ደስ የሚሰኘው በይሖዋ ሕግ ነበር
ደስ የሚሰኘው በይሖዋ ሕግ ነበር
የይሖዋ ምሥክሮች የበላይ አካል አባል ሆኖ ያገለገለው ወንድም አልበርት ዳርጀር ሽሮደር፣ ረቡዕ መጋቢት 8, 2006 ምድራዊ ሕይወቱን አጠናቅቋል። ወንድም ሽሮደር 94 ዓመቱ ነበር። በሙሉ ጊዜ አገልግሎት ከ73 ዓመታት በላይ አሳልፏል።
ወንድም ሽሮደር በ1911 በዩናይትድ ስቴትስ፣ በሚቺጋን ግዛት ውስጥ በሚገኘው በሳግኖ ከተማ ተወለደ። a ልጅ እያለ ስለ መጽሐፍ ቅዱስ ይበልጥ እንዲያውቅም ሆነ የይሖዋን ቃል የማንበብ ፍቅር እንዲያድርበት ያደረጉት ሴት አያቱ ነበሩ። ወንድም ሽሮደር በሚቺጋን ዩኒቨርሲቲ የኤሌክትሪክ ምህንድስና፣ ላቲንና ጀርመንኛ አጥንቷል። ሆኖም ለቅዱሳን ጽሑፎች ያለው አድናቆት እየጨመረ ሲሄድ ትምህርቱን በማቋረጥ የሙሉ ጊዜ የመንግሥቱ ሰባኪ ሆነ። በ1932 ብሩክሊን፣ ኒው ዮርክ የሚገኘው የቤቴል ቤተሰብ አባል ሆነ።
ወንድም ሽሮደር 26 ዓመት ሲሆነው ማለትም በ1937 በብሪታንያ ያለውን የይሖዋ ምሥክሮች ሥራ በበላይነት እንዲከታተል ተሾመ። ለስብከቱ ሥራ የነበረው ቅንዓት በብሪታንያ ብዙዎች በሙሉ ጊዜ አገልግሎት እንዲካፈሉ አበረታቷቸዋል። በለንደን ቤቴል ውስጥ ከወንድም ሽሮደር ጋር ይሠሩ ከነበሩት ወጣቶች መካከል አንዱ ጆን ባር ነበር። ከጊዜ በኋላ እነዚህ ሁለት ወንድሞች ለብዙ ዓመታት የበላይ አካል አባላት ሆነው አብረው አገልግለዋል።
ወንድም ሽሮደር በጦርነቱ ዓመታት የይሖዋ ምሥክሮችን ወክሎ ያከናውን የነበረውን ሥራ ባለ ሥልጣናቱ በማወቃቸው ነሐሴ 1942 ከብሪታንያ አባረሩት። በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ወቅት የአትላንቲክን ውቅያኖስ ለማቋረጥ ካደረገው አስቸጋሪ ጉዞ በኋላ በመስከረም ወር ብሩክሊን ደረሰ።
በዚያን ጊዜ የይሖዋ አገልጋዮች ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት በኋላ ብዙ የሚሠራ ሥራ እንደሚኖር አውቀው ነበር። ወንድም ሽሮደር ቀጣዩን ምድቡን ማለትም በጊልያድ የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ቤት የሚሰጠውን ትምህርት በማዘጋጀት እንዲረዳ መመደቡን ሲያውቅ ቢገረምም ሥራውን በደስታ ተቀብሎታል። ለተወሰኑ ዓመታት ሚስዮናውያንን በማሠልጠን አስተማሪ ሆኖ አገልግሏል። በጊልያድ ከዚያም በመቀጠል በመንግሥት አገልግሎት ትምህርት ቤት ያስተማራቸው ተማሪዎች አስደሳች ትዝታዎች አሏቸው። ወንድም ሽሮደር፣ ተማሪዎቹ ለአምላክ ሕግጋት ፍቅር እንዲያዳብሩ መርዳት ያስደስተው የነበረ ከመሆኑም ሌላ ይሖዋን ማወቅ አስፈላጊ ነገር እንደሆነ አጥብቆ ይናገር ነበር።
በ1956 ወንድም ሽሮደር፣ ሻርለት ቦወንን ያገባ ሲሆን በ1958 ጁዳ ቤን የተባለውን ወንድ ልጃቸውን ወለዱ። ወንድም ሽሮደር ግሩም ክርስቲያን ባልና አባት ነበር። በ1974 የማስተዋል ችሎታውን በመጠቀም ይበልጥ መሥራት በሚችልበት መስክ ማለትም የበላይ አካል አባል ሆኖ ማገልገል ጀመረ። ደግና ትሑት የነበረ ከመሆኑም በላይ የአምላክን ታላቅ ስም ከፍ ከፍ ማድረግ ይፈልግ ነበር። ወንድም ሽሮደር ‘በይሖዋ ሕግ ደስ የሚሰኝ’ ቅቡዕ ክርስቲያን በመሆኑ በሰማይ ሽልማቱን እንዳገኘ እርግጠኞች ነን።—መዝሙር 1:2
[የግርጌ ማስታወሻ]
a የወንድም ሽሮደር የሕይወት ታሪክ በመጋቢት 1, 1988 መጠበቂያ ግንብ (እንግሊዝኛ) ላይ ይገኛል።