በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

‘ምንጊዜም ነቅቶ መጠበቅ’ በጣም አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው?

‘ምንጊዜም ነቅቶ መጠበቅ’ በጣም አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው?

‘ምንጊዜም ነቅቶ መጠበቅ’ በጣም አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው?

“የመገኘትህና የዚህ ሥርዓት መደምደሚያ [ምልክት] ምንድን ነው?” (ማቴ. 24:3) ኢየሱስ ደቀ መዛሙርቱ ለጠየቁት ለዚህ ጥያቄ መልስ ሲሰጥ በ⁠ማቴዎስ ምዕራፍ 24 እና በ⁠ማርቆስ ምዕራፍ 13 እንዲሁም በ⁠ሉቃስ ምዕራፍ 21 ላይ የሚገኘውን ግልጽ፣ ዝርዝር ሐሳቦችን የያዘ፣ በቀላሉ የሚለይና የማያምታታ ምልክት ተናግሯል። በተጨማሪም “ምንጊዜም ነቅታችሁ ጠብቁ” ብሏቸዋል።​—ማቴ. 24:42

ምልክቱ በግልጽ የሚታይ ከሆነ ተጨማሪ ማስጠንቀቂያ መስጠት ለምን አስፈለገ? መልስ ሊሆኑ የሚችሉ ሁለት ምክንያቶችን እንመልከት። በመጀመሪያ፣ አንዳንዶች ትኩረታቸውን ሊሰርቁ በሚችሉ ነገሮች ሳቢያ ምልክቱን ችላ ሊሉት ይችላሉ፤ ይህ ደግሞ መንፈሳዊ ኪሳራ የሚያስከትልባቸው ከመሆኑም ሌላ ነቅተው እንዳይጠብቁ ያደርጋቸዋል። ሁለተኛ፣ አንድ ክርስቲያን አንዳንድ የምልክቱን ገጽታዎች ቢያስተውልም እነዚህ ነገሮች በአካባቢው እየተፈጸሙ ባለመሆናቸው ነገሩ እሱን እንደማይነካው ሊሰማው ይችላል። በመሆኑም ኢየሱስ የተናገረው ትንቢት ፍጻሜ የሆነው ‘ታላቁ መከራ’ የሚመጣው ገና ወደፊት እንደሆነና በአሁኑ ወቅት ‘ምንጊዜም ነቅቶ መጠበቅ’ ያን ያህል አስፈላጊ እንዳልሆነ ሊያስብ ይችላል።​—ማቴ. 24:21

“ምንም አላስተዋሉም”

ኢየሱስ በኖኅ ዘመን ስለነበሩት ሰዎች መለስ ብለው እንዲያስቡ ተከታዮቹን አሳስቧቸዋል። የኖኅ ስብከት፣ ይገነባ የነበረው ግዙፍ መርከብና በዘመኑ ተንሰራፍቶ የነበረው ዓመፅ ከሰዎች እይታ የተሰወረ ነገር አልነበረም። ያም ሆኖ አብዛኞቹ ሰዎች “ምንም አላስተዋሉም።” (ማቴ. 24:37-39) በዛሬው ጊዜም ማስጠንቀቂያዎችን በተመለከተ ተመሳሳይ አስተሳሰብ ተስፋፍቷል። ለምሳሌ ያህል፣ የፍጥነት ወሰን ምልክቶች ግልጽ የሆነ መልእክት የሚያስተላልፉ ቢሆኑም ብዙዎች ችላ ይሏቸዋል። ስለሆነም ባለሥልጣናት፣ አሽከርካሪዎች ፍጥነታቸውን እንዲቀንሱ የሚያስገድዱ ነገሮችን በከተማ ጎዳናዎች ላይ ለመሥራት ተገደዋል። በተመሳሳይም አንድ ክርስቲያን የመጨረሻዎቹ ቀኖች ምልክት እየተፈጸመ እንዳለ ቢገነዘብም አኗኗሩ ይህን የሚያሳይ ላይሆን ይችላል። በምዕራብ አፍሪካ የምትኖረው አሪኤል እንዲህ ያለ ሁኔታ አጋጥሟት ነበር።

አሪኤል የሴቶች የእጅ ኳስ ጨዋታ በቴሌቪዥን ሲተላለፍ መመልከት ያስደስታት ነበር። በምትማርበት ትምህርት ቤት ውስጥ የእጅ ኳስ ቡድን ሲቋቋም፣ ለመጫወት ያላት ጉጉት መንፈሳዊነቷን ለአደጋ ሊያጋልጡ የሚችሉ ነገሮችን እንዳታስተውል አደረጋት። በዚህ ቡድን ውስጥ ግብ ጠብቂ ሆና ተመዘገበች። ከዚያስ ምን አጋጠማት? እንዲህ ብላለች፦ “ከቡድኔ አባላት መካከል አንዳንዶቹ ዕፅ የሚወስዱና የሚያጨሱ የወንድ ጓደኞች ነበሯቸው። ከሌሎች የተለየሁ በመሆኔ ያፌዙብኝ ጀመር፤ ቢሆንም ይህን መቋቋም እንደምችል አሰብኩ። ይሁን እንጂ ስፖርቱ ራሱ ሳላስበው መንፈሳዊነቴን እያዳከመው መጣ። የማስበውና የማልመው ስለ እጅ ኳስ ብቻ ሆነ። በክርስቲያናዊ ስብሰባዎች ላይ ብገኝም ብዙውን ጊዜ ሐሳቤ ያለው ጨዋታው ላይ ነበር። የነበሩኝ ጥሩ ክርስቲያናዊ ባሕርያትም እየጠፉ ሄዱ። እጅ ኳስ ለመጫወት የነበረኝ ፍቅር መልኩን ቀየረና የማሸነፍ ስሜት ተጠናወተኝ። ይህን የማሸነፍ ጥማት ለማርካት ስል ቀን ከሌት ልምምድ አደርግ ነበር። በዚህም የተነሳ ውጥረት ውስጥ ገባሁ። ለእጅ ኳስ ስል ወዳጆቼን እንኳ እስከማጣት ደረስኩ።

“ያለሁበትን ሁኔታ ማስተዋል የቻልኩት በአንድ ጨዋታ ላይ የተቃራኒው ቡድን ፍጹም ቅጣት ምት በተሰጠው ጊዜ ነበር። ጎል እንዳይገባብኝ ለመጠበቅ በተጠንቀቅ ቆምኩ። በዚህ ጊዜ ኳሱን መያዝ እንድችል ይሖዋ እንዲረዳኝ ሳላስበው ጸለይኩ! ይህ አጋጣሚ መንፈሳዊነቴ ምን ያህል እንደተዳከመ እንድገነዘብ አደረገኝ። ታዲያ መንፈሳዊ አቋሜን እንደገና ለማስተካከል የቻልኩት እንዴት ነው?

“የወጣቶች ጥያቄ​ሕይወቴን እንዴት ብጠቀምበት ይሻላል? * የተሰኘውን ፊልም ከዚህ ቀደም አይቼው ነበር። በዚህ ጊዜ ግን ይህን ፊልም እንደገና ላየውና በቁም ነገር ላስብበት እንደሚገባ ተሰማኝ። እኔም ፊልሙ ላይ የሚታየው አንድሬ የተባለ ወጣት ያጋጠመው ዓይነት አጣብቂኝ ውስጥ ገብቼ ነበር። በተለይ ደግሞ አንድ ሽማግሌ ለአንድሬ በሰጠው ሐሳብ ላይ ትኩረት አደረግሁ፤ ሽማግሌው ፊልጵስዩስ 3:8⁠ን እንዲያነብበውና እንዲያሰላስልበት አንድሬን መክሮት ነበር። እኔም ይህን ማድረጌ ረድቶኛል። በመጨረሻም ከእጅ ኳስ ቡድኑ ወጣሁ።

“ይህም በሕይወቴ ውስጥ ትልቅ ለውጥ አመጣ! የተጠናወተኝ የፉክክር መንፈስና ይህ ያስከተለብኝ ውጥረት ተወገደልኝ። ደስታዬ የጨመረ ከመሆኑም ሌላ ከክርስቲያን ጓደኞቼ ጋር ይበልጥ ተቀራረብኩ። መንፈሳዊ እንቅስቃሴዎች ይበልጥ ትርጉም ይሰጡኝ ጀመር። በጉባኤ ስብሰባዎች ላይ በትኩረት የማዳምጥ ሲሆን ስብሰባዎች እንደ በፊቱ አስደሳች ሆኑልኝ። አገልግሎቴም እየተሻሻለ መጣ። አሁን በቋሚነት ረዳት አቅኚ ሆኜ አገለግላለሁ።”

ትኩረትህን የሚከፋፍል አንድ ነገር ኢየሱስ የሰጠንን የማስጠንቀቂያ ምልክት ችላ እንድትል እያደረገህ ከሆነ ልክ እንደ አሪኤል ቁርጥ እርምጃ ውሰድ። ከዚህ ቀጥሎ የቀረቡትን ሐሳቦች ተግባራዊ ለማድረግ ሞክር። የተደበቀ ሀብት ለማግኘት የሚረዳ ካርታ ተብሎ የተገለጸውን የመጠበቂያ ግንብ ማኅበር ጽሑፎች ማውጫ (እንግሊዝኛ) ተመልከት። ይህ ማውጫ፣ ግሩም ምክሮችን እንዲሁም ሌሎች ሰዎች ያጋጠሟቸውን ፈተናዎች እንዴት እንደተወጡ ራሳቸው የተናገሩትን ሐሳብ የያዙ ጽሑፎችን ይጠቁምሃል። ጥሩ ዝግጅት በማድረግና ማስታወሻ በመያዝ ከክርስቲያናዊ ስብሰባዎች የተሟላ ጥቅም ለማግኘት ጥረት አድርግ። አንዳንዶች ከፊት ባሉት ወንበሮች ላይ መቀመጥ ጠቃሚ እንደሆነ ተገንዝበዋል። የሚቀርበው ክፍል አድማጮች የሚሳተፉበት ከሆነ ገና ከመጀመሪያው ሐሳብ ለመስጠት ጥረት አድርግ። ከዚህም በተጨማሪ በየጊዜው የምትሰማውን ዜና ከምልክቱ ገጽታዎችና ‘የመጨረሻዎቹ ቀኖች’ መለያ ከሆኑት የሰዎች ባሕርያት ጋር በማዛመድ በመንፈሳዊ ምንጊዜም ንቁ ሆነህ መኖር ትችላለህ።​—2 ጢሞ. 3:1-5፤ 2 ጴጥ. 3:3, 4፤ ራእይ 6:1-8

“ዝግጁ ሁኑ”

የመጨረሻዎቹ ቀኖች ምልክት “በመላው ምድር” ላይ የሚፈጸምና ዓለም አቀፋዊ ይዘት ያለው ነው። (ማቴ. 24:7, 14) በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች በቸነፈር፣ በምግብ እጥረት፣ በምድር ነውጥና አስቀድመው በተነገሩት ሌሎች ክንውኖች እየተጠቁ ባሉ አካባቢዎች ይኖራሉ። ከዚህ በተቃራኒ ደግሞ በአንጻራዊ ሁኔታ ሰላምና መረጋጋት በሰፈነባቸው አካባቢዎች የሚኖሩ ሰዎች አሉ። አንዳንድ የምልክቱ ገጽታዎች በግለሰብ ደረጃ ጨርሶ ነክተውህ የማያውቁ ከሆነ ታላቁ መከራ የሚመጣበት ጊዜ ገና ሩቅ እንደሆነ አድርገህ ማሰብ ይኖርብሃል? ይህ ጥበብ የጎደለው አካሄድ ነው።

ኢየሱስ ስለ “ቸነፈርና የምግብ እጥረት” የተናገረውን ትንቢት እንደ ምሳሌ እንውሰድ። (ሉቃስ 21:11) በመጀመሪያ ደረጃ፣ ኢየሱስ እነዚህ ሁኔታዎች በሁሉም ስፍራ በአንድ ጊዜ ወይም በእኩል መጠን እንደሚከሰቱ አልተናገረም። ከዚህ ይልቅ እነዚህ ነገሮች “በተለያየ ስፍራ” እንደሚከሰቱ ገልጿል። በመሆኑም በሁሉም ስፍራዎች ተመሳሳይ ክንውኖች በአንድ ጊዜ እንደሚፈጸሙ መጠበቅ የለብንም። በሁለተኛ ደረጃ፣ ኢየሱስ የምግብ እጥረት እንደሚኖር ከተናገረ ብዙም ሳይቆይ ከተከታዮቹ መካከል አንዳንዶቹ ከልክ በላይ ላለመብላት መጠንቀቅ እንዳለባቸው ገልጿል፤ “ከልክ በላይ በመብላት . . . ልባችሁ ሸክም እንዳይበዛበት ለራሳችሁ ተጠንቀቁ” ብሎ ነበር። (ሉቃስ 21:34) እንግዲያው ሁሉም ክርስቲያኖች የምልክቱ ገጽታዎች በሙሉ በእነሱ ላይ እንደሚፈጸሙ መጠበቅ የለባቸውም። ኢየሱስ “እነዚህ ነገሮች ሲከሰቱ ስታዩ የአምላክ መንግሥት እንደቀረበ እወቁ” ብሏል። (ሉቃስ 21:31) በአካባቢያችን ያለው ሁኔታ ምንም ይሁን ምን በዘመናዊ የመገናኛ ዘዴዎች አማካኝነት የምልክቱ ገጽታዎች በሙሉ ሲፈጸሙ ማየት እንችላለን።

ከዚህም ሌላ፣ ይሖዋ ታላቁ መከራ የሚጀምርበትን “ቀንና ሰዓት” አስቀድሞ እንደወሰነ አስታውስ። (ማቴ. 24:36) በምድር ላይ የሚከሰቱት ነገሮች እሱ በወሰነው ቀን ላይ ለውጥ አያመጡም።

ኢየሱስ በየትኛውም ቦታ ለሚኖሩ ክርስቲያኖች “ዝግጁ ሁኑ” የሚል ማሳሰቢያ ሰጥቷል። (ማቴ. 24:44) ምንጊዜም ዝግጁ መሆን ይኖርብናል። እርግጥ ነው፣ እያንዳንዱን ቀን በቲኦክራሲያዊ እንቅስቃሴዎች ተጠምደን ማሳለፍ አንችልም። ከዚህም ሌላ ታላቁ መከራ በሚጀምርበት ጊዜ ምን እየሠራን እንደምንሆን ማናችንም ማወቅ አንችልም። አንዳንዶች በእርሻ ቦታ እየሠሩ ወይም በቤት ውስጥ ሥራዎች ተጠምደው ሊሆኑ ይችላሉ። (ማቴ. 24:40, 41) ታዲያ ዝግጁ ሆነን ለመገኘት ምን ማድረግ እንችላለን?

ኢማኑዌል እና ቪክቶሪን ከስድስት ሴቶች ልጆቻቸው ጋር በአንድ የአፍሪካ አገር ውስጥ የሚኖሩ ሲሆን የምልክቱ ገጽታዎች በሙሉ በአካባቢያቸው ሲፈጸሙ የማየት አጋጣሚ የላቸውም። በመሆኑም ምንጊዜም ዝግጁ ሆነው ለመጠበቅ እንዲረዳቸው ሲሉ በየዕለቱ በመንፈሳዊ ጉዳዮች ላይ ለመወያየት ወሰኑ። ኢማኑዌል እንዲህ ብሏል፦ “ለሁላችንም አመቺ የሆነ ጊዜ ማግኘት አስቸጋሪ ነበር። አመቺ ሆኖ ያገኘነው ሰዓት ማለዳ ላይ ከአሥራ ሁለት እስከ አሥራ ሁለት ተኩል ያለው ጊዜ ነበር። በዕለቱ ጥቅስ ላይ ከተወያየን በኋላ በዚያ ሳምንት በጉባኤ ከሚጠኑት ጽሑፎች አንዱን መርጠን የተወሰኑ አንቀጾችን እንዘጋጃለን።” ታዲያ ይህ ፕሮግራም ምንጊዜም ነቅተው እንዲጠብቁ ረድቷቸው ይሆን? እንዴታ! ኢማኑዌል በጉባኤው ውስጥ የሽማግሌዎች አካል አስተባባሪ ሆኖ ያገለግላል። ቪክቶሪን ብዙ ጊዜ ረዳት አቅኚ ሆና የምታገለግል ሲሆን ብዙዎች እውነትን እንዲያውቁ ረድታለች። ሴቶች ልጆቻቸው በሙሉ በመንፈሳዊ ጥሩ እድገት እያደረጉ ነው።

ኢየሱስ “ምንጊዜም በንቃት ተከታተሉ፣ ዘወትር ነቅታችሁ ጠብቁ” በማለት አሳስቦናል። (ማር. 13:33) ትኩረት የሚከፋፍሉ ነገሮች በመንፈሳዊ ምንጊዜም ነቅታችሁ እንዳትጠብቁ እንቅፋት እንዲሆኑባችሁ አትፍቀዱ። ይልቁንም አሪኤል እንዳደረገችው በጽሑፎቻችንና በክርስቲያናዊ ስብሰባዎች ላይ የምናገኛቸውን ግሩም ምክሮች አስተውሉ። እንዲሁም ዝግጁ ለመሆንና “ምንጊዜም ነቅታችሁ [ለመጠበቅ]” እንድትችሉ ልክ እንደ ኢማኑዌል ቤተሰብ፣ በየዕለቱ አንድ ዓይነት መንፈሳዊ እንቅስቃሴ ለማከናወን ጥረት አድርጉ።

[የግርጌ ማስታወሻ]

^ አን.8 አንድ ክርስቲያን ወጣት በይሖዋ ዓይን ትክክል የሆነውን ለማድረግ ሲል የሚያደርገውን ትግል የሚያሳይ ዘመናዊ ፊልም።

[በገጽ 4 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ኢማኑዌልና ቤተሰቡ በየዕለቱ በመንፈሳዊ ነገሮች ላይ መወያየታቸው ‘ዝግጁ እንዲሆኑ’ ረድቷቸዋል