በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የአምላክን ቃል ማጥናት ያስደስትሃል?

የአምላክን ቃል ማጥናት ያስደስትሃል?

የአምላክን ቃል ማጥናት ያስደስትሃል?

“የአምላክን ቃል አዘውትሬ ማንበብ ስጀምር አስደሳች ሳይሆን አሰልቺ ሆኖብኝ ነበር” በማለት ሎሬን ትናገራለች። “የማነበውን ነገር ለመረዳት ስለሚያስቸግረኝ ብዙውን ጊዜ ትኩረቴ ይከፋፈል ነበር።”

ሌሎች ሰዎችም መጽሐፍ ቅዱስን ማንበብ ሲጀምሩ አስደሳች እንዳልሆነላቸው ተናግረዋል። ሆኖም ቅዱሳን መጻሕፍትን ማንበብ ሊደረግ የሚገባው ነገር እንደሆነ ስለተገነዘቡ ማንበባቸውን ቀጥለዋል። ማርክ እንዲህ ይላል፦ “መጽሐፍ ቅዱስን በማነብበትና የግል ጥናት በማደርግበት ጊዜ ሐሳቤ በቀላሉ ይበታተናል። የመጽሐፍ ቅዱስ ንባብ በየዕለቱ ከማከናውናቸው ነገሮች መካከል እንዲሆን ለማድረግ ደጋግሜ መጸለይና ብዙ ጥረት ማድረግ ጠይቆብኛል።”

አንተስ በጽሑፍ ለሰፈረው የአምላክ ቃል ይኸውም ለመጽሐፍ ቅዱስ ይበልጥ አድናቆት እንዲኖርህ ምን ማድረግ ትችላለህ? መጽሐፍ ቅዱስን ማንበብ አስደሳች እንዲሆንልህ ማድረግ የምትችለውስ እንዴት ነው? ከዚህ በታች የቀረቡትን ሐሳቦች ተመልከት።

ግቦችና ዘዴዎች

መጽሐፍ ቅዱስን ማንበብ ከመጀመርህ በፊት ጸልይ፤ እንዲሁም ትኩረትህን ለመሰብሰብ ሞክር። ይሖዋ ቃሉን ለማጥናት ጉጉት እንድታዳብር እንዲረዳህ በጸሎት ጠይቀው። የእሱን ጥበብ ይበልጥ በተሟላ መልኩ መረዳት እንድትችል አእምሮህንና ልብህን እንዲከፍትልህ ተማጸነው። (መዝ. 119:34) ጥናትህን በዚህ ዓይነት መንገድ ካልጀመርህ መጽሐፍ ቅዱስን ማጥናት እንዲሁ ማድረግ ስላለብህ ብቻ የምታደርገው ነገር ሊሆንብህና ፍላጎትህ ሊጠፋ ይችላል። ሊን እንዲህ ትላለች፦ “አንዳንድ ጊዜ በፍጥነት ሳነብ ጥሩ ጥሩ ነጥቦችን ልብ ሳልል አልፋለሁ። ብዙውን ጊዜ ዋና ዋናዎቹ ሐሳቦች ሙሉ በሙሉ አይገቡኝም። ይሁንና ራሴን መግዛት እንድችል መጸለዬ አእምሮዬ እንዳይባዝን ለማድረግ ረድቶኛል።”

የምታጠናውን ነገር ከፍ አድርገህ ተመልከተው። መጽሐፍ ቅዱስ የያዛቸውን እውነቶች መረዳትና በሥራ ላይ ማዋል የዘላለም ሕይወት እንደሚያስገኝልህ አስታውስ። ስለዚህ ተግባራዊ ሊሆኑ የሚችሉ ነጥቦችን ለማግኘትና በሥራ ላይ ለማዋል ልባዊ ጥረት አድርግ። ክሪስ “በውስጤ ያሉ የተሳሳቱ አመለካከቶችንና ዝንባሌዎችን ለማስተዋል የሚረዱኝን ነጥቦች ከማነበው ነገር ላይ ለማግኘት እሞክራለሁ” በማለት ይናገራል። “መጽሐፍ ቅዱስንም ሆነ አብዛኞቹን ጽሑፎቻችንን የጻፉት ሰዎች ባያውቁኝም እንኳ የጻፏቸው ነገሮች በግለሰብ ደረጃ የሚጠቅመኝ እውቀት የያዙ መሆናቸው ያስደስታል።”

ልትደርስባቸው የምትችላቸውን ግቦች አውጣ። በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ስለተጠቀሱት ሰዎች አዳዲስ የሆኑ ነገሮችን ለማወቅ ጥረት አድርግ። ቅዱሳን ጽሑፎችን ጠለቅ ብሎ ማስተዋል (እንግሊዝኛ) ወይም የመጠበቂያ ግንብ ማኅበር ጽሑፎች ማውጫ (እንግሊዝኛ) በተባሉት መጻሕፍት አሊያም በቋንቋህ በሚገኙ ሌሎች የማኅበሩ ጽሑፎች ላይ ምርምር በማድረግ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ከተጠቀሱት ሰዎች መካከል ስለ ብዙዎቹ አስደናቂ ሐሳቦችን ልታገኝ ትችላለህ። በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የተጠቀሱት ወንዶችና ሴቶች የራሳቸው ስብዕና እንዲሁም ስሜት ያላቸው እውነተኛ ሰዎች እንደሆኑ እየተገነዘብህ ስትሄድ ከእነሱ በምታገኘው ትምህርት ይበልጥ ትጠቀማለህ።

ቅዱሳን መጻሕፍትን የምታስረዳባቸው አዳዲስ መንገዶችን ፈልግ። (ሥራ 17:2, 3) ሶፊያ የምታጠናው እንዲህ ያለ ግብ ይዛ ነው። እንዲህ ብላለች፦ “ዓላማዬ በአገልግሎት ላይም ሆነ በሌሎች ጊዜያት ሰዎችን የማስረዳባቸው አዳዲስ መንገዶች ማግኘት ነው፤ ይህን ማድረጌ የመጽሐፍ ቅዱስን እውነቶች በግልጽ ለማብራራት ይረዳኛል። በመጠበቂያ ግንብ ላይ ሐሳቡ የሚቀርብበት መንገድ በዚህ ረገድ ጥሩ ምሳሌ ነው።”​—2 ጢሞ. 2:15

የመጽሐፍ ቅዱስን ዘገባዎች በዓይነ ሕሊናህ ለመመልከት ሞክር። ዕብራውያን 4:12 “የአምላክ ቃል ሕያው . . . ነው” በማለት ይናገራል። መጽሐፍ ቅዱስን ስታነብ ባለ ታሪኮቹ ያዩትን ነገር በዓይነ ሕሊናህ በመመልከት የአምላክ መልእክት ሕያው እንዲሆንልህ አድርግ። ባለ ታሪኮቹ የሰሙትን ነገር ለመስማትና ስሜታቸውን ለመረዳት ሞክር። ያጋጠሟቸውን ነገሮች በሕይወትህ ውስጥ ከሚከሰቱ አንዳንድ ሁኔታዎች ጋር ለማያያዝ ጥረት አድርግ። ያጋጠሟቸውን ሁኔታዎች ከተወጡባቸው መንገዶች ትምህርት ውሰድ። እንዲህ ማድረግህ የመጽሐፍ ቅዱስን ታሪኮች ይበልጥ እንድትረዳና እንድታስታውስ ያስችልሃል።

ከበድ የሚሉ ጥቅሶችን በደንብ መረዳት እንድትችል ለእነዚህ ጥቅሶች የተሰጠውን ማብራሪያ ጊዜ ወስደህ መርምር። ለእያንዳንዱ የጥናት ፕሮግራም በቂ ጊዜ መድብ። ተጨማሪ ምርምር ማድረግ የሚሹ ጥያቄዎች በጥናትህ ወቅት ያጋጥሙህ ይሆናል። ትርጉማቸውን የማታውቃቸውን ቃላት ፍቺ ለማወቅ ሞክር፤ የግርጌ ማስታወሻዎቹንና በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ያሉትን ማጣቀሻዎች አመሳክር። የምታነበውን ነገር ይበልጥ በተረዳኸውና በሥራ ላይ ባዋልከው መጠን በጽሑፍ በሰፈረው የአምላክ ቃል ይበልጥ ትደሰታለህ። አንተም “[የይሖዋ ምስክርነት] የዘላለም ውርሴ ናት፤ ልቤ በዚህ ሐሤት ያደርጋልና” በማለት እንደተናገረው መዝሙራዊ ማለት ትችላለህ።​—መዝ. 119:111

የምታጠናውን ነገር ቶሎ ለመጨረስ አትጣደፍ። ለግል ጥናት በምትመድበው ጊዜ ረገድ ምክንያታዊ ሁን። ለጥናት የምትመድበውን ጊዜ ለጉባኤ ስብሰባዎች ለመዘጋጀት ከምታውለው ጊዜ ጋር አመጣጥን። ራኬል “ብዙ ጊዜ ውጥረት ስለሚሰማኝ ትኩረት ማድረግ ያቅተኛል” በማለት ትናገራለች። “በመሆኑም አጠር ላለ ጊዜ ማጥናቱን ጠቃሚ ሆኖ አግኝቼዋለሁ። በጥናት የማሳልፋቸው ጊዜያት አጠር ያሉ መሆናቸው ከጥናቴ ከፍተኛ ጥቅም እንዳገኝ ረድቶኛል።” ክሪስም እንዲህ ብሏል፦ “ጥናቴን በጥድፊያ ሳከናውን ካጠናሁት ነገር ላይ ማስታወስ የምችለው በጣም ጥቂት ስለሚሆን ሕሊናዬ ይወቅሰኛል። አብዛኛውን ጊዜ የማጠናው ነገር ወደ ልቤ ጠልቆ አይገባም።” እንግዲያው ለጥናት በቂ ጊዜ መድብ።

ለአምላክ ቃል ጉጉት አዳብር። ሐዋርያው ጴጥሮስ እንዲህ ብሏል፦ “ገና እንደተወለዱ ሕፃናት በአምላክ ቃል ውስጥ ለሚገኘው ያልተበረዘ ወተት ጉጉት አዳብሩ፤ ይህም በእሱ አማካኝነት ወደ መዳን ማደግ እንድትችሉ ነው።” (1 ጴጥ. 2:2) ሕፃናት ለእናታቸው ጡት ጉጉት ማሳደር አያስፈልጋቸውም። ይህ በተፈጥሮ የሚመጣ ነገር ነው። ለአምላክ ቃል ግን ጉጉት ማሳደር እንደሚያስፈልገን ቅዱሳን መጻሕፍት ይገልጻሉ። በየቀኑ ከመጽሐፍ ቅዱስ አንድ ገጽ ብቻ እንኳ ብታነብ ብዙም ሳትቆይ እንዲህ ያለ ጉጉት ታዳብራለህ። መጽሐፍ ቅዱስን ማንበብ መጀመሪያ ላይ ከባድና አሰልቺ ቢመስልም እያደር አስደሳች ይሆንልሃል።

ባነበብካቸው ጥቅሶች ላይ አሰላስል። ባነበብከው ነገር ላይ ማሰላሰልም ብዙ ጥቅሞች ያስገኛል። ይህም የመረመርካቸው መንፈሳዊ ርዕሰ ጉዳዮች እርስ በርስ ያላቸውን ግንኙነት ለማስተዋል ይረዳሃል። ውሎ አድሮም በአንገት ዙሪያ እንደሚደረግ ጌጥ የሆኑ መንፈሳዊ የጥበብ ዕንቁዎች ይኖሩሃል፤ ይህ ደግሞ አስደሳች የሆነ ሀብት ነው።​—መዝ. 19:14፤ ምሳሌ 3:3

ጊዜ ቢመደብለት የማያስቆጭ ልማድ

ጥሩ የጥናት ልማድን በጥብቅ መከተል ጥረት የሚጠይቅ ቢሆንም የሚያስገኛቸው በረከቶች እጅግ ብዙ ናቸው። ይህን ስታደርግ መንፈሳዊ ነገሮችን የመረዳት ችሎታህ እያደገ ይሄዳል። (ዕብ. 5:12-14) በመንፈስ መሪነት ከተጻፉት ቅዱሳን መጻሕፍት ማስተዋልና ጥበብ ማግኘትህ ደስታ እንዲሁም ሰላም ያስገኝልሃል። በመንፈስ መሪነት በተጻፈው የአምላክ ቃል ውስጥ የሚገኘው ጥበብ ለሚይዙትና ተግባራዊ ለሚያደርጉት “የሕይወት ዛፍ” ነው።​—ምሳሌ 3:13-18

የአምላክን ቃል በጥልቀት ማጥናት አስተዋይ ልብ እንዲኖርህ ያደርጋል። (ምሳሌ 15:14) ይህ ደግሞ በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተመሠረተ ከልብ የመነጨ ምክር ለመስጠት ይረዳሃል። ከቅዱሳን መጻሕፍት እንዲሁም “ታማኝና ልባም ባሪያ” ከሚያዘጋጃቸው ጽሑፎች በምታነበው ነገር ላይ ተመሥርተህ ውሳኔዎች የምታደርግ ከሆነ በመንፈስ መሪነት የተጻፈው የይሖዋ ቃል የሚያሳድረውን ደስ የሚያሰኝና የሚያረጋጋ መንፈስ ታገኛለህ። (ማቴ. 24:45) ይበልጥ አዎንታዊና ብሩህ አመለካከት ያለህ እንዲሁም መንፈሳዊ ሰው ትሆናለህ። ከዚህም በተጨማሪ ከአምላክ ጋር ካለህ ዝምድና ጋር በተያያዘ ሁሉ ነገር ይሳካልሃል።​—መዝ. 1:2, 3

ልብህ ለአምላክ ባለህ ፍቅር ሲሞላ እምነትህን ለሌሎች እንድታካፍል ያነሳሳሃል። ይህም በጣም የሚክስ ነው። ሶፊያ የቤት ባለቤቶችን ትኩረት የሚስቡ የተለያዩ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅሶችን ለማስታወስና ለመጠቀም እየጣረች ሲሆን ይህም ክርስቲያናዊ አገልግሎቷ ውጤታማና አስደሳች እንዲሆን አድርጓል። “ሰዎች ከመጽሐፍ ቅዱስ ላይ ለሚነበብላቸው ነገር የሚሰጡትን ምላሽ መመልከት በጣም ያስደስታል” ትላለች።

በአምላክ ቃል መደሰት የሚያስገኘው ከሁሉ የላቀው ጥቅም ከይሖዋ ጋር የጠበቀ ዝምድና መመሥረት ነው። መጽሐፍ ቅዱስን ማጥናት የይሖዋን መሥፈርቶች እንድታውቅ እንዲሁም ፍቅሩን፣ ለጋስነቱንና ፍትሑን እንድትገነዘብ ብሎም ከፍ አድርገህ እንድትመለከት ያስችልሃል። ከዚህ ይበልጥ ጠቃሚ ወይም አርኪ የሆነ ሌላ ምን ነገር አለ! እንግዲያው የአምላክን ቃል በማጥናት ተጠመድ። በእርግጥም ይህ ጊዜ ቢመደብለት የማያስቆጭ ልማድ ነው!​—መዝ. 19:7-11

[በገጽ 5 ላይ የሚገኝ ሣጥን/​ሥዕሎች]

የአምላክን ቃል ለማጥናት የሚረዱ ግቦችና ዘዴዎች

▪ መጽሐፍ ቅዱስን ማንበብ ከመጀመርህ በፊት ጸልይ፤ እንዲሁም ትኩረትህን ለመሰብሰብ ሞክር።

▪ የምታጠናውን ነገር ከፍ አድርገህ ተመልከተው።

▪ ልትደርስባቸው የምትችላቸውን ግቦች አውጣ።

▪ ቅዱሳን መጻሕፍትን የምታስረዳባቸው አዳዲስ መንገዶችን ፈልግ።

▪ የመጽሐፍ ቅዱስን ዘገባዎች በዓይነ ሕሊናህ ለመመልከት ሞክር።

▪ ከበድ የሚሉ ጥቅሶችን በደንብ መረዳት እንድትችል ለእነዚህ ጥቅሶች የተሰጠውን ማብራሪያ ጊዜ ወስደህ መርምር።

▪ የምታጠናውን ነገር ቶሎ ለመጨረስ አትጣደፍ።

▪ ለአምላክ ቃል ጉጉት አዳብር።

▪ ባነበብካቸው ጥቅሶች ላይ አሰላስል።

[በገጽ 4 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

አንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ዘገባ ስታነብ አንተም በታሪኩ ውስጥ እንዳለህ አድርገህ አስብ