 2:4

• ፍቅር የሚንጸባረቅበት እርምጃ ውሰዱ።—1 ቆሮንቶስ 13:4-7

[በገጽ 23 ላይ የሚገኝ ሣጥን/ሥዕል]

አሁን ምን ማድረግ ትችላላችሁ?

ከዚህ በታች የተዘረዘሩትን ጥያቄዎች ለትዳር ጓደኛህ አንሣላትና መልስ በምትሰጥህ ጊዜ ጣልቃ ሳትገባ በጥሞና አዳምጣት። እርሷም ተመሳሳይ ጥያቄዎች ልትጠይቅህ ትችላለች።

• ተጨቃጫቂ ነኝ?

• ሐሳብሽን ስትገልጪ በጥሞና አዳምጥሻለሁ ወይስ ተናግረሽ ሳታበቂ መልስ ለመስጠት እቸኩላለሁ?

• የምናገራቸው ቃላት ምንም የማላስብልሽ ወይም ደግሞ የተናደድኩ ያስመስሉኛል?

• በተለይ የማንስማማበት አንድ ጉዳይ በሚኖርበት ወቅት ሐሳባችንን የምንገልጽበትን መንገድ በየበኩላችን ማሻሻል የምንችለው እንዴት ነው?

[በገጽ 21 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ትደማመጣላችሁ?

[በገጽ 22 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

“ችላ እንዳለኝና እንደማይወደኝ ይሰማኛል”

[በገጽ 22 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

“ከእኔ ጋር ምንም ጊዜ አታሳልፍም!”

[በገጽ 22 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

“ባለፈው ወር አንድ ቀን ሙሉ አብረን አልዋልንም?”

[የግርጌ ማስታወሻ]

a በዚህ ርዕስ ውስጥ የተሰጠው ምክር ለባሎችም ሆነ ለሚስቶች ይሠራል።