ሽማግሌዎች “የዛለችውን ነፍስ” ታጽናናላችሁ?
አንጀላ * በ30ዎቹ ዕድሜ የምትገኝ ነጠላ እህት ናት። ሽማግሌዎች ሊጠይቋት ቤቷ እንደሚመጡ ማወቋ ትንሽ ረብሿታል። ምን ይሏት ይሆን? እርግጥ ነው፣ የተወሰኑ ቀናት ከጉባኤ ቀርታለች፤ ሆኖም ቀኑን ሙሉ አረጋውያንን ስትንከባከብ ስለምትውል ይደክማታል። ከኑሮ ውጣ ውረድ በተጨማሪ የእናቷ ጤንነት በጣም ያሳስባታል።
ለአንጀላ ጉብኝት የምታደርግላት አንተ ብትሆን ኖሮ ይህችን ‘የዛለች ነፍስ’ እንዴት ታበረታታት ነበር? (ኤር. 31:25) በቅድሚያ ግን የሚያጽናና የእረኝነት ጉብኝት ለማድረግ ምን ዓይነት ዝግጅት ማድረግ ይኖርብሃል?
ወንድሞችህ ስላሉበት ሁኔታ አስብ
በሰብዓዊ ሥራችን ወይም በቲኦክራሲያዊ ኃላፊነታችን ምክንያት የምንዝልበት ጊዜ ይኖራል። ለምሳሌ ነቢዩ ዳንኤል ያየውን ራእይ መረዳት ባቃተው ጊዜ ‘ዐቅሙ ተሟጦ’ ነበር። (ዳን. 2:48) በዚህ ጊዜ መልአኩ ገብርኤል በመገለጥ ረድቶታል። ይህ የአምላክ መልእክተኛ ለነቢዩ ራእዩን ያስረዳው ከመሆኑም ሌላ ይሖዋ ጸሎቱን እንደሰማው ማረጋገጫ ሰጥቶታል፤ እንዲሁም አሁንም ቢሆን ‘እጅግ የተወደደ’ እንደሆነ ገልጾለታል። (ዳን. 9:21-23) በሌላ ጊዜም ቢሆን ይህ ነቢይ፣ ሌላ መልአክ የሚያጽናና ሐሳብ በነገረው ጊዜ ከድካሙ ተበረታቷል።—ዳን. 10:19
አንተም በተመሳሳይ፣ የዛለ ወይም ተስፋ የቆረጠ የእምነት ባልንጀራህን ከመጎብኘትህ በፊት ይህ ወንድምህ ስላለበት ሁኔታ ጊዜ ወስደህ አስብ። ምን ዓይነት ችግሮችን እየተጋፈጠ ነው? እነዚህ ችግሮች ኃይሉን እያሟጠጡበት ያሉት እንዴት ነው? ምን ጥሩ ባሕርያት አሉት? ከ20 ዓመታት በላይ በሽምግልና ያገለገለ ሪቻርድ የተባለ አንድ ወንድም እንዲህ ብሏል፦ “ትኩረት የማደርገው በወንድሞቼ ጠንካራ ጎን ላይ ነው። እረኝነት ከማድረጌ በፊት ስላሉበት ሁኔታ ማሰቤ በወቅቱ የሚያስፈልጋቸውን ማበረታቻ ለመስጠት ቀላል እንዲሆንልኝ አድርጓል።” ጉብኝት ስታደርግ አብሮህ የሚሄድ ሌላ ሽማግሌ ካለ ስለ ወንድም ሁኔታ ለምን አብራችሁ አትነጋገሩም?
ወንድሞችህ ዘና ያለ ስሜት እንዲሰማቸው አድርግ
ስሜታችንን አውጥተን መናገር ትንሽ ሊከብደን እንደሚችል የታወቀ ነው። ለምሳሌ አንድ ወንድም፣ ሽማግሌዎች መጥተው ሲጎበኙት የልቡን አውጥቶ መናገር ሊከብደው ይችላል። ታዲያ በነፃነት እንዲናገር መርዳት የምትችለው እንዴት ነው? ከልብ የመነጨ ፈገግታ ማሳየትና ጥቂት የሚያጽናኑ ቃላትን መናገር ጥሩ ውጤት ሊያመጡ ይችላሉ። ከ40 ዓመታት በላይ በሽምግልና ያገለገለ ማይክል የተባለ ወንድም በጉብኝት ወቅት ውይይቱን እንደሚከተለው ብሎ መጀመሩን ጥሩ ሆኖ አግኝቶታል፦ “ይገርምሃል፣ ሽማግሌ መሆን ከሚያስገኛቸው ግሩም መብቶች መካከል አንዱ ወንድሞችን ቤታቸው ድረስ ሄዶ መጠየቅና እነሱን ይበልጥ ማወቅ ነው። ለዚህ ነው የዛሬውን ጉብኝት በጉጉት ስጠብቀው የነበረው።”
ምናልባትም በጉብኝቱ መጀመሪያ ላይ ልባዊ ጸሎት ማቅረብ ትመርጥ ይሆናል። ሐዋርያው ጳውሎስ በጸሎቱ ላይ ወንድሞች ያሳዩትን እምነት፣ ፍቅርና ጽናት ጠቅሷል። (1 ተሰ. 1:2, 3) ወንድም ስላሉት ግሩም ባሕርያት ምን እንደሚሰማህ በመግለጽ የአንተም ሆነ የወንድም ልብ ለውይይቱ ዝግጁ እንዲሆን ማድረግ ትችላለህ። በተጨማሪም የምትናገረው ሐሳብ ዘና ያለ ውይይት ለማድረግ ያስችላል። ሬ የተባለ ተሞክሮ ያካበተ አንድ ሽማግሌ “ሁላችንም ብንሆን ያደረግናቸውን መልካም ነገሮች የምንረሳበት ጊዜ አለ። አንድ ሰው ይህን ሲያስታውሰን ነፍሳችን ይታደሳል” ብሏል።
መንፈሳዊ ስጦታ አካፍል
ቅዱስ ጽሑፋዊ ሐሳቦችን ምናልባትም አንድ ጥቅስ በመጥቀስ፣ አንተም እንደ ጳውሎስ ለወንድሞችህ “መንፈሳዊ ስጦታ” ማካፈል ትችላለህ። (ሮም 1:11) ለምሳሌ ያህል፣ አንድ የተጨነቀ ወንድም ራሱን ‘ጢስ በመጠጣቱ’ ብዛት ከተቆራመደ “አቁማዳ” ጋር እንዳወዳደረው እንደ መዝሙራዊው ዋጋ እንደሌለው ሊሰማው ይችላል። (መዝ. 119:83, 176) ይህን አገላለጽ በአጭሩ ካብራራህለት በኋላ ወንድም የአምላክን ትእዛዛት ‘እንደማይረሳ’ ያለህን እምነት ልትገልጽለት ትችላለህ?
በተመሳሳይም ስለጠፋው የብር ሳንቲም የሚናገረውን ምሳሌ ከጉባኤ ለራቀች ወይም ለቀዘቀዘች አንዲት እህት ብትጠቀምበት ልቧን ይነካው ይሆን? (ሉቃስ 15:8-10) የጠፋው ሳንቲም ከብዙ የብር ሳንቲሞች ከተሠራ ውድ የአንገት ሀብል ላይ የወደቀ አንድ ሳንቲም ሊሆን ይችላል። በዚህ ምሳሌ ላይ በመወያየት ይህች እህት ውድ የክርስቲያን ጉባኤ አባል መሆኗን እንድትገነዘብ ልትረዳት ትችላለህ። በምሳሌው ላይ ከተወያያችሁ በኋላ ይሖዋ እሷን እንደ በጉ በመቁጠር ከልብ እንደሚያስብላት ጎላ አድርገህ ልትገልጽላት ትችላለህ።
አብዛኛውን ጊዜ የእምነት ባልንጀሮቻችን በአንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅስ ላይ ሐሳባቸውን መግለጽ ያስደስታቸዋል። በመሆኑም አንተ ብቻ ተናጋሪ አትሁን! እነሱ ካሉበት ሁኔታ ጋር የሚስማማ ጥቅስ ካነበብክላቸው በኋላ ቁልፍ የሆነውን ቃል ወይም ሐረግ ነጥለህ በማውጣት በዚያ ላይ ሐሳብ እንዲሰጡ ልትጋብዛቸው ትችላለህ። ለምሳሌ አንድ ሽማግሌ 2 ቆሮንቶስ 4:16ን ካነበበ በኋላ “በግለሰብ ደረጃ ይሖዋ እንዳደሰህ የተሰማህ ጊዜ አለ?” በማለት ሊጠይቅ ይችላል። ይህን ዘዴ መጠቀም “እርስ በርሳችን እንድንበረታታ” ያስችለናል።—ሮም 1:12
የእምነት ባልንጀሮቻችንን ማጽናናት የምንችልበት ሌላው መንገድ የእነሱ ዓይነት ስሜት የነበረው ሰው ከመጽሐፍ ቅዱስ መጥቀስ ነው። በሐዘን የተዋጠ አንድ ክርስቲያን እንደ ሐና ወይም አፍሮዲጡ ያሉ ሰዎች ከእሱ ጋር የሚመሳሰል ስሜት ተሰምቷቸው እንደነበረ ማወቁ ሊያበረታታው ይችላል፤ እነዚህ ሰዎች የተጨነቁበት ወቅት ቢኖርም በይሖዋ ፊት ውድ ነበሩ። (1 ሳሙ. 1:9-11, 20፤ ፊልጵ. 2:25-30) ሁኔታው የሚያመች ከሆነ መጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ በሚገኙ እንዲህ ያሉ ግሩም ምሳሌዎች ላይ ለመወያየት ለምን አትሞክርም?
ክትትል ማድረግህን አትርሳ
ለወንድሞችህና ለእህቶችህ የእረኝነት ጉብኝት ካደረግክ በኋላም ክትትል በማድረግ ለእነሱ ከልብ እንደምታስብላቸው ማሳየት ትችላለህ። (ሥራ 15:36) የእረኝነት ጉብኝቱን ስታጠናቅቅ አብራችሁ ለማገልገል ቀጠሮ መያዝህ ጠቃሚ ሆኖ ልታገኘው ትችላለህ። በርናንድ የተባለ ተሞክሮ ያካበተ አንድ ሽማግሌ በቅርቡ ከጎበኘው አንድ ወንድም ጋር በድጋሚ ሲገናኝ፣ ቀደም ሲል የሰጠውን ምክር ሠርቶበት እንደሆነ በዘዴ ለመጠየቅ “እንዴት ነው፣ ተሳካልህ?” ይለዋል። አንተም እንዲህ ያለ አሳቢነት የምታሳይ ከሆነ ለግለሰቡ ተጨማሪ እርዳታ መስጠት ያስፈልግ እንደሆነና እንዳልሆነ ለማወቅ ያስችልሃል።
ከመቼውም ጊዜ ይበልጥ ወንድሞቻችንና እህቶቻችን የሚያስብላቸው፣ ስሜታቸውን የሚረዳላቸውና የሚወዳቸው ሰው መኖሩን ማወቅ ይፈልጋሉ። (1 ተሰ. 5:11) በመሆኑም የእረኝነት ጉብኝት ከማድረግህ በፊት ጊዜ ወስደህ ወንድሞችህ ስላሉበት ሁኔታ አስብ። በጉዳዩ ላይ ጸልይ። እንዲሁም ተስማሚ ጥቅሶችን ምረጥ። እንዲህ የምታደርግ ከሆነ “የዛለችውን ነፍስ” የሚያጽናና ሐሳብ መናገር ትችላለህ!
^ አን.2 ስሞቹ ተቀይረዋል።