በሰላም ለመኖር ጥረት አድርጉ
ታስታውሳለህ?
በቅርቡ የወጡትን የመጠበቂያ ግንብ እትሞች በማንበብ ተጠቅመሃል? እስቲ የሚከተሉትን ጥያቄዎች ለመመለስ ሞክር፦
• ሐቀኝነት የጎደለው ተግባር እንድንፈጽም የሚገፋፋንን ዝንባሌ ለመቋቋም የሚረዱን ሦስት ቁልፍ ነገሮች ምንድን ናቸው?
(1) ለይሖዋ ጤናማ ፍርሃት ማዳበር። (1 ጴጥ. 3:12) (2) በመጽሐፍ ቅዱስ የሠለጠነ ሕሊና ማዳበር። (3) ባለን ነገር የመርካት ዝንባሌ ለመያዝ መጣር።—4/15 ገጽ 6, 7
• ለይሖዋ የምናቀርበውን አገልግሎት በቁም ነገር መመልከት ሲባል ሁልጊዜ ኮስታራ መሆን አለብን ወይም ከሌሎች ጋር ዘና ያለና አስደሳች ጊዜ ማሳለፍ አንችልም ማለት እንዳልሆነ እንዴት እናውቃለን?
በዚህ ረገድ የኢየሱስን ምሳሌ መመልከት እንችላለን። ከሰዎች ጋር አብሮ ምግብ በመመገብ ዘና ያለ ጊዜ ያሳልፍ ነበር። ምንጊዜም ፊቱ የማይፈታ ወይም ኮስታራ እንዳልነበረ እናውቃለን። ሰዎች ሌላው ቀርቶ ልጆች እንኳ ይቀርቡት እንዲሁም ከእሱ ጋር መሆን ደስ ይላቸው ነበር።—4/15 ገጽ 10
• አንድ ባልና ሚስት ልጆች ከወለዱ በኋላ በመካከላቸው ያለው ቅርበት እንደ ድሮው እንዳልሆነ ከተሰማቸው ምን ማድረግ ይችላሉ?
አንዳቸው ለሌላው ያላቸውን ፍቅር በድጋሚ ማረጋገጥ ያስፈልጋቸዋል። አንድ ባል ሚስቱ ሊያጋጥማት የሚችለውን ያለመረጋጋትና የመጣል ስሜት ለማስወገድ ጥረት ማድረግ ይኖርበታል። ከዚህም በተጨማሪ ባልና ሚስት ከስሜታቸውና ከፍላጎታቸው ጋር በተያያዘ ግልጽ ውይይት ማድረግ ያስፈልጋቸዋል።—5/1 ገጽ 12, 13
• በሮም ምዕራፍ 11 ላይ የተጠቀሰው የወይራ ዛፍ የምን ምሳሌ ነው?
የወይራው ዛፍ፣ የአብርሃም ዘር ሁለተኛ ክፍል ከሆኑት መንፈሳዊ እስራኤላውያን ጋር የተያያዘ ነው። የዚህ ምሳሌያዊ የወይራ ዛፍ ሥር ይሖዋን የሚያመለክት ሲሆን ኢየሱስ ደግሞ የዛፉ ግንድ ነው። አብዛኞቹ ሥጋዊ አይሁዳውያን ኢየሱስን ለመቀበል ፈቃደኞች ባለመሆናቸው ወደ ክርስትና የመጡ አሕዛብ በምሳሌያዊው የወይራ ዛፍ ላይ መጣበቅ ቻሉ፤ በዚህ መንገድ ይሖዋ የአብርሃም ዘር ሁለተኛ ክፍል የሚሆኑት ቁጥር እንዲሞላ አድርጓል።—5/15 ከገጽ 22-25
• ለድሆች ምን ልዩ ምሥራች ልንነግራቸው እንችላለን?
ለድሆች የሚሆነው ምሥራች የሚከተለው ነው፦ አምላክ ኢየሱስን ንጉሥ አድርጎ ሾሞታል። ኢየሱስ ድህነትን ለማጥፋት የሚያስችል ብቃት ያለው መሪ ነው። እንዲህ የምንለው ለምንድን ነው? ምክንያቱም የሚገዛው መላውን የሰው ዘር ከመሆኑም በላይ እርምጃ ለመውሰድ የሚያስችል ኃይል አለው፤ ለድሆች ይራራል። የድህነትን መንስኤ ይኸውም ከአዳም የወረስነውን የራስ ወዳድነት ዝንባሌ የማስወገድ ችሎታ አለው።—6/1 ገጽ 7
• ኢየሱስ ቀያፋን “አንተው ራስህ ተናገርከው” ሲለው ምን ማለቱ ነበር?—ማቴ. 26:63, 64
“አንተው ራስህ ተናገርከው” የሚለው አባባል አንድ ነገር እውነት መሆኑን ለማረጋገጥ አይሁዳውያን የሚጠቀሙበት የተለመደ ዘይቤያዊ አነጋገር ሳይሆን አይቀርም። ሊቀ ካህናቱ ቀያፋ፣ ኢየሱስ የአምላክ ልጅ ክርስቶስ መሆን አለመሆኑን እንዲነግረው ጠይቆት ነበር። ኢየሱስ “አንተው ራስህ ተናገርከው” ብሎ መመለሱ ሊቀ ካህናቱ የተናገረው ነገር ትክክል መሆኑን የሚያረጋግጥ ነበር።—6/1 ገጽ 18
• ፍጹም ሰው በነበረው በኢየሱስ አብራክ የነበሩ ልጆች የቤዛው ክፍል ሊሆኑ ይችላሉ?
አይችሉም። ፍጹም ሰው የነበረው ኢየሱስ በቢሊዮን የሚቆጠሩ ፍጹም ልጆች ሊኖሩት ይችል የነበረ ቢሆንም በአብራኩ የነበሩት ልጆች የቤዛው ክፍል አይደሉም። ከአዳም ጋር ተመጣጣኝ ቤዛ የሚሆነው የኢየሱስ ፍጹም ሕይወት ብቻ ነው። (1 ጢሞ. 2:6)—6/15 ገጽ 13
• ክርስቲያኖች በሐዋርያት ሥራ 20:29, 30 ላይ ስለ ሐሰተኛ አስተማሪዎች የተሰጠውን ማስጠንቀቂያ ልብ እንደሚሉ የሚያሳዩት እንዴት ነው?
ሐሰተኛ አስተማሪዎችን በቤታቸው አይቀበሏቸውም ወይም ሰላም አይሏቸውም። (ሮም 16:17፤ 2 ዮሐ. 9-11) ክርስቲያኖች የከሃዲዎችን ጽሑፎች አያነቡም፣ እነሱ የሚቀርቡባቸውን የቴሌቪዥን ፕሮግራሞች አይመለከቱም ወይም የእነሱ ትምህርት የሚወጣባቸውን ድረ ገጾች አይቃኙም።—7/15 ገጽ 15, 16
• ልጆችን ስለ አምላክ ማስተማር ያለበት ማን ነው?
መጽሐፍ ቅዱስ እንደሚለው አባትም ሆነ እናት በዚህ ረገድ ድርሻ ሊኖራቸው ይገባል። (ምሳሌ 1:8፤ ኤፌ. 6:4) ጥናቶች እንደሚያሳዩት ሁለቱም ወላጆች በዚህ ረገድ ተሳትፎ ሲኖራቸው ልጆቹ ይጠቀማሉ።—8/1 ገጽ 6, 7